ያሳለፍነው ሳምንት የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ/ም ለኢትዮጵያ የሥነ-ጽሁፍም ሆነ የምርምር ዓለም ጥሩ ቀን አነበረችም። ሊነጋጋ ሲል ሰማዩ ይጠቁራል፤ ያቺ ሌሊት ግን የምርም የጠቆረችና ምህረት የለሽ ጨለማን ያዘለች ነበረች። ምክንያቱ ደግሞ ጉምቱውን የኢትዮጵያ ሥነ- ፅሁፍ ሰው መመለሻ በሌለው የሞት ሀዲድ ይዛ እብስ ማለቷ ነው።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው፣ በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሁፍና የምርምር ስራዎች ውስጥ ትውልድን ከመቅረጽ አንስቶ የነበራቸው ሚና ይህ ነው ተብሎ በቀላሉ የሚነገር አይደለም። ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ማን ነበሩ፤ ለሀገራቸውስ ምን አበረከቱ የሚለውን ጉዳይ በዛሬው የዝነኞች ገፅ ከብዙ በጥቂቱ እንቃኘው።
ጥቅምት 10 ቀን 1944 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሰማይ የፈካበት ብሩህ እለት ነበረ። ለምን ካላችሁ የምናወራው ስለ አንድ ታላቅ ሰው ነውና እኚህ ሰው የተወለዱበት እለት ነበር። እኚህ ታላቅ የሥነ-ፅሁፍ ሰው ባይዘመርላቸውም በዝምታና በጠመዝማዛው ጎዳና እየተጓዙ በተለይ ለሥነ-ጽሁፉ ዓለም ዋርካ የሚያስብላቸውን እልፍ ተግባራት ከውነዋል። ከነበራቸው የልጅነት ታሪክ ስንጀምርም የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በተወለዱባት የደሴ ከተማ ሲሆን፣ በወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት በመጀመር፣ በዚያው በደሴ በዕደ ማርያም ትምህርት ቤት አጠናቅቀዋል። ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት በነበሩበት ወቅት ከነበራቸው የትምህርቱ ዓለም ብቃት ባሻገር ሙዚቃ የመጫወት ልዩ ተሰጥኦና ፍቅርም ነበራቸው። ከዚያ በመውጣትም የተወለዱባትን ቀዬ ለቀው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የሀገር ኩራት ለመሆን ያበቃቸውን የትምህርት ጉዞ ቀጠሉ። በዚህም በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በአንድ ወቅትም የአርቲስት ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ተማሪ ነበሩ።
ዩኒቨርሲቲው በሚሰጠው ማህበረሰባዊ አገልግሎት ላይም ቀዳሚነታቸውን በማሳየት በኤርትራ ከረን ለአንድ ዓመት በማስተማር እንዲሁም በእድገት በህብረት ዘመቻ ደግሞ በዓድዋ አካባቢ ዘምተው የህብረተሰብ አገልግሎትን በተሳካ ሁኔታ ሰጥተዋል።
ከዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከተቀበሉ በኋላም በስሩ ወደ ነበረው ወደ አለማያ ግብርና ኮሌጅ በማቅናት በረዳት ምሩቅነት ተቀጥረው ክህሎትና የስራ ደረጃቸውንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻሉ እስከ ዩኒቨርሲቲ መምህርነት ደረጃ በመድረስ በመምህርነትና በተከታታይ ትምህርት አስተባባሪነት ቀጠሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋና ፎክሎር ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ውስጥ ደግሞ በተለያዩ ማዕረጎችና ኃላፊነቶች ለማገልገል ችለዋል። ከብዙ የመማር ሂደት በኋላም ከትምህርት ቤቶችና ከሕይወት የቀሰሙትን እውቀት ለትውልዱ በማካፈል ለአርባ ዓመታት ያህል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲያስተምሩና ትውልዱን ሲቀርጹም ቆይተዋል።
በእነዚህ አርባ ዓመታትም የሥነ-ጽሁፍ መምህር በመሆን በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ትልቅ ዋርካ ሆነው ከስራቸው ብዙዎችን አስጠልለው ጠቢባንን ማፍራት ችለዋል። በሥነ ፅሑፍ ሃያሲነታቸው አንቱታን ያተረፉት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን ለ42 ዓመታት ባገለገሉበት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ሥነ ፅሑፍ ትምህርት ክፍል ውስጥም ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል።
የመምህርነት ሙያ እንደ ድልድይ ሆኖ ትውልዱን ማሸጋገር ነው። ደስታና እርካታው የሚገኘውም በእነርሱ ድልድይነት ተሸጋግረው ከወደ ማዶው በሚመለከቷቸው ሰዎች ስኬት ነው። ረዳት ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ለኢትዮጵያ የሥነ-ጽሁፍም ሆነ ለሌላ ያበቋቸውን እንቁ ሰዎችን ቤቱ ይቁጠረው ከማለት ውጭ በቁጥር ለማስቀመጥ እጅግ በጣም አዳጋች ነው። የእሳቸው ስራ ሌሎችን ከማብቃት በተጨማሪ በተለያዩ የስነ-ጽሁፍ ጉዳዮች ላይ ጠለቅ ያለ ምርምር ማድረግም ነበር። ከምርምር ስራዎቻቸው መሃከል አንደኛው ከፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ጋር በመሆን የተለያዩ የሥነ ሕዝብ ጥናቶችን የሰሩት ተጠቃሽ ነው። ከዚህም በሻገር በትልቅ ሀያሲነታቸውም የታወቁ ነበሩ።
በሕይወት ዘመናቸው ትንሽ ትልቅ ሳይሉ ከጀማሪ ደራሲያን እስከ ትላልቅ ሀያሲያን እና ተማራማሪዎች ድረስ በማማከርና ልዩ ልዩ ሙያዊ ድጋፍን መስጠት ስለቻሉት ታላቅ ሰው ከእሳቸው ጋር በተለያዩ አጋጣሚዎች መገናኘት የቻሉ ሁሉ በልበ ሙሉነት ታላቅነታቸውን ይመሰክራሉ። ከእነዚህም መሃከል ከ1976 ዓ/ም ጀምሮ እንደሚያቋቸውና በተለያዩ ጉዳዮች ላይም አብረው እንደሰሩ የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር ደረጀ ገብሬ “ዘሪሁን በተገኙበት ሁሉ የተመሰገኑና ነገሮችን ጥበብ በተሞላበት መንገድ የሚከውኑ የስኬት ሰው ነበሩ” በማለት ይገልጿቸዋል።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ለትውልድ አሻራቸውን ለማኖር ከሰሯቸው ትላልቅ ስራዎች መሃከል አንደኛው ‘የሥነጽሁፍ መሠረታውያን’ የተሰኘው መጽሃፋቸው ሲሆን፣ ሌላኛው እውቅናን ያገኙበት መጽሃፍ ደግሞ ‘ከበዓሉ ግርማ እስከ አዳም ረታ’ የተባለው የሥነ ጽሑፍ ትምህርት አጋዥ መጽሃፍቶችን ጨምሮ አራት የተለያዩ መጽሃፍትን በመጻፍ ለአንባቢያን አድርሰዋል። በበሳል ሀያሲነታቸው ከሚሰሯቸው የአርትኦት ስራዎች በተጨማሪ የተለያዩ ጥናት እና ምርምሮችን በመሥራት ሀገርና ትውልድ ገንቢ ለሆኑ ዓላማዎች አውለዋል። ዋነኛው ዓላማቸውም በትውልዱ ውስጥ የእውቀትና የጥበብን ብርሃን ማስረጽ ነበር። በዚህም ከመጀመሪያ ዲግሪ ጀምሮ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ በርካታ ተማሪዎችን አስተምረው ለወግ ለማዕረግ አብቅተዋል።
ከማስተማርና ከማሰልጠን ጎን ለጎን በተለያዩ ጊዜያት 143 የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂዎችን ፣ 80 የማስተርስ ዲግሪ እንዲሁ 20 የዶክቶሬት ዲግሪ ተማሪዎችን በምርምር ሥራዎቻቸው በማማከርና ድጋፍ በመስጠት አለኝታነትታቸውን አሳይተዋል። ይህን ሁሉ ሲያደርጉ ግን ያለ አንዳች ሳንቲም ከንጽሁ የበጎነት ስሜት በመነጨ መልካምነት ነበር። ከእነዚህም መሃከል በዛሬይቱ የኢትዮጵያ የሥነ-ጽሁፍና የምርምር ማህደር ውስጥ ስማቸው የሰፈሩ የእሳቸው ፍሬዎች በርካቶች ናቸው።
እሳቸው ‘የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ዋርካ ናቸው’ ሲባል በምክንያት ነው። ከእዚህ ዋርካ ስር ቁጭ ብለው የእውቀትና የጥበብን ሀሁ ከተማሩት መሃከል አንዷ የአሁኗ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ሥራ አስኪያጅ በመሆን የምታገለግለውና በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ የመጀመርያዋ ሴት የአጭር ልብ ወለድ ጸሐፊት መሆን የቻለችው የዝና ወርቁ ናት። እሷም ስለ እውቀት አባቷ ቃል በቃል እንዲህ ትገልጻለች፣ “ጋሽ ዘሪሁን ትዕግስተኛ ፣ መካሪ ነበር። ኢትዮጵያ እጅግ ታላቅ የሥነ ጽሑፍ ምሁር ነው ያጣችው።”
ሌላኛው ከእሳቸው ጥላ ስር ረዥም የሆነ የጥበብ ብርሃንን አሻግሮ የተመለከተው ከያኒ አንዷለም አባተ በኀዘን ተክዞ “እኚህን ሰው ማጣት የተደገፍክበት ወንበር ድንገት ሸርተት ሲልብህ ያለውን ስሜት የሚፈጥር ነው” ሲል ስሜቱን ያጋራል።
በነበራቸው የሙያ ክህሎትና ሁለ ገብ እውቀት በተለያዩ ጊዜያት ያቀረቧቸው የምርምር ሥራዎች በውጭና በሀገር ውስጥ የምርምር መፅሔቶች ላይ ለመታተም በቅተዋል፡፡ የምርምር ስራዎቹ ከሀገር አልፈው ለዓለም ሁሉ ጠቃሚና አዲስ መንገድ ቀያሽ ናቸው። በብዙ ውጣ ውረዶች እያለፋ ለኢትዮጵያ ሀገራቸው ዘመን አይሽሬ የሆኑ ስራዎችን ማበርከት በመቻላቸውም በሥራ ዘመናቸው የተለያዩ ሽልማቶችን ተቀዳጅተዋል። በሕይወት ዘመናቸው ብዙ ደክመው ብዙ የሰሩ ቢሆንም እሳቸው ግን ገና ምን ሰራሁ የሚሉ እንጂ ይሄን ሰራሁ ብለው የማኮሩ አልነበሩም። በሚዲያዎች እንኳን ቀርበው እምብዛም የማይታዩ ሙያ በልብ ስለመሆናቸው የሚያውቋቸው ይናገራሉ።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን ከህልፈተ ሕይወታቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ በአንድ ትልቅ ስራ ላይ ተጠምደው ነበር። የታላቁ ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ መጽሃፍ የሆነውን ‘ፍቅር እስከ መቃብር’ን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽ ከሰው መሆን ፊልም ፕሮዳክሽን ጋር በመተባበር መፅሐፉን ወደ ቴሌቪዥን ድራማ ለመቀየር በሚሰራው ስራ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን ሙያዊ ድጋፋቸውን በመለገስ ላይ ነበሩ። በመጽሃፉ ዙሪያም ጠለቅ ያለ የምርምር ስራ በማካሄድ ላይ ነበሩ።
የአጭር ልብወለድ ንድፍና ተግባራዊነት ላይ የሚያተኩር መፅሐፍ አጠናቀው ለሕትመት ለማብቃት ዝግጅት በማድረግ ላይም ነበሩ። በብዙ ድካም የዘሩትን የእውቀት አዝመራ እሸቱንም ሳይቀምሱ ያቺ ለሊት ደርሳ ወደ ሞት ብትወስዳቸውም። የሚሰሩት ሁሌም ለትውልዱ ነውና ትውልዱም ከሚያምረው የእውቀት አዝመራ እየቀጠፈ መብላቱና እሳቸውን ማመስገኑ የማይቀር ነው። ትልልቅ ሰዎች ሁሌም በትልቅ ስራቸው ውስጥ በህያውነት ተቀርጸው ይኖራሉ።
ከጥበቡ ዓለም ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ጥሩ የሆነ የቤተሰብ መሰረት መገንባት የቻሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው የአንድ ሴት ልጅና የሶስት ወንዶች አባትም ነበሩ። አስደንጋጭ የሆነው ድንገተኛ ህልፈተ ሕይወታቸው ለቤተሰቡ እጅጉን አስደንጋጭ ነበር። ያቺ መጥፎ ለሊት ከመድረሷ ሰዓታትን ቀደም ብሎ ረዳት ፕሮፌሰር ዘሪሁን በሞት ሳይሆን በጥበብና እውቀት ባህር ውስጥ እየዋኙ በስራ ተወጥረው ነበር። በዚያች ሌሊት አድፍጦ የሚጠብቃቸውን የሞትንም ሴራ አልተረዱም ነበርና በብሩህ ተስፋ አሻግረው ነገን እየተመለከቱ ግብራቸውን ይከውናሉ። ነገን ለማየት ቢጓጉም፣ ነገን ለማየት ሳይችሉ ቀሩ። እናም በዚያች ሌሊት የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም የነብስና ስጋቸው አብሮነት አከተመና እስትንፋሳቸው ጸጥ አለች። በተወለዱ በ71 አመታቸውም ስራዎቻቸውን አስረክበውን ከዚህች ዓለም ድካም በሞት ተለዩን። ነብሳቸውን በአጸደ ገነት ያኑርልን።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን መጋቢት 10 ቀን 2015 ዓ.ም