ግብር በዘመናዊው ዓለም የመንግስትን መመስረት ተከትሎ ተግባራዊ መሆን እንደ ጀመረ የታሪክ መዛግብት ይጠቁማሉ። አስከ ዛሬም የተለያዩ ምዕራፎችን አልፎ ለመንግስታት ዋነኛ የጥንካሬ ምንጭ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
በእኛም አገር የመንግስት ምስረታ ካለው የረጅም ዘመን ታሪክ አንጻር፤ የግብር ጉዳይ በተመሳሳይ መልኩ የሚቃኝ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ያለበት ሁኔታ ግን እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ካሉ አገራት ምድብ የሚያስቀምጣት ነው።
አንድም በማኅበረሰቡ ውስጥ ስለ ግብር ያለው አመለካከት የተዛባ መሆን፤ ይህንን የሚገራ የአስተሳሰብ ግንባታ በስፋትና በጥልቀት አለመካሄዱ፤ ግብርን ፍትሀዊና ዘመናዊ በሆነ መንገድ መሰብሰብ የሚያስችል አገራዊ ስርአት መፍጠርና መተግበር አለመቻሉ እና ሙስና ለችግሩ ዋነኛ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው።
ከዚህም የተነሳ በአገሪቱ የግብር ስወራ እንደ አንድ መሰረታዊ ችግር የሚጠቀስ ከሆነ ውሎ አድሯል፣ በዚህም በቢሊዮን የሚቆጠር በግብር መልክ ሊሰበሰብ የሚችል ሃብት ሳይሰበሰብ እየቀረ ስለመሆኑም የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ። ግብር በአግባቡ ያለመሰብሰቡ በልማት ውጥኖች አፈጻጸምም ላይ አሉታዊ ጥላ ሆኗል። አሁን ላለው የሕዝባዊ አገልግሎት ክፍተትም ሆነ ድህነት እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀስ ነው።
ይህንን አገራዊ ችግር ለመፍታት ከለውጡ ማግስት አንስቶ ከግብር ጋር የተያያዙ አሰራሮችን ከማዘመን ጀምሮ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን የተዛባ የግብር አስተሳሳብ ለማረቅ የሚያስችሉ ስራዎች በስፋት እየተሰሩ ነው። በዚህም እየተስተዋለ ያለው ለውጥ የሚበረታታ ነው።
በተለይም ከፍተኛ ግብር ከፋይ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚጠበቅባቸውን ግብር በአግባቡና በታማኝነት እንዲከፍሉ ለማስቻል፤ የሚካሄዱ የማነቃቃት/የማነሳሳት ስራዎች በተጨባጭ እያስመዘገቡት ያለው ውጤት ተስፋ ሰጭ ነው።
ለዚህም ባለፈው እሁድ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ”ግብር ለአገር ክብር” በሚል መሪ ቃል በ2014 ዓ/ም በጀት ዓመት ሞዴል ግብር ከፋዮች ለሆኑ 300 ግብር ከፋዮች የሰጠው ዕውቅና የዚሁ እውነታ ማሳያ ነው። ቢሮ በወቅቱ እንዳስታወቀው፤ በበጀት ዓመቱ ሰባት ወር ለመሰብሰብ ካቀደው 59 ነጥብ 11 ቢሊዮን ብር ውስጥ 58 ነጥብ 43 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ችሏል። ይህም ከእቅዱ 98 ነጥብ 8 ከመቶ ነው። በመርሀ ግብሩ እውቅና የተሰጣቸው ከ56745 ግብር ከፋዮች ውስጥ 300 የሚሆኑት ናቸው። እውቅና የተሰጣቸውም ትክክለኛ መረጃዎችን በጊዜው አሟልተው በመገኘታቸው እንደሆነ ታውቋል።
በርግጥ ከግብር ከፋዩ ቁጥር፤ አስፈላጊውን መረጃ በትክክል እና በጊዜው አሟልተው ከተገኙት ግብር ከፋዮች አንጻር በዘርፉ ያለው እውነታ ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ አመላካች ቢሆንም፤ ከመጣንበት የተበላሸ የግብር አሰባሰብ መንገድ አኳያ ያለውን እያበረታቱ መጓዝ የግድ ነው።
በተለይም አዲስ አበባ እንደ ስሟ ሁሌም አዲስ እንድትሆን የሚደረገው ጥረት ስኬታማ የሚሆነው በከተማዋ ያሉ ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር በአግባቡ መክፈል ሲችሉ ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ ግብር ከፋዩ ኅብረተሰብ በታማኝነት ግብር በመክፈል ራሱንና መላውን ኅብረተሰብ እያገለገለ መሆኑን በአግባቡ ሊረዳ የሚችልበትን ዕድል መፍጠር ወሳኝ ነው
የከተማዋ ነዋሪም ቢሆን መንግስት ሕዝባዊ አገልግሎቶችን በሚፈለገው መልኩ ማቅረብ የሚችለውና ልማት የሚፋጠነው ከግብር በሚሰበሰበው ሀብት መሆኑን በሚገባ ተረድቶ፤ ግብር በአግባቡ ለመሰብሰብ በሚደረገው ጥረት ንቁ ተሳታፊ ሊሆን ይገባል። ይህንን ማድረግ የተሻለች ከተማ ለመጭው ትውልድ የመፍጠር ያህል ከፍያለ ሕዝባዊ ተልእኮ መሆኑንም ሊያስተውል ይገባል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2015