በአትሌቲክስ ሕይወቷ ለመቁጠር የሚታክቱ ሜዳሊያዎችን በተለያዩ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ማጥለቅ ችላለች። ይህም የረጅም ርቀት የምንጊዜም ጀግና አትሌት አሰኝቷታል። በተለያዩ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች እጅን በአፍ የሚያስከድኑ ድሎችን በመቀዳጀት ለበርካታ አትሌቶች ለማሳካት ቀርቶ ለማሰብ የሚከብዱ ገድሎችን ቀለል አድርጋ መስራት ተክናበታለች። አልሸነፍ ባይነትና ጠንካራ የጀግንነት ስሜቷ ጥበብ ከተሞላው የአሯሯጥ ስልቷ ጋር ተደምሮ እንኳን የአገሯ ዜጎች የዓለም ሕዝብም አድናቆት እንዲቸራት አድርጓል። ወርቅ አነፍናፊዋ የረጅም ርቀት ቀወርዋሪ ኮከብ ጥሩነሽ ዲባባ ቀነኒ።
አትሌቲክስን ባህሉ ካደረገ ቤተሰብ የፈለቀችው ኮከብ የታላላቆቿን በተለይም የአክስቷ ደራርቱ ቱሉና የታላቅ እህቷን እጅጋየሁ ዲባባ ፋና ተከትላ ወደ አትሌቲክሱ ዓለም ከገባች በኋላ ተነግሮ የማያልቅ ታሪክ ፅፋለች።
ጥሩነሽ ገና በለጋ እድሜዋ አትሌት የመሆን ዕድል የነበራት ቢመስልም የሩጫ ሕይወቷ ምን ያህል አስደናቂ ታሪክ የሚፃፍበት እንደሚሆን ቀደም ብለው የተነበዩ ጥቂቶች ነበሩ። ያም ሆኖ በአትሌቲክስ ታሪክ በትንሽ ዕድሜ የዓለም ቻምፒዮን የሆነች ሴት፣ በትንሽ ዕድሜዋ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ የሜዳለያ ተሸላሚ ሴት፣ በኦሊምፒክ 5 ሺና 10ሺ ሜትር የመጀመርያዋ ሴት አትሌት ከመሆን በተጨማሪ ስድስት የኦሊምፒክ ሜዳሌዎች፣ አምስት የዓለም ቻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያዎችንና ሌሎች በርካታ ድሎችን ከዓለም ክብረወሰኖች ጋር ለማሳካት በቅታለች። ይህች በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅ የሆነች ኮከብ ስለእሷ መስማትና ማንበብ የሚፈልጉ አያሌ ቢሆኑም እሷ ግን ውድድሮችን ስታደርግ እንጂ ብዙ ጊዜ ወደ መገናኛ ብዙሃን ወጥታ የምትታይ አይደለችም። በቅርቡ ግን ከሰላምታ መፅሄት ጋር ባደረገችው ቃለምልልስ በአትሌቲክስ ሕይወቷ ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶችን ሰንዝራለች።
እንደሷ ሁሉ በርካታ እንቁ ኦሊምፒያኖች የፈለቁባትን የአትሌቶች ምድር በቆጂን በተመለከተ ጥሩነሽ ዓመታትን መለስ ብላ የአትሌቲክስ ሕይወቷን ጅማሬ ስታስታውስ “በቆጂ ከፍታ ላይ የምትገኝ ትንሽ ከተማ ነች። ትንሸ ቀዝቃዛም ነች!” ትላለች። ይህም በስልጠና ወቅት አትሌቶችን የሚረዳ እንደነበር ታስታውሳለች። አሰልጣኞችም መልክአምድሩ የሚቸረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው የሩጫ ጥበብና ቴክኒካዊ እንቅስቃሴን በማከል ብዙ ኮከብ አትሌቶችን ሊዲያፈሩ እንደቻሉ ትናገራለች።
ጥሩነሽ መሮጥ የጀመረችው ገና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለች ሲሆን ጎበዝ አትሌት የመሆኗ ነገር ግልጽ ሆኖ መታየት የጀመረውም በዚያ ወቅት ነበር። የመጀመርያ ዓለም አቀፍ ውድድር ያደረገችው እአአ በ2001 ነበር። ውድድሩን ስታካሄድ የ15 ዓመት ልጅ የነበረች ሲሆን አምስተኛ በመሆን ነበር ያጠናቀቀችው። ወደ አገር አቋራች ውድድሮች ለመግባት ዕድሉን ያገኘችውም ብዙም ሳይቆይ ነበር። ይህም ወደ ታላቅ አትሌትነት ለማቅናት ማርሽ ቀያሪ አጋጣሚ ሆኗታል። ምንም እንኳን አንፀባራዊ አትሌትነት ህይወቷ በትራክ (መም) ውድድሮች ላይ የበዛ ቢሆንም እአአ ከ2003-2008 ዓመት ድረስ በአገር አቋራጭና በተለያዩ የዓለም ቻምፒዮና ውድድሮች አምስት የወርቅ ሜዳለያዎችን በማስመዝገብ ሁለገብ የሆነ ድንቅ ችሎታዋን ማሳየት ችላለች፡፡
እአአ 2003 በፓሪስ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የረጅም ርቀት ስኬቷን አንድ ብላ የጀመረችው ጥሩነሽ፣ ገና በ18 ዓመቷ በ5 ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ በማሸነፍ በአትሌቲክስ ታሪክ ትንሿ ሴት የዓለም ቻምፒዮን መሆን ችላለች፡፡
ያንን የበኩር ድሏን ስታስታውስም “በሕይወቴ ከተደሰትኩባቸው ወቅቶች አንዱ ነበር፣ በሙቀት ውስጥ ነው ያሳለፍኩት ከዚያም በመጨረሻው ውድድር ላይ ነበርኩ፤ እና ሳሸንፍ ማመን አቃተኝ፣ ለመሮጥ አንድ ተጨማሪ ዙር ይቀራል ብዬ አሰብኩኝ! አሸንፋለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር፣ ምክንያቱም ከመላው ዓለም የተሳተፉ ትልልቅ አትሌቶች ነበሩ፤ ህልም እያለምኩ መስሎ ተሰማኝ” ትላለች፡፡
ከመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ድሏ ከጥቂት ወራት በኋላ ወደ አገር ውስጥ ውድድሮች ተመልሳ በታላቁ ሩጫ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር መሳተፍ እንደቻለችም ኮከቧ ታስታውሳለች።
ከድሎቿ ሁሉ እጅግ አንፀባራቂ የሆነውና አሁንም ድረስ በታሪክ ብቸኛ ሆኖ የሚጠቀሰው የቤጂንግ 2008 ኦሊምፒክ የ 10 እና 5ሺ ሜትር ጥምር የወርቅ ሜዳሊያ ስኬቷ ነው። ለእሷ ግን የተለየ ቦታ ያለው ምናልባትም በፓሪሱ የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ድሏ ምክንያት ይሆናል የ5ሺ ሜትር ስኬቶቿ በልቧ ውስጥ ልዩ ቦታ አላቸው። “5 ሺ ሜትርን ለመሮጥ በጣም የምወደው ርቀት ነው፣ ሁልጊዜ ብዙ ፉክክር አለ፣ ስለዚህ በዚህ ርቀት ውድድሮችን ባሸነፍኩ ቁጥር በጣም ደስ ይለኛል” ትላለች።
ተወርዋሪዋ ኮከብ በጎዳና ላይ ውድድሮችም የዋዛ አይደለችም። እአአ በ2012 በእንግሊዝ በተካሄደው ተወዳጁና ታላቁ የግማሽ ማራቶን የመጀመርያ ውድድሯን አድርጋ በድንቅ ብቃት ማሸነፍ ችላለች። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ጥሩነሽ ፊቷን ወደ ማራቶን አዙራም በለንደንና በርሊንና በዓለም አቀፍ እውቅና በተሰጣቸው ውድድሮች ድንቅ ብቃቷን አሳይታለች። በ2017 በብዙ አትሌቶች ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን የቺካጎ ማራቶንን በማሸንፍም ይህንኑ አስመስክራለች።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከወሊድ ጋር በተያያዘ ከውድድር ርቃ የቆየችው ጥሩነሽ በቅርቡ ወደ ውድድር ብትመለስም ዘመን አይሽሬ ታሪኮችን በሰራችባቸው የመም ውድድሮች ሳይሆን በማራቶን ነው።
ከሩጫ ውጪ ከቤተሰቧ ጋር በማሳለፍ የበለጠ ደስታን እንደምታገኝ የምትናገረው ጥሩነሽ፣ የሩጫ ፍቅሯ ግን እንደቀድሞ ጠንካራ መሆኑንም ትገልጻለች። “ሩጫ በደሜ ውስጥ ነው፣ እናም ለስልጠና በወጣሁበት ጊዜ ሁሉ አሁንም ቀድሞ የነበረኝ አይነት ስሜት ይሰማኛል። ሁልጊዜ ልቤ እዚያው ሩጫ ላይ ነው” ስትልም አትሌቲክስ በሕይወቷ ውስጥ ያለውን ቦታ ታብራራለች።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን መጋቢት 10 ቀን 2015 ዓ.ም