በሰሜናዊ የሀገራችን ክፍል ለሁለት ዓመት የቆየው ጦርነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተቋጭቷል። ጦርነቱ ሀገርና ሕዝብን ለከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጥፋት ዳርጓል። ጥሎት ያለፈው ጠባሳም በአግባቡ ያላገገመ፤ ለማገገምም ጊዜ የሚፈልግ እንደሆነም ይታመናል።
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ወቅት ጀምሮ ከጦርነቱ ለማትረፍ ብዙ አካላት ራሳቸውን/ እጃቸውን አስገብተዋል። የአንድን ቡድን ፍላጎትና ዓላማ ታሳቢ ያደረጉ ፍትሃዊነት የጎደላቸው እና ወገንተኝነት የተላበሱ ተግባራት በአደባባይ ሲከወኑ እና ሲደመጡ ተስተውለዋል።
መንግስት ችግሩን በሰላማዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት ያደረጋቸውን ጥረቶች የሚገዳደሩ የአንድን ቡድን አሸናፊነት የሚናፍቁ፣ ለዚህም የተገዙ ያልተገቡ ተግባራት በተለይም ከአንዳንድ ሀገራትና ከመገናኛ ብዙኀኖቻቸው በስፋት ታይተዋል።
እነዚህ ሀገራትና መገናኛ ብዙኀኖቻቸው ሀገርን ከጥፋት የመታደግ የህግና የሞራል ኃላፊነት ያለበት የኢትዮጵያ መንግስት ፤ ይህን ኃላፊነቱን ለመወጣት ያደረጋቸውን ጥረቶች ያልተገባ ትርጉም ከመስጠት ጀምሮ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሳሳተ ትርጉም እንዲይዙ በተናበበና በተቀናጀ መንገድ ተንቀሳቅሰዋል።
መንግስት ከጦርነቱ አትራፊ ሊሆኑ የሚችሉት ለሀገሪቱ በጎ የማያስቡ ኃይሎችና ቡድኖች ናቸው በሚል፤ በአንድ በኩል በኃይል ሕዝብን ለማንበርከክ የተደረገውን ጥረት በኃይል እየመከተ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለዘላቂ ሰላም ቁጭ ብሎ መወያየትን ግብ አድርጎ በሀገሪቱ በድርድር ላይ የተመሰረተ ሰላም እንዲሰፍን አድርጓል።
ከዚህም ባለፈ በጦርነቱ ለተጎዱ አካባቢዎች አስፈላጊ የሆኑ ሰብዓዊ ርዳታዎች እንዲቀርቡ እያደረገ ነው፤ አስፈላጊ የመሰረተ ልማት አቅርቦቶች እንዲሟሉም በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። አብዛኞቹ የግጭት አካባቢዎች ወደ ቀደመው ሕይወት እንዲመለሱም በትኩረት እየሰራ ነው።
መንግስት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረሰ ስምምነት መሰረት፤ ከሕወሓት ጋር ተቀራርቦ በመስራት ስምምነቱ መሬት እንዲወርድ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ነው። በዚህም ተስፋ ሰጭ ሂደቶች ስለመኖራቸው በየዕለቱ /ከመንግስትና ከሕወሓት/ የሚደመጡ መረጃዎች የሚያመላክቱት እውነታ ነው።
ከዚህም ባለፈ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያስችል የሽግግር ፍትሕ እውን ለማድረግ ፖሊሲ አማራጮችን በመለየት ብሔራዊ ምክክር ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነው። ይህ ደግሞ ለመላው ሕዝባችን ትልቅ ትርጉም ያለውና በተስፋ የሚጠብቀው ጉዳይ ነው።
ይህ እየሆነ ባለበት ወሳኝ ወቅት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ጦርነት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተከስቷል ሲል የደረሰበትን ድምዳሜ በኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ዘንድ በፍፁም ተቀባይነት ሊኖረው የሚችል አይደለም። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር በጋራ ካደረጉት ምርመራ እና ከደረሱበት ምርመራ አንፃር ሲታይም ደምዳሜው ስህተት መሆኑ የሚያሳይ ነው።
የመስሪያ ቤቱ በመግለጫ ያወጣው ያልተገባ ድምዳሜ ኢትዮጵያውያን ችግሮቻችውን በራሳቸው አቅም መፍታት እንደሚችሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስመሰከሩበትን ትልቅ ክስተት /አጋጣሚ ያላገናዘበና በሀገሪቱ ዘላቂ እርቅና ሰላም ለማምጣት ለሚደረገው ጥረት ከበሬታ የሌለው ነው።
ኢፍትሃዊነት የተንጸባረቀበት፣ ይህ የአሜሪካ አካሄድ ሀገሪቱ በኢትዮጵያ አካታች የሰላም ሂደት እንዲረጋገጥ ስታደርገው የቆየችውን ድጋፍ የሚጻረር፤ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ከአሜሪካ መንግስትና ሕዝብ ጋር ያለውን ወዳጅነት የሚሸረሽር ጭምር ነው።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ፤ ተስፋ የተደረገበትን የሁለቱን ሀገራት የግንኙነት መሻሻል መልሶ ጥያቄ ውስጥ የሚጨምር ነው።
ኢትዮጵያውያን ዛሬም ቢሆን በሀገሪቱ ብሔራዊ እርቅ ፤ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ለሚያደርጉት ጥረት የአሜሪካ መንግስት እና ሕዝብ ሁነኛ አጋር እንደሚሆን ከፍ ያለ አመኔታ አላቸው። ከአንቶኒ ብሊንከን ጋር በአዲስ አበባ የተደረጉ ግልጽ ውይይቶች እና የተደረሰባቸው መግባባቶችም ሁለቱን ሀገራት ስትራቴጂያዊ አጋርነት ለማስቀጠል እንደሚረዳም ይታመናሉ! ወዳጅነቱና ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም የአሜሪካ መንግስት ኢፍትሃዊ ከሆኑና ተቀባይነት ከሌላቸው ርምጃዎችን ራሱን ማቀብ ይኖርበታል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም