እንደአገር አዲሱ የትምህርት ሥልጠናና ፖሊሲ በተለያዩ አካላት ውይይት ሲደረግበት ቆይቷል። በቅርቡ ደግሞ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቋል። ይህ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ ከዚሁ ፖሊሲ ጋር ተያያዥ የሆኑ ሰነዶችም መጽደቅ ችለዋል። ለአብነት የዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ (አውቶኖሚ) የሚደነግግ አዋጅ፤ በከፍተኛ የመንግሥት ተቋማትና ማስተማሪያ ሆስፒታሎች ውስጥ የሚሰሩ አካዳሚክ ቴክኒክ ረዳቶችን ተግባር፣ ኃላፊነትና ጥቅማጥቅም ለመወሰን የሚያስችል ረቂቅ ደንብ፤ የከፍተኛ ትምህርት ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ፣ የምርምር ተቋማትና የኢንዱስትሪ ትስስር ረቂቅ አዋጅ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ከእነዚህ መካከል ዋናውና የጀርባ አጥንት የሆነውን የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲን ለዛሬ ለማንሳት ወደናል። ይህንን በሚመለከት ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውን መረጃና ከኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት ሃሳብ በማካተትም እናቀርበዋለን። መነሻችንን የ1986 ዓ.ም የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲን እናድርግ። ምን ምን ክፍተቶች ነበሩበት የሚለውም ዋና ትኩረታችን ነው። ከዚህ አኳያ ይህ ፖሊሲ አብዛኛው ትምህርት የሚሰጠው በውጭ ቋንቋ ነበር። አፍ መፍቻን አላካተተም። ይዘቱም ቢሆን አውሮፓዊ ቋንቋን በማስተማር፣ በአውሮፓ ታሪክና ባሕል ላይ ያተኮረ ነበር። የአገር ውስጥ ሁኔታና ፍላጎት እንዲሁም የሙያ ሥልጠናን አላካተተምም። በዚህም ባህሉን የማያውቅና ውጭውን የሚናፍቅ ትውልድ እንዲበዛ አድርጓል። በአገሩ ያለውን ሀብት እንዳያይም መጋረጃ ሆኖበታል።
በዩኔስኮ መስፈርት መሠረትም የ21ኛው ክፍለ ዘመን ምላሽ የማይሰጥ ትምህርት የሚሰጥበትም ነበር። ምክንያቱም ከተግባር ይልቅ በንድፈ-ሃሳብ ላይ የታጨቀ ትምህርት የሚሰጥበት በመሆኑ። በሁሉም እርከን ያለው ሥርዓተ-ትምህርት ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን መሠረት ያደረገም አልነበረም። በየጊዜው እየተፈተሸ የማይከለስም ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ አገር በቀል የዳበረ የእውቀት ክምችትን በአግባቡ አለማካተቱ ብዙ ችግሮችን ሲፈጥር ቆይቷል። ተጨባጭ ሥርዓተ ትምህርት ያልተዘጋጀበት ማለትም ለቴክኖሎጂና ለሥራ ፈጠራ በቂ እድል ያልሰጠ፤ እውቀትን ያላጎናጸፈ ነው። በዘርፉ ክህሎት ያላቸው ጭምር ያልወጡበት ነበር። መምህራን ላይ የሚሰጠው ሥልጠናም አቅም የሚገነባ አልነበረም። ለዚህም ማሳያው ከ2006 እስከ 2009 ዓ.ም በተካሄደ የሙያ ፍቃድ ምዘና ፈተና ከ140 ሺህ 435 የመጀመሪያ እና 24ሺህ 063 ሁለተኛ ደረጃ መምህራን ተፈታኞች ውስጥ የመቁረጫ ነጥቡን በማሟላት ያለፉት 22 በመቶ መምህራን ብቻ ናቸው። ስለሆነም አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ እንዲወጣ አስገድዷል። ምን ይዞ መጣ ከተባለ ደግሞ ዶክተር ቴዎድሮስ የሚሉት ነገር አላቸው።
ዶክተር ቴዎድሮስ ሸዋረገድ በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ ትምህርት ማበልጸጊያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት፤ ፖሊሲው በትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታው የቀረቡ ምክረ ሃሳቦችን በመመልከት በትምህርቱ ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶችን ሊፈታ በሚችልና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የተዘጋጀ ነው። ከዚህ አንጻርም በፊት የነበሩ ችግሮችን በደንብ ገምግሟል፤ በምን መልኩ ቢሠራ ውጤታማ ይኮናል የሚለውንም መፍትሄ ያቀረበ ነው። ለምሳሌ፡- የሚሰጡ ሥልጠናዎች እውቀት አስጨባጭ እንጂ ተግባር ላይ ያተኮሩ አልነበሩም። ይህ ደግሞ ተጨባጭ የሆነ ትምህርት ለመስጠት አዳጋች ሆኖ ቆይቷል። ያለንበት ዘመን የሳይንስና ቴክኖሎጂ እውቀትን የሚጠይቅ ነው። በዓለም ላይ ተወዳዳሪ ለመሆንም ግድ ያስፈልገናል። ስለዚህ ከዓለም ሥርዓት ውስጥ ላለመውጣት ይህንን ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ በማመን የትምህርትና ሥልጠናው ፖሊሲ በዚህ ተቃኝቶ እንዲጸድቅ ሆኗል።
1986ቱ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ሰዎችን በማሰልጠኑ በኩል ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ አበርክቶ ነበረው። ይሁንና የሰለጠነው ምን ያህል ብቁ ነው፤ ምንስ ያህል በሥራ ተሰማርቶበታል፤ በጥራት በሰለጠነበት ሙያ እየሠራ ነው ወይ? ሲባል መልሱ ላይ ችግሮቹ ይበዛሉ። ምክንያቱም የአንድ ፖሊሲ መለኪያው የሚታይ ውጤት ነውና። ለዚህም በአብነት የምናነሳው የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል ውጤት ነው። ተጨባጭ የሆኑ ነገሮች ባለመማራቸው ብዙዎቹ ወድቀዋል። በዚያ ውስጥም አገር የሠራችው ምን ያህል ነው የሚለው ታይቷል። ስለዚህም የአዲሱ ትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ አስፈላጊነት ከዚህ አኳያ ነው የሚታየው።
ፖሊሲው በርካታ ነገሮችን ይዟል። ከእነዚህ መካከል ፈተና የነበረው የተማሪዎች ግብረገብነት ጉዳይ ነው። የእስከዛሬዎቹ ትምህርቶች መብት እንጂ ግዴታዎችን አያሳውቁም። በዚህም የሥነምግባር ስብራት በትምህርት ሥርዓቱ ላይ እንዲፈጠር አድርጓል። በተመሳሳይ አገር በቀል ቴክኖሎጂዎቻችን በትምህርት ሥርዓቱ ማስገባት ባለመቻላቸው ትምህርት ወደ ሥራ የሚቀየርበት እድል አናሳ ነበር። እናም ኢትዮጵያ ብዙ አገር በቀል እውቀት ያለባት አገር ብትሆንም ባላት ሀብት ልክ መጠቀም አልተቻለም። ከተጨባጭ ትምህርትና ሥራ ጋር የተያያዙ ተግባራትንም ለመከወን አዳጋች ሆኗል። ስለዚህም ይህንን በሚያስተካክል መልኩ አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ እንዲዘጋጅ ተደርጓል ይላሉ።
አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ በአጠቃላይ ትምህርት ብቻ ብናነሳ የትምህርት እርከኑን ሳይቀር የለወጠ ነው። ማለትም 1986ቱ ከ1 እስከ 4 የመጀመሪያ ሳይክል ከ5 እስከ 8 ሁለተኛ እያለ ነበር የሚሄደው። ሁለተኛ ደረጃ ላይ ደግሞ በ10 ትምህርት ይጠናቀቃል። 11 እና 12 የከፍተኛ ተቋማት ዝግጅት ተብሎ ነው የሚሰጠው። ይህ ደግሞ ተማሪዎች እድሜያቸው ሳይደርስ ወደ ሥራ እንዲሰማሩ ያደርጋቸዋል። በዚህ የተነሳም ለሥራም ሆነ ለትምህርቱ ዝግጁ ሳይሆኑ ይቀሩና ውጤታማ ሥራ ሠርተው ለማሳየት ይቸገራሉ። እናም አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ይህንን የማስተካከል ሥራ ሠርቷል። እድሜን የሚመጥን ትምህርት ለመስጠት እርከኑ እንዲሻሻል አድርጓል። በዚህም ከዚህ በፊት ቅድመ መደበኛ የምንለው ቅድመ አንደኛ በሚል ተተክቷል። በተመሳሳይ ይህ የክፍል ደረጃ ለግል ባለሀብት ብቻ የተተወ ስለነበር እንደመንግሥት እንዲሠራበት እድል ከፍቷል። ማለትም ተማሪዎች ሁለት ዓመታት በትምህርት ሲያሳልፉ ነጻና ግዴታ በሆነ መልኩ አድርጎ ነው።
የነጻና ግዴታ ትምህርትም ከአምስት ዓመት ልጅ የሚጀምር ሲሆን፤ እስከ ስምንተኛ ክፍል እስኪዘልቅ ድረስ የሚቀጥል ነው። ከ9 እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ ነጻ የሚለው ብቻ ይተገበራል። ለዚህ ደግሞ የወላጅ ድርሻ እንዳለ ሆኖ የመንግሥት ድርሻን ግን ሰፋ አድርጎ ይዞ የመጣ ነው። የመምህራንና የግብዓት ማሟላት እንዲሁም ተቋማትን ለመማር ማስተማር ሥራው ምቹ የማድረግ ጉዳይ የመንግሥት ትልቁ ግዴታ ነው። ነጻና ግዴታ ብሎ በሚጠበቀው ልክ ካላሟላ ተጠያቂ ይሆናል። ስለዚህም ከዚህ በፊቱ በተሻለ መንገድ እንዲሰራ የሚያስገድደው ነው። ይህንን ሊያስፈጽም የሚችል ደግሞ የአጠቃላይ ትምህርት አዋጅ እየተዘጋጀ ይገኛል።
ዶክተር ቴዎድሮስ እንደሚሉት፤ ከ 1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል የግብረገብ ትምህርት መሰጠቱ በራሱ አዲስ ለውጥ ነው። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርትም እንዲሁ መሰጠቱ ሌላው የፖሊሲ ቱሩፋት ነው። የሥራና ተግባር ትምህርት በሚል እንደአንድ የትምህርት ዓይነቶችም ለሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ይሰጣል። ይህ ደግሞ በአዲሱ የትምህርት ፖሊሲ ለሚማር ተማሪ ብዙ እድሎችን የሚያመቻች ነው። የመጀመሪያው በሥነምግባር የታነጸ ዜጋ ያደርገዋል። ከዚያ ባሻገር ቴክኖሎጂውን የሚያውቅና የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብት መጠቀም የሚችል እንዲሁም ሥራ ፈጣሪና ሥራ ወዳድ እንዲሆን ያስችለዋል። ምክንያቱም ታችኛው ክፍል ላይ በተማረው ትምህርት ሳይቀር አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር የሚችልበትን ክህሎት ያዳብራል። 11ኛ 12ኛ ክፍል ሲገባ ደግሞ አንድ የትምህርት ዓይነት መርጦ በዚያ ላይ ስፔሻላይዝድ እንዲያደርግና የተሻለ አቅም ፈጥሮ እንዲሠራ ያበረታዋል።
ይህ እድል በተለይም ለ12ኛ ክፍል ተማሪ የተለየ ምቾትን የሚፈጥር ነው። አንደኛው አገር አቀፍ የብቃት ማዕቀፍ እየተሠራ በመሆኑ በዚያ መስፈርት መሠረት ብዙ አማራጮችን ያገኛል። የመጀመሪያው በራሱ ውሳኔ ላይ መሠረት ያደረገ ተግባርን እንዲከውን ማስቻሉ ነው። ከፈለገው ከፍተኛ ተቋማትን ይቀላቀላል፤ አልፈልግም ካለ ደግሞ የራሱን ሥራ ተፈትኖ ባለፈበት መስክ መሥራት ይችላል። ይህ አይሆንም ካለ ደግሞ ቴክኒክና ሙያ ገብቶ እርሱን በሚመጥን ደረጃ እንዲማር እድልን ያገኛል። ፈተናው ሁለት ዓይነት ሲሆን፤ በሙያ የተግባር ፈተናና የአካዳሚካል የሆነው የጽሑፍ ነው። እናም የመግቢያ ውጤት ያመጣ ሰው ምርጫው የሚጠበቀው በከፍተኛ ደረጃ ነው። ፈተናውን ያላለፈም ቢሆን በቃህ የሚባል አይደለም። ሰርቶ የሚለወጥበትን ብዙ የሙያና የአካዳሚክ ትምህርቶችን በመቅሰሙ ብዙ አማራጮች ይኖሩታል። እናም አዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ብዙ መሠረታዊ ነገሮችን ማስተካከል የቻለ እንደሆነ ታይቶበታል። በዚህም የሚኒስትሮች ምክርቤት አጽድቆታል ይላሉ።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት እንዲሁም የአካዳሚክ ጉዳዮች ኃላፊ ዶክተር ገነነ አበበም የዶክተር ቴዎድሮስን ሃሳብ ያጠናክራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ይህ ፖሊሲ እንደበፊቱ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትን ለብቻው የሚሰጥ አይደለም። ሙያውም ሆነ ትምህርቱን ተወዳጅ ለማድረግ በአጠቃላይ ትምህርት ጭምር እንዲካተት ተደርጎ የሚሰጥበትን ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ነው። ይህ ደግሞ የአመለካከት ለውጥን ከመቀየሩ ባለፈ ከታች ክፍል ያሉት ተማሪዎች ሙያ ወዳድ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በቴክኒክና ሙያም ገብተው እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ መማር እንደሚችሉ ግንዛቤ የሚፈጥርና የሚገፋፋቸው ነው።
ቴክኒክና ሙያ በባህሪው ሥራ ተኮር ትምህርት ነው። በሙያ ተመርቀው ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የሚደረግ ትምህርት ይሰጥበታል። ለዚህ ደግሞ የኢንዱስትሪው ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ ነው። እናም አዲሱ ፖሊሲ ይህንን ከማሳለጥ አኳያ ብዙ እድሎችን ይዞ የመጣ ነው። ለአብነት ከዚህ በፊት የነበረውን የኢንዱስትሪዎች ትስስርን በእጅጉ የሚያጠናክርና የሚያሠራ ነው። ኢንዱስትሪዎች እንዴት ማሳተፍ እንደሚችሉና እንዴት ትርፋማ ማድረግ እንደሚቻል የማበረታታ ሥርዓት ይዞ የመጣ በመሆኑ ለዘርፉ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ይላሉ።
የቴክኒክና ሙያ ትምህርት በማህበረሰቡ ዘንድ ዝቅተኛ አመለካከት ያለው በነበረው አሠራርና ፖሊሲ ምክንያት ነው። የትምህርት ደረጃው ጭምር ብዙዎችን ወደኋላ የሚጎትት ነበር ማለትም ትምህርቱ እስከ ደረጃ አምስት ድረስ ብቻ የሚሰጥ በመሆኑ፤ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲን እንጂ እዚህ መግባትን አይፈልጉትም፤ ውጤት ሲመጣላቸውና አማራጭ ከሌላቸው ብቻ ነው ምርጫቸው የሚያደርጉት። ሆኖም ከገቡበት ወዲያ ብዙዎች ወደውት ሕይወታቸውን ለውጠውበታል። እንደ አገር ያለው ለውጥና የሥራ እድልም ቢሆን ከዚህ በወጡ ተማሪዎች የመጣ እንደሆነ ነጋሪ አያሻውም። ስለዚህም በአዲሱ ትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል በርካታ ነገሮች ተከተው እንዲተገበሩ ይሆናሉ። ከእነዚህ መካከልም እስከ ደረጃ ስምንት ድረስ የሚያድጉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ታሳቢ ተደርጎ ተዘጋጅቷል። ይህ ማለት ደግሞ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ መማር እንዲች እድል ተፈጥሯል።
በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ደረጃ አምስት አድቫንስድ ዲፕሎማ ሲሆን፤ ደረጃ ስድስት መጀመሪያ ዲግሪ ነው። ሰባትና ስምንት ደግሞ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ይሆናሉ። ስለዚህም አንድ የ12ኛ ክፍል ተማሪ የከፍተኛ ተቋም የመግቢያ ነጥብ ካገኘ በአዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ መሠረት ቴክኒክና ሙያ ውስጥ ገብቶ የመጀመሪያ ዲግሪውን መከታተል ይችላል። ይህ ደግሞ የሚሆነው ልክ እንደ ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ አራት ዓመታትን በትምህርት በማሳለፍ ነው። በአዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ትምህርት የሚጠናቀቀው 12ኛ ክፍል በመሆኑ እንደዚህ ቀደሙ የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነ ተማሪ ወደ ቴክኒክና ሙያ አይገባም። ይህ ደግሞ የሙያን ጥቅም በአግባቡ ተረድቶ ለትምህርቱ ዝግጁ ሆኖ የሚገባ ተማሪን ያበራክታል የሚሉት ዶክተር ገነነ፤ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ መማር ከዚህ በኋላ የምርጫ ጉዳይ እንጂ የውጤት ጉዳይ አይሆንም። ምክንያቱም ቴክኒክና ሙያና ከፍተኛ ተቋም የመግባት ሁኔታው ተመሳሳይነት ያላቸው እድሎችን አመቻችተዋል። ስለዚህም ውጤት ያለው ተማሪ ቴክኒክና ሙያንም መቀላቀል ይችላል ብለውናል።
ሌላው ቴክኒክና ሙያን በተመለከተ ያነሱት ጉዳይ የዓመቱ ጉዳይ ሲሆን፤ ከደረጃ ስድስት በላይ ያሉ ትምህርቶች ልክ እንደከፍተኛ ተቋሙ ዓመቱን ጠብቀው የሚከናወኑ ይሆናል። ከዚህ በታች ያሉት ግን እንደተማሪው አቅምና ፍጥነት ይወሰናሉ። ቴክኒክና ሙያ ላይ ዋጋ የሚሰጠው የዓመታት ቆይታ ጉዳይ ሳይሆን የብቃት ጉዳይ ነውና በትንሽ ጊዜ በጣም ሙያዊ ብቃታቸውን እያሳዩ ከመጡ ደረጃውን መሻገር ይችላሉ። አጠር ባለ ጊዜ ውስጥ የብቃት ምዘና ወስደው ወደ ሥራ መሰማራት ይችላሉ። ፈጥኖ የማወቅ ብቃት ምርቃቱንና የሥራ መውጪያ ጊዜውን ይወስናል ይላሉ።
በአዲሱ ትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ መሠረት ከቴክኒክና ሙያ የሚወጡ ተማሪዎች በሁለት ዓይነት መልኩ እንዲሠሩ ተደርገው ይመረቃሉ። የመጀመሪያው በራሳቸው ሥራ እንዲፈጥሩ ሲሆን፤ ሁለተኛው ተቀጥረው እንዲሠሩ የሚሆኑበት ነው። ይህ የሥራ እድል ደግሞ የሚመጣው ገበያው የሚፈልገው ተጠንቶ ትምህርት ስለሚሰጥ ነው። ሥልጠናው የሚሰጠውም ከኢንዱስትሪዎች ጋር በመተባበር ነው። አሁን የተለየነው በፍልስፍና ደረጃ ነው። ይህም ከውስጥ ወደ ውጪ የሚል ሲሆን፤ ከራሳችን ተነስተን ነገሮችን እያሰፋን ገበያውን እንይዛለን። በዚህም የአቅርቦትና ፍላጎት ልዩነት እንዳይኖር አምስት ዋና ዋና የሥራ ዘርፎች ተለይተዋል። ግብርና፣ ሆቴልና ቱሪዝም፣ ማይኒንግ፣ ማኑፋክቸሪንግና አይሲቲ ናቸው።
ሌላው ደግሞ ተቋማት ሥልጠና ሲሰጡ ከአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት ጋር በተዛመደ መልኩ እንዲሰጡ መደረጉ አዲሱ ፖሊሲ ያመጣው መልካም እድል ነው። ይህ ደግሞ ለሥራ እድል ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ምክንያቱም ልክ እንደ ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችም እንደ አካባቢያቸው የተፈጥሮ ሀብት ተለይተው ትምህርት የሚሰጡ ይሆናል። አካባቢያቸውን ለይተው የተመረጡትን ዘርፎች ብቻ በመለየት ኮሌጆቹ እንዲያስተምሩ ይሆናሉ። ይህ ደግሞ ለኢንዱስትሪውም ሆነ ለሥራ እድል ፈጠራ ብዙ ምቹ ሁኔታዎችን የሚያስገኝ ነው ይላሉ። ሁለቱም አካላት እንዳሉት፤ ፖሊሲ ብቻውን ሥራ አይሆንም፤ ተግባርን ይፈልጋል። ስለዚህም ትም ህርት የማይመለከተው አካል የለምና ለትግበራው ሁሉም የበኩሉን ማበርከት አለበት። ተማሪም ሆነ አገር የሚወጣው በተሰራው ሥራ ልክ በመሆኑ እያንዳንዳችን ድርሻ አለንና ጠጠራችንን ከመወርወር አንቦዝን በማለት ሃሳባችንን ቋጨን።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 11 ቀን 2015 ዓ.ም