የለውጥ ኃይሉ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ መንግስት መሆኑን ተከትሎ በአገር ውስጥም ሆነ ውጪ ያሉ አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ በድርድር የሚፈቱበትን አቅጣጫ አስቀምጧል፤ በሮቹን ለውይይትና ለድርድር ክፍት በማድረግም በመተማመን ላይ የተመሰረተ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ረጅም መንገድ ተጉዟል። በዚህም በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍያለ እውቅና ተችሮታል።
በተለይም በአገሪቱ ፖለቲካ ዘመናት ያስቆጠረውን ፤ አገርና ሕዝብን በየዘመኑ ብዙ ዋጋ ያስከፈለውን የሴራ ፖለቲካ በመቀየር፤ በመተማመን ላይ የተመሰረተ አዲስ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ፤ በብዙዎችም ዘንድ ከፍያለ ተስፋ የተጣለበት መሆኑ የሚታወስ ነው።
በመንግስት እና በተቃዋሚ ኃይሎች መካከል ይዘነው የመጣነውን በጠላትነት የመፈራረጅ ባህል በመቀየር ተቃዋሚ ኃይሎች ለአዲሱ የፖለቲካ ዕሳቤ መበልጸግ ተጨማሪ አቅም የሚሆኑበትን የተሻለ እድል ይዞ የመጣ፤ ይህም በአብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ መልካም ጅማሮ ተቀባይነት አግኝቶ በተወሰነ ደረጃ መተማመን ፈጥሮም ነበር።
በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአገር ውስጥ ትልቅ የለውጥ ሀዋርያ ተደርገው የተወሰዱበት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም የዓለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ የሆኑበት እውነታ ታሪካዊ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህም የአገራችን ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተሻሻለ የመጣበት ሁኔታም በስፋት ተስተውሏል ።
ይህ ተስፋ ሰጭ እውነታ አገራዊ የፖለቲካ ምህዳሩን እያጠራ ባለበት ሁኔታ ፤ ቁጭ ብሎ መነጋገርን ሆነ ቁጭ ብሎ በመነጋገር ችግሮችን ለማስወገድ የተያዘው የመንግስት የፖለቲካ አቅጣጫ በአንዳንድ ወገኖች ያልተገባ ትርጓሜ በመያዙ፤ አገር ወዳልተገባ ጦርነት ውስጥ ለመግባትና በዚህም ብዙ ዋጋ ለመክፈል ተገዳለች።
በተለይም መንግስት ከሕወሓት ጋር የነበረውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት፤ ከፖለቲካ መስመሩ በተጨማሪ የአገር ሽማግሌዎችንና እናቶችን በመላክ የሄደበት ርቀት የቱን ያህል ለሰላም የነበረውን ቁርጠኝነት በተጨባጭ ያመላከተ ነበር።
ይህም ሆኖ ግን በአሸናፊና ተሸናፊ ትርክት ላይ የተመሰረተው እና ዘመናት ያስቆጠረው አሮጌው የፖለቲካ አስተሳሰብ ባጠላው የጥፋት ጥላ አገርና ሕዝብ ወዳልተፈለገ ጦርነት ገብተው፤ የሽግግር ወቅት ፖለቲካውም ባልተጠበቁ ተግዳሮቶች ለመፈተን ተገዷል።
መንግስት አገርንና ሕዝብን ከየትኞቹም የሽብር ጥቃቶች የመከላከል የህግና የሞራል ኃላፊነት ስለነበረበት፤ በአንድ በኩል በአገር ላይ በግልጽ የታወጀውን ጦርነት እየመከተ፤ በሌላ በኩል ቀድሞ የጀመረው የሰላም ጥረት ፍሬ እንዲያፈራ በኃላፊነት መንገድ ተንቀሳቅሷል።
ብዙ መስዋዕትነት የጠየቀውን ግጭት በዘላቂ የሰላም ስምምነት በመቋጨት ከቀደመው የአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት በመውጣት አገር እንደ አገር አሸናፊ የምትሆንበትን የሰላም ስምምነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ ተፈራርሟል። በዚህም አገራዊ የግጭት አፈታት ስርአታችን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ እንዲገባ አስችሏል።
ትናንት የኢፌዴሪ ተወካዮች ምክር ቤት ሕወሓትን ከሽብርተኝነት መዝገብ የማንሳቱ ውሳኔ የዚሁ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አንድ አካል ነው፤ መንግስትም ሆነ ሕወሓት ቀደም ሲል ለተደረሱ ስምምነቶች ተገዥ ስለመሆናቸው እንደ አንድ ማረጋገጫ ተደርጎም የሚወሰድ ነው።
ውሳኔው በጦርነቱ ውድ ዋጋ የከፈሉ የአገራችንን ሕዝቦች በሰላም ለመካስና ከግጭት ይልቅ ለሰላም እና ለሰላም እሴቶች ትኩረት ለመስጠት እንደ ትልቅ አቅም የሚቆጠር ነው።
ከግጭትና ከጦርነት ከሰብአዊ እልቂትና የሀብት ውድመት ውጪ ማንም ተጠቃሚ ሊሆን እንደማይችል፤ ከዚህ ባለፈ በአሸናፊና ተሸናፊ ትርክት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ዕሳቤ አገር እና ሕዝብን ያልተገባ ዋጋ ከማስከፈል ባለፈ የተረጋጋች እና የበለጸገች አገር መፍጠር እንደማያስችል በአግባቡ ለመረዳት የተሻለ አጋጣሚ የሚፈጥርም ነው፡፡ በአጠቃላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ የተጀመረውን የሰላም ሂደት ለፍሬ ለማብቃት የተወሰደ በጎ ርምጃ ነው ማለት ይቻላል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 14/2015