የዓለም አገራት አይናቸውን ኢትዮጵያ ላይ ከተከሉ ቆየት ብለዋል:: ልክ ሰጎን እንቁላል ስትፈለፍል አይኖቿን ከእንቁላሎቿ ላይ እንደማታነሳ ሁሉ የዓለም አገራት አይኖቻቸውን ኢትዮጵያ ላይ ተክለው ማንሳት ካቃታቸው ዓመታት እየተቆጠሩ ነው:: ሰጎንስ ፈልፍላ ስትጨርስ አይኖቿ ከእንቁላሎቿ ላይ ታነሳለች::
እነዚህ አገራት ግን እንኳን አይናቸውን ሊያነሱ ይቅርና ዕለት ተዕለት ስሟን የጣፈጣቸው እስኪመስል ድረስ ሳያነሷት ውሎ ማደር አልሆነላቸውም:: ይህ አልበቃ ብሏቸው በየጉባኤዎቻቸው የኢትዮጵያን ጉዳይ እንደ ራሳቸው ጉዳይ አጀንዳ አድርገውታል::
የኢትዮጵያ ውስጣዊ ሆነ ውጫዊ ጉዳዮች ይመለከተናል የሚሉት የዓለም አገራት በሁሉም ጉዳዮቿ ጣልቃ ከመግባት ባዝነው አያውቁም:: እራሳቸው ፈላጭ ቆራጭ አድርገው ስለሚያዩ የኢትዮጵያን ጉዳይ በእጃቸው አስገብተው እንደፈለጉት ሊያደርጉት እንደሚችሉ ያስባሉ::
የቅርቡን ብናነሳ እንኳን የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት የኢትዮጵያ ጉዳይ ከአስራ ሁለት ጊዜ በላይ አጀንዳ አድርጎ ማቅረቡን እናስታውሳለን:: አሁን ላይ ደግሞ የአረብ ሊግ ምክር ቤት የኢትዮጵያን ጉዳይ ቋሚ አጀንዳ ማድረጉ እየሰማን ነው::
ታዲያ እነዚህ አገራት ምን ፈልገው ይሆን ነጋ ጠባ የኢትዮጵያ ጉዳይ የራሳቸው ጉዳይ እንደሆነ ሁሉ መጨነቅና መጠበባቸው ስንል መጠየቅ ይገባል:: መቼም የሚፈልጉ አንዳች ነገር ከሌላቸው በስተቀር እንዲህ የሙጥኝ የሚሉበት ምክንያት ይኖራቸዋል ብሎ መገመት ይከብዳል ::
ኢትዮጵያን እንዲህ አይን ውስጥ እንድትገባ ያደረጓትን የተለያዩ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል:: ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የአፍሪካ አገራት በቀኝ ግዛት ለመቆጣጠር የነደፉትን ስትራቴጂ በማክሸፍ ብቸኛ አፍሪካዊት ፋና ወጊ አገር መሆኗ ዋንኛው ነው ::
ሌላው ደግሞ አሁን ላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካን ጉዳይ በአፍሪካውያንና በአፍሪካ ኀብረት አማካይነት ብቻ ሊታይ ይገባል በሚል የያዘችው ጽኑ አቋም የጎረበጣቸው ለመሆኑ ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል::
ይህ የኢትዮጵያ አቋም ደግሞ ዛሬ ላይ ለሚፈልጉት ዘመናዊ ባርነት እንዲመቻቸው የነደፉትን ስትራቴጂ ቀድሞ እያከሸፈባቸው መሆኑ ስለገባቸው እንዳሻቸው እንዳይፈነጩ ማሰሪያ ልጓም ሆኖ መቸገራቸው በምክንያትነት የሚጠቀሱ ናቸው::
ታዲያ በመንገዳቸው ሁሉ እንቅፋት እየሆነች አላማቸውን እንዳይሳካ እያስቸገረቻቸው እንደሆነ የሚገምቱትን ኢትዮጵያን እነሱ ወደ ሚፈልጉት መሥመር እስክትገባ ድረስ በሚችሉት መጠን ለማዳከም ከዚህ የተሻለ ምን ምክንያት ሊኖራቸው አይችልም::
ስለዚህ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ አማራጭ ይሆናል ብለው ያሰቡትን በውጫዊም ሆነ በውስጣዊ ጉዳዮቿ ጣልቃ ከመግባት ኢትዮጵያን ሰላም መንሳት ከተቻላቸው መበታተንና ማፍረስ በስውር እያሰሩበት ያለ ዓላማ ነው::
ይህንን ዓላማቸው ለማሳካት የማይሞክሩት፤ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም:: በተለይ ኢትዮጵያ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ያለምንም እርዳታ በራሷ ዜጎች አንድነትና ትብብር ለመገንባት መነሳቷ ከእንቅልፋቸው ያባነናቸው ግብጽና ሱዳን የግድቡ ግንባታ እንዳይካሄድ ብዙ ጥረት አድርገዋል::
ሕዳሴውን ግድብ በተመለከተ በሚደረጉ ድርድሮች ላይ አገራቱ በተደጋጋሚ የሀሳብ መዋዥቆችን ከማሳየት ጀምሮ፤ ግንባታውን ዓለም አቀፍ አጀንዳ ለማድረግ ረጅም ርቀት ሄደዋል። አሁን ላይም የአረብ ሊግ በቅርቡ ያወጣው መግለጫ የዚሁ እውነታ ማሳያ ነው ::
የአረብ ሊግ ለየት የሚያደርገው የኢትዮጵያ ግድብ ጉዳይ 140 ሚሊዮን አረብ አገራት ዜጎችን የሚመለከት ጉዳይ አድርገው መውሰዳቸው ነው:: መግለጫ በግልጽ ለግብጽ ያላቸውን ወገንተኝነት የሚያረጋግጥ ነው:: በዚህ ውስጥ እንደተለመደው የግብጽ እጅ ጎላ ብሎ ታይቷል::
የግብጽ አሁናዊ ማስፈራሪያ ‹‹ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳደራለች›› አይነት ነው:: የግብጽ አቋም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር እና የአፍሪካ ህብረት ድንጋጌን እንዲሁም ኢትዮጵያን ጨምሮ ግብጽና ሱዳን በግልጽ እ.ኤ.አ መጋቢት 2015 ያደረጉትን ስምምነት የሚጥስ ነው::
ግድቡን በተመለከተ ኢትዮጵያ በያዘችው ጠንካራ አቋም እና በተደጋጋሚ ባሳየችው ቁርጠኝነት ጉዳዩ በአፍሪካ ኀብረት በኩል እንዲታይ ተደርጓል። ይህ እውነታ አፍሪካውያን ችግሮቻችውን በራሳቸው አቅም መፍታት እንደሚችሉ እንደ አንድ ማሳያም ተደርጎ ተወስዷል። ይህ የአፍሪካዊነት ከበሬታ ግን ለግብጽ መንግስት ብዙም የሚዋጥለት አልሆነም::
ግብጽ በመርህ ደረጃ ሳይቀር ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ፍትሀዊ የውሀ አጠቃቀም ዙሪያ የተቀመጡ ዓለም አቀፍ ህጎችን ሳይቀር ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኗ፤ መቼም ቢሆን በሕዳሴው ግድቡ ዙሪያ ገንቢ አተያይ ሊኖራት አይችልም። ለዚህም ነው በየጊዜው በምትፈጥረው አዳዲስ አጀንዳ ለማደናቀፍ የምትሞክረው:: ግራም ነፈሰ ቀኝ በኢትዮጵያ ላይ የምትሸርበው ሴራ በዚህ የሚያበቃ አይመስልም::
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ከአሥር ዓመታት በፊት ጀምሮ ግብጽ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ በግድቡ አሞላል እና ኦፕሬሽን ከስምምነት ለመድረስ በርካታ ድርድሮችን አድርገዋል፤ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይም ስምምነት ላይ ቢደርሱም ስምምነቶቹን መሬት በማውረድ ሂደት ውስጥ ግን የግብጽ ዳተኝነት እንዳለ ነው።
ኢትዮጵያ የአባይን ውሀ ለብቻዬ ልጠቀም ሳትል፤ ሁሉን ተጠቃሚ በሚያደርግ መርህ ላይ በመመርኮዝ ታላቁን የህዳሴ ግድብ በመገንባት የውሃ ድርሻዋን በመጠቀም አገርና ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራች ነው:: ይህ ደግሞ በግብጽ በኩል ወንጀለኛ የሚያስብል እየሆነ ነው::
በርግጥ ግልጽነትን ለማስፈን ካልሆነ በስተቀር ዓለም አቀፍ ህግን ተከትሎ መስራት በራሱ የህጋዊነት ማረጋገጫና መሰረት ነው። ብዙ መጮህንና አድምጡኝ ማለትን የሚፈልግ አይደለም። ይህም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውነታውን በአግባቡ እንዲረዳና ከጎኗ እንዲሰለፍ ባለመሰልቸት በየጊዜው ድምጻን እያሰማች ትገኛለች::
አሁን ላይ የሕዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌትም መጠናቀቁን ይፋ ከተደረገ በኋላ በሁለት ተርባይኖች አማካይነት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ሥራ መጀመሩም የሚታወቅ ነው:: የግድቡ ግንባታም ከጥቂት ወራት በፊት 83 በመቶ መድረሱ ተገልጻል::
የሕዳሴው ግድብ ለኢትዮጵያውያን የኃይል ምንጭ ከመሆን ባለፈ አሁን ላለው ሆነ ለሚመጣው ትውልድ የይቻላል መንፈስ ዘር ሆኖ የሚያገለግል፤ የአገርና የህዝብን አንገት ቀና ማድረግ የሚያስችል የልብ ፈውስ የሚያመጣ ፕሮጀክት እንደሆነ ይታመናል። ይህም ኢትዮጵያውያን በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ወደኋላ የሚመልሳቸው አንዳች ነገር እንደማይኖር የማረጋገጫ ማሕተም ነው::
ለዚህም ነው ያለማንም ድጋፍ ያላቸውን ቋጥረው የታላቁን የሕዳሴ ግድብ ከፍ ባለ አንድነትና መተባባር ጀምረው አሁን ያለበት ደረጃ ያደረሱት፤ እስከ ፍጻሜውም ለመጓዝ በፅናት የተሰለፉት:: ትናንት በአድዋ ያሳዩትን ተምሳሌታዊ ገድል በግድቡ ለመድግም ቀን ከለሊት የሚተጉት:: ሰላም::
ትንሳኤ አበራ
አዲስ ዘመን መጋቢት 14/2015