የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እያደገ ይገኛል። በስንዴ ምርትና ምርታማነት ላይ እየታየ ያለው ለውጥ ለዚህ አንድ ሁነኛ ማሳያ ነው። ስንዴ በመኸር ብቻ ይለማ ከነበረበት ሁኔታ በበጋ መስኖ እንዲለማ በማድረግ በምርታማነቱ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ተችሏል። በመኸር ወቅት ይገኝ የነበረው የስንዴ ምርት መጠንም እየጨመረ መጥቷል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የግብርናው ምርትና ምርታማነቱ እየጨመረም በዘርፉ ካለው እምቅ አቅምና የግብርና ምርት ፍላጎት ከፍተኛነት ጋር በተያያዘ የሚፈለገውን ያህል እየተመረተ አለመሆኑ በመንግሥት በኩል ታምኖበት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደጉ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ነው። ይህን ተከትሎም ምርትና ምርታማነቱ መጨመሩ ቀጥሏል።
የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እየጨመረ ከመጣባቸው ምክንያቶች መካከል መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ይጠቀሳል፤ መንግሥት ለአፈር ማዳበሪያና ለምርጥ ዘር አቅርቦት፣ ለሜካናይዜሽን አገልግሎት እና ለኩታ ገጠም እርሻ መስፋፋትና ለመሳሰሉት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። ለአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ብቻ በየዓመቱ ብዙ ቢሊዮን ብር ድጎማ እያደረገ ያለበት ሁኔታም ይህንኑ ያረጋግጣል።
መንግሥት ባለፈው የምርት ዘመን ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ 15 ቢሊዮን ብር ድጎማ አድርጓል። ከሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ ላይ ተደርጎ በነበረው ጫና የተነሳ ማዳበሪያ የመግዛት አቅሙም እያለ የሚገዛባቸው ሀገሮች ማዳበሪያ ለኢትዮጵያ እንዳይሸጡ መደረጋቸውን ተከትሎ ብዙ ፈተናዎች አጋጥመው እንደነበርም ይታወሳል። ይሁንና መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ ባለው ቁርጠኛ አቋም በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ጭምር የአፈር ማዳበሪያ ገዝቶ አቅርቧል፤ በሃገር ውስጥ በተፈጥሮ ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ በስፋት እንዲሠራም አርጓል። በዚህም የግብርናው ሥራ በማዳበሪያ እጥረት ሳይስተጓጎል ተካሂዶ የዘርፉን ምርትና ምርታማነትም ማስቀጠል ተችሏል።
መንግሥት ዘንድሮም 2015/16 የምርት ዘመን ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ የሚውል 21 ቢሊዮን ብር ድጎማ ማድረጉን ሰሞኑን የግብርና ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። በዚህም 12 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሞ አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታሉ ወደ ክልሎች ተጓጉዟል። ለዚህ የምርት ዘመን ለበጋ መስኖ፣ ለበልግና ለመኸር ካለፈው ዓመት የተረፈ ማዳበሪያን ጨምሮ 15 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ጥቅም ይውላል።
ድጎማው በየዓመቱ እየተመዘገበ ያለው የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት በማዳበሪያ አቅርቦት ምክንያት እንዳይስተጓጎል ለማድረግና በአርሶ አደሩ ላይ ሊኖር የሚችለውን ጫና ለመቀነስ ታስቦ የተደረገ መሆኑም ተጠቁሟል። በዋጋ አኳያም አርሶ አደሩ ባለፈው የምርት ዘመን ማዳበሪያ ይገዛበት ከነበረው ገንዘብ መጠን ጋር ተመጣጣኝ እንዲሆን ተደርጓል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ምክንያቶች ዋጋው እየጨመረ ያለው የአፈር ማዳበሪያ በአርሶ አደሩ ላይ ጫና እንዳያሳርፍ የድጎማው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።
ሀገርና መንግሥት ከግብርናው ከሚጠብቁት ምርትና ምርታማነት መጨመር፣ የሀገር ውስጥ የግብርና ፍላጎት መሟላት፣ የግብርናው ዘርፍ በውጭ ምንዛሪ ግኝት እያስገኘ ካለው ጥቅም፣ ዘርፉ በምርትና ምርታማነት ብዙ ርቀት መጓዝ ያለበት ከመሆኑ በተለይ በስንዴ ልማት ላይ እየተከናወነ ካለው መጠነ ሰፊ ተግባር አኳያ ሲታይ የመንግሥት ድጎማ ተገቢና ለግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ማደግ ያለውን ቁርጠኛ አቋም አሁንም ያረጋገጠበት ነው ማለትም ይቻላል።
እንደሚታወቀው ሃገሪቱ ለእርሻ ሥራ ሊውል የሚችል ሰፊ ለም መሬት፣ ጉልበት፣ የውሃ ሀብትና አየር ንብረት ባለቤት ናት፤ ይህ ሁሌም ሲጠቀስ ኖሯል። እነዚህ ሀብቶች ብቻቸውን ግን ብዙም የፈየዱት ነገር የለም። ከእዚህ ሁሉ እምቅ ሀብት ተጠቃሚ ለመሆን እነዚህን የልማት አቅሞች አስተባብሮ መምራት፣በቴክኖሎጂ መደገፍ፣እና ምቹ ፖሊሲዎችን ወደ ሥራ ማስገባት የግድ ነው። መንግሥት እያደረገ ያለውም ይሄው ነው።
መንግሥት ግብርናው ምርትና ምርታማነት እያደገም ምርትና ምርታማነቱ የሚጠበቀውን ያህል ስለአለመሆኑና ይበልጥ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት ሲያስገነዝብ ቆይቷል። ማስገነዝብ ብቻም ሳይሆን ለዘርፉ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች፣ ቴክኖሎጂዎች አቅርቦት፣ በባለሙያዎች ስምሪት ስልጠናና የመሳሰሉት ላይም በ ስፋት ተንቀሳቅሷል።
የአፈር ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ የተባይ ማጥፋያ አቅርቦት ላይ በስፋት ተሠርቷል፤ እየተሠራም ነው። በቴክኖሎጂ በኩልም ሜካናይዜሽን እንዲስፋፋ በተደረገው ጥረት በርካታ አካባቢዎች በትራክተር ማረስ፣ በኮምባይነር አዝመራ መሰብሰብና መውቃት ውስጥ የገቡበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በበጋ ስንዴ መስኖ ልማት ለተሰማሩ አርሶ አደሮች የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ማቅረብ ላይም በስፋት እየተሠራ ይገኛል።
ይህን ተከትሎም ከግብርናው ዘርፍ በየዓመቱ የሚገኘውን ምርት በከፍተኛ መጠን ማሳደግ እየተቻለ ነው። የበጋ ስንዴ መስኖ ልማትን አጠናክሮ በመቀጠል አርሶ አደሮች ከመሬታቸው በዓመት ከሚያገኙት ምርት በእጥፍ ብልጫ ያለው ምርት የሚያገኙበትን ሁኔታ መፍጠር እየተቻለ ነው።
ግብርናው ሲሰጡት አብልጦ ይሰጣል እንደተባለው ለግብርናው አስፈላጊውን አቅርቦት በማድረግ ግብርናው የሚፈልገውን ውጤት እንዲሰጥ ማድረግ እየተቻለ ነው። መንግሥት ዘንድሮም ለግብርናው ዘርፍ ማድረግ ያለበትን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠሉም ለምርትና ምርታማነቱ ቀጣይነት መሠረታዊ አቅርቦት የሰጠውን ትኩረት ያረጋገጠበት ሊባል ይችላል።
ድጎማው መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እድገት ቀጣይነት ያሳየው ቁርጠኝነት ተጨባጭ መገለጫ ነው። ይህ ቁርጠኝነት የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት የሚችለው የአፈር ማዳበሪያው አርሶ አደሩ ዘንድ ደርሶ ለተፈለገው ዓላማ ሲውል ነው።
ቀሪው ሥራ ማዳበሪያው ለበልግና ለመኸር እርሻ እንዲሁም ለበጋ መስኖ ልማት በወቅቱ እንዲዳረስ ማድረግ ይሆናል። ለዚህ ደግሞ ማዳበሪያውን በማጓጓዝና በማሰራጨት ከፍተኛ ሚና ያላቸው አካላት ቁርጠኝነት ወሳኝ ይሆናል። በዚህ በኩል ለአርሶ አደሮች ቅርበት ያላቸው የአርሶ አደሮች የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ዩኒየኖች እንዲሁም የክልል፣ የዞንና የወረዳ የሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ላይ የሚሠሩ ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው።
እነዚህ አካላት ማዳበሪያው ለየወቅቶቹ እንዲደርስ ቅንጅታዊ ርብርብ ማድረግ ይኖርባቸዋል፤ በዚህ ወቅት ቅድሚያ ሊሰጣቸው ከሚገቡ ተግባሮች መካከል አንዱና ዋናውም ይሄው የአፈር ማዳበሪያን ለአርሶ አደሩ ማድረስ ይሆናል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 8 ቀን 2015 ዓ.ም