በማዕድን ልማትና የዘርፉ ገቢ ውጤቶች የታዩበት የአማራ ክልል

የአማራ ክልል የከበሩ ማዕድናትን ጨምሮ ወርቅ፣ የድንጋይ ከሰል፣ ጂብሰም፣ የኖራ ድንጋይ እና ሌሎች በርካታ ማዕድናት መገኛ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ። ክልሉ የከበሩና ጌጣጌጥ ማዕድናት በተለይ የኦፓል ዋንኛ መገኛ በመሆንም ይታወቃል።

በክልሉ እስካሁን በተደረገው የዳሰሳ ጥናት በክልሉ ከ40 አይነት በላይ ማዕድናት (ብረትና ብረት ነክ ማዕድናት፣ ለኢንዱስትሪና ለኮንስትራክሽን ግብዓትነት የሚውሉ ግብዓቶች፤ የከበሩ ጌጣጌጥ፣ የኢነርጂ እንዲሁም የማዕድን ውሃ እና ጂኦተርማል ማዕድናት) ክምችት እንዳለ ተረጋግጧል።

የክልሉ የማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ ክልሉ ካሉት እምቅ የማዕድን ሀብቶች መካከል እስካሁን በተደረጉ ጥናቶች የተለዩት 70 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው። ጥናቱ የሸፈነው ከክልሉ የቆዳ ስፋት ከ33 ነጥብ 3 በመቶ በታች ያህሉን ነው። በክልሉ የሚገኙ ሌሎች ማዕድናት ለመለየት የሚደረገው ጥናት ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በክልሉ ማዕድን ዘርፍ ላይ በትኩረት ከመሥራቱና ወደ ሙሉ ትግበራ ከገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ ማዕድንን ከማምረት አኳያም ሆነ ከገቢ አንጻር አበረታች ውጤቶች መታየት ችለዋል። በተለይ ማዕድናት ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት በኩል ዘንድሮ ከባለፈው ዓመት በተሻለ መልኩ አበረታች ውጤት መመዝገቡን የክልሉ የ2017 በጀት ዓመት የአስር ወራት ሪፖርት ያመላክታል።

አቶ ዝናው አበበ የክልሉ የማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ጂኦሎጂስት እና በምክትል ቢሮ ኃላፊ ደረጃ የሕዝብና ሚዲያ ግንኙነት ኃላፊ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ በክልሉ እስካሁን በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ከ40 በላይ የማዕድናት ዓይነቶች ክምችት እንዳለ ተረጋግጧል። ተጨማሪ የማዕድን ሀብቶችን በጥናት ለመለየት ሰፊ ርብርብ እንደተደረገም ነው። በዚህም በ2017 በጀት ዓመት በማዕድን ዘርፉ በርካታ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል።

በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት የማዕድናት የአለኝታ ቦታ ለይታ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ጠቅሰዋል። ከእነዚህም መካከል በደቡብ ወሎ ዞን የተካሄደው አንዱ ነው፤ አዲስ ፕሮጀክቶች አንድ በሃምሳ ሺ ስኬል /በ1፡50,000 /መስፈርት 10ሺ755 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ላይ ለማጥናት በደቡብ ወሎ ዞን በአርጎባ ልዩ ወረዳ በ310 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ የሥነምድር ጥናት ለማካሄድ ታቅዶ ተሰርቷል። ከዚህም እስከ አስር ወራት 75 በመቶ ለመሥራት ታቅዶ፤ 80 በመቶ ማከናወን መቻሉን ተመላክቷል።

በሰሜን ጎንደር ዞን በጠለምት ወረዳ በሶስት ሺ 871 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ እንዲሁም በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን በአርጡማ ፋርሲ ወረዳ በአንድ ነጥብ 073 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ የሥነምድር ጥናት ለማካሄድ ታቅዶ፤ ጥናቱ መካሄዱን በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በሰሜን ሸዋ ዞን በእንሳሮ ወረዳ በ441 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ በራስ አቅም ለመሥራት ለሚደረገው የሥነ-ምድር ካርታ ጥናት ለማከናወን እስከ 10 ወሩ 75 በመቶ ያህል ጥናት ለማድረግ ታቅዶ፤ የጥናቱን 70 በመቶ ያህል ማከናወን ተችሏል።

በክልሉ በአሥር ወራት 5000 ካሬ ኪሎ ሜትር የማዕድን ልማት ቀጣናዎችን በአለት ስርጭት፤ በማዕድን አይነት፣ በስፋትና በኢኮኖሚ ፋይዳ በመለየት የማዕድን አይነቱን የሚያሳይ ካርታ 75 በመቶ ለመሥራት ታቅዶ፤ 70 በመቶ ያህሉ ተከናውኗል። ይህም አፈፃፀሙን 93 ነጥብ ሶስት በመቶ እንዲሆን አድርጎታል።

በክልሉ 15 ካሬ ኪሎ ሜትር የጂኦሀዛርድ የሚከስትባቸው ቦታዎችን መለየትና በካርታ ላይ የማመላከት፣ ተግባር በተመለከተ 75 በመቶ ለመሥራት ታቅዶ፤ 80 በመቶ ያህል መሥራቱን ሪፖርቱ ያመላክታል።

ክልሉ ለውጭ ገበያ ካቀረባቸው የማዕድን ምርቶች ከታቀደው በላይ ገቢ መገኘቱም በሪፖርቱ ተጠቁሟል። በተያዘው በጀት ዓመት በአሥር ወራት 18ሺ 779 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም የጌጣጌጥ ማዕድናት ለማምረት ታቅዶ፤ 23ሺ 558 ነጥብ ስምንት ኪሎ ግራም የጌጣጌጥ ማዕድናት ማምረት ተችሏል። ይህም ምርቱ ከእቅድ በላይ እንዲሆን አድርጓል።

ከገቢም አንጻር ከጌጣጌጥ ማዕድናት በአሥር ወራት አራት ሚሊዮን 927ሺ 230 ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ፤ ስምንት ሺ 768 ነጥብ 98 ኪሎ ግራም ምርት ወደ ውጭ በመላክ ከዘጠኝ ሚሊዮን 034ሺ 539 በላይ ዶላር ገቢ ተገኝቷል። የተገኘው ገቢ ከእቅዱ በላይ መሆኑ ተጠቁሟል።

ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር 44 ነጥብ አምስት በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የተገለጸ ሲሆን፣ ከገቢም አንጻር እስከ አሥር ወራት የተገኘው አፈጻጸም ከፍተኛ መሆኑ ተጠቁሟል።

በበጀት ዓመቱ አሥር ወራት በክልሉ 45 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ በማስገባት ታቅዶ፤ 75 ነጥብ ዘጠኝ ኪሎ ግራም ወርቅ ማስገባት መቻሉን አስታውቀዋል።

ይህ የወርቅ ማዕድን አፈጻጸም በአጠቃላይ የወርቅ ምርትና የውጭ ምንዛሬ አፈጻጸም ከዕቅዱ በላይ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል። አፈጻጸሙ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር ከ50 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለው ያመላክታሉ።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት በአሥር ወራት ከማዕድን ዘርፉ ከተለያዩ (ከሮያሊቲ፤ ከመሬት ኪራይ፣ እና ሌሎች ተዛማጅ አገልግሎት ክፍያዎች) 68 ሚሊዮን 833 ሺ 944 ብር ተሰብስቧል። አፈጻጻሙ በአሥር ወራት መቶ ከመቶ በላይ ሆኗል።

የባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም 50 ነጥብ አራት በመቶ እንደነበረ ጠቅሰው፣ ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ34 ነጥብ ሶስት በመቶ ብልጫ እንዳለው አመላክተዋል።

በክልሉ በማዕድን ዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል ሥራ መሠራቱን ተከትሎ በቀጥታም ይሆን በተዘዋዋሪ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ይገልጻሉ። እሳቸው እንዳብራሩት፤ በበጀት ዓመቱም አሥር ወራት በከፍተኛ፣ በአነስተኛና በባሕላዊ በተሰጡ ፈቃዶች እና በማዕድን ነክ ፋብሪካዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ተሠርቷል። በዚህም በማዕድን ዘርፉ ከሚሰማሩ ባለሃብቶች፣ ኩባንያዎች እና ኢንተርፕራይዞች ለ34 ሺ 387 (ወንድ 24,152 ሴት 10,235) ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ፤ ለ42ሺ 136 (ወንድ 22,170 ሴት 8,966) ዜጎች ሥራ ዕድል ተፈጥሯል።

በክልሉ የተፈጠረው የሥራ ዕድል አፈጻጸም ከዕቅዱ መቶ ከመቶ በላይ ነው። ከዓመቱ ዕቅድ አንጻር ሲታይ ደግሞ 92 ነጥብ ስድስት በመቶ ያህል ነው። ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት ጋር ሲነጻፀር 12 ነጥብ ሶስት በመቶ ብልጫ አሳይቷል። አጠቃላይ በቋሚነት የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው 26ሺ 076 (84 ነጥብ 6 በመቶ ያህሉ) መካከል ወንዶች 19 ሺ 291 እንዲሁም ሴቶች ስድስት ሺ 785 መሆናቸውን ገልጸዋል። በአጠቃላይ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው መካከል 82 ነጥብ ሰባት በመቶ ያህሉ ወጣቶች መሆናቸውን አብራርተዋል።

በክልሉ በዘንድሮው በጀት ዓመት የማዕድን ሥራዎች ፍቃድ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ሥራ መሰራቱንም ጠቅሰዋል። የማዕድን ነክ ፋብሪካዎች እንዲገነቡ በአሥር ወራት 196 የምርመራ እና የምርት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ፤ 159 የምርመራ እና የምርት ፈቃዶችን ተሰጥተዋል ብለዋል። ይህም አፈጻጻሙን 81 በመቶ በላይ እንዲሆን አድርጎታል። የባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም 42 ነጥብ ስድስት በመቶ እንደነበረ አስታውሰው፣ ከባለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት ጋር ሲነጻፀር 47 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ብልጫ ማሳየቱን አመልክተዋል።

በተለይም በዚህ ዓመት የክልሉን የምርመራ እና የምርት ፍቃድ ለየት የሚያደርገው የክልሉን የግብርና ምርታማነትን ለመጨመር (የአፈርን አሲዳማነት) ለመከላከል የሚረዳ እና የመሬት ምርታማነት በሚጨመረው ኖራ ላይ የተሠራው መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም አምስት (ሦስት ምርመራ እና ሁለት ምርት) ኖራ ድንጋይ የምርመራ እና የምርት ሥራ ፍቃድ መስጠት ተችሏል ብለዋል።

በአነስተኛ ኮንስትራክሸንና በባሕላዊ የማዕድን ማምረት ሥራ ለሚሠማሩ ሶስት ሺ 555 አምራቾች ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ፤ ለሁለት ሺ 701 አምራቾች የማምረት ፈቃድ መሰጠቱን ተናግረዋል። ይህም አፈጻጸሙን 75 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ እንዲሆን አድርጓታል ሲሉ ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በክልሉ በአሥር ወራት በማዕድን ዘርፍ የሚሰጡ የኢንቨስትመንት ፍቃዶች ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማስገባት ታቅዶ፤ ከዕቅድ በላይ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ማስመዝገብ ተችሏል ሲሉም ገልጸዋል። አፈጻጸሙ ከባለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት ጋር ሲነጻፀርም በ37 ነጥብ ስምንት በመቶ ብልጫ ማሳየቱን አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በክልሉ ከማዕድናት ፍለጋና ክምችት ግመታ ጥናት በነባር ፕሮጀክቶች በተለያዩ መስፈርቶች 40 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ላይ ለማጥናት ታቅዶ ብዙ ተሠርቷል። ከተሠሩት መካከልም በዋግህምራ ዞን በሰቆጣ ወረዳ የተሠራው አንዱ ነው። በወረዳው በ20 ካሬ ኪሎ ሜትር የብረት ማዕድን አይነት፣ ክምችት፣ ጥራት እና ስርጭት ሽፋን ላይ ጥናት ለማካሄድ ታቅዶ ሲሠራ መቆየቱን ጠቅሰው፤ ሙሉ ለሙሉ በጥናት በመሸፈኑን አመላክተዋል።

በሰሜን ጎንደር ዞን አድርቃይ/ጠለምት ወረዳ በ10 ካሬ ኪሎ ሜትር በተመረጠ ቦታ የወርቅ ማዕድን አይነት፣ ክምችት፣ ጥራት እና ስርጭት ሽፋን ላይ ጥናት በአስር ወራት 75 በመቶ ለመሥራት ታቅዶ፤ 85 በመቶ ያህሉ የወርቅ ማዕድን የመለየት ሥራ ተከናውኗል።

በክልሉ አዲስ ፕሮጀክቶች በተለያዩ መስፈርቶች 130 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ላይ ለማጥናት የሚያስችሉ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል። በዚህም ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ የተከናወነው ይጠቀሳል። በወረዳው በ50 ካሬ ኪሎ ሜትር የድንጋይ ከሰል ማዕድን አይነት፣ ክምችት፣ ጥራት እና ስርጭት ሽፋንን ጥናት ለማካሄድ በተሠራው ሥራ ከታቀደው በላይ አፈጻጸም መመዝገቡን አስታውቀዋል። በምዕራብ ጎጃም ዞን በወንበርማ ወረዳ በ10 ካሬ ኪሎ ሜትር የወርቅ ማዕድን፣ በምስራቅ ጎጃም ዞን እናርጅ እናውጋ ወረዳ በ60 ካሬ ኪሎ ሜትር እና ፣ በአዊ ዞን ዳንግላ ወረዳ ጋይታ ቀበሌ በ10 ካሬ ኪሎ ሜትር ሰንቡ አካባቢ የብረት ማዕድን ክምችት፣ ጥራት እና ስርጭት ሽፋን ጥናት ለማካሄድ 30 በመቶ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን አመልክተዋል።

በትግበራ ወቅት ደግሞ የቢሮ ተግባራት /Desk Work/፣ የዳሰሳ ጥናት እና ዋና የመስክ ተግባር መጠናቀቁን ገልጸው፣ ለናሙና ማስመርመሪያ ክፍያ በውሉ መሰረት መፈጸሙንም ተናግረዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You