የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት (ኢትዮጵያ ፣ ኬንያ ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ ዑጋንዳ) በተደጋጋሚ በድርቅ ከሚጠቁ አካባቢዎች ዋነኞቹ ናቸው። ዓመታት እየጠበቀ የሚከሰተው ይኸው ድርቅ በሀገራቱ ከተንሰራፋው ድህነት ጋር ተዳምሮ በሕዝቦቻቸው ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጥፋት እያስከተለ ይገኛል።
አንድም በሀገራቱ ያለው የግብርናው ዘርፍ በዝናብ ውሃ ላይ ጥገኛ መሆኑ ፣ ከዚያም ባለፈ ዘርፉ አሁንም ኋላቀር በሆነ የአመራረት ሥርዓት የሚመራ ፤ እራሱን ለማዘመን የሚያስችል አቅምና መነቃቃት ያጣ መሆኑ ፤ ለሀገራቱ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ሆኖባቸው ድርቅ በተከሰተ ቁጥር እጆቻቸውን ለልመና እንዲዘረጉ ዳርጓቸዋል።
ይህ እውነታ ዛሬም ቢሆን ለሀገራቱ ትልቅ ፈተና ሆኗል። ዓለም አቀፍ ተቋማት እያወጡት ባለው መረጃ መሰረት ፤ በአካባቢው ለአምስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ዝናብ ባለመጣሉ ምክንያት በአሁኑ ወቅት በእነዚህ ሀገራት ወደ 60 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ ለከፍተኛ የምግብ እህል እጥረት ተጋልጧል ። ፈጥኖ እርዳታ ሊደርስለት ካልተቻለም ለከፋ አደጋ ይጋለጣል።
ችግሩ በኛም ሀገር (በኢትዮጵያ) በስፋት የታየ ሲሆን፤ በኦሮሚያ ፣ በሶማሊ እና በደቡብ ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች ተከስቶ ጥፋት እያስከተለ ይገኛል ። ከችግሩ ጋር በተያያዘ 11 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በምግብ እህል እጥረት ውስጥ ናቸው። 23 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ ለድርቅ ተጋላጭ እንዲሁም ተጎጂ በሆኑ አካባቢዎች ይኖራሉ። ከዚህም ባለፈ ስድስት ነጥብ 85 ሚሊዮን የቤት እንስሳት በድርቁ ምክንያት ሞተዋል።
ይሄን ችግር ለመቋቋም የሚያስችሉ ርምጃዎች የተጀመሩ እና ድጋፍም እየተደረገ ሲሆን፤ ለአብነትም በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የተከሰተውን ድርቅ እና እያስከተለ ያለውን አደጋ ለመከላከል መላው ሕዝብ በስፋት እየተንቀሳቀሰና ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገበ ነው። በአካባቢው ያለውን ነዋሪ / አርብቶ አደር ሕይወት ለመታደግ የሚደረጉ የነፍስ አድን ስራዎች ውጤታማ በመሆናቸው እስካሁን በሰው ሕይወት ላይ ጥፋት አልደረሰም ።
የአርብቶ አደሩን የሕይወት መሰረት የሆኑ የቤት እንስሳቱን ለመታደግ የሚደረጉ ጥረቶች በሚፈለገው ደረጃ ስኬታማ ባይሆኑም ፤ አሁንም እንስሳቱን ለመታደግ የሚደረጉ ርብርቦች የሚበረታቱና አርብቶ አደሩን ነገ ላይ መልሶ /ለማቋቋም ለሚደረግ ጥረት ትልቅ አቅም ሊሆን እንደሚችል ይታመናል ።
ይህ መልካም የመተባበርና ለወገን የመድረስ ከፍታን የሚያሳይ እንደመሆኑ አሁን ባለው ሁኔታም በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን እንዲሁም በሶማሊ ክልል አብዛኞቹ ዞኖች ለተከሰተው ድርቅና እያስከተለ ላለው ችግር ለቦረና ዞን የተሰጠውን ያህል በቂ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በተለይም ድርቁ በአካባቢው አርብቶአደር ሕይወት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጥፋት ለመታደግ የተሰሩት ሥራዎች መልካም ቢሆኑም፤ የቤት እንስሳቱን ከጥፋት ለመታደግ ፈጥኖ መንቀሳቀስ ይገባል።
በሀገር ውስጥ ሆነ በውጭ ያለውን ሕዝባችንን ጨምሮ ፣ ዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ በማስተባበር እንደሀገር የተደቀነብንን ይህንን ፈተና ለመሻገር የሚመለከታቸው አካላት ድርቁ በአካባቢው ባሉ ዜጎቻችን ላይ እያስከተለ ያለውን ጥፋት የሚያሳዩ መረጃዎችን ፈጥኖ በማሰራጨት ችግሩ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ በትጋት መስራት ይጠበቅባቸዋል።
የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት በበኩላቸው ችግሩ ከሁሉም በላይ የራሳችን በመሆኑ፤ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት በአግባቡ በማስገንዘብ ዜጎቻችን በያሉበት ባላቸው አቅም በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖቻቸው የሚችሉትን የሚያበረክቱበትን ምቹ ሁኔታ ማመቻቸት ይኖርባቸዋል።
ዜጎችም ”ለወገን ደራሽ ወገን ነው” በሚለው ሀገራዊ ብሂል በመነሳት ፣ መጠኑንና ብዛቱን ሳይሆን ለወገን መድረስን ማዕከል በማድረግ በሚቻላቸው ሁሉ የአቅማቸውን በማበርከት ለወገኖቻቸው የክፉ ቀን ደራሽነታቸውን በተጨባጭ ማስመስከር ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ የማንንም ውትወታ ባለመጠበቅ ለወገን ደራሽ ወገን መሆናችንን በተግባር ማሳየት ይኖርባቸዋል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 9 ቀን 2015 ዓ.ም