ዛሬ የሕገወጥነትን ትርጉም ለመናገር መሞከር ከቂልነት ባለፈ መሳቂያ መሆን ነው። ምናልባት ለፍትህ ሂደት ሲባል በፍርድ ቤቶች ጉዳዩ ይብራራ ይሆን እንደሆነ እንጂ፣ በሌሎች ቦታዎች ላይ ሕገወጥነትን ለመበየን መነሳት ኋላ ቀርነት ነው የሚሆነው። “ለምን?” ከተባለ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ ገብቶ እያተራመሰን ያለን ጉዳይ የመዝገበ ቃላት ብያኔን ለመስጠት መሞከር የአይኑን በጆሮ ስለሚሆን ብቻ ነው። ቀጥለን በተጨባጭ መረጃና ማስረጃ እንመለከተዋለን።
ድሮ ድሮ ሕገወጥነት (Illegal ወይም Unlawful) የሚታሰብ ተግባር አልነበረም ነው የሚባለው። “እንዴት?” ቢሉ የመጀመሪያው የፈሪሀ እግዚአብሔር መኖር ሲሆን፤ ቀጣዩ ይሉኝታ (በተራዛሚው ባህል) ነው አሉ ምክንያቱ። በቃ፣ እነዚህ ሁለቱን ጥሶ መሄድ የሚታሰብ አይሆንም። የሚያስብ እንኳን ቢኖር ሕገወጥነቱን ይዞ አገር ጥሎ መሄድ ነው መፃኢ ዕድሉ። ከእነ አገላለፁ “የእገሌ ልጅ . . .” ከመባል ሰውረኝ ነበር የሚባለው። ዛሬ ዛሬ ነገሩ ሁሉ ‹‹በኮታ ገብቶ›› “ኧረ በሕግ” ሲባል፣ “ስትፈልጉ ወይዘሮ በሉኝ” እንዳለው ጥቅመኛ ነውና ምን ማድረግ እንደሚቻል ለጊዜው ግልፅ አይደለም።
ባለፈው አመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥን ጠቅሶ ለንባብ የበቃ ዜና “በሕገወጥ የውጭ አገራት ገንዘብ ምንዛሬ ላይ የተሰማሩ አካላትን ለጠቆመ እስከ 25 ሺህ ብር ወረታ እከፍላለሁ” (ባንኩ “391 ሕገወጥ ገንዘብ አዘዋዋሪዎች በሕግ ጥላ ስር ናቸው” ያለውንም ከዚሁ ጋር አዳምሮ ማየት ይቻላል) በማለት ያስነበበንም የሚያመለክተው ይህንኑ በሕገወጥነት የመዝረፍ ተግባርን ነውና ሕገወጥነት በየዘርፉ ሥራ ላይ ሲውል ይታያል። ወደ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ቢኬድም ሕገወጥነትን በሕጋዊነት የመከላከሉ ተግባር ፋታ ሲያሳጣ ነው የሚገኘው። ይህንን ስንል ስለእውነት በእውነት እየተሠራ ነው በሚል ከብረት የጠነከረ እምነት ነው።
በዚሁ አመት፣ “ከ33 ሺሕ በላይ ሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ” የሚል አስደንጋጭና አስደማሚ ዜናምን እኮ ሰምተናል። የሚገርመው ይህንን ያህል ቁጥር ያለው ወንበዴ፣ የጅቡቲን ሕዝብ ለማከል ጥቂት ፈሪ የሆነ ዘራፊ ባለበት አገር እንዴት ሆኖ ነው ሸማች ሥርዓት ያለው ገበያ ተጠቃሚ የሚሆነው።
በተመሳሳይ አመት (ጥር 19፣ 2014 (ኤፍቢሲ)) “በደቡብ ክልል ሕገወጥ ተግባር ፈጽመዋል የተባሉ ከ29ሺህ በላይ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ” የሚል ዜና መስማታችንም የሚዘነጋ አይደለም። “በጎንደር ከተማ 14 ሕገወጥ ነጋዴዎች እስከ 11 ዓመት በሚደርስ እስራት ተቀጡ” (ሐምሌ 27/2011 አ.ም)። “በቀን የገቢ ግመታ ሥራው የተለዩ ከ43ሺህ በላይ ሕገወጥ ነጋዴዎችን ወደ ሕጋዊ ግብር አከፋፈል ሥርዓት ማስገባቱን የኦሮሚያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አስታወቀ።” (ጁላይ 14, 2017) ወዘተርፈ . . .። እነዚህ ሁሉ ባሉበት ነገሮች በኑሮ መወደድ ብቻ መመለሳቸው የሚገርም ሲሆን፤ ወደ ሌላና የራሳቸውን መንግሥት እስከ ማቋቋም አለመሄዳቸው ሊያስመሰግናቸው ይገባል። ጎበዝ፣ በሕገመንግሥቱ መሰረት እንሂድ ካሉ እኮ እነዚህ የሕገወጡ ቡድን አባላት ተሰባስበው ክልል መሆን እንፈልጋለን (የሕገወጥ ነጋዴዎች ክልል፤ የሕገወጥ ገንዘብ አዘዋዋሪዎች ክልል፤ የሕገወጥ ደላላዎች ክልል . . .፤ ኧረ እንዳይሰሙን፣ ደሞ እውነት መስሏቸው . . .)፣ ይፈቀድልን የማለት መብት የላቸውም ማለት እንደማይቻል ስንቶቻችን፣ በሕገወጥ ንግድ የቆሰልንና የቆሳሰልን እናውቅ ይሆን?።
ሕገወጥነት በጨለማም ይታጀባልና “ሕገወጥ ነጋዴዎች የራሳቸውን ሀብት ያለአግባብ ለማካበት ጨለማን ተገን አድርገው መንቀሳቀስን መርጠዋል” የሚለውን ስናስታውስ “ሆሆ…” ማለታችን የግድ ይሆናልና ሕገወጥነት ሰዓትና ሁኔታ የማይገድበው የ24 ሰዓት ሥራ ነው ማለት ይሆናል። እነዚህን ሕገወጦች ከሌሎቹ ለየት የሚያደርጋቸው ጭለማን (“ሌቦች” ማለት ይቻላል) ተገን ማድረጋቸው ነውና በጭለማም መጠንቀቅ እንዳለብን ሁላችንም ለሁላችንም ማሰብና ማሳሰብ ይገባናል ማለት ነውና እነሆ ማሳሰቢያው።
“የከተማችን ነዋሪዎች ይህን ማስጠንቀቂያ ተላልፎ የሚገኙ ሕገወጥ ነጋዴዎች በአካባቢው ለሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ወይም በቢሮው ነፃ ስልክ ቁጥር …. ደውላችሁ አሳውቁኝ”፤ “ወቅቱ ከትርፋችን በላይ አገራችንና ሕዝባችን ስለማትረፍ የምናስብበት መሆኑም ሊዘነጋ አይገባም” ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ለንግዱ ማህበረሰብ (ነጋዴው) ማሳሰቢያ መስጠቱ የሚታወስ ሲሆን፤ ቢሮው “አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ በአቋራጭ ለመክበር እና ሆን ብሎ ሕገወጥ የዋጋ ጭምሪ እና ኢኮኖሚያዊ አሻጥር ለመፍጠር ጥረት ማድረግ ላይ መሆናቸውን” (ነሐሴ 19 ቀን 2013 አ.ም) ከሚለው ውስጥ “ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ . . .” የሚለውን ነቅሎ በማውጣት ግርግር ምን ያህል ለሌባ መልካም አጋጣሚ ስለመሆኑ መረጃም፣ ማስረጃም ነው።
መቼም ሕገወጥ ንግድንና ሕገወጥ ነጋዴን ለማጥፋት ያልተደረገ ጥረት የለም፣ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ቃላትና ሐረጋት አለመኖራቸው፣ ያልተሰደሩ ሥርዓተ ነጥቦች ያልነበሩ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን ከላይ የጠቀስናቸውና ቀጥለን የምናያቸው ለዚህ፣ እየተነጋገርንበት ስላለው ጉዳይ ተገቢና ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው። እንቀጥል፡-
በየመንደሩ በመዞር ሚዛን ይዘው ግዢ የሚፈጽሙት ሁሉ ሕገወጥ ነጋዴዎች ከሕገወጥ ነጋዴዎቹ ተርታ እንደሚሰለፉ እናውቅ ይሆን? አናውቅም። ምክንያት ብናውቅ ኖሮ እንደ ሕጋዊ ተግባር ቆጥረን አናስተናግዳቸውም ነበራ። ለነገሩ ፖሊስ እያየ ዝምታን ያጎናፀፋቸውን እኛ ምን ብለን ነው “ኧረ በሕግ!!!” የምንለው? ብንልስ ሕገወጦቹ መልሰው “የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ” አይሉንም ማለት ይቻላል? ይላሉ። እነሱ ምን የማያፍሩትና የሚፈሩት አካል አለ።
መንገድ መዝጋት ሲባል ምን ማለት ይሆን? ይህንን በተመለከተ እስካሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰጠ ብያኔ የለም፤ በጦርነት ወቅት ካልሆነ በስተቀር። በመሆኑም ይመስላል፣ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ፣ ለሌቦች፣ ዘራፊዎችና ዘጊዎች ምቹ ሁኔታን የፈጠረው። የሚገርመው የእነሱ ምቹ ሁኔታን መጠቀም አይደለም። የሚገርመው እነሱን ሃይ ባይ መጥፋቱ እንጂ።
መረጃና ማስረጃችንን እያጣቀስን እንቀጥል።
ሰሞኑን በዚሁ ጋዜጣ (መጋቢት 3 ቀን 2015 አ.ም) ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ “ምርትን በመያዝ ለሌላ የፖለቲካ ቀውስ መጠቀሚያ ለማድረግ የሚደረጉ ሙከራዎች ላይ መንግሥት ጠንካራ ቁጥጥር እንደሚያደርግ፤ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱንና የጤፍ ዋጋ ከተጋነነው ጭማሪ ዝቅ እንዲል እንደሚሠራ” መግለፃቸውን ይዘን፤ “ከአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር በማስተሳሰር በሕገወጥ መንገድ ዋጋን በማናር ሕዝብን ለማነሳሳት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸው የሚካድ አይደለም”፤ “በመንገድ ንግድ ላይ ያሉና ድለላ ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት እየገዙ የማከማቸትና [ምርት] ወደ ግብይት እንዳይገባ የማድረግ ሁኔታዎች አጋጥመዋል”፤ “በወፍጮ ቤቶች ብዙ ምርቶችን በመያዝና ወደ ግብይት የሚገባውን ውስን በማድረግ ዋጋ ሲወደድ ለመሸጥ የሚደረጉ ፍላጎቶችና ሕገወጥ እንቅስቃሴዎች” አሉ፤ “ኬላዎችን በመዝጋት ምርት በነፃ እንዳይንቀሳቀስ እና ግብይቱ እንዳይሳለጥ በማድረግ፤ በዚህም በመዲናዋ የምርት እጥረት እንዲኖር” የሚካሄደውን ከንቱ ድካም አይተን ታዝበናል። “ችግሩን ለመፍታት ከፌዴራል መንግሥትና ከክልሎች ጋር በመነጋገር በሕገወጥ መንገድ የተዘጉ ኬላዎች እየተከፈቱና ምርት የሚገባበት ሁኔታ እየተፈጠረ” ይገኛል ማለታቸውን የሰማና ፖለቲካም ለሕገወጥነት ተግባር ሲያገለግል የተመለከተ “ጎበዝ፣ ምንድን ነው መላው??” ቢል ምን ይገርማል?
“ባለፈው ረቡዕ ምሽት ሀዋሳ ላይ ፖሊሶችና የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ሲታኮሱ አደሩ፡፡” (ማርች 17፣ 2012 (www.worancha.com)) የሚል ዜና ሰምተን “እንዴ ይሄ ነገር ወዴት እያመራ ነው? ሕገወጡ ቡድን ጭራሽ መሣሪያም ታጥቋል?” እንዳላልን ሁሉ፤ ዛሬ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ጤፍ እንዳይገባ እየተደረገ መሆኑን ስንሰማ የሕገወጦች እድገት አዝጋሚ አለመሆኑን ከመረዳት ውጪ ሌላ ምንም ማለት አይቻልም፤ ለጊዜውም ቢሆን። ግን ግን፣ “የሕግ የበላይነት ይከበር!!!” ብሎ መፈክር ማሰማት ይቻላል። ሕገወጡን በሕግ ዱላ ማለት ግን ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ አይደደለም። ኧረ ለመሆኑ ሕገወጡ ሁሉ እየተነሳ በሕግ አምላክ እንዳይለን።
የገቢዎች ሚኒስቴር በይፋዊ ድረገፁ (http://www.mor.gov.et) ላይ 42 አንቱ የተባሉ ድርጅቶችን ስም ዝርዝር በሰንጠረዥ በመግለፅ “ሀሰተኛ ደረሰኝ በማሰራጨት አገራቸውን ሲሰርቁ የነበሩ ድርጅቶች ተለዩ” በሚል ርእስ አስፍሮት እንደተነበበው ከሆነ ሕገወጥነት በእድገቱም ሆነ ተግባራቱ በከፍተኛ ደረጃ እየተሻሻለ መሄዱንና፤ ከግለሰብ(ቦች)ም አልፎ ወደ ድርጅት(ቶች) ደረጃ እንዳደገ፤ በተግባሩም ከሀብትና ንብረት መዝረፍ ደረጃ አልፎ አገር ወደ መስረቅ ደረጃ እንደተሸጋገረ ለማየት ይቻላል። ምናባቱ፣ ከሆነ አይቀር እንዲህ ነው።
“በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በትናንትናው ዕለት ይፋ የተደረገው ጥናት “መጤ ባህሎችና ልማዳዊ ድርጊቶች በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች፣ በተለይም በወጣቶችና ሴቶች ላይ እያስከተሉት ያለው አሉታዊ ተጽእኖ” በሚል ርዕስ የተካሄደ ሲሆን ከ3ሺህ 600 በላይ ሕገወጥ የወሲብ ድርጊት የሚፈፀምባቸው ቤቶች እንዳሉ” (ዛሬ ስንት ደርሰው ይሆን?) ለማወቅ የተቻለ ሲሆን፤ ለማወቅ የተቻለውም “አዲስ አበባ በሕገወጥ ልማዶችና የወሲብ ድርጊቶች እየተናጠች ነው” በሚል ርእስ ለንባብ በበቃው ዜና (እሁድ፣ ጃንዋሪ 13፣ 2013) አማካኝነት ነው። “ወይ አዲስ አበባ . . .” እንዳትሉ፤ ገና ነው።
ይህ ብቻም አይደለም፣ “በከተማዋ የቀንና የሌሊት ጭፈራ ቤቶች፣ የራቁት ዳንስ ቤቶች፣ የሺሻና የጫት ቤቶች፣ የቁማር ቤትና ሕገወጥ የቪዲዮ ቤቶች ቁጥር በከፍተኛ መጠን” እያደገ ይገኛል። ጥናቱ እንደደረሰበት ከሆነ “አሥሩም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ የፖሊስ መምሪያዎች የተሰበሰበ መረጃ እንዳመለከተው፣ 3ሺህ 691 ቤቶች ለእነዚሁ ተግባራት ተከፍተው በከተማዋ ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ ቤቶች መበራከትና በስፋት መሰራጨት ሳቢያም በርካታ ወጣቶች ለወንጀል ተግባራት፣ ለአደገኛ እፆች ሱሰኝነት፣ ለዝርፊያ፣ ለስደት፣ ለጐዳና ተዳዳሪነት፣ ለኤችአይቪና ተያያዥ በሽታዎች፤ እንዲሁም፣ ላልተፈለገ እርግዝና ተዳርገዋል፡፡” (ሌሎቹን፣ ጥናቱ የደረሰባቸውን ገመናችንን እዚህ የመዘርዘር ድፍረቱ ስላልተገኘ አንባቢ በራሱ ሊደርስበት መብት አለው) ጎበዝ፣ መላው ምንድን ነው ታዲያ?
ኢትዮጵያ ውስጥ የሕገወጥነት ችግር የለም። ከጥፍራችን እስከ ፀጉራችን ድረስ ተዘፍቀንበታል። ይህ ደግሞ እስከ “የመንግሥት ሌቦች” ድረስ የዘለቀ ስለመሆኑ ያልሰማን ካለን ጥቂቶች መሆን አለብንና ለእኛ ሕገወጥነት ‹‹ብርቅ›› አይደለም። ችግሩ ብርቅ ባለመሆኑ ጭራሹኑ ጠራርጎን ወደ መውሰዱ መቃረቡ ነው።
እንደ በኢትዮጵያ የዓለምአቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) አቤቱታ (ኢዜአ፤ ታኅሣሥ 8/2012) “ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችና ደላሎች ሕገወጥ ስደትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ አድርጎታል”።
እንደው ለነገሩ ምን ምንድን ናቸው ሕገወጦቹ? ሕገወጥ የሆኑትን ከመፈለግ ያልሆኑትን መዘርዘር ቢቀልም፣ የሕገወጥነት ወሰን ዲካው የት ድረስ እንደሆነ ለማሳየት የሚከተሉትን መጠቃቀስ ይቻላል።
ሕገወጥ የውጭ ማስታወቂያ ሰሌዳዎች፣ ሕገወጥ መድኃኒቶች፣ ሕገወጥ ቤቶች፣ ሕገወጥ የትምህርት ማስረጃዎች፣ ሕገወጥ የውጭ አገር የሥራ ስምሪት፣ “ሕገወጥ የእንቁላል ዝውውር” (አሜሪካ “ሕገወጥ የእንቁላል ዝውውር” አሳስቦኛል አለች። ጃን. 24, 2023)፣ ሕገወጥ ሰፋሪ፣ ሕገወጥ የጦር መሳሪያ (ሕገወጥ ቱርክ ሰራሽ ሽጉጦችን ጨምሮ)፣ ሕገወጥ የገንዘብ መላኪያ፣ ሕገወጥ ስደት፣ ሕገወጥ አደን፣ ሕገወጥ እርምጃ፣ ሕገወጥ የመሬት ወረራ (“ወረራ” ብሎ ሕገወጥ ባይሆን ነው የሚገርመው)፣ ሕገወጥ ግብይት፣ ሕገወጥ እቃዎች (“የሕገ-ወጥ እቃዎች መረጃ አሰጣጥ፣ አያያዝና የወሮታ አከፋፈል”ን ያነቧል)፣
እርግጥ ነው፣ ጉዳያችን ሕገወጥነትን እያገላበጡ ማሳየት ሆነና ነው እንጂ ምድራችን ሕጋዊያንን አላፈራችም ማለት አይደለም። ከሚገባው በላይ አፍርታለች። በማፍራቷም ነው አገራችን እዚህ የደረሰችው፤ የእነሱ ቁጥር በመብዛቱም ነው ወደ ፊትም የምትቀጥለው።
በየዘርፉ፣ በየአካባቢው፣ በየክፍለ ዓለማቱ ሕጋዊያን ሞልተዋል። በየሄድንበት፣ በየተሰማራንበት፣ በምንሸምትበት ወዘተርፈ ሁሉ ኢሕጋዊነትን አምርረው የሚጠየፉ ሕጋዊያን አሉ። እንደውም አንድ አባባል አለ። ይህች ዓለም እስካሁን ያለችው በገጠሩ ሕዝብ ቅንነትና ሕጋዊነት ነው የሚል። እውነት ነው። ቅንነትና ሕጋዊነትን ጨምሮ፣ ግልፅነት፣ የዋህነት፣ ጀግንነት . . . እዛ አሉ። “አብሮ እሚበላ፣ አብሮ እሚጠጣ . . .” የሚለው ሁሉ እንደ ወረደ የሚገኘው እዛ እንጂ እዚህ ኢሕጋዊያን ጫካ ውስጥ አይደለም። አስተዋይነትን፣ ሰብአዊነትን፣ ታታሪነትን፣ ጥብቅ አማኝነትን፣ ባለማተብነትን፣ በሕግ የበላይነት ማመንን፣ ሩህሩህነትን፣ እንግዳ ተቀባይነትን፣ ከእግዚአብሔር ሰላምታ ጀምሮ ሰው አክባሪነትን፣ አድማጭነትን፣ አስታራቂነትን . . . ወዘተርፈ ሁሉ እዛ ይገኛሉ።
በመሆኑም፣ ኢሕጋዊያንን ወደ ሕጋዊነት ለማምጣት አንዱና ዋናው መሳሪያ (እሴት) ይሄው የገጠሩ ቱባ ማንነት ነው ስንል፣ በእነዚህና ሌሎችም በቂ ምክንያቶች መሆኑን ስንገልፅ “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!” (ይህንን አባባል ለመጀመሪያ ጊዜ መደበኛ በሆነ መልኩ ተጠቅመው ያገኘሁት ጀኔራል ዐቢይ አበበን ሲሆን፣ እሱም በ“አውቀን እንታረም” ድንቅ መጽሐፋቸው ውስጥ ነው) በማለት ነው። በ“ታሪክን የኋሊት” እንደግመዋለን፣ “ኢሕጋዊነት ይውደም!!!” “ፀረ-ኢሕጋዊነት ትግል ይፋፋም!!!”፤ “ሕጋዊነት ይለምልም!!!” “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!”
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም