የዘንድሮን ነገር አልቻሉም:: የኑሮ ውድነቱ ያንገዳግዳቸው ይዟል:: ዛሬን እንደነገሩ ቢያልፉ ነገ ፈጥኖ ይተካል:: ገበያው ከአቅማቸው በላይ ሆኗል:: እንደ እጃቸው ልግዛ፣ ልሸምት ቢሉ አልሆነም:: የጓዳ፣ የቤታቸው ችግር አላስተኛቸውም:: ‹‹ሞላሁት›› ሲሉ ይጎድላል:: ‹‹አገኘሁ›› ሲሉት ይጠፋል:: ሆድ ይሉት ጣጣ ርሃብ ድካም አስከትሎ እያናወዛቸው ነው:: ተጨንቀዋል::
ወይዘሮ ሙሉ ዲንቃ ዛሬ እንደትናንቱ አይደሉም:: ዕድሜያቸው ገፍቷል:: አቅማቸው ጠፍቷል:: ቀድሞ ጉልበታቸው ሳለ ለስራ አይቦዝኑም:: ከንግዳቸው ውለው፣ ከገበያው ሸምተው ይገባሉ:: የዛኔ በወጉ ልጆቻችውን አሳድገው፣ ድረዋል፣ ኩለዋል:: ትናንት ያለፉበት መንገድ አሁን ህልም ይመስላቸው ከያዘ ቆይቷል::
ዓመታትን የቆጠረው ህመማቸው ከብዷቸዋል:: ‹‹ራሴን..›› ማለት ከጀመሩ ወዲህ ነገሮች ተቀይረዋል:: ብዙ ለማውራት ፣ ርቆ ለመሄድ አልቻሉም:: አንዳንዴ የውስጣቸው ችግር ቀናቸውን ይዞት ይውላል:: ይህኔ ይጨነቃሉ፣ ያስባሉ፣ ጓዳቸው ከተራቆተ፣ እጃቸው ከነጣ ቆይቷል:: አንዳች ማድረግ አልቻሉም:: ራሳቸውን ደግፈው፣ አንገታቸውን ደፍተው ሲተክዙ ይውላሉ::
ወይዘሮዋ ውልደታቸው ከወሊሶ ነው:: አዲስ አበባ የገቡት በአፍላ ዕድሜቸያቸው ነውና ቁንጅናቸው ብዙዎችን ያማልል ነበር:: የዛኔ ገጠር ሳሉ ተድረው ሁለት ልጆች ወልደዋል:: ሙሉ ውሎ አድሮ የሕይወት ለውጥ አሰኛቸው:: የልጅነት ልባቸው ለመንገድ ፈጥኖ ተነሳ::
ርቀው መሄድ ፈለጉ:: ከተማን ደግመው ደጋግመው እያሰቡ ነው:: ሲባል እንደሰሙት በዚያ ስፍራ ሁሉ ነገር ይለያል:: ጥሩ መልበስ፣ ጥሩ መብላት ፣ አምሮ መታየት፣ ድምቆ መዋብ ሁሉ:: የማያውቁት አገር ናፈቃቸው:: ገጠሩን ሊያዩት ፣ ሊኖሩበት ጠሉት:: ከፍ አድርገው አለሙ:: ጥቂት ቆይቶ ልባቸው ቀረት ሲል ተሰማቸው:: ሚስጥሩን ያውቁታል:: ደነገጡ፣ ልጆቻቸውን አስታወሱ::
ልጆች ይዞ በሰው ቤት እንግድነት አይሆንም:: እያወጡ እያወረዱ:: ከራሳቸው ተጨቃጨቁ:: ቀናት ወስደው አሰቡ:: ውስጣቸው ቀድሞ ካቀደው ሌላ አዲስ ነገር አላላቸውም:: አዎ ! ብቻቸውን፣ ሌጣቸውን መሄድ አለባቸው:: በቃ ወሰኑ:: ይህን ሲወስኑ የእናትነት አንጀት አልተዋቸውም:: ይፈትናቸው ያዘ:: ልሂድ? ልቅር ? ሲሉ ከረሙ::
አንድ ቀን የክራሞታቸው ሚስጥር በቁርጥ ሃሳብ ተቋጨ:: ይህ ስሜት ቢያሸንፍ እንደዋዛ ቤታቸውን ተዉት:: ሁለት ልጆቻቸውን ስመው አገር ቀዬውን ለቀው ወጡ:: አገር ቤት የተዋቸው ሁለት እንቦቃቅላዎች በድንገት ከእናታቸው ተለዩ::
ህፃናቱ ውስጣቸው እንደ እሳቸው የሆነ አይመስልም:: ምናልባትም እናት ገበያ ሄደው ፣ እንደወትሮው አረፋፍደው ይመለሱ መስሏቸዋል:: ሙሉ ወሰኑ፣ ልባቸውን አረጋጉ:: በልጅነት ዕድሜያቸው የወለዷቸውን ልጆች አገርቤት አስቀምጠው አዲስአበባ ገቡ::
አዲስ አበባ
የዛኔ የከተማ ሕይወት አልከበዳቸውም:: ከሚሄዱበት አካባቢ የቅርቦቹን ጨምሮ በርከት ያለ ዘመድ አላቸው:: ካሰቡት ሲደርሱ እንግድነታቸውን የሚሹ ሁሉ ስለእሳቸው መልካም ሆኑ:: ቀድመው አዲስ አበባ የገቡ እህት ወንድሞቻቸው እንደብርቅ አይተው ተቀበሏቸው:: ሙሉ ከገጠሩ ኑሮ የከተማው ሕይወት ተመቻቸው:: ውበት ጨመሩ:: ፈገግታቸው ደምቆ ፊታቸው ፈክቶ ታየ::
ወይዘሮ ሙሉ ኑሮን በአዲስ አበባ ቀጠሉ:: ገጠር ያሉ ልጆቻቸው በሌሎች እጅ እያደጉ ነው:: ለእነሱ ቤት ያፈራው አይጠፋም:: ወተት ዳቦው ከማጀት፣ እሸት ጥንቅሹ ከማሳው ሞልቷል:: የገጠሯ ጉብል አሁን ከተሜ ሊሆኑ ነው:: የሰውን ባህርይ፣ የአካባቢውን ሁኔታ መልመድ ይዘዋል:: ለመኖር ሕይወትን ለመምራት ደግሞ ከስራ ትግል ይዘዋል:: ያሉበት አካባቢ ሮጦ ለማደር ፣ ሰርቶ ለመግባት ያመቻል:: ሙሉ የልጅነት ዕድሜያቸው ለዚህ አላነሰም:: ያሻቸውን ሰርተው ለማደር አገዛቸው::
ሕይወት በአዲስ አበባ እንደቀጠለ ነው:: ሙሉና የልጅነት ዕድሜ ተግባብተዋል:: በዘመድ እጅ ናቸውና የቸገራቸው የለም:: ያገኙትን እየሰሩ፣ በሰሩት ልክ
ይኖራሉ:: ስለነገው ተስፋቸው ብሩህ ነው:: መልክ ቁመናቸው ያምራል፣ ያስተዋሏቸው በርካቶችን ይማርካል::
ሕይወት ከልጆች ጋር
ወይዘሮ ሙሉ ዓመታትን በአዲስ አበባ አሳለፉ፣ በትዳር ሕይወትም ልጆች ወልደው ሳሙ:: ልጆቻቸውን ለማሳደግ፣ ቤታቸውን ለመምራት ጠንክረው መስራት ነበራቸው:: የሚኖሩበት ቤት የቀበሌ በመሆኑ ለኪራይ አልተቸገሩም:: ሙሉ ስድስት ልጆች አላቸው:: እነሱን ለማሳደግ ደፋ ቀናውን ይዘዋል::
ኑሮ ቀላል አልሆነም:: የአቅማቸውን እየሮጡ፣ የእጃቸውን ያስገባሉ:: ስራቸው ከዕለት የማያልፍ አነስተኛ የንግድ ውሎ ነው:: እንዲያም ሆኖ ለጎጇቸው አላነሱም:: የትዳር ሕይወታቸው በጎ ቢሆንም ፈተና በዛበት:: ልጆቹ በወጉ ሳያድጉ፣ ከቁምነገር ሳይደርሱ ባለቤታቸው በሞት ተለዩ::
ለእማዋራዋ ይህ አጋጣሚ ቀላል የሚባል አልሆነም:: ያለ አጋር ልጆችን ማሳደግ፣ ቤተሰብን መምራት ይከብድ ነበር:: ሙሉ ገጠር ያሉትን ሁለት ልጆች ጨምሮ ቀሪዎቹን ያለአባት ሊያሳድጉ ግድ ሆነ:: ባለቤታቸው በሞት ሲለዩ ሸክሙ በእሳቸው ጫንቃ ወደቀ:: በአንድ እጅ የቆመው የቤት ምሰሶ ሲያጋድል፣ እሱን ሊያቃኑ መሮጥ ያዙ:: አንዳንዴ ጎጇቸው የሞላ በመሰላቸው ጊዜ በእፎይታ ጥቂት ያርፋሉ::
ጠንካራዋ ሙሉ እንዲህም እንዲያም እያሉ ሕይወትን ገፉ:: እንደ እናት ስለ ልጆቻቸው ነገ ያስባሉ፣ ይጨነቃሉ:: የዛሬው ልፋታቸው ዋጋ የሚኖረው እነሱ አድገው፣ ቁምነገር ሲደርሱ ነው:: ይህ እንዲሆን ውስጣቸው በምኞት ይሞላል፣ በተስፋ ነገን ያስባሉ::
ሙሉ እናትነታቸው ከተማ ላሉት ልጆች ብቻ አይደለም:: በልጅነት ገጠር ለተውዋቸው ሁለት ልጆችም ይጨነቃሉ:: ከቀናት በአንዱ ግን ከዚህ ስሜት በላይ የሆነ መከራ አገኛቸው:: ከሁለቱ የገጠር ልጆች አንደኛው መሞቱን አወቁ:: ልባቸው ክፉኛ ተሰበረ:: የእናትነት አንጀታቸው በብሶት ተንሰፈሰፈ::
ቀናት አለፉ:: ወራት ተተኩ:: ዓመታትም በሂደት ተፈራረቁ:: ጠንካራዋ ሙሉ የውስጣቸውን ኀዘን በልባቸው ይዘው ለሌሎቹ ልጆች መኖር ታገሉ:: ሕይወት እንደቀድሞው ቀጠለ:: ልጆች ማደግ ፣ መማር ጀመሩ:: ከፍ ያሉት ትዳር ይዘው ጎጆ ቀለሱ:: የእናት ሸክም በግማሽ ቀለለ:: በመጠኑ ‹‹እሰይ፣ እፎይ›› አሉ::
ሌላው ፈተና
ዳግም የሙሉን ብርታት የሚገዳደር ክፉ አጋጣሚ ድንገት ተከሰተ:: አሁንም የመጣው ችግር አላለፋቸውም :: ገጠር የነበረው ሁለተኛ ልጅ መሞቱን ሰሙ:: ለእሳቸው ይህ መርዶ በእጅጉ ከባድ ነበር:: ፀፀት፣ ቁጭትና ተስፋ መቁረጥ በልባቸው ደምቆ ታተመ:: ሁሉም ስሜት በውስጣቸው ውሎ አድሮ ማንነታቸውን፣ አንገዳገደ::
ሙሉ ገጠር የተዋቸውን ሁለቱን ልጆች ካጡ በኋላ ውስጣቸው ናወዘ:: ምንነቱን በውል የማይለዩት ከባድ ስሜት ያስጨንቃቸው ያዘ:: ደጋግመው ‹‹ራሴን››ይላሉ:: ብዙዎች ቀርበው ይጠይቋቸዋል:: እሳቸው ህመማቸውን በቃላት ሊያስረዱ ይሞክራሉ:: እሳቸው የሚያማቸው ውስጥ ራሳቸውን እንጂ የተለመደው ራስ ምታት አለመሆኑን ይ ናገራሉ::
የሕይወት ትግሉ ቀጥሏል:: ፤ያለ አባት ያደጉት የሙሉ ልጆች የራሳቸውን ሕይወት ይዘዋል:: ሁሉም የሆነው በጠንካራዋ እናታቸው ብርታት ነው:: አሁን እናት አቅማቸው እየደከመ፣ ዕድሜያቸው እየገፋ ነው:: እንደወጉ ማረፍ፣ ጊዜ መውሰድ አለባቸው:: ሁሉም ነገር እንደታሰበው አልሆነም:: ከወይዘሮዋ ቤት ኀዘን አልወጣም:: በተለያዩ ጊዜያት ሶስት ልጆቻውን በሞት ተነጠቁ::
ሕይወት ከድካም ጋር
የወይዘሮ ሙሉ የሕይወት ውጣ ውረድ ከእፎይታው አልደረሰም፤ አሁንም በልጆች ሞት እየተፈተነ ትግሉን ቀጥሏል:: ሙሉ በመጦሪያ ጊዜያቸው የልጅ ልጆች አሳዳጊ ሆነዋል:: ዛሬ እንደቀድሞ ሮጦ የሚያድር፣ ጉልበት የላቸውም:: አሁንም ልጅ ከማሳደግ፣ አርቀው ከማሰብ አልወጡም:: ከሚያሳድጓቸው ልጆች ገሚሶቹ እናት አባት የላቸውም:: ሁለቱንም በሞት የተነጠቁት በጠዋቱ ነው:: እነሱን አሳድጎ ቁምነገር ለማድረስ አቅም ያስፈልጋል፣ ገቢያቸው እንደቀድሞው አይደለም:: ‹‹ከእጅ ወደአፍ›› ነውና ኑሯቸው፣ ጓዳቸው ያሳስባል::
በሕይወት ያለው አንድ ልጃቸው የራሱ ልጆች አሉት:: የእሱን ልጆች ሳይቀር የሚንከባከቡት እንደአያት ብቻ አይደለም:: እንደእናት ጭምር ነው:: እንዲህ መሆኑ ለዕድሜ ጠገቧ ወይዘሮ ሕይወትን አክብዷል:: በጓዳቸው ሁሉ አይገኝም፣ ከማጀታቸው ይጎድላል፣ ከሞሰባቸው ይታጣል::
ወይዘሮ ሙሉ ያለፉበት የሕይወት መንገድ በከፋ ኀዘን የተሞላ ነው:: ሁሉን መለስ ብለው ሲያስቡ ውስጣቸው ይከፋል:: እየደጋገሙ ‹‹ምንዋጋአለው?›› ይላሉ:: ተስፋ ይቆርጣሉ፣ አንገታቸውን ደፍተው ያዝናሉ:: አሁን ደግሞ ኑሮው ተወዷል:: ችግሩ ጠንቷል:: የጤፍ ዘይቱ ዋጋ ሽቅብ ንሯል:: የሽሮ በርበሬው ነገር አይቀመስም::
እሳቸውን ጨምሮ የልጅ ልጆቻቸው በልተው ማደር አለባቸው:: በየቀኑ የጎደለውን መሙላት ይከብዳል:: በእነ ወይዘሮ ሙሉ ቤት እንደፊቱ ከቁርስ እስከ እራት ምን ይሰራ? ምን ይበላ ? የሚባልበት አይደለም:: ሁሉ ነገር ይቸግራል:: ሁሉም ጉዳይ ያስጨንቃል:: ግን አሁንም ሕይወት በቤቱ ቀጥሏል:: መኖር ከተባለ ደግሞ እማወራዋም ከነቤተሰባቸው እየኖሩ ነው::
ወይዘሮ ሙሉ ጮክ ብሎ ማውራት፣ ደጋግሞ መናገር ያስጨንቃቸው ይዟል:: አሁንም ‹‹ራሴን ያመኛል›› ይላሉ:: ዛሬም ቀርበው ለሚጠይቋቸው የተለመደው ራስ ምታት እንዳልሆነ ያስረዳሉ:: ብቻ ‹‹ራሴን ያመኛል›› ይሉት ቃል ከአፋቸው አይጠፋም:: እንደምንም ከሀኪም ቀርበው ችግራቸውን ሊያስረዱ ሞክረዋል:: ደጋግመው ስላልታከሙ መፍትሄ አላገኙም::
አንዳንዴ ሙሉ ከቤታቸው ወጥተው ለመግባት መንገድ ይጠፋቸዋል:: ያሉበትን ለማስታወስ፣ በመጡበት ለመመለስ ይቸገራሉ:: ከሰፈር መውጣታቸውን እንጂ ወዴት እንደሚሄዱ የማያውቁበት ጊዜ ይበረክታል:: ይህ እውነት ስጋት ቢሆናቸው ከቤታቸው ርቀው አይሄዱም:: ይህ ህመማቸው በአንድ ወቅት ከአንድ ወር በላይ ራሳቸውን አስቶ ካልጋ አውሏቸው ነበር:: ዛሬ ቆመው በመሄዳቸው ፈጣሪን ያመሰግናሉ:: እንዲያም ሆኖ አሁንም ስጋቱ ከእሳቸው ጋር ቀጥሏል::
ሁለቱ የልጅ ልጆቻቸው የአንደኛው ሟች ልጃቸው ፍሬዎች ናቸው:: እነሱ እናት አባታቸውን ያጡት ገና በህፃንነታቸው ነው :: የዛኔ ይኖሩበት ከነበረው ጅማ ድረስ ተጉዘው ያመጧቸው አያታቸው ሙሉ ነበሩ:: ሁለቱ ልጆች ይማራሉ:: ትምህርት ውለው ሲመጡ ለአያታቸው የአቅማቸውን በማድረግ ያግዛሉ::
ወይዘሮ ሙሉ ዛሬ የዕድሜ መግፋት፣ ከኀዘን ተደርቦ እያንገላታቸው ነው:: ከአምስት ዓመታት በፊት የጀመራቸው የራስ ህመም ከበርካታ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች አግዷቸዋል:: አሁን አጠገባቸው ሁነኛ ሰው ከሌለ ከቤት መውጣት አይደፍሩም:: ደጋግሞ የሚያስጨንቃቸውን ህመም ደጋግመው ያስባሉ::
ወይዘሮ ሙሉን ያገኘኋቸው ልደታ አካባቢ ከተገነባው የምገባ ማዕከል ውስጥ ነበር:: ገና ሳያቸው የእናትነት ወዘናቸውን ወደድኩት:: ዛሬም ቆንጆ የሚባሉ ሴት ናቸው:: ሲያወሩ ቀስ እያሉ ነው:: ርጋታቸው አስደነቀኝ :: አረፍ እያሉ ያጫውቱኝ ያዙ:: የሚሉትን በጥንቃቄ እየሰማሁ ጥያቄ አቀረብኩላቸው::
‹‹በተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል›› የተገኙት እሳቸውን ለመሰሉ ወገኖች ግልጋሎት እንደሚሰጥ ሰምተው ነው:: ይህን ባወቁ ጊዜ ዓይናቸውን አላሹም:: ደስ እያላቸው የሚያውቋቸውን ሰዎች ተከትለው መጡ:: የሰሙት ሁሉ እንደተባለው ሆኖ አገኙት::
እማማ ሙሉ ባመጡት ባዶ ሰሀን የሚሰጣቸውን ትኩስ ምግብ ቋጥረው ይወስዳሉ:: ቤት ሲገቡ የልጅ ልጆቻቸው በናፍቆት ይጠብቋቸዋል:: የእጃቸውን አቅርበው፣ ቤት ካፈራው ዘንቀው በጋራ ማዕድ ይቆርሳሉ:: ሙሉ ትናንት የእሳቸው ዓለም ሌላ ነበር:: ሰርተው፣ ሸምተው፣ ነጭ ከጥቁር ጋግረው በልተዋል:: በአውደዓመት፣ በዝክሩ፣ ሙክት ከዶሮ አርደው ዘመድ ጎረቤት ጠርተዋል::
ዛሬ ደግሞ ታሪካቸው ተቀይሯል:: ልጆቻቸውን ሞት ነጥቆ፣ ጤናቸውን ህመም ይዞ፣ የሰው እንጀራን እያዩ ነው:: ወይዘሮዋ ትናንትና የሆነባቸውን አይረሱም:: ዛሬ በሕይወት ቆመው የሆነላቸውን ሲያስቡት ደግሞ ፈጣሪን አያማርሩም:: ደግመው ደጋገመው ‹‹ተመስገን›› ይላሉ:: ‹‹ተመስገን…››
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መጋቢት 9 ቀን 2015 ዓ.ም