በዝናብ ላይ ሙሉ በሙሉ ተመሥርቶ ዘመናትን ያሳለፈው የኢትዮጵያ ግብርና፤ ሀገርን በአግባቡ መመገብ አቅቶት ሕዝባችን ዓመታትን እየቆጠረ በሚከሰት የድርቅ አደጋ ከፍያለ ዋጋ እንዲከፍል አደርጓል። ኢትዮጵያም ከድርቅ ጋር ተያይዞ በሚከሰት ረሀብ እና ከረሀብ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ችግሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደጋግማ እንድትነሳ ሆኗል። ችግሩም ለዜጎች አንገት መድፊያ እና የልብ ስብራት ሆኖም ዓመታት ተቆጥረዋል።
ችግሩ በዚህ ብቻ የሚያቆም አይደለም፡፡ በዝናብ ወቅቶች/በክረምትና በበልግ/ከመጠን በላይ ሞልተው አካባቢ የሚያጥለቀልቁ፤ ከዛም በላይ ከዓመት ዓመት ያለ ሥራ የሚፈሱ ብዙ ወንዞች፤ ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል ባለባት ሀገራችን የሚስተዋለው ይህ የድርቅ ችግር በአግባቡ ካልተገራ ፤ አሁን አሁን ከአካባቢ አየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ ከሚችሉ ችግሮች ጋር ተዳምሮ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።
ከዚህም ባለፈ በሀገሪቱ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ያለውን የሕዝብ ቁጥር መመገብ የሚያስችል አዲስ የግብርና እስትራቴጂ ተነድፎ በፍጥነት ወደ ትግበራ ካልተገባ፤ በቀጣይ ከድርቅ ጋር በተያያዘ ሊያጋጥሙን የሚችሉት አደጋዎች ከዚህ ቀደም ካሳለፍናቸውና በበለጠም ብዙ ዋጋ ሊያከፍሉን ይችላሉ።
በተለይም ዓመታት እየቆጠረ የሚከሰተውን የድርቅ አደጋ ለመታደግ፤ከሁሉም በላይ ሃገራዊ የግብርና ምርትን ከማሳደግ የተሻለ አማራጭ እንደማይኖር ብዙዎች ይስማማሉ። ለዚህ ደግሞ ግብርናውን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ማዘመን ወሳኝ ነው። ግብርናውን ከዝናብ ውሃ ጥገኝነት አውጥቶ ሕዝብን የመመገብ አቅም እንዲኖረው ማድረግ፤ ከዚያም በላይ የውጪ ምንዛሪ ምንጭ እንዲሆን ለማድረግ የሃገሪቱን የውሃ ሀብት ወደ ሥራ ከማስገባት ውጪ ሌላ አማራጭ የለም። ይህንን ለማድረግ መንግሥት ፣ ባለሀብቱና አርሶ አደሩ ለዘመናዊ ግብርና ትኩረት ሰጥተው ሊንቀሳቀሱ ፤ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት ሊፈጥሩ ይገባል።
በባለሀብቶች የሚደገፉ ከፍተኛ የመስኖ ልማቶችን ጨምሮ ፤ በአነስተኛ ኢንቨስትመንትና ቴክኖሎጂ ያለንን ሀብት /በተለይ የመሬት፣ የውሀ እና የሰው ኃይል /አቀናጅተን ፈጥነን ወደ ሥራ መግባት፤ ይህንንም የልማት አቅም አድርገን መጠቀም አለብን። ከዚህ ውጪ ለዘመናት በመጣንበት መንገድ መጪውን ዘመን እንሻገራለን ብሎ ማሰብ በብዙ መልኩ ራስንና ሀገርን ለከፋ አደጋ የማጋለጥ ያህል ነው የሚሆነው።
በተለይም በየአካባቢው መለስተኛ የመስኖ ግድቦችን በመገንባት የመስኖ ልማትን የግብርናው ዘርፍ አማራጭ አቅም አድርጎ ማስቀጠል ያስፈልጋል። ይህ ለሰብል ልማቱ ብቻ ሳይሆን በድርቅ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ ለአደጋ ተጋላጭ የሚሆኑትን የቤት እንስሳት ሕይወት ለመታደግ የሚያስችል የተሻለ አማራጭ ነው። ከዚህም በላይ የአካባቢ ሥነ ምሕዳርን በመጠበቅ ደረጃም የሚኖረው አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም።
በዘርፉ የሚያጋጥመውን የፋይናንስ ችግር ለመፍታትም ባንኮች ፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ባለሀብቶችን ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በተለይም ባንኮች እና የኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚያስተዳድሩት የሕዝብ ገንዘብ ከመሆኑ አንጻር ወለድ ላይ ከሚያተኩረው የተጠቃሚነት ስሌታቸው ወጥተው ሃገርን ጠቅመው እራሳቸውን ወደሚጠቅሙበት የተሻለ አሠራር መሻገር አለባቸው። ለዚህ የሚሆን የኃላፊነት ስሜት ሊኖራቸውም ይገባል።
መንግሥት ቀደም ባሉት ጊዜያት ተጀምረው ድምጻቸው የጠፉ መለስተኛ የመስኖ ግድቦች ግንባታ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሱ በአግባቡ በመገምገም ፣ ያጋጠማቸውን ችግር ፈጥኖ በመፍታት በፍጥነት ወደ ሥራ የሚገቡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይኖርበታል። በተለይም በተደጋጋሚ በድርቅ በሚጎዱ አከባቢ ሊገነቡ ታቅደው የነበሩ መለስተኛ የመስኖ ግድቦች የውሃ ሽታ የመሆናቸውን ነገር በአግባቡ ሊፈተሹ ይገባል። ምክንያቱም መለስተኛ የመስኖ ልማት ግድቦች በዘርፉ ያለውን ችግር ከማቃለል አኳያ ያላቸው ድርሻ ከፍ ያለ ነው፡፡ ይሄንኑ ተገንዝቦ መስራትም ከሁሉም የሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅ ኃላፊነትም፣ የቤት ሥራም ነው!
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 11 ቀን 2015 ዓ.ም