ማህበራዊ ደህንነቱ የተረጋገጠ ሕዝብ ማህበራዊ ፍትህና ተጠቃሚነቱ ይበልጥ ይረጋገጣል። ማህበራዊ ችግሮቹም ተቀርፈው ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንደሚኖር ሁሉንም የሚያስማማ ሐቅ ነው። በመሆኑም ማህበራዊ ችግሮችን በመቅረፍ ማህበራዊ ደህንነትን በማረጋገጥ ሂደት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
በሀገራችን ከጥንት አባቶቻችን ጀምሮ በቅብብሎሽ የመጣው የዜጎች የእርስ በእርስ መረዳዳት ባህል በጣም አስደሳችና ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው። ይህ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንቅስቃሴ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ከተከሰተበት ጊዜ ይበልጥ ጎልቶ መውጣት እንደቻለ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
በኢትዮጵያ ቃላት በማይገልጸው የኑሮ ውድነትና የመኖሪያ ቤት እጦት ምክንያት እየተንገላታ ያለውን የሕዝብ ቁጥር ሆድ ይፍጀው። ምንም እንኳን አብዛኛው ዜጋ የዚህ ገፈት ቀማሽ ቢሆንም ችግሮቹን ለመቅረፍ መንግሥትም ይሁን መላው ሕዝብ የበጎ ፍቃድ ስራዎችን በዚህ ችግር ወቅት ከማድረግ ይልቅ የበዓላትና የክረምት ወቅትን ሲጠብቁ ነው የሚስተዋለው።
በዓላትን ጠብቀው በኑሮ የተጎሳቆሉ እናቶችንና አቅመ ደካሞችን ከተለያዩ ስፍራዎች በመሰብሰብ ጥቁር መነፅር አድርጎ ከፊት ለፊት ካሜራ ደቅኖ ዘይትና ዱቄት ማደል በሀገራችን የተለመደ ተግባር ነው። የመስጠት መጥፎ የለውም ይሁን። እኔን ‹‹አጃኢብ›› የሚያሰኘኝ ነገር ግን ከመስጠቱ ጀርባ ለሳምንት የማይሆን ሸቀጥ ድጋፍ ለማድረግ የሚዲያዎች ጋጋታና የሚደረጉ ቃለመጠይቆች በተረጂዎቹ ሥነ ልቦና ላይ ምን አይነት ጫና ሊያሳድር እንደሚችል ማሰቡ ነው።
ለሌላው መርዳት መልካም ስራ ሆኖ ሳለ የካሜራ ጋጋታና ተረጂ ዜጎችን ቃለ መጠይቅ ማድረጉ ለምን እንዳስፈለገ አይገባኝም። እግዜሩም ቢሆን የሚደረጉ መልካም ተግባራት ለፅድቅ እንጂ ለካሜራ እይታ ሲሆን ደስ የሚለው አይመስለኝም። የምታደርጉትን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በልባችሁና ከካሜራ ጀርባ ቢሆን እንዴት ጥሩ ይሆን ነበር ብዬ አሰብኩኝ፤ እናንተም ሀሳቤን እንደምትጋሩ እምነቴ ነው። ሕይወታችን የካሜራ ሰለባ እንደሆነ ይሰማኛል። በየማህበራዊ ትስስር ገፃችን የምንለጥፈው ፎቶግራፍ እና በገሀዱ ዓለም ኑሯችን የተለያየ መሆኑ የሚታወሰኝ የሚያምር ህንፃና አረንጓዴ ስፍራዎችን ስናገኝ ያለማንገራገር ፎቶ ስንነሳ ነው።
ወደ ጉዳዬ ስመለስ፤ እነዚህን ዜጎች በዓል በመጣ ቁጥር ሸቀጥ ከማደል ይልቅ በቋሚነት ስራዎችን በመስራት ከራሳቸው አልፎ ለቤተሰቦቻቸው የሚተርፉበትን እድል በማመቻቸት የመንግስትም ይሁን የግለሰቦችን እጅ እንዳይጠብቁ ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው። በዓል ሲመጣ እርዳታ ማድረጉ በጣም የሚያስመሰግን ነው፤ ዳሩ ግን ለታይታ የምንጥረውን ያህል ከችግር የሚወጡበትን መንገድ ለማመቻቸት ብንሰራ ለተረጂዎችም ለአገርም የበለጠ ጠቃሚ ይሆናል።
ክረምት ሲመጣ አካፋና ዶማ ይዞ ያረጁ ቤቶችን የማደስ ስራ ለምን ዘወትር እንደማይካሄድ ሌላኛው ጥያቄዬ ነው። ለዚህ ተግባር ከክረምት ይልቅ በጋ የተሻለ እንደሆነ ግልጽ ነው። ምክንያቱም የሚታደስላቸው ዜጎች አይቸገሩም።
ሕዝቡ የበጎ ፍቃድ ስራዎች ላይ ያለው ተሳትፎ የሚበረታታ ቢሆንም፤ ታዲያ ይሄንን በተደራጀ መልኩ የሚያሰራ የመንግስት ተቋምም ሆነ የሲቪል ማህበራት እንደሚያስፈልጉ ሳይታለም የተፈታ ነው።
አገራችን እያራመደችው ያለውን የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ ስኬታማ ለማድረግ እንዲቻል በጎ ፈቃደኛ ዜጎች በአካባቢ ልማት፣ በችግኝ ማፍላትና ተከላ፣ በደን ልማት፣ ሀገር በቀል ዝርያዎችን በማፍላትና በመትከል ሂደት ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ ማስቻል ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው።
እንደ ኢትዮጵያ ያሉና በኢኮኖሚ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት የአደጋ ስጋትና ተጋላጭነትን ለመቋቋም ያላቸው አቅም ውስን በመሆኑ ለከፋ ችግርና ቀውስ ሲጋለጡ ይስተዋላል። በመሆኑም የአደጋ ተጋላጭነትንና ችግርን በዘላቂነት ለመቅረፍ በሚከናወነው ስራ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጉልህ ሚና አለው።
በጎ ፈቃደኛ ዜጎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በመደገፍና መልሶ በማቋቋም፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስና በመገንባት፣ ወላጆቻቸውን ያጡና ለችግር የተጋለጡ ህፃናትን በመንከባከብ፣ አካል ጉዳተኞችንና አረጋውያንን በመንከባከብ፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችንና ሌሎች ተጋላጭ ዜጎችን መርዳትና መደገፍ አለባቸው።
ሰላም ልማትና ዕድገት በቀላሉ ለማረጋገጥ የሚያስችል ቁልፍ መሳሪያ በመሆኑ ለዘላቂ ሰላም መስፈን የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ርብርብ በተለይም ደግሞ የወጣቱ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን በአግባቡ በመጠቀም ለሀገር ግንባታ ልናውል እንደሚገባ አምናለሁ፤ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዜጎች በአዎንታዊ አስተሳሰብ ስብዕናቸው እንዲገነባ አስተዋጽኦ ያደርጋል። በዚህ መንገድ ያለፉ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሻለ ስብዕና ኖሯቸው ስለሰውና ስለሀገር እንዲያስቡ ያስችላል። በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚከናወኑ ተግባራት ለሀገር ከሚሰጡት ጠቀሜታ ባሻገር በገንዘብ ቢተመን መንግስት ሊያወጣ የሚችለውን ከፍተኛ ወጪ ማዳን እየተቻለ እንደሆነ ግልፅ ነው።
ወጣቶች የበጎ አድራጎት ስራዎችን በሚያከናውኑበት ጊዜ እውቀት፣ ባህል፣ በአንድነትና በፍቅር አብሮ የመኖር እሴቶችን ከማህበረሰቡ ያገኛሉ። አንድ ዜጋ ደም በሚለግስበት ወቅት የሱ ደም ዘርና ጎሳን ሳይለይ የሰው ፍጥረትን ይታደጋል።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን በአግባቡ ከተጠቀምንበት እድሜ፣ ጾታ፣ ብሔር፣ ፖለቲካና ኃይማኖት ሳይገድባቸው ዜጎች ጥላቻንና ቁርሾን በመተው የሚሳተፉበትና ለሀገር ግንባታ ያለው ሚና ትልቅ በመሆኑ ህብረተሰቡ ስለ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ሚዲያዎችና ሁሉም ባለ ድርሻ አካል ሊረባረብ የሚገባው ጊዜና ወቅት ጠብቆ መሆን የለበትም።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን በተደራጀ መልኩ ለማስቀጠል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተለያዩ የበጎ ፍቃድ ህብረቶችን በመፍጠር በሌላው የዓለም ክፍል ላይ ያሉትን መልካም ተግባራት ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋትና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ፖሊሲ በማዘጋጀት ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶ ቢሰራበት ብዙ ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚያገኙ እሙን ነው።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም