የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት እንደተለመደው በበርካታ የዓለም ከተሞች የጎዳና ላይ ውድድሮች በብዛት የተካሄዱበት ነው። በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም በነዚህ ውድድሮች የተለመደ ድልና ውጤታማነት አልተለያቸውም።
በተለያዩ ከተሞች ከተካሄዱ ውድድሮች መካከል በደቡብ ኮሪያዋ ሴኡል የተከናወነው ማራቶን በቀዳሚነት ይጠቀሳል። በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ በተሰጠው በዚህ የማራቶን ውድድር በወንዶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ አምስት ያለውን ደረጃ በመያዝ በፍፁም የበላይነት አጠናቀዋል።
በውድድሩ ቀዳሚ ሆኖ ያጠናቀቀው ኢትዮጵያዊ አትሌት አምደወርቅ ዋለልኝ ሲሆን በርቀቱ የግሉን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ጭምር ማሸነፍ ችሏል።
አትሌት አምደወርቅ ከወራት በፊት በዚሁ ከተማ በተካሄደ የማራቶን ውድድር ላይ ተሳትፎ ፉክክሩን ያጠናቀቀው በአሸናፊነት ነበር። በወቅቱ የገባበት ሰዓትም 2:06:59 ቢሆንም፤ ከትላንት በስቲያ በነበረው ውድድር አንድ ደቂቃ በማሻሻል 2:05:27 በሆነ ሰዓት ርቀቱን በቀዳሚነት ማጠናቀቅ ችሏል።
እአአ የ2020 የዓለም ግማሽ ማራቶን የነሃስ ሜዳሊያ አሸናፊ የነበረው አትሌት አምደወርቅ የአገሩን ልጆች አስከትሎ በቀዳሚነት ያጠናቀቀው በጥቂት ሰከንዶች ልዩነት ሲሆን ይህም ውድድሩን በጠንካራ ፉክክር የታጀበና አጓጊ አድርጎታል። ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ሽፈራ ታምሩ እና ሃፍቱ ተክሉ በሰከንዶች ልዩነት ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ባጠናቀቁበት በዚህ ውድድር፤ ኦሊቃ አዱኛ እና አሸናፊ ሞገስ በአንድ ደቂቃ ልዩነት አራተኛ እና አምስተኛ ደረጃን በመያዝ ጠንካራ ፉክክር አድርገው ውድድራቸውን ማጠናቀቅ ችለዋል።
በፈረንሳይ ሊል ከተማ በተካሄደ ሌላ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድርም በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊ አትሌት አሸናፊ ሊሆን ችሏል። በ5 ኪሎ ሜትር በተካሄደው ውድድር አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ ቀዳሚ ሆኖ ያጠናቀቀ አትሌት ሲሆን የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን ለመስበር ያደረገው ጥረት ሊሳካለት አልቻለም።
የሁለት ጊዜ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮኑ አትሌት ዮሚፍ በአገሩ ልጅ አትሌት በሪሁ አረጋዊ ተይዞ የቆየው የርቀቱን ክብረወሰን (12:49) ለማሻሻል ያደረገው ጥረት በአንድ ሰከንድ በመዘግየቱ ከእጁ ሊወጣ ችሏል። አትሌቱ የገባበት 12:50 የሆነ ሰዓትም በርቀቱ የግሉ እንዲሁም የርቀቱ ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት ሆኖ ሊመዘገብ ችሏል።
ዮሚፍን ተከትሎ ኬንያዊው ሪኖልድ ኪፕኮሪር ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፤ አትሌት ጥላሁን ኃይሌ ደግሞ ሶስተኛ ሆኖ ውድድሩ የፈጸመ ኢትዮጵያዊ አትሌት ሆኗል። በተመሳሳይ በሴቶች መካከል በተካሄደው ውድድር አትሌት መቅደስ አበበ በሁለት ኬንያውያን መካከል በመግባት ሁለተኛ ሆና ውድድሯን ፈጽማለች።
ሌላው ትልቅ ትኩረት በተሰጠው በኒውዮርክ ግማሽ ማራቶን ውድድር የሁለት ጊዜ የ5ሺ ሜትር የዓለም ቻምፒዮኗ ኬንያዊት አትሌት ሄለን ኦቤሪ አሸንፋለች። ከኦቢሪ ጋር ብርቱ ፉክክር ያደረገችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ በበኩሏ በ34 ሰከንዶች ብቻ ተቀድማ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ጨርሳለች። ከውድድሩ የመነሻ አንስቶ ከፍተኛ ትንቅንቅ ሲያደርጉ የቆዩት ሁለቱ አትሌቶች በሰከንዶች ልዩነት ብቻ ተከታትለው ለመግባት ያደረጉት አስደናቂ ፉክክር የብዙዎችን ቀልብ የገዛ ነበር። በዚህም ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሰንበሬ የገባችበት ሰዓት 1:07:55 ሆኖ ተመዝግቦላታል።
ሌላኛው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በስፋት የተካፈሉበትና ለውድድሩም ድምቀት የነበሩበት ውድድር የሮም ማራቶን ሲሆን፣ በወንዶች መካከል በተካሄደው ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት ቢሰጣቸውም ቀዳሚውን ውጤት ማስመዝገብ ሳይችሉ ቀርተዋል። አበበ ቢቂላ ከ63 ዓመታት በፊት በዚህችው ታሪካዊ ከተማ በባዶ እግሩ ያስመዘገበው የኦሊምፒክ ማራቶን ድል የተዘከረበት መንገድ የብዙዎችን ትኩረት አግኝቶ ውሏል። የቀድሞ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ የነበረው ኤርሚያስ አየለ የጀግናውን አትሌት አበበ ቢቂላ የሮም ኦሊምፒክ ገድል ለማስታወስ፤ 42 ኪሎ ሜትሩን ቃል በገባው መሰረት በባዶ እግሩ በመሮጥ አጠናቋል።
ይህም በውድድሩ ተሳታፊ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይልቅ የበርካታ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ያገኘ ሆኗል። በአንጻሩ በሴቶች መካከል በተካሄደው ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ቀዳሚ ሆነው ማጠናቀቅ ባይችሉም በአትሌት ፎዚያ አሚድ እና ዝናሽ ደበበ አማካኝነት የሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ውጤት ሊመዘገብ ችሏል።
ከሮም ማራቶን ይልቅ በአንፃራዊነት ብዙ ግምት ባልተሰጠው በሎሳንጀለስ ማራቶን በወንዶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተከታትለው በመግባት አሸናፊነታቸውን አረጋግጠዋል። ርቀቱን በቀዳሚነት የፈጸመው አትሌት ጀማል ይመር ሲሆን፤ የገባበት ሰዓትም 2 ሰዓት ከ13 ደቂቃ ከ14 ሰከንድ ሆኖ ተመዝግቧል። አትሌት የማነ ጸጋዬ ደግሞ በአንድ ደቂቃ ዘግይቶ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ የፈፀመ ኢትዮጵያዊ አትሌት ነው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2015