የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት የሥነምድር ካርታ ሥራን ጨምሮ በጥናትና ምርምር የሥነምድር መረጃዎችን በስፋትና በጥራት በማጥናት ለተጠቃሚዎች ተደራሽ የማድረግ ተልዕኮ ይዞ ሲሰራ ቆይቷል። ኢንስቲትዩቱ የማእድን አለኝታና ክምችት ጥናት በማካሄድ ይታወቃል፤ በስነምድር ላይ ለመንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማትም የምክር አገልግሎት ይሰጣል። በአሁኑ ወቅት ተልዕኮውን የበለጠ ለመወጣት የሚያስችለውን አደረጃጀት አግኝቷል።
ኢንስቲትዩቱ እያከናወናቸው ስለሚገኙ ተግባሮች፣ በአዲስ መልክ መደራጀቱ ስላለው ፋይዳና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ከኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ደጀኔ ኃይለማርያም ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ በዛሬው የምድር በረከት አምዳችን ይዘን ቀርበናል።
አዲስዘመን፡- በቅድሚያ ኢንስቲትዩቱ ስለሚሰጣቸው የሥነምድር መረጃዎችና ስለ አዲሱ አደረጃጀቱ ቢገልጹልን?
ዶክተር ደጀኔ፡– ኢንስቲትዩቱ እንደ መንገድ ላለ መሠረተ ልማት እንዲሁም የህንፃ ግንባታ ከመከናወኑ በፊት በሚያስፈልጉ መረጃዎች ላይ በጥናት የተደገፈ የሥነምድር መረጃ ይሰጣል። መረጃውን ዩኒቨርሲቲዎች ለጥናት መነሻ እንዲጠቀሙበት ምቹ ሁኔታም ይፈጥራል።
መሠረታዊ የጂኦሎጂ ወይንም የሥነምድር ካርታ ያጠናል። በዚህም የሥነምድር አለኝታ ቦታን ይለያል። በዚህ የሥነምድር ካርታ ጥናቱም ማዕድን የሚገኝበትን ሥፍራ ያመላክታል፤ ይህ ብቻ ሳይሆን ክምችቱንም ጭምር የሚያሳይ መረጃ ለይቶና ከልሎ ለተጠቃሚው እንዲደርስ ያደርጋል። በዚህ መረጃ ውስጥም መሬት ውስጥ ያለ የጂኦተርማል ወይንም የእንፋሎትና የነዳጅ ዘይት፣ የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት ካርታና የጥናት ሪፖርት ዝግጅት ይገኝበታል። የሥነምድር ጥናት ምርምርን አቅም ለማጎልበት የሚያስችሉ የቁፋሮ፣ የቤተሙከራ (ላብራቶሪ) እና የምክር አገልግሎቶችን መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት በመስጠትም ኢንስቲትዩቱ ይሰራል።
ኢንስቲትዩቱ ላለፉት 55 ዓመታት በዚህ መልኩ ሲሰራ የቆየ ቢሆንም፣ አሁን ከሚሰራው በላይ አቅም ፈጥሮ ውጤታማ ሥራ እንዲሰራ በማድረግ ረገድ የሚያገኘው ድጋፍ አናሳ ነበር። በመሆኑም ኢንስቲትዩቱ መረሳት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር ማለት ይቻላል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ኢንስቲትዩቱ የበለጠ ተልዕኮውን እንዲወጣ የሚያስችለው አደረጃጀት ተፈጥሯል። ይህም መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ያመለክታል። አሁን ባለው አደረጃጀት መሠረት ኢንስቲትዩቱ በጥናት ያደራጀውን መረጃ ለማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ይሰጣል። ይህ ክፍል ደግሞ የአዋጭነት ጥናት ያካሂዳል።
ማዕድኑ በምን ቴክኖሎጂ ሊለማ እንደሚችል ጭምር በጥናቱ አካቶ ለማዕድን ሚኒስቴር ይሰጣል። ማዕድን ሚኒስቴር ደግሞ በዚህ ሂደት ማለፉን ካረጋገጠ በኋላ ለአልሚዎች ፈቃድ በመሥጠት ልማቱ እንዲከናወን ያደርጋል። እንዲህ አይነት የተናበበ አሰራር ቀደም ሲል አልነበረም። በአዲሱ አደረጃጀት ሥራዎች በዚህ መልኩ ነው የሚከናወኑት።
በሰው ኃይል በኩልም ቀደም ሲል ኢንስቲትዩቱ በአንድ ዋና ዳይሬክተርና ዋና ጂኦሎጂስት ነበር የሚመራው። በአሁኑ አደረጃጀት ግን በአንድ ዋና ዳይሬክተርና በሶስት ሥራ አስፈጻሚዎች እንዲመራ ተደርጓል።
አንዱ የማዕድን ሀብት ሥራ አስፈፃሚ ሲሆን፣ በሥሩ የማዕድን ፍለጋ ምርምር፣ የጂኦተርማል ሀብት ምርምር እንዲሁም የድሪሊንግ አገልግሎትና የጂኦፊዚክስ ምርምር ዴስክ ወይንም ክፍሎች ይገኛሉ። በሁለተኛው ሥራ አስፈጻሚ ሥር ደግሞ የጂኦሣይንስ ካርታ ሥራ፣ ምርምር፣ የሥነምድር አደጋዎችና ጂኦቴክኒክ ምርምር፣ የጂኦሳይንስ መረጃና የጂኦኬሚስትሪ ምርምር ዴስኮች ወይንም ክፍሎች አሉት። ሶስተኛው የጂኦሳይንስ ላብራቶሪ ሥራ አስፈጻሚ ሲሆን፣ በሥሩም የጂኦኬሚካል፣ የሚኖሮሎጂና የሳይንቲፊክ መሳሪያዎች ጥገና ይገኛሉ።
በአዲሱ አደረጃጀት አገልግሎቶችን የጋራ በማድረግ ለሥራ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት ተደረገ እንጂ ኢንስቲትዩቱ ተጠሪነቱ ለማዕድን ሚኒስቴር ቢሆንም፣ በራሱ በጀት ነው የሚተዳደረው። አደረጃጀቱ ሥራን የሚያቀላጥፍ እና የማያቀላጥፍ መሆኑ እየተፈተሸ ለአሰራር ምቹ የሆነ ነገር እንዲፈጠር ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱ በእስካሁኑ እንቅስቃሴው ምን ተልእኮዎችን ተወጥቻለሁ ይላል?
ዶክተር ደጀኔ፡– ኢንስቲትዩቱ ባለው የሰው ኃይል፣ በጀትና አደረጃጀት የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር ለመወጣት የሚችለውን ሲያደርግ ቆይቷል። ከእነዚህ መካከልም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የብረት ምርት/ጥሬ እቃ/ በአገር ውስጥ ለመተካት በመንግሥት የተያዘውን አቅጣጫ ለማሳካት እያደረገ ያለው ጥረት ይጠቀሳል።
ኢንስቲትዩቱ በዚህ በኩል እየተወጣ ባለው ድርሻ ባደረገው የጥናት ሥራ በሰቆጣ፣ ምእራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ ባሌ፣ መካነሰላም በሚባሉ አካባቢዎች የብረት ማዕድን ልየታ ሥራ አከናውኗል። ክምችቱን በጥናት የመለየት ሥራ ከተከናወነ በኋላ ደግሞ ክምችቱን ለማረጋገጥ ወደ ሁለተኛው ምእራፍ የቁፋሮ ሥራ መሸጋገር ተችሏል። የቁፋሮው ሥራውም ልየታ በተደረገበት ጉጂ ላይ ነው ለጊዜው የሚከናወነው።
ኢንስቲትዩቱ በልየታ ላይ ነው ትኩረት አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው። የለየውንም ቁፋሮውን ለሚያከናውን አካል ወይንም ኩባንያ ነበር አሳልፎ የሚሰጠው። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ምን ያህል ክምችት አለው የሚለው በኢንስቲትዩቱ እንዲረጋገጥ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ለጊዜው በብረት ማዕድን ላይ ቁፋሮ እንዲጀመር ተደርጓል።
ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ለኃይል ግብአት በሚውል የድንጋይ ከሰል ላይም በተመሳሳይ በተከናወነው ሥራ ጅማ፣ ደቡብ ምእራብ፣ ቤኒሻንጉልጉሙዝ ልየታ ማድረግ ተችሏል። በወርቅ ማዕድን ዙሪያም እንዲሁ ኢንስቲትዩቱ በየጊዜው የጥናት ሥራ ያከናወናል። ባለፈው ዓመት በሲዳማ ክልል ላይ ጥናት ተደርጓል።
የጥናት ውጤቱም ለየክልሎቹ የማድረስ ሥራ ይሰራል። በጥናት የተደራጀ መረጃ አልሚ ሲመጣ ጥናቱን መሰረት አድርጎ እንዲያለማ ከማስቻሉ በተጨማሪ ክክሎችም ሥራ ያቀልላቸዋል። በደቡብ ክልል አካባቢም በጌጣጌጥ ማዕድን ላይ የጥናት ሥራ ተሰርቷል።
አዲስ ዘመን፡- የቁፋሮ ሥራው ለጊዜው በብረት ማዕድን ላይ ነው የሚከናወነው። በወርቅና ሌሎቹ የማዕድን አይነቶች ላይ በተመሳሳይ ቀጣይ ተግባር ይኖራል?
ዶክተር ደጀኔ፡- የወርቅ ማዕድንን በተመለከተ በጥናት የቦታ ልየታው ይካሄዳል፤ የማዕድን ክምችት ግን በግምት ነው መረጃው የሚጠናቀረው። ግምቱ ግን ለእውነት የተጠጋ ነው። ኢንስቲትዩቱ በዚህ ደረጃ ያለውንና ያረጋገጠውን መረጃ ለሚመለከተው አካል ይሰጣል።
እስካሁን ባለው አሰራርም ለኩባንያ ነው አሳልፎ የሚሰጠው። የወርቅ ቁፋሮ ሥራ አስር ዓመትና ከዚያም በላይ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ኢንስቲትዩቱ አለኝታ ቦታን ለይቶ መሥጠቱ በራሱ ከፍተኛ መረጃ ነው። ኩባንያዎችም ሆኑ በአነስተኛ ተደራጅተው በዘርፉ የሚሰሩ መረጃውን ካገኙ አስፍተው ለመቀጠል ዕድል ይሰጣቸዋል።
የጌጣጌጥ ማዕድን ዘርፍ ግን ለየት ይላል፤ ማዕድኑ በቀላሉ አይገኝም። ቦታውን በራሱ መለየት አንድ ነገር ነው። ክምችቱን ማወቅ ያስቸግራል። እስካሁን ባለው አሰራር አካባቢውን በማመላከት ሥራ ላይ ነው ትኩረት የተደረገው።
የነዳጅ ዘይትና የተፈጥሮ ጋዝ ላይ ኢንስቲትዩቱ ጥናት እንዲያካሂድ ተልእኮ ቢሰጠውም ሥራውን ግን አልሄደበትም። በዘርፉ ኩባንያዎች ናቸው እየተንቀሳቀሱ ያሉት። ዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ከፍተኛ መዋእለነዋይና ቴክኖሎጂ ይጠይቃል። ኢንስቲትዩቱ በዚህ ደረጃ የተደራጀ ባለመሆኑ ነው ወደ ሥራ ያልገባው። ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ከኦጋዴን አካባቢ በተጨማሪ በስምጥ ሸለቆና በሌሎችም የአገሪቱ አካባቢዎች የሀብት ክምችቱ አለ።
ለግንባታው ዘርፍ ግብአት በሚውሉ የማዕድን ዘርፎች ላይም ኢንስቲትዩቱ ጥናት ያካሂዳል። በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ በአምስት አካባቢዎች ላይ ግራናይት መኖሩን የሚያረጋግጥ መረጃ ለክልሉ ሰጥቷል።
አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱ የማዕድን ሀብትን እንደየዘረፉ በመለየት ተደራሽ ያደርጋል። ሀብቱ መኖሩን ከማረጋገጥ ባለፈ ጥቅም ላይ ውሎ በምጣኔ ሀብቱ ላይ አስተዋጽኦ ሲያበረክትና ማህበረሰቡም ከልማቱ ተጠቃሚ ሲሆን ማየት ነው የመጨረሻው ግብ። በመሆኑም ውጤቱስ ለሚሉ ምላሽዎ ምንድነው? በእያንዳንዱ የማዕድን ዘርፍ ያለው የክምችት መጠንስ ምን ያህል ይታወቃል?
ዶክተር ደጀኔ፡- ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ካላት እምቅ የከርሰምድር ሀብት ለይተናል ብለን መናገር የምንችለው ከ20 በመቶ አይበልጥም። ከዚህ በላይ ላለመሄዳችን ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው። የትኩረት ማነስ እንደ አንድ ምክንያት ይወሰዳል። ኢንስቲትዩቱ በሙሉ አቅሙ ይንቀሳቀስ ነበረ ለማለት አያስደፍርም።
ይህ ተቋም የማዕድን ሚኒስቴር የጀርባ አጥንት ነው ማለት ይቻላል። አሁን ላይ የተሻለ ትኩረት ቢያገኝም፣ ብዙ ለመሥራትና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በቴክኖሎጂ መታገዝ አለበት። ያደጉ አገሮች የማዕድን ልየታ ጥናት ሥራን በአውሮፕላን በመታገዝ ጭምር ነው የሚሰሩት።
አዲስ ዘመን፡- በዘርፉ ገና ብዙ ሥራ የሚጠበቅ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ እምቅ ሀብት አላት የሚባለው ምንን መሰረት በማድረግ ነው?
ዶክተር ደጀኔ፡- በባህላዊ የአሰራር ዘዴም ሆነ አነስተኛ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተሰሩት ሥራዎች እንዲሁም በዘርፉ ላይ ተሰማርተው ከሚንቀሳቀሱና በተለያየ መንገድ ከተገኘ መረጃ መረዳት የሚቻለው ኢትዮጵያ እምቅ ሀብት ያላት መሆኑን ነው።
አዲስዘመንለ፡- ኢንስቲትዩቱ በተጠናከረ አደረጃጀት ውስጥ ባልነበረበት ወቅትም ሆነ አሁን በአዲስ መነቃቃት ባደረገው እንቅስቃሴ ፈተናዎች እንደሚያጋጥሙት ይታወቃልና ፈተናዎቹ ምንድናቸው? እንዴትስ እያለፋቸው ነው?
ዶክተር ደጀኔ፡- የሰለጠነ ባለሙያ ፍልሰት አንዱ የዘርፉ ተግዳሮት ነው። የተሻለ አሰራር ያለው ኩባንያና ክፍያ ፍለጋ ብዙ የዘርፉ ባለሙያዎች ስራ ትተው ይሄዳሉ። ዘርፉ አሁን ላይ በአዲስ አደረጃጀት መዋቀሩን ተከትሎ ባለሙያዎችን ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ነው። ለእዚህም ዩኒቨርሲቲዎች የዘርፉን ባለሙያ እንዲያፈሩ በጋራ እየተሰራ ይገኛል። በራስ አቅም በማሰልጠን ክፍተቱን ለመሙላትም ጥረት እየተደረገ ነው።
ሌላው የኢንስቲትዩቱ የጥናት ሥራ በቤተሙከራ መደገፍ ይኖርበታል። ይሁን እንጂ ቤተሙከራው በቆየ አደረጃጀት ውስጥ ነው ያለው። የሚጠበቅበትን መውጣት እንዲችል ለምርምር አጋዥ ነገሮች ሊሟሉለት ይገባል።
ቤተሙከራው የቤተሙከራ ፍተሻ እንዲደረግላቸው የሚፈልጉ አካላትን ጨምሮ የፍተሻ አገልግሎት ለሚፈልጉ ሁሉ በክፍያ አገልግሎት ይሰጣል። የክፍያ አገልግሎቱ አሁን ካለው ወቅታዊ ገበያ ጋር የሚጣጣም ሆኖ ባለመገኘቱ አገልግሎት ሰጥቶ የሚያገኘው ገቢ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር አይደለም። ክፍተቶች ቢኖሩም፣ ባለው ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ ነው።
በዚህ ብቻ ውጤታማ መሆን ስለማይቻል ቤተሙከራውን ማዘመን ግዴታ ነው። ለእዚህም ጥረቶች ተጀምረዋል። ከአንድ የካናዳ ድርጅት እና ቤተሙከራውን ለማስፋት እንዲመችም ከአዲስ አበባ ከተማ መሬት አስተዳደር ጋር ዘመናዊ ቤተሙከራ ለመገንባት ሥራዎች ተጀምረዋል። በተለይም ከተማ አስተዳደሩ ቤተሙከራው ከሚገኝበት ሁለት ሄክታር መሬት ላይ አንድ ሄክታር ተጨማሪ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ እየተሰራ ነው። ፈቃደኝነቱም ስላለ በዚህ በኩል ይሳካል። የካናዳ ድርጅትም በተለያየ መልኩ እገዛ ያደርጋል።
አዲስ ዘመን፡- ለቤተሙከራ የሚሆን የኬሚካል ግብአት አቅርቦትም ከውጭ ምንዛሪ ጋር የሚያያዝ በመሆኑ በዚህ ረገድ በአገር ውስጥ ለመተካት እድል ይኖራል?
ዶክተር ደጀኔ፡- ክፍተቱ እስካሁን ባያጋጥምም ተግዳሮት መሆኑ ግን አይቀርም። በአገር ውስጥ የሚቀርብ ቢኖርም የግድ ከውጭ መምጣት ያለባቸው ግብአቶች አሉ። እነዚህን መተካት በሚችልበት ሁኔታ ላይ ከወዲሁ መነጋገር ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- የጂኦተርማል ወይንም የእንፋሎት ዘርፉ አንዱ የማዕድን ሀብት ነው ማለት ይቻላል?
ዶክተር ደጀኔ፡– ዘርፉን በሁለት ከፍለን ማየት ይቻላል። አንዱ ለኤሌክትሪክ ኃይል የሚውልና ሌላኛው ደግሞ ለመዝናኛ የሚውል ነው። ለኤሌክትሪክ ኃይል የሚውለውን እንፋሎት የሚገኝበትን አካባቢና ክምችቱን በጥናት የመለየት ሥራ በማከናወን ለሚመለከተው አካል መረጃ ይሰጣል። በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች ከመጡም መረጃውን እንዲያገኙ ይደረጋል። ለአብነትም ኢንስቲትዩቱ ባካሄደው ጥናት መሠረት አሉቶ ላንጋኖና ቱሉሞዬ ላይ የውጭ ባለሀብቶች ገብተው በቁፋሮ ሥራ ላይ ይገኛሉ። አሉቶ ላንጋኖ ላይ ቁፋሮውን እያከናወነ ያለው ኬንጂን የሚባል የኬኒያ ኩባንያ ነው። እስከ 150 ሜጋ ዋት ድረስ መለየት ችለዋል። ቁፋሮው አሁንም ቀጥሏል።
ለመዝናኛ የሚውለውም ቢሆን ወጣቶች ተደራጅተው ለተጠቃሚዎች አገልግሎት የሚሰጡበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ይደረጋል። ለጤናም ሆነ ለመዝናናት ሙቅ ውሃ የሚፈልጉ ሰዎች ብዙ ናቸው፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞም የገቢ ምንጭ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ምን ምን እቅዶችን አዘጋጅቶች እየሰራ ይገኛል?
ዶክተር ደጀኔ፡- የሥራ ባህሪው ከሌሎች የሥራ ዘርፎች ይለያል። በዚህ ዓመት ሲጠና የቆየው ሥራ ዓመቱ መጨረሻ ላይ አይጠናቀቅም። በረጅም ጊዜ መንግሥት በውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚያስገባቸውን በአገር ውስጥ ለመተካት የያዘውን አቅጣጫ ማሳካት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልሱ ላደረጉልን ትብብር በእጅጉ እናመሰግናለን።
ዶክተር ደጀኔ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2015