የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በስሩ ከሚገኙ አራት ዘርፎች መካከል የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ዘርፍ/ኢትፍሩት/ አንዱ ነው።ዘርፉ “ኢትፍሩት” ተብለው በሚታወቁት መሸጫ ኮንቴነሮቹ በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ለሸማቾች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ይታወቃል።
በዛሬው የንግድና ግብይት አምዳችን ይህ ዘርፍ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ለሸማቾች በማቅረብ እያከናወነ ያለውን ተግባርና የድርጅቱን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ አስመልክቶ ከአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መህዲ አስፋው ጋር ያደረግነውን ቆይታ ይዘን ቀርበናል።መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፦ የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ዘርፍ የሚያከናውናቸውን ዋና ዋና ተግባራት ቢያብራሩልኝ?
አቶ መህዲ፦ የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ዘርፍ ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎችን ይዞ ይሰራል። በቀዳሚነት አምራቾችን የመደገፍ አላማ ያለው።ይህም ሲባል አምራቾች አምርተው ገዢ እንዳያጡ ካሉበት ቦታ ሄዶ ይገዛል።በተለይም ዋጋ በሚቀንስበት ጊዜ ከአዲስ አበባ ከተማ ራቅ ባሉ አካባቢዎች ጭምር በመሄድ ምርታቸውን ያነሳል።በዚህም ሸማቾች ምርቱን እንዲያገኙ እድሉን ይፈጥራል።ሁለተኛው ከአምራቹ የመጣውን ምርት ከተማ ውስጥ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች እንዲሁም በክልል ከተሞች በሚገኙ ማከፋፈያዎችና የሽያጭ መደብሮች አማካኝነት በተመጣጣኝ ዋጋ ያከፋፍላል።
በተያዘው 2015 በጀት አመት ባለፉት ሰባት ወራትም 40 ሺ ኩንታል የሚደርሱ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ከተለያዩ አካባቢዎች ገዝቶ ለተጠቃሚው ማሰራጨትና ማከፋፋል ችሏል።ይህም በገንዘብ ሲተመን 150 ሚሊዮን ብር ይደርሳል።በሰባት ወራት ውስጥ ለማህበረሰቡ ተደራሽ ካደረጋቸው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት አይነቶች ከፍራፍሬ ምርት በዋናነት ብርቱካን፣ ማንጎ፣ ሙዝ፣ ከአትክልት ምርት ደግሞ ቲማቲም፣ ድንች፣ ስኳር ድንች ይጠቀሳሉ።
አዲስ ዘመን፦ ለገበያ ራቅ ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ አምራቾች ምርት አምርተው ገበያ ሲያጡ ምርቱ የሚበላሽበት አጋጣሚ ይፈጠራል። ለዚህ ችግር የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ዘርፍ አምራቹን እንዴት እያገዘው ይገኛል?
አቶ መህዲ፦ የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ዘርፉ ረጅም ርቀት ተጓጉዞ ከአምራቹ ምርቱን በመግዛት አምራቹ ተጠቃሚ እንዲሆንና በቀጣይም የማምረት ፍላጎት እንዲኖረው ያበረታታል።ባለፈው ዓመት ከአዲስ አበባ ዘጠኝ መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኘው በደቡብ ኦሞ ዳሰነች ወረዳ ውስጥ በመግባት የሰራበትን ሁኔታ በአብነት መጥቀስ ይቻላል።በወቅቱ የክልሉ መንግሥት በአካባቢው የሚገኙ አርብቶ አደሮችን ወደ ከፊል አርሶ አደር ለመለወጥ በያዘው ፕሮጀክት በርካታ አርሶ አደሮች የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን አምርተው ነበር።ነገር ግን በአካባቢው መሰረተ ልማት የተሟላ ባለመሆኑ ወደ አካባቢው ገብቶ ምርቱን የሚገዛ ነጋዴ ባለመኖሩ አርሶ አደሮቹ ያመረቱትን ምርት ለገበያ ማቅረብ አልቻሉም ነበር።በመሆኑም የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ዘርፍ ወደ አካባቢው በመጓዝ ምርቶቹን ገዝቶ ወደ ማዕከላዊ ገበያ እንዲቀርቡ አድርጓል።
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ አማካኝነት የሰዎችና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ በተገደበበት ወቅትም እንዲሁ በሰሜን ሸዋ ጫጫ አካባቢ እያንዳንዱ አርሶ አደር ከአራት መቶ ኩንታል በላይ ካሮት አምርቶ ገዢ ያጣበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር።በዚህ ወቅትም የአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ንግድ ሥራ በአካባቢው ተገኝቶ ምርቱን ወደ ማዕከላዊ ገበያ በማምጣት ለማህበረሰቡ ተደራሽ አድርጓል።ይህን የተመለከቱ ሌሎች ነጋዴዎችም ወደ አካባቢው በመግባት ምርቱ ሳይበላሽ ወደ ተጠቃሚው ማድረስ ችለዋል።በመሆኑም የታሰበውን ያህል ጉዳት በአርሶ አደሩ ላይ እንዳይደርስ በማድረግ የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ዘርፉ ጉልህ ሚና ተጫውቷል።
በቅርቡም አፋር ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው የቲማቲም ምርት ተመርቶ በአካባቢው አንድ ኪሎ ቲማቲም እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ በብር አምስት ብቻ ሲሸጥ ነበር።ይህንንም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ወደ አካባቢው በመግባት የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ዘርፉ ምርቱን ማንሳት ችሏል።አምራቹ ለምርቱ ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ በማድረግ በአሁኑ ወቅት አፋር ላይ አንድ ኪሎ ቲማቲም ከ17 እስከ 20 ብር የሚሸጥበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።በመሆኑም የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ዘርፍ አምራቹን ከመደገፍ ባለፈ ለነዋሪዎች የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን እየሠራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፦ የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ዘርፉ በዋነኝነት ምርቶቹን ተደራሽ የሚያደርገው ለየትኞቹ አካባቢዎችና የማህበረሰብ ክፍሎች ነው?
አቶ መህዲ፦ ዘርፉ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አራት ማከፋፈያዎችና 52 የሽያጭ መደብሮች አሉት።እነዚህ የሽያጭ መደብሮች የሚገኙትም በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ሲሆን፤ ከስድስት ኪሎ ጀምሮ እስከ አቃቂ እንዲሁም ከጦር ኃይሎች ወይም ከአየር ጤና አንስቶ እስከ ሲኤምሲ ሃያት አደባባይ ድረስ የመሸጫ ሱቆች ወይም ኮንቲነሮች አሉ።በአጠቃላይ በከተማዋ በሁሉም አካባቢዎች ማለት በሚቻል መልኩ በሚገኙት በእነዚህ ሱቆች አማካኝነት ህብረተሰቡ ማግኘት ይችላል።በእነዚህ የመሸጫ ሱቆችም መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ናቸው ተጠቃሚ የሚሆኑት።
አዲስ ዘመን፦ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን እንዴት ነው የምታገኙት?
አቶ መህዲ፦ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ከተመረቱባቸው አካባቢዎች የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም እናነሳለን።አንደኛው ከገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበራት፣ ከዩኒየኖች፣ ከኮሜርሻል ፋርሞችና በቀጥታ ከገበሬዎች ማሳ ላይ በመግዛት ምርቶቹን ሰብስበን፣ አከማችተንና አዘጋጅተን ለማህበረሰቡ ተደራሽ እናደርጋለን።
አዲስ ዘመን፦ ዘርፉ ከአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በተጨማሪ ለማህበረሰቡ የሚያቀርባቸው ምርቶች ምንድናቸው? እሴት ጨምሮ በማቅረብ ረገድስ ምን እየሠራ ነው?
አቶ መህዲ፦ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ይበልጥ ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግ በጥሬው ብቻ ሳይሆን ወደፊት እሴት ጨምሮ ለማቅረብ እየተሠራ ነው።የተለያዩ ሥራዎችን ለአገር በሚጠቅም መንገድ ለመሥራት ኮርፖሬሽኑ አቅዶ እየሠራቸው ከሚገኙ ሥራዎች መካከል አሽጎ ማቅረብ አንዱ ነው።
እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ ባለው እቅድ መሰረት ፍራፍሬና ስኳርን አሽጎ ለገበያ ማቅረብ የሚያስችሉ ማሸጊያ ማሽኖች ተተክለዋል።በመሆኑም ወደፊት ስኳርና ፍራፍሬዎች ከኢትፍሩት ማከፋፈያ ሱቆች በተጨማሪ በተለያዩ ሱፐርማርኬቶች ጭምር ታሽገው እንዲቀርቡ ይደረጋል።ይህም ዘርፉን በማሳደግ ይበልጥ ውጤታማ ሊያደርገው ይችላል።ኮርፖሬሽኑ በአስር ዓመት ውስጥ አሳካዋለሁ ብሎ ከያዛቸው ተግባራት መካከል በተለይም እሴት በመጨመር ረገድ የሚሠሩ የተለያዩ ሥራዎችን በሂደት ተግባራዊ የሚያደርግ ይሆናል።
ፍራፍሬዎች ሳይበላሹ ለብዙ ጊዜ መቆየት እንዲችሉ በማድረግ አሽጎ ለገበያ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት በሰዎች ጤና ላይ ጉዳት የማያደርሱ የተለያዩ ኬሚካሎች ማሸጊያው ላይ ይቀባሉ።ወደፊትም ምርቱ የሚታሸጉት እነዚህ ኬሚካሎች ተቀብተው ነው።ይህም የፓኬጁን ደረጃ በጠበቀ መንገድ የሚዘጋጅ ሲሆን፤ ምርቶቹም ከኢትፍሩት በተጨማሪ በሱቆችና በሱፐር ማርኬቶች ለገበያ የሚቀርቡ ይሆናል።ይህም እሴት በመጨመር ረገድ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚራምድ ነው።በአሁኑ ወቅትም ማሽኑ ተተክሎ አንዳንድ የማጠናቀቂያ ሥራዎች የሚቀሩ ሲሆን፤ በቀጣይም ቀሪ ሥራዎችን በማጠናቀቅ የፍራፍሬ ምርቶቹ ታሽገው ለገበያ የሚቀርቡ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፦ የዋጋ ግሽበትን ከመከላከልና ገበያን ከማረጋጋት አንጻር ያለው ሚናስ ምን ይመስላል?
አቶ መህዲ፦ የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ስራ ዘርፍ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች የሚያገለግል እንደመሆኑ የዋጋ ንረትን ከመከላከል አንጻር በተቻለ መጠን ገበያን ለማረጋጋት ይሰራል።የምርቶች ዋጋ የሚተመነውም እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ባገናዘበ መልኩ ነው።
ዘርፉ በገበያው ካለው የምርቶች ዋጋ እስከ 40 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ አለው።አብዛኛው ምርት በዚህ መጠን ልዩነት ያለው በመሆኑ በተጠቃሚው ማህበረሰብ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያለው ተቋም ነው።
በተለይም በአሁኑ ወቅት ባለው ከፍተኛ የሆነ የኑሮ ውድነት ዘርፉ እስከ 40 በመቶ ልዩነት በመያዝ ከአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በተጨማሪ የተለያዩ የሰብል ምርቶችንም ጭምር ለማህበረሰቡ በማቅረብ ገበያን የማረጋጋት ሥራ ይሠራል።በመሆኑም ለአብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ዘርፉ ተመራጭና ፋታ የሚሰጥ ሆኗል።በዚህ ረገድ በተለይም የኑሮ ውድነቱ በህብረተሰቡ ላይ ጫና እንዳያሳድር በማድረግ አንጻር አበርክቶው የጎላ እንደሆነ ይሰማናል።
ዘርፉ በኢትፍሩት መደብሮቹ አማካኝነት ለማህበረሰቡ እያሰራጫቸው ከሚገኘው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በተጨማሪ የተለያዩ የፍጆታ ዕቃዎችን በማቅረብ ለህብረተሰቡ ሰፊ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።ለአብነትም የስኳር ምርትን ከስኳር ኮርፖሬሽን ተቀብሎ ለሆቴል፣ ለሬስቶራንት፣ ለካፌዎች፣ እንዲሁም የመንግሥት ተቋማት ለሆኑ ሆስፒታሎችና ለሌሎችም በማከፋፈል ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።በተመሳሳይ የዘይት ምርትንም እንዲሁ በኮርፖሬሽኑ አማካኝነት ከውጭ አገር በማስመጣት ለሸማቾችና ለመንግሥት ተቋማት ያከፋፍላል።
አዲስ ዘመን፦ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በማስቀረትና በአገር ውስጥ በመተካት እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ብልሽትን በመከላከል ረገድ ዘርፉ ምን እየሠራ ነው?
አቶ መህዲ፦ ፍራፍሬን በሚመለከት በቅርቡ ለማስተዋወቅ የአፕል ምርትን ከውጭ ከሚያስገቡ አስመጪዎች በመቀበል የማከፋፈል ሥራ እየሠራ ነው።ይህም ለማስተዋወቅ ተብሎ በቅርቡ የተጀመረ ሥራ ሲሆን፤ ወደፊት ግን በጥናት የምናየው ይሆናል።ነገር ግን ዘርፉ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የአትክልት ዘሮችን ከውጭ አገር በማስመጣት ለአምራቾች ማለትም ለዩኒየኖች፣ ለህብረት ሥራ ማህበራትና ለሌሎች ኮሜርሻል ፋርሞች የማከፋፈል ሥራ ይሠራል።ይህም ከውጭ የሚገቡ የአትክልት ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የሚደረገውን ጥረት የሚያበረታታ ነው።
በአሁኑ ወቅትም የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ተግባራዊ ሊያደርገው የተዘጋጀው ባለማቀዝቀዣ መጋዘን ዘርፉን ውጤታማ ማድረግ እንደሚያስችል ይታመናል። በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት ለብልሽት የሚጋለጡ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ለመታደግ ኮርፖሬሽኑ 10 ሺ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ በአንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር የሚስገነባው ህንጻ አይነተኛ ሚና ይኖረዋል።ምርቶቹ ሳይበላሹ ወደ ገበያ መድረስ እንዲችሉ ጉልህ አበርክቶ የሚኖረው ይህ ባለማቀዝቀዣ መጋዘን አትክልትና ፍራፍሬዎች ውድ በሆኑ ጊዜና ምርት በስፋት በሚገኝበት ወቅት በብዛት ገዝቶ ለማቆየት ያስችላል።የምርት እጥረት በሚፈጠርበት ወቅትም ምርቱን አውጥቶ ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የማድረግና ገበያን በማረጋጋት ረገድ አበርክቶው የጎላ ነው።
ከኤክስፖርት አንጻር እንዲሁ ጠቀሜታው የጎላ ነው፤ የአምራቾችን የፍራፍሬ ምርት ገዝቶ፣ አቆይቶ፣ አከማችቶና አዘጋጅቶ ጥራቱን በጠበቀ መንገድ ለውጭ ገበያ እንዲደርስ በማድረግ ለአገሪቷ የውጭ ምንዛሪ እድገት ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።
አዲስ ዘመን፦ በሀገራችን የአትክልትና ፍራፍሬ የብክነትና የብልሽት ምጣኔ ምን ያህል ነው?
አቶ መህዲ፦ አትክልትና ፍራፍሬ እየነገዱ ብክነትና ብልሽትን መቀነስ ይቻል ይሆናል እንጂ መቶ በመቶ ማስወገድ አይቻልም።ከዚህ አንጻር ዘርፉ በ40 ዓመት ቆይታው ምንም እንኳን የአትክልትና ፍራፍሬ ማቀዝቀዣ መጋዘኖችና መኪናዎች ባይኖሩትም ሠራተኛው በዘርፉ የረጅም ጊዜ ልምድ ያለው በመሆኑ በተለይም ምርቶቹ ሲገቡ በምን አግባብ መግባት እንዳለባቸው፤ እና ሲወጡ እንዴት መውጣት አለባቸው በማለት የራሱን የአሰራር ዘዴ በመጠቀም የብክነትና የብልሽት መጠን ይቀንሳል።በመሆኑም የምርት ብልሽትና ብክነትን በከፍተኛ ደረጃ እየቀነስ መጥቷል።ከዚህ በተጨማሪም ኢትፍሩት ካይዘንን ተግባራዊ በማድረግ የምርት ብልሽትን በመቀነስ ረገድ ለውጥ ማምጣት ተችሏል።
ተቋሙ ስድስት በመቶ ያህሉን የአትክልትና ፍራፍሬ ብክነትን መቀነስ የቻለ ሲሆን፤ ብክነቱ በትነት መልክም የሚፈጠር እንደመሆኑ አትክልትና ፍራፍሬ ከፍተኛ እርጥበት በውስጣቸው የያዙ በመሆናቸው በትነት መልክ የሚፈጠር ብክነትን ሁለት በመቶ፤ ብልሽትን ደግሞ አራት በመቶ በድምሩ ስድስት በመቶ ብክነትንና ብልሽትን መከላከል ተችሏል።ከዚህ በተሻለ ለመከላከልም እየተሠራ ነው።ይህም እንደየአገራቱ ባህሪው የተለያየ መጠን ያለው ሲሆን እንደ አገር የኢትፍሩትን የብክነትና የብልሽት መጠን ብንመለከት አነስተኛ ነው ብለን ማለት እንችላለን።
አዲስ ዘመን፦ ለቃለ ምልልሱ ላደረጉልን ትብብር በእጅጉ እናመሰግናለን!
አቶ መህዲ፦ እኔም አመሰግናለሁ!
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም