መቅደስ ደስታ ትባላለች:: ወደ አዲስ አበባ ከተማ የመጣችው የዛሬ ስድስት ዓመት ነው:: ለአዲስ አበባ እንግዳ ብትሆንም ሕይወቷን ለመግፋት የሰው እጅ መመልከትን አማራጭ አላደረገችም:: ከአንድ ሁለት ይሻላል በሚልም የሚመስላትን አግብታ ከአዲስ አበባን ኑሮ ጋር መጋፈጥ ከጀመረች ሰነባብታለች::
የተገኘውን ሥራ ከመሥራት አንስቶ ከኑሮ ውድነቱ ጫና ራሷን ለማዳን መሸሸጊያ ያደረገችው ጥንድ ሆኖ ጎጆ የሚሞቅበትን ትዳር ነው:: 20 ዓመቷን የያዘችው ገና በዚህ ወር ቢሆንም 16ኛ ዓመቷን እንደያዘች የወለደቻት አንዲት የአራት ዓመት ሴት ልጅ አለቻት:: አሁን ላይ ደግሞ ሁለተኛ ልጇን ለመውለድ የተቃረበች የሰባት ወር ነፍሰ ጡር ናት:: መቅደስን ያገኘናት አራት ኪሎ አካባቢ ጫማ ስትጠርግ ነው:: የወንድ ተብሎ በሚፈረጀው የጫማ መጥረግ ሥራ(ሊስትሮ) መሰማራትና በተለይም ነፍሰ ጡር ሆኖ ጫማ መጥረግ ጎንበስ ቀና ማለት የሚጠይቅ አስቸጋሪ በመሆኑ ብዙዎች አድናቆታቸውን ሲቸሯት ተመልክተናል::
ወደ ጫማ መጥረግ ሥራ የገባችውም በድንገት እንደሆነ ትናገራለች:: ‹‹ጫማ ይጠርግ የነበረው ባለቤቴ አባቱ ሞተውበት ውርስ ለመካፈል ወላይታ ዞን ወደ አለችው በዴሳ ወረዳ ያሉት ቤተሰቦቹ ጋር ሲሄድ እኔ የእሱን ቦታ ተክቼ መሥራት ጀመርኩ፤ከዛ ጊዜ ጀምሮም ሙያውን ወደድኩት›› ትላለች :: በርግጥ ከማርገዟ በፊት ቱሪስት ፊት ለፊት ያለው ፓርኪንግ ነበር የምትሠራው:: ሥራውን ከወላይታ ወደ አዲስ አበባ እንደመጣች አንዲት አዲስ አበባ ከተማ የምትኖር ዘመዷ ነበረች ያስገባቻት:: ታዲያ ባለቤቷ ሊስትሮ እሷ ደግሞ ፓርኪንግ እየሠሩ በ1ሺህ 200 ብር ፈረንሳይ አካባቢ ቤት ተከራይተው በጋራ ይኖሩ እንደነበር መቅደስ ትናገራለች::
‹‹ባለቤቴን ያገኘሁት አዲስ አበባ በመጣሁ በ15ኛው ቀኔ ነው:: በተዋወቅን በሦስት ወርም አገባሁት››የምትለው መቅደስ ማግባቷ በጋራ በመኖር ኑሮ ውድነቱን በመተጋገዝ እንድታቀለው ያስቻላት መሆኑን ታወሳለች:: ሆኖም ገና 16ኛ ዓመቷን በያዘችበትና በዛው በተጋቡበት ወር የመጀመሪያ ልጇን አረገዘች:: እንደነገረችን ታድያ እዚህ አዲስ አበባ መውለድም ሆነ ልጅ ማሳደግ ከባድ በመሆኑ ባለቤቷ ቤተሰቦች ጋር እዛው እሷ ትውልድ አካባቢ ወላይታ ሄዳ ተገላግላለች:: የባለቤቷ ቤተሰቦች እርሻ ያላቸውና የተሻለ ኑሮ የሚኖሩ በመሆናቸው ልጇን እዛው እነሱ ጋር ትታ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰች::
አሁን ደግሞ ሁለተኛ ልጇን አርግዛለች:: ካረገዘች ሰባተኛ ወሯን ይዛለች:: በቀጣይም ሥራን ሳታማርጥ የተገኘውን ሁሉ በመሥራት ልጆቿን የማሳደግ ዓላማ እንዳላት አጫውታናለች:: ምክንያቱም አዲስ አበባ ከተማ ላይ ከየትኛውም በአገሪቱ ያለ ሥፍራ በላይ ኑሮ ውድ ነው:: በየወሩ የሚከፈል የቤት ኪራይ ወጪ እንዲሁም በየቀኑ የቀለብ፤የትራንስፖርት ወጪን ለመሸፈን የሚያስችል የገንዘብ ገቢ ማግኘት ያስፈልጋል:: ይህን ሁሉ ለማሟላት ደግሞ ሥራን ሳይንቁ መሥራት ግድ ይላል::
መቅደስ ልጇን ለመውለድና ለማሳደግ እሷ እንደ ቀድሞው ባለቤቷ ቤተሰቦች ጋር መሄድ አትፈልግም:: ስለዚህ አሁን ያረገዘችውን ልጇን ለመውለድና ለማሳደግ ያሰበችው እዚሁ አዲስ አበባ ነው:: ለዚህ ደግሞ እንደ አማራጭ የያዘችውን የሊስትሮ ሥራ አጠናክሮ መሥራት ነው:: በተሻለ መልኩ ለመሥራትም የሊስትሮ ሳጥን ገዝታለች፤ የጫማ ቀለሞችንም እያሟላች ነው::
መቅደስ እንደምትናገረው ሴት ልጅ ስትሠራ ደስ የሚላቸው የሚያበረታቷት ብዙ ሰዎችን መመልከቷን ትናገራለች:: ከወዲሁ ቋሚ ደንበኛ የሆኗት በርካታ ሰዎች እንዳሉም ትገልጻለች:: ከ25 እስከ 50 ብር ድረስ ጉርሻ የሚሰጧት ደንበኞችም እንዳሉ አጫውታናለች::
መቅደስ ከልጅነቷ ጀምሮ መከራ ቢፈራረቅባትም እጅ እንዳልሰጠች ትናገራለች:: እናቷ የስድስት ወር ልጅ ሳለች ከአባቷ ጋር በመጋጨታቸው ጥላት እንደሄደች አባቷ ነግረዋታል:: በእንጀራ እናት ያደገችው መቅደስ በእንጀራ እናቷ ብዙ በደሎች ደርሰውብኛል ትላለች:: ‹‹ገና ሕፃን ሳለች ጀምሮ ነበር ከባድ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ታሠራኝ ነበር:: በጨቅላ ዕድሜዬ የአዋቂ ልብሶችን ታሳጥበኛለች:: ደግሞ ልብስ ማጥበው ወንዝ ወርጄ በመሆኑ ለኔ ከባድ ነበር:: ልብሶቹን ተሸክሞ ወደ ወንዝ መሄዱ በራሱ በጣም ያደክማል:: የቤት ውስጥ ሥራዎችንም የምሠራው እኔ ነኝ:: ቤት ማጽዳቱ፤ከብት መጠበቁ፤ምግብ ማዘጋጀቱ የእኔ ዕዳዎች ነበሩ:: ያለ አቅሜ የበቆሎ ገንፎ ታሠራኝና ሲጓጉልብኝ ትገርፈኝ የነበረውን መቼም አልረሳውም›› ትላለች መቅደስ የልጅነት ሐይወቷን ስታስታውስ::
መቅደስ እንደምትናገረው ከፍ እያለች ስትመጣ የእንጀራ እናቷ የምታሠራት ሥራም ጫናው እየጨመረ መጣ:: እንዲህም ሆኖ አባቷ ‹‹እሷ ትምህርት ቤት ከገባች የቤቱን ሥራ ማን ሊሠራ ነው››ስትል ትምህርት ቤት መግባቷን ተቃውማ ለነበረችው ባለቤቱ ጆሮ ሳይሰጥ በአካባቢው የሚገኝ ፋና የተሰኘ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አስገብቷት ነበርና ትምህርቷን ስትከታተል ቆይታለች:: እውነት ለመናገር በፈጣሪ ኃይል ከክፍል ክፍል ትዛወር እንጂ ስምንተኛ ክፍል እስክትደርስ ድረስ ለደረሰችበት ደረጃ የሚመጥን ዕውቀት እንዳልቀሰመች ትናገራለች::
እንጀራ እናቷ በተደጋጋሚ የሰጠሁሽን ሥራ ሳትጨርሽ ትምህርት ቤት እትሄጂም ስለምትላት ብዙ ጊዜ ከትምህርት ቤት ትቀር ነበር:: አብዛኛውን ጊዜም ታረፍዳለች:: ትምህርት ያመልጣታል:: በዚህ ሁሉ ምክንያት በቅጡ ለማንበብና ለመፃፍ እንኳን ይቸግራት እንደነበርም ትናገራለች:: ትምህርቷን እስከ ስምንተኛ ክፍል ብቻ ነው የተከታተለችው:: የስምንተኛ ክፍል ትምህርቷንም ቢሆን ከእንጀራ እናቷ ጋር የመረረ ፀብ ውስጥ በመግባቷ ምክንያት ከቤት በመውጣቷ ምክንያት ከሦስት ወር በላይ የመከታተል ዕድል አላገኘችም::
ሆኖም ያቀረጠችው ትምህርት ያንገበግባታል:: ተምራም ሰው ለመሆን ዕቅድ አላት:: በሚቀጥለውም ዓመት በማታው ክፍለ ጊዜ ተመዝግባ ትምህርቷን ለመቀጠል ከወዲሁ አስባለች:: ከዚሁ ጎን ለጎን ተስፋ ያየችበትንና በርካታ ደንበኞች ያፈራችበትን የሊስትሮ ሙያ በማጠናከር ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና በማለት ላይ እንደምትገኝ እኛም ከእርሷ ጋር በነበረን ጥቂት ቆይታዎች ለመረዳት ችለናል::
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም