የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች የስፖርት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑም ከሕፃናት እስከ አዋቂዎች በሚገኙ የዕድሜ ክልሎች የተለያዩ የስፖርት ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየተገበረ እንደሚገኝ አስታወቀ። ከተማ አስተዳደሩ የአገሪቱን ስፖርት እድገትና ሕዝባዊ አንድነት የሚያጠናክሩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም ገልጿል።
አስተዳደሩ በስፖርቱ ዘርፍ ከተማ አቀፍ ብቻ ሳይሆን አገር አቀፍ ኹነቶች የሆኑትን ማህበረሰብ አቀፍ ስፖርት(የማስ ስፖርት)፣ የብስክሌት፣ እግር ኳስና ሌሎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ የከተማ አስተዳደሩ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ደርጊቱ ጫሌ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ ገልፀዋል። እንደ ኃላፊዋ ገለፃ፣ ከተማ አስተዳደሩ በተለይም ስፖርት የከተማው ባህል እንዲሆን፣ ለክልሉ እና ለአገር ጠቃሚ ትውልድ ለመፍጠር የሚያስችል 24 የሕፃናት እና የታዳጊዎች ስፖርት ፕሮጀክቶችን ቀርፆ በሥራ ላይ አውሏል።
የአገሪቷን ስፖርትና አንድነት ለማጠናከር በተሠራው ሥራ በ2014 ዓ.ም 34 ተጫዋቾችን በመላው አገሪቱ በሚገኙ ክለቦች ከፕሪሚየር ሊግ እስከ ታችኛው ሊግ ድረስ እንዲጫወቱ ማድረግ የቻለ ሲሆን፣ በዘንድሮ ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት ደግሞ 14 ተጫዋቾች በተለያዩ የአገሪቱ ሊጎች እንዲጫወቱ ማድረግ ተችሏል። ይህም ወጣቶች ላይ መስራት ለከተማዋ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቷ የስፖርት እድገት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ማሳያ መሆኑን ኃላፊዋ ገልጸዋል።
የከተማዋን የስፖርት እንቅስቃሴ ለማስፋት እና የወጣቶችን ተሳተፎ ለማሳደግ ከዚህ በፊት ለአረንጓዴ ስፍራ ተብለው የታጠሩና አገልግሎት የማይሰጡ ቦታዎች ተለይተው ለወጣቶችና ሕፃናት ስብዕ መገንቢያ እንዲሁም ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ክፍት እንዲሆኑ የከተማው የስፖርት ምክር ቤት ጉባዔ ጸድቋል።የቦታዎቹ መከፈት ለስፖርቱ ማህበረሰብ ከሚሰጠው አገልግሎት እና ጠቀሜታ በተጓዳኝ ወጣቶችና ሕፃናት አልባሌ እና አላስፈላጊ ቦታ እንዳይውሉ፣ በሥነ ምግባር እንዲታነጹ፣ ብሩህ አዕምሮ እንዲኖራቸው እና አምራች ዜጋ ለማድረግ ያግዛሉ ሲሉ አብራርተዋል።
በከተማዋ ስምንት ክፍለ ከተሞች እንዳሉ የጠቀሱት ኃላፊዋ፣ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ ክፍለ ከተሞች የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ስለሌላቸው በቀጣይ እንዲኖራቸው ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል። ለዚህም በተለይም ለአረንጓዴ ስፍራ ተብለው የተለዩ ስፍራዎችን ለወጣቶች ክፍት የማድረግ ሥራ ቅድሚያ እንዲሰጠው በስምምነቱ ትኩረት እንደተደረገበት አብራርተዋል።
የሐዋሳ ከተማን ለስፖርት ምቹ ለማድረግ በሚሠሩ ሥራዎች አገር አቀፍ የሴቶች ከፍተኛ ሊግ፣ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ እና ሌሎች ስፖርታዊ ውድድሮች ወደ ከተማዋ እየመጡ መሆኑንም ኃላፊዋ አክለዋል። ሐዋሳ ከተማ የተለያዩ ስፖርታዊ ኹነቶችን በስፋት ከማስተናገድ ባሻገር በተለይም በእግር ኳስ ኢትዮጵያን በተለያዩ አህጉርና ዓለምአቀፍ ውድድሮች መወከል የቻሉ በርካታ ተጫዋቾችን ማፍራት መቻሏ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ እንደ አዲስ 1990 ላይ ከተጀመረ ወዲህ ሁለት ጊዜ ቻምፒዮን መሆን ከቻሉ ጥቂት ክለቦችም የሐዋሳ ከተማ አንዱ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ ሰፊ ሕዝባዊ መሠረት ያለውና በሊጉ ለረጅም አመታት ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ መዝለቅ እንደቻለ ይታወቃል።
ከተማዋ በየዓመቱ ተተኪ እግር ኳስ ተጫዋቾችን ለማፍራት በሚከናወነው የሴንትራል ሐዋሳ ታዳጊዎች ዋንጫ ውድድር ላይ በከተማዋ የሚገኙ 37 ክለቦች ተካፋይ በመሆን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ እያበረከቱ የሚገኘው አስተዋፅኦም ተጠቃሽ ነው።
ኤፍሬም አንዳርጋቸው
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 11 ቀን 2015 ዓ.ም