በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተካሄደው ጦርነት በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ዜጎች ለሞት፣ ለስደትና ለረሃብ ዳርጓል። ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ፈጥሯል። ጦርነቱን ለማቆም በኢትዮጵያ መንግስት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተፈርሟል።
አሁን ላይ ይህ የሰላም ስምምነት ከአራት ወራት በላይ አስቆጥሯል። በስምምነቱ መሰረት በሁለቱ አካላት መካከል መተማመን የሚፈጥሩ ተግባራት ተከናውነዋል። በቅርቡ ደግሞ ሕወሓትን ከሽብርተኝነት ስያሜ የመሰረዝና በስምምነቱ አንቀፅ 10(1) መሰረት በትግራይ ለሚቋቋመው ጊዜያዊ አሰተዳደር ርዕሰ መስተዳድር እንዲሆኑ መንግስት አቶ ጌታቸው ረዳን ሾሟል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ አሳታፊና አቃፊ እንደሚሆን ይጠበቃል። ይህ ሂደት በትግራይ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ዳግም ግንባታ ለማስጀመር ያስችላል ተብሎ ይታመናል።
የሰላም ስምምነቱ ትግበራ ተከትሎ በትግራይ ክልል ያለው አጠቃላይ ሁኔታ አሁን ተቀይሯል። ሰብአዊ ርዳታ እየገባ ነው፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች ወደነበሩበት እየተመለሱ ነው። ይህ ሰላም ለትግራይ ህዝብ ትልቅ እፎይታን የሰጠና ስለ ዳግም ግንባታ እንዲያስብ እድል የፈጠረ ነው። ሰላም ከማንም በላይ ለትግራይ ሕዝብ ጠቃሚ መሆኑን በተጨባጭ ያመላከተም ነው።
የትግራይ ሕዝብ ያለፉትን አስቸጋሪ ውጣ ውረዶች ግምት ውስጥ በማስገባት አሁን ያለውን የሰላም ምዕራፍ ለማስጠበቅና ዘላቂ ለማድረግ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅበታል። እንደ አገርም ካለፈው ታሪካችንና ስህተታችን ተምረን ጦርነት ከጥፋት ውጪ አንዳች ጠቀሜታ እንደሌለው ተረድተን አሁን ያለውን ሰላም በመጠበቅ ለመልሶ ግንባታ ትኩረት ሰጥተን መንቀሳቀስ ይኖርብናል።
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ መንግስት በጦርነቱ የወደሙ መሰረታዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በመጠገን ወደ ስራ እያስገባ ነው። በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ የደረሰውን ውድመት ተረባርቦ በመጠገን ሕዝቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጓል።
በተመሳሳይ መልኩ በቴሌኮሙኒኬሽን መሰረተ ልማት ላይ የደረሰውን ጉዳት ጠግኖ አብዛኛቹ የትግራይ አካባቢዎች የስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል። መንገዶችን፣ ድልድዮችን፣ የትምህርትና እና የጤና ተቋማትንም ከፍተኛ ወጪ አውጥቶ በማስተካከል ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ አድርጓል፤ እያደረገም ነው።
አሁን ባለው እውነታ መልሶ ግንባታው በፌደራል መንግስት እና በጊዜያዊ አስተዳደሩ አቅም ብቻ ሊፈታ የሚችል አይደለም። ለግንባታው የትግራይ ተወላጅ ከሆኑ ዳያስፖራዎችና ምሁራን ብዙ ይጠበቃል። እነዚህ ወገኖች በሚሰሩባቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ በማስረዳት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲገኝ በስፋት ሊንቀሳቀሱ ይገባል። ጠንካራ የገንዘብ አቅም ያላቸውም በክልሉ ኢንቨስት በማድረግ ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራና ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር መስራት ይኖርባቸዋል፡።በትግራይ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎችም የፖለቲካ ልዩነነታቸውን ጠብቀው ደጋፊዎቻቸውን በማስተባበር ለትግራይ መልሶ ግንባታ እና ለግዚያዊ አስተዳደሩ ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ነገ ምረጠኝ የሚሉት ሕዝብ ከችግር በማውጣት ስራ ላይ ተሳታፊ በመሆን ህዝባዊነታቸው ከወዲሁ በተጨባጭ ሊያሳዩ ይገባል።
የትግራይ ሕዝብ በተለይም የትግራይ ወጣቶችም ለክልሉ መልሶ ግንባታ ያላቸውን ትልቅ አቅም በመረዳት፤ የወደሙ ተቋማትን በመጠገንና በተፈጥሮ ሀብትና በተፋሰስ ጥበቃ ሥራ ላይ በመሰማራት ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ግዴታቸውን በመወጣት የትግራይን መልሶ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ለማድረግ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል።
ዓለም አቀፍ ተቋማትም ቢሆኑ በትግራይ ክልል የሚካሄደው መልሶ ግንባታ ከፌደራል መንግስትና ከጊዜያዊ አስተዳደሩ በተጨማሪ በብዙ መልኩ የዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ ድጋፍ የሚሻ መሆኑን በአግባቡና በቅንነት በመረዳት የሞራልና የሰብኣዊነት ግዴታዎቻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
በአጠቃላይ የተገኘው ሰላም ለትግራይ ህዝብ ሆነ በመላው አገሪቱ ከፈጠረው እፎይታ አኳያ፤ ሰላሙን በመልሶ ግንባታ በመደገፍ ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ መላው ሕዝባችን በተለይ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ፣ ልሂቃን፤ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ዳያስፖራው እና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች በጋራ ተቀናጅተው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2015