አላሮ ጳውሎስ የ10 ዓመት ታዳጊ ነው።ከአላባ አዲስ አበባ ከመጣ ሁለት ዓመት እንደሆነው ይናገራል።ሆኖም እስከ አሁን የሚያድረው ጎዳና ላይ ነው።ሰሞኑን ዝናብ ስለጣለ አስፋልት ኮሪደር ላይ አብረውት ከሚያድሩት ሌሎች ልጆች ጋር ቤሄራዊ ቲያትር አካባቢ ማደር ጀምሯል።እዚህ መኪና ላይ ይለምናሉ።“ ከሆቴል ቤት ትርፍራፊ (ቡሌ) ይበላሉ።ነገር ግን የሚሰራ ነገር አግኝተው ገንዘብ ከሌላቸው ሳይበሉ ሊያድሩ ይችላሉ። አሁን ታዳጊ አላሮ ወደ አላባ መመለስ ይፈልጋል።
“ተወልጄ ያደኩትና ነዋሪነቴ እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው” ያሉን ወይዘሮ ቀለሟ ወይሶ ሌላዋ ጎዳና የወጡ የሦስት ልጆች እናት ናቸው።ጎዳና ለመውጣታቸው ዋናው ምክንያት ደግሞ የኑሮ ውድነቱን ነው።ልጆቻቸውን ያለ አባት ነው የሚያሳድጉት እነሱን ለማስተዳደር ይሰሯቸው የነበሩት ብዙ የጉልበት ሥራዎች አሁን የሉም፤ እንጀራና ዳቦ እየጋገሩ ገበያ አውጥቶ መሸጡ በዋናነት ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩበት የገቢ ምንጫቸውም ነበር።ስንዴና ጤፍ እየተወደደ በመምጣቱ ግን ሊያዋጣቸው ባለመቻሉ ትተውታል።በዚህ ምክንያት ደግሞ ለተከራዩት የግለሰብ ቤት ኪራይ መክፈል ቀርቶ ለልጆቻቸው የሚሰጡት ቁራሽ ሲያጡ ወደ ጎዳና ወጥተዋል።
በአሁኑ ወቅት በተለይ በመዲናችን አዲስ አበባ እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች ወደ ጎዳና የወጡበትና እየወጡም ያሉበት ሁኔታ አብዝቶ ይስተዋላል። የሴቶችና የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት ይሄንኑ እውነታ አረጋግጧል።በጉዳዩ ዙርያ ያነጋገርናቸው የሴቶችና የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እታገኝ አሰፋ እንደገለፁልን በተለይ በመዲናችን አዲስ አበባ በርካታ ሰዎች ወደ ጎዳና መውጣት እውነትነን ያለውና በእጅጉ አሳሳቢ የሆነ ጉዳይ በመሆኑ ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱም በትኩረት እየተሰራበት ነው።ሴቶች፤ ወጣቶች፤ አረጋዊያን፤ ሕፃናት፤ የአካል ጉዳተኞች ሁሉም ዓይነት የሕብረተሰብ ክፍሎች አሁን ላይ በተለይ ጎዳና የሚወጡ ዜጎች ሆነዋል።
ኃላፊዋ የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ በአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ በኩል የሚወጡት ምን ዓይነት የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደሆኑ፤ በምን ምክንያት እንደሚወጡ፤ ከየት አካባቢ እንደሚመጡ የሚያመላክት ሁኔታን ያካተተ ጥናት በአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ በኩል ማስጠናቱን ይናጋራሉ።በጥናቱ እንደተመላከተው ታዲያ ጎዳና ላይ የማናየው የሕብረተሰብ ክፍል የለም።ሴቶች፤ ወጣቶች፤ አረጋውያን፤ ሕፃናት፤ የአካል ጉዳተኞች ሁሉም ዓይነት የሕብረተሰብ ክፍሎችን እናስተውላለን።ምክንያታቸው ምንድነው ከተባለ በአብዛኛው የኑሮ ውድነት ነው።ኑሮውን መቋቋም ባለመቻላቸው ነው የሚወጡት።በተለይ ታዳጊዎችና ወጣቶች ከቤተሰብ ጋር በመጋጨት በድርቅ፤ በጦርነትና ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች በፍልሰት ከሌሎች ክልሎችም እንደሚወጡ ታይቷል። ከአዲስ አበባ ከተማ የወጡም ይገኙበታል።የአዲስ አበባዎቹ ቁጥራቸው በአጠቃላይ በመዲናዋ ከሚገኙትና ጎዳና ከወጡት 50 ሺህ ዜጎች ውስጥ አምስት በመቶውን እንደሚይዝ ጥናቱ ማሳየቱን ኃላፊዋ ያነሳሉ።የነዚህ ዜጎች ወደ ጎዳና መውጣት በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ ያስከተለው መዘዝ ዘርፈ ብዙ እንደሆነም ይናገራሉ።ከፍተኛ የኑሮ ጫና ማስከተሉ ዋናው እንደሆነ የሚጠቅሱት ኃላፊዋ ወደ ጎዳና የወጡት አምስት በመቶ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የመውጣታቸው መንስኤ ይሄው እንደሆነም መገመት እንደሚቻልም ይናገራሉ።መዘዙ በነዋሪው ላይ የምግብ፤ የመኖሪያ ቤት፤ የመጠጥ ውሀ አቅርቦትና ፍላጎቶች ላይ ከፍተኛ ጫና እያስከተለ ይገኛል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጫናውን በማቃለል ችግሩን ለመቅረፍ በተለይ ከክልል ፈልሰው ወደ አዲስ አበባ የመጡትን ወደ የመጡበት አካባቢ የመመለስ ሥራ በተደጋጋሚ ሲያከናውን መቆየቱንም ያስታውሳሉ።ተግባሩ ሲከናወን የነበረው የሚናገሩትን ቋንቋ መሰረት በማድረግ ነው ነገር ግን አማርኛ የሚናገር ሁሉ ከአማራ ክልል መጥቶ ላይሆን ይችላል፤ ከንባትኛ እየተናገረ ከሌላ ክልል ሊመጣም ይችላል።በመሆኑም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚናገሩትን ቋንቋ መሰረት አድርጎ የመጡበት ብሎ ወደሚገምተው ክልል በሚመልሳቸው ወቅት ክልሎቹ የኛ ስላልሆኑ አንቀበልም ስለሚሉ ሁኔታውን ፈታኝ አድርጎታል እንደ ኃላፊዋ ገለጻ።በሌላ በኩልም ስራው ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅም መሆኑን ያብራራሉ።
ለጊዜው እነዚህን የሕብረተሰብ ክፍሎች ለመሰብሰብ ማገገሚያ ተቋማት እንዲገቡ እየተደረገ ነው።በዚህ ምክንያት ለጊዜው አብዛኞቹ ወደ ጎዳና የወጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ወደ ማገገሚያ እንዲገቡ ይሆናል።ሆኖም በቂ ማረፊያ ይህ ብቻውን በቂ ባለመሆኑ ችግሩን በጊዜ እንዳይቀረፍ አድርጎታል ይላሉ።
በአጠቃላይ ጎዳና የወጣውን የሕብረተሰብ ክፍል ለማንሳት በቅድሚያ ጎዳና በቂ በጀት አለ ወይ፤ የሰው ኃይል በቂ ነው ወይ፤ በቂ ማቆያ አለው ወይ? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል የሚሉት ኃላፊዋ መሥሪያ ቤታቸው ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ባለፈው ያስጠናውን ጥናት መነሻ በማድረግ በቅርብ የመወያያ ጽሑፍ ማዘጋጀቱንም አንስተዋል።ጽሑፉ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ቀርቧል ብለዋል።
በርካታ የሕብረተሰብ ክፍሎች በችግር ተጋልጠው ወደ ጎዳና መውጣት ጉዳይ የአንድ ከተማ አስተዳደር ችግር ስላልሆነ የክልል ፕሬዚዳንቶች በሙሉ ባሉበት ጽሑፉ ቀርቦም ውይይት ይደረግበታል። ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወስድ ለማድረግ ይረዳል ብለው ያምናሉ።ሁሉም ሰው ከተረባረበበት ችግሩ ሊቀንስ ይችላል ያሉት ኃላፊዋ ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ቤተሰብ ላይ በትኩረት መሥራትና ለፍልሰቱም ለጎዳ ሕይወቱም ምክንያት የሆኑትን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች በተቻለ መጠን ተረባርቦ መቀነስ መፍትሄ እንደሚሆንም መክረዋል።እኛም መፍትሄው እንዳሉት የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ እንረባረብ መልዕክታችን ነው።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መጋቢት 14/2015