ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ! ሳምንቱ እንዴት አለፈ? አሁን የትምህርት ወቅት እንደመሆኑ በጥናት እንዳሳለፋችሁት እንገምታለን። ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ብቸኛው ወደሆነውና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኘውን የእንስሳት የተፈጥሮ ቅርስ መዘክር ጎብኝተን በመዘክሩ ስለሚገኙ የወፍ ዝርያዎች አስነብበናችሁ እንደነበር ታስታውሳላችሁ አይደል። ዛሬ ደግሞ ቀጣዩን ክፍል ይዘን ቀርበናል፡፡
ልጆች! እነዚህ እንስሳት እናንተ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የተማራችሁትን በተግባር እያያችሁ የምታረጋግጡባቸው እንደመሆናቸው ሕይወት የላቸውም። በመዘክሩ የአደን ሠራተኞች ታድነው የሚመጡ ያረጁ፤ ወይም በተለያየ አደጋ የሞቱና ጫካ ውስጥ ወድቀው የተገኙ እንስሳት ናቸው። በመሆኑም አስጎብኛችን ወይዘሮ አምሳለ ተፈራ እንደነገሩን እነዚህ እንስሳት ወደ መዘክሩ ከመጡ በኋላ የእናንተን የተማሪዎችንና የሌሎች ጎብኚዎችን ትኩረት እንዲስቡ ተደርገው በሦስት መንገድ ይዘጋጃሉ።
በመዘክሩ ከሚገኙ አብዛኞቹ እንስሳት የሚዘጋጁት የውስጥ አካላቸው ይወጣና ሌላ ሰው ሠራሽ አካል ይገባላቸዋል። ከተፈጥሮ ዓይናቸው ጋር ፍፁም ተመሳሳይ የሆነና ከጠርሙስ የተሰራ ሰው ሠራሽ ዓይንም ይገጠምላቸዋል። ቆዳቸውና ቀንዳቸው ግን የራሳቸው የእንሰሶቹ ነው። ይሔም ሕይወት ያላቸው ያስመስላቸዋል። እንደ ጢንዚዛ ያሉት ደግሞ ሙሉ አካላቸው እንዳለ የራሳቸው ሆኖ በኬሚካል በመድረቅ ነው ለጉብኝት የሚቀርቡት። እንደ እባብ፤ ዘንዶና እንቁራሪት ያሉት ደግሞ ሙሉ አካላቸው እንዳለ ሆኖ በኬሚካል በማንበር ወይም በመዘፍዘፍ ነው ለዕይታ የሚቀርቡት። ልጆች ስለዚህ ሁሉም ሕይወት ያላቸው ይመስላሉ። ነገር ግን ሕይወት የላቸውምና ስትጎበኙ አትፍሯቸው። ቀርቦ በእጅ መንካት ግን አይቻልም፤ እሽ ልጆች!
ልጆች በመጀመርያ የምናስጎበኛችሁ የጽሑፍ፤ የስዕልና የፎቶ መረጃ ያለበት ክፍል ሲሆን ሁለተኛው የጀርባ አጥንት የሌላቸው እንስሳት ስብስብ ያለበት ነው። ሆኖም ልጆች እዚህ ክፍል ዋልያም አለ። ነገር ግን ዋልያ እዚህ ክፍል ውስጥ ተካትቶ የተቀመጠው በአገራችን የሚገኝ ብርቅየ ስለሆነ የጎብኚዎችን ትኩረት እንዲስብ ተብሎ መሆኑን አስጎብኛችን ነግረውናል። ሦስተኛው ክፍል ውስጥ የሚገኙት እንደ እንቁራሪት ፤ ጉርጥ ያሉና በውሃ ውስጥም ሆነ በመሬት የሚኖሩ እንስሳት ናቸው፤ ልጆች እዚሁ ክፍል ውስጥ በአንድ ጎን እንደ እባብ፤ ዘንዶና ሌሎች በደረታቸው የሚሳቡ እንስሳቶች አሉ። አራተኛው ክፍል አጥቢ እንስሳቶች የሚገኙበት ነው። ልጆች አምስተኛውም የአጥቢዎች ክፍል ሲሆን ቀንዳቸው ፤ ቆዳቸውና ከአንገታቸው በላይ ያለው የሰውነታቸው ክፍል ብቻ የሚገኝበት ነው። እነዚህም በሁለት በኩል ሲሆን የተቀመጡት በአንደኛው ጎን ተሰድረው የተቀመጡት ሥጋ በል እንስሳት ናቸው። በሌላው በኩል ያሉት ደግሞ ሣርና ቅጠላ ቅጠል የሚበሉ እንስሳት እንደሆኑም አስጎብኛችን ነግረውናል። ልጆች ታዲያ በዚህ ክፍል ውስጥ ትልቅ ቆዳ አለ። ቆዳው የወንድ አንበሳ ሲሆን ከላይ ጎፈር እንዳለውም አይተናል። ትልቅ የሆነው የወንድ አንበሳ እንደሆነም ነግረውናል። ከታች ያሉት ቆዳዎች ደግሞ የጅብና የቀበሮ እንዲሁም የሚዳቆና የአንባራይሌ እንደሆኑ አስረድተውናል። ከጅብ ዝርያ ተራ ጀብ የሚባለው ፤ የትም ቦታ የሚገኝ እንደሆነ ኃይለኛና ሰው ሳይቀር የሚበላው ጅብ ይሄው ተራ ጅብ የሚባለው እንደሆነም አስረድተውናል። በመጠን ይሄ ጅብ ግዙፍም ነው። ቆላማ ቦታ ላይ የሚገኘው ጅብ በላተኛ ቢሆንም እንደ ተራው ጀብ ኃይለኛ አይደለም።
በዚሁ ክፍል በሌላው ጎን የድመት ዝርያ የሆኑ እንስሳት ቆዳዎችም ይገኛሉ። ቆዳዎቹ የአቦ ሸማኔ፤ የነበርና የአነር ናቸው። ታዲያ አስጎብኛችን ቆዳቸው በዚህ ክፍል ውስጥ ከሚገኘው አጥቢና የድመት ዝርያ ያላቸው እንስሳት መካከል አቦ ሸማኔ ምድር ላይ ካሉት አጥቢ እንስሳቶች ፈጣኑ ሯጭ መሆኑን ነግረውናል። እሳቸው እንዳሉን አቦሸማኔ በሰዓት እስከ 120 ኪሎ ሜትር ይሮጣል፡፡
ልጆች አስጎብኛችን ስለነዚህ የድመት ዝርያ እንስሳት አንዳቸው ከሌላው የሚለያዩበትንም ነግረውናል። እንደነገሩን ታዲያ አቦ ሸማኔ ፊቱ ላይ ጥቋቁር መስመር ሲኖረው ነብር ግን የለውም። በተጨማሪም አቦ ሸማኔ ድፍን ጥቁር ነጠብጣብ ሲኖረው ነብር ደግሞ እንደ አበባ ክብ ነጠብጣቦች ናቸው ያሉት። በመሆኑም ሁለቱም በነጠብጣባቸው በእጅጉ ይለያሉ። የዝንጀሮና ጦጣ፤ የአይጥ ቆዳዎችም በክፍሉ ውስጥ አሉ። የሌሊት ወፎች ቆዳም ክንፍ ስላላቸውና ስለሚበሩ እንጂ አጥቢዎች በመሆናቸው በዚሁ ክፍል ውስጥ ተካትቶ ይገኛል። አነር ደግሞ ዳር ዳሩ ጠቃጠቆ መካከሉ ሰረዝ ጅራቱ ደግሞ አጭር ነው።
አምስተኛው ክፍል አጥቢ እንስሳቶች የሚገኙበትና ከአንገት በላይ የእንስሳት አካል ሲሆን በዓለማችን ግዙፉ የምድራችን እንስሳ የሆነው የዝሆን የራስ ቅል አለ። ልጆች ታዲያ አስጎብኛችን እንደገለፁልን ትልቅ የሚባለው የአንዱ ዝሆን ሙሉ የሰውነት አካል እስከ 6ሺህ ኪሎ ግራም ይመዝናል። ቅልጥሙ እንዲሁም የእግሩ መርገጫ ጫማውም ከራስ ቅሉ ጋር አብሮ ተቀምጧል። በተጨማሪም ውሃ የሚጠጣበትና ምግብ ወደ አፉ የሚያደርስበት ኩንቢውም ያውም ደግሞ የታችኛውን መንጋጋ ሳይጨምር በዚሁ ሥፍራ ተቀምጦ የሚገኝ ሲሆን እንስሳው ግዙፍ በመሆኑ ሰፊ ቦታ መውሰዱንም አስተውለናል። በዚሁ ክፍል ውስጥ የሰጎን እንቁላሎችም ይገኛሉ። እንቁላሎቹ ትልልቅ ሲሆኑ ስዕል እየተሳለባቸው ለገበያ የሚቀርቡ መሆናቸውን አስጎብኛችን ገልፀውልናል፡፡
የአንበሳ፤ የጉማሬ፤ የዝሆንና የከርከሮ ጥርሶችም በዚሁ ክፍል ውስጥ ይገኛሉ። ጥርሶቹ ረጃጅም አንዳንዶቹም ሹል ናቸው። በተለይ በጎንና በጎን የሚወጡት ሁለቱ የዝሆን ጥርሶቹ በጣም ረጃጅም ናቸው። ልጆች! ይሄ የዝሆን ጥርስ በከፍተኛ ገንዘብ የሚሸጥ ውድ ሲሆን በአብዛኛው ዝሆን የሚታደነው ለዚህ ለጥርሱ ሲባል ነው። ጥርሱ ለጌጣጌጥና ለተለያዩ ነገሮች መሥርያ ይውላል።
ሌላው ውሃና መሬት ላይ የሚኖር ከዝሆን ቀጥሎ ያለ ግዙፍ እንስሳ የጉማሬ የራስ ቅል እዚህ ክፍል ይገኛል። የታችኛው መንጋጋ ከነጥርሱ ሲገኝ ትልልቅ በመሆኑ ከዝሆን የማይተናነስ ስፍራ ይዟል። በተለይ የውሻ ክራንቻ የሚባለው ጥርሱ እያደገ፤ እያደገ በመምጣት መጨረሻ ላይ ከዳርና ከዳር ያሉትን ረጃጅም የዝሆን ጥርሶችን ሊያክል እስኪደርስ ያድጋል። ልጆች! እኛ እንደጎበኘናቸው እናንተም ከአባባና ከእማማ ጋር ሆናችሁ ወደ መዘክሩ በመሄድ እነዚህን እንስሳት ጎብኝዋቸው እንድትጎበኟቸው እጋብዛለን ።
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መጋቢት 10 ቀን 2015 ዓ.ም