ኢትዮጵያ ሉዓላዊት ሀገር ናት። በቅኝ ያልተገዛች ፣ ክብሯን የማታስነካ፤ የሌላውንም የማትፈልግ ፤ ሰላም ፈላጊና ሰላምን የምትሻ ሀገር ናት። ከጎረቤት ሀገራትም ሆነ ከሌሎች ጋር ያላት ግንኙነት በሰላም አብሮ በመኖርና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በጋራ ጥቅምና መከባበር ላይ መሠረት ያደረገ የውጪ ፖሊሲ ያላትና ይሄንኑም በተግባር የምታረጋግጥ ሀገር ናት።
በዚህም ረጅም ዓመታትን ባስቆጠረ የየሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከበርካታ ሀገራት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ትብብር ስታደርግ ቆይታለች። በትምህርት፣ በባህል፣ በቴክኖሎጂ፣ በግብርና በሚሊቴሪ ፣ በኢንቨስትመንት እንዲሁም በሌሎች መስኮች ከብዙ ሀገራት ጋር በጋራ ሠርታለች፤ እየሠራችም ትገኛለች። ለልማቷ የፋይናንስ ድጋፍ፣ ብድርና እርዳታ ከሚያደርጉ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር አሁንም ይሄው ግንኙነቷን ቀጥላለች ።
ይሁን እንጂ ሀገራችን አጋጥሟት ከነበረው የሰላም መደፍረስ በተለይ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ጦርነት አንዳንድ ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ እንደነበር ይታወሳል። በኢኮኖሚ ዘርፍ ድጋፍና እርዳታን በመቀነስ፣ በአሜሪካ ከቀረጥ ነጻ የገበያ ዕድል(አጎዋ)እንዳትጠቀም እንዲሁም በፖለቲካው በተለያየ መልኩ ተጽዕኖ ለማድረግ ተሞክሯል። በአጠቃላይ ዲፕሎማሲውን ጥያቄ ውስጥ በሚከት መልኩ የተለያየ ጫናዎች ሲደረጉ ነበር። ይሁን እንጂ አሁን በሀገራችን ሰላም ከሰፈነና የሰሜኑ ጦርነት አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካዊ መፍትሔ እንዲያገኙ የሰላም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ከአንዳንድ ሀገራት ጋር ሻክሮ የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደነበረበት ከፍታ በመመለስ ላይ ይገኛል።
ለዚህም ዋነኛው ማሳያ በቅርቡ ያደጉት ሀገራት በውጭ ጉዳዮቻቸው አማካይነት በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት ነው። ለምሳሌ ያህል የጀርመኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ባየርቦክ እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪ ኮሎናን ከጥር 4 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የጋራ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል። በኢትዮጵያ ለሚካሄደው የመልሶ ግንባታ ሥራ ድጋፍ እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል። ይህም ከሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ባለፈ በኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረት መካከል መተማመን እና መግባባት በመፍጠር ሁሉም የኅብረቱ አባል አገራትና ኅብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር መልሶ ለማጠናከር የሚያግዝ ሆኗል።
በቅርቡ ደግሞ የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቺን ጋንግ የመጀመሪያውን የአፍሪካን ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያ አድርገዋል። ይህም ጠንካራውን እና የቆየ ታሪክ ያለውን ግንኙነታቸውን ይበልጥ ወደ ተለያዩ መስኮች በማስፋት በፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ዘርፍ ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ የሚያግዝ ነው። በግጭቱ ተጎጂ በሆኑ አካባቢዎች ለሚደረገው መልሶ ግንባታ እና ማቋቋሚያ የፋይናንስ ድጋፍ ትብብር እንደሚያደርጉም መግባባት ላይ ደርሰዋል።
ሰሞኑን ደግሞ የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጉዟቸውን ወደ ኢትዮጵያ አድርገዋል። ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ድጋፍ እንደሚያደርጉና የሰብዓዊ ድጋፍም ከ133ሚሊዮን ዶላር በላይ መደረጉን አስታውቀዋል። ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያና አሜሪካ የቆየውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስም ተስማምተዋል። ይሄ ከየሀገራቱ ጋር ያለንን የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ማሳያ ነው።
ከሀገራቱ ጋር ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አሁን ባለው ደረጃ መሻሻል የታየው በመንግሥት በተሠራ ጠንካራ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ፣ በየሀገራቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች የተቀዛቀዘው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደነበረበት ጠንካራ ግንኙነት ለመመለስ በሠሩት ሰፊ ሥራ ፣የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅና በኢትዮጵያ ላይ ጫና ሊደረግባት አይገባም በሚል የተንቀሳቀሰው ዲያስፖራም ለዚህ ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክቷል። በአጠቃላይ ከሃገር ውስጥ እስከውጪ የተሠራው ሥራ አሁን ዲፕሎማሲው በተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አግዟል። ይሄን አሁንም ወደፊትም ተጠናክሮ ሊያዝና ሊቀጥል የሚገባው ነው።
በዲፕሎማሲው ዘርፍ አሁን ያለው እንቅስቃሴ እያደገና እየተጠናከረ መምጣቱ የዲፕሎማሲያዊ ጥረቱ ውጤት ቢሆንም በቀጣይም ከዚህ የበለጠ ሥራ በመሥራት በሁሉም ሀገራት በኩል ያለንን ግንኙነት ይበልጥ ማሳደግ ይገባል። ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ፣በፖለቲካ እና በሌላውም መስክ ተመራጭ፣ተወዳጅና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር እንድትሆን መሥራት ይገባል፤ ያስፈልጋልም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 10 ቀን 2015 ዓ.ም