ረመዳን በእስልምና ዘመን አቆጣጠር 12 ወራቶች ውስጥ አንደኛውና በቅዱስ ቁርዓን ጾም ግዴታ የተደረገበት ወር ነው። ከእስልምና መሰረታዊ መመሪያዎች ውስጥ የረመዳንን ፆም መፆም ዋነኛው ሲሆን ማንኛውም አቅም ያለው፤ ጤነኛ የሆነ ሰው፤ እድሜው የደረሰ መፆም ይገደዳል። ይህም ጎህ ከቀደደችበት ጊዜ ጀምሮ ፀሐይ እስከምትጠልቅ ድረስ የሚፈጸም የፆም ተግባር ነው። በአጠቃላይ የእምነቱ መሰረት ስለሆነ ፆም ግዴታ ነው።
የረመዳን ፆም ለፈጣሪ ያለን ታዛዥነት ውስጣችን ታማኝነት፣ ርህራሄና ይቅርባይነት የምናሳይበት ነው። በተለይ ባሳለፍናቸው ወራቶች ውስጥ በንግግራችንና በተግባራችን የተገለፁ ጥፋቶች፤ ከፈጣሪ ያፈነገጡ ተግባራት፣ የእምቢተኝነት ባህሪያት፣ በሰው ላይ የፈጸምናቸውን ትክልል ያልሆኑ ድርጊቶች በማስታወስ የምንጸጸትበትና በአጠቃላይ ፆም የተበላሹብንን ነገሮች ለማስተካከልና ራሳችንን በትክክለኛ መንገድ ለማነፅና ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመሸጋገር የሚረዳ መንፈሳዊ ማሰልጠኛ ማዕከል ነው። ስለዚህም ከግለሰብ እስከ ሀገር ድረስ የተፈጸሙ ስህተቶች ካሉ መለስ ብለን የምናይበትና የእርምት እርምጃ የምንወስድበት ጊዜ ነው።
ረመዳን የእዝነት ወር ነው። ይህም ማለት እርስበርስ የመተዛዘን፤ የመረዳዳት፤ የመደጋገፍ ወቅት ነው። በተለይም ደግሞ አብሮነት፤ መተጋገዝ፤ መረዳዳት የኢትዮጵያውያኖች አንዱ መገለጫ ነው። የረመዳን ወርም ሙስሊሙ ኅብረተሰብ የእምነቱ ግዴታ የሆነውን ዘካውን (አስራቱን) የሚወጣበት ነው። እንደሚታወቀው ማንኛውም አቅም ያለው ሰው ዘካ ይሰጣል፤ ወይም ካለው ገንዘብ ላይ ላጡ ለነጡ ወገኖቹ ያካፍላል። ይህንን በጎ ተግባር መፈጸም በተለይም በረመዳን ወር ከእያንዳንዱ ሙስሊም ይጠበቃል።
በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በድርቅ የተጎዱ፤ በግጭት የተፈናቀሉ ወገኖች በየቦታው ይገኛሉ። እነዚህን ወገኖች መደገፍ ደግሞ ኃይማኖታዊም ሆነ የዜግነት ግዴታ ጭምር ነው። በረመዳን ወር የሚሰጠውም ዘካ (ምፅዋት) አንዱ ዓላማም ዝም ብሎ መስጠት ብቻ ሳይሆን ሰዎችን እያቋቋሙ አዲስ ምዕራፍ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ነው። ሰዎች ከችግርና ከተረጂነት የሚወጡበትን ስርዓት ለማበጀት ዘካ በአግባቡ እንዲሰጥ ነው እስልምና የሚያዘው። ዘካ ድህነትን ለመከላከል እስልምና እንደመፍትሔ ካቀረባቸው መንገዶች አንዱ ነውና በሁሉም አካባቢ የተቸገሩና የታረዙ ወገኖች በመርዳት የረመዳንን አጅር (ትሩፋት) ልናገኝ ይገባል።
የእስልምና እምነት ካለን ሃብት 2 ነጥብ5 በመቶ የሚሆነውን ለተቸገሩ እንድንሰጥ ያዘናል። ይህም ደግሞ ለትክክለኛው ዓላማ መዋል ስላለበት ተበታትኖ ሳይሆን በተደራጀ መልኩ ለባለቤቶቹ ደርሶ ሰዎች እንዲለወጡበትና ከተረጂነት ወደ ረጂነት እንዲሸጋገሩ፤ ስራ ላይ ውጤታማ የሚሆኑበትን የማቋቋም ስራ መስራት ያስፈልጋል። በተለይም አሁን በሀገራችን ላይ ከተከሰተው ድርቅ፣ ረሃብ፣ መፈናቀል፣ የተነሳ በርካታ ወገኖች በአስከፊ ችግር ውስጥ የሚገኙ በመሆኑ ከተለያዩ ወገኖች ዘካዎችን (ምጽዋቶችን) በማሰባሰብ ለወገን መድረስ ከሙስሊሙ ኅብረተሰብ የሚጠበቅ ነው።
ቅዱስ ቁርዓን ‹‹ለጎረቤቱ የማያዝን ሰው አማኝ አይደለም›› ይላል። ጎረቤቱ ተርቦ እሱ ጠግቦ ያደረ ሰው እንደለመነ ነው የሚቆጠረው። ስለዚህም በየቦታው ተቸግረው የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን መርዳት በረመዳን ወቅት ከሚጠበቁ በጎ ተግባራት ውስጥ አንዱ ሊሆን ይገባል።
በርካታ ኢትዮጵያውያን በድርቅ፤ በግጭት፤ በመፈናቀልና በስደት ምክንያት ተርበዋል፤ እንስሳቶቻቸውን አጥተዋል፤ ማሳዎቻቸው ፍሬ አጥተዋል፤ እነሱም ሆኑ ልጆቻቸው ተርበዋል፤ ታርዘዋል። ስለዚህም ለእነዚህ ወገኖች መድረስ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።
ዛሬ የተቸገሩት ወገኖቻችን ትናንት ሰጪዎች ነበሩ። ዛሬ የተራቡት ወገኖቻችን ትላንት ከራሳቸው አልፈው ብዙዎችን አጥግበው ሲያሳድሩ ኖረዋል። ስለዚህም በዚህ በተቀደሰው የረመዳን ወር ዛሬ እኛ መከታ ልንሆናቸው ይገባል። የመረዳዳት፤ የአብሮነት፤ የመተዛዘን ወር በሆነው በረመዳን ወቅትም የሚጠበቀው ይኸው ናውና!
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2015