ጠንካራ ተቋማት የጠንካራ ሀገር መሠረቶች ናቸው። የጠንካራ ተቋማት ባለቤት የሆኑ ሀገራት ጽኑ መሠረት ያላቸው በመሆኑ ሀገርን ከትውልድ ወደ ትውልድ ያሸጋግራሉ፤ የሀገርን ገጽታ ይገነባሉ፤ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖም ይፈጥራሉ፤ ቋሚ አምባሳደር ሆነውም ሀገርን ያስተዋውቃሉ። በአጠቃላይ የሀገር መለያ ሰንደቅ ዓላማ ተደርገው ይወሰዳሉ።
ይህንኑ በመረዳት ኢትዮጵያም ዘላቂ የሆኑ ተቋማትን ለመገንባት ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች። መንግሥት በተቀያየረ ቁጥር የማይቀያየሩ፤ ዘላቂነት ያላቸውና በየትኛውም ጊዜና ቦታ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርገው የሚያስተዋውቁ ተቋማትን ለመፍጠር ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።
ተቋማት ሕግና ሥርዓትን በማስከበር በኩል የማይተካ ሚና አላቸው። የፀጥታም ይሁኑ የዴሞክራሲ ተቋማት የሕዝቦችን የዕለት ተዕለት ሕይወት የተሳካ በማድረግ እና ዘላቂ ዲሞክራሲ እና የሕዝቦች አንድነት እንዲያብብ መሠረቶች ናቸው። የእነዚህ ተቋማት ማበብ ሀገራዊ ፋይዳቸው ከፍ ያለ ሲሆን የምንመኛትንም ሀገር እውን ለማድረግ የማይተካ ሚና አላቸው።
ሆኖም በአንዳንድ አካላት በኩል ለሕጋዊ ተቋማት ተገቢውን ክብር አለመስጠት ይታያል። ተቋማቱ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተቋቋሙና ሕጋዊ ዕውቅና ያላቸው መሆኑ እየታወቀ፤ ውሳኔያቸውን ማጣጣል እና አለፍ ሲልም አለመቀበል ይስተዋላል። ይህ ደግሞ በቀጥታ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አለመቀበል እና አለፍ ሲልም ማፈንገጥ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ለዚህ ደግሞ ወደ ኋላ ሄዶ አንድ አብነት ማንሳት ይቻላል።
ጊዜው 2012 ዓ.ም ነው። ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምርጫ ለማድረግ እየተሰናዳች ባለችበት ወቅት ኮቪድ 19 ተከሰተ። ሰዎች ከመቀራረብ እና ከመነካካት እንዲርቁ በዓለም ደረጃ ታወጀ። ኢትዮጵያ ይህንኑ ተገበረች። ምርጫውንም አራዘመች።
በነሐሴ ወር 2012 መጨረሻ ታቅዶ የነበረው ምርጫ በሕገ መንግሥታዊ ትርጉም በተሰጠ ትንታኔ የኮሮና ወረርሽኝ የኅብረተሰብ ጤና ሥጋት መሆኑ ሲያበቃ እንዲካሄድ ቢባልም፣ ሕወሓት ምርጫው መራዘም የለበትም ሲል ተቃውሞውን አሰማ። ምርጫው መራዘም የሌለበትና የማያወላውል ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ያለው ሒደት ነው በማለት የተከራከረው ሕወሓት፣ የፌዴራል መንግሥት ምርጫውን በሕገ መንግሥት ትርጉም ቢያራዝምም በትግራይ የምርጫ ዝግጅት እንደሚደረግና ክልላዊ ምርጫም እንደሚከናወን አስታወቀ። በመጨረሻም ምርጫውን ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በማከናወን አዲስ ምክር ቤትና ሥራ አስፈጻሚ አቋቋመ።
የፌዴራል መንግሥት አካል የሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫው ከመደረጉ አስቀድሞ ቢካሄድም ሕገወጥ ነው ሲል ቆይቶ፣ ምርጫው በትግራይ ቢደረግም ምርጫው እንዳልተደረገ የሚቆጠርና ተፈጻሚነት የማይኖረው ነው ሲል አስታወቀ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በጤና ሚኒስቴር ምክረ ሐሳብ ላይ በመንተራስ ምንም እንኳን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የኅብረተሰብ የጤና ሥጋት መሆኑ ባያበቃም፣ አስፈላጊ የሆኑ ጥንቃቄዎችን በማድረግ ከዘጠኝ እስከ 12 ወራት ባሉ ጊዜያት ውስጥ ዝግጅት ተደርጎ ምርጫው እንደሚከናወን አስታወቀ። የፓርላማው አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ይኼንን ውሳኔ ተከትሎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በትግራይ የተከናወነው ክልላዊ ምርጫ እንዳልተደረገ እንደሚቆጠርና ተፈጻሚነት የማይኖረው በወቅቱ ቢገልጹም ሕውሓት ሊቀበል አልቻለም። በዚህም ከመካረር አልፎ ወደለየለት ደም አፋሳሽ ጦርነት ተገባ።
በጦርነቱም በርካታ የሰው ሕይወት ጠፋ፤ ንብረት ወደመ፤ ዜጎች ተፈናቀሉ፤ ከፍተኛ ሰብዓዊ ጉዳት ደረሰ። የሀገሪቱም ኢኮኖሚ ክፉኛ ተጎዳ።
ይህ ሁሉ ጦስ የመጣው በሕገ መንግሥቱ እውቅና ያላቸውን ተቋማት ውሳኔ በአግባቡ ማክበር ባለመቻሉ ነው። ምርጫ ቦርድ፤ ፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ ጤና ሚኒስቴር የመሳሰሉ ተቋማት በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በትግራይ ምርጫ መካሄድ እንደሌለበት ደጋግመው ቢያስታውቁም ሰሚ ባለማግኘታቸው በሀገሪቱ ታሪክ ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ልንገባ ችለናል።
ሆኖም ለሁለት ዓመታት ያህል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል ሲደረግ የነበረው ጦርነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በፕሪቶርያ በተካሄደው የሰላም ስምምነት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መሠረት አድርጎ ሉዓላዊነትንና የግዛት አንድነትን እና ብሔራዊ ጥቅምን ባከበረ መልኩ ዕልባት አግኝቷል። የተደረሰው ስምምነት ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስቆም፣ ዕርዳታ እና መሠረታዊ አገልግሎቶች ለማስጀመርና የሀገሪቱን የድንበርና የግዛት አንድነት እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲከበር የማድረግ ዓላማ አለው።
ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱ ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የሚመነጭ ነው። በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 በፌዴራልና በክልል የምርጫ ክልሎች ነፃና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኝነት እንዲካሄድ የማድረግ ሥልጣን ያለው የምርጫ ቦርድ እንደሆነ በግልጽ ተደንግጓል። ሆኖም ከዚህ ድንጋጌ በተቃረነ መልኩ በትግራይ ክልል ‹‹ምርጫ ›› ተካሂዷል በሚል የትግራይ መንግሥት መቋቋሙን ስሁት በሆነ መልኩ ማወጁ ሀገሪቱን ለዚህ ሁሉ ጦስ ዳርጓታል። በወቅቱም የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ የተካሄደውን ‹‹ምርጫ›› እንዳልተካሄደ የሚቆጠር፤ በመግለጽ ተቀባይነት እንደሌለው ቢያሳውቅም ሰሚ ጆሮ አላገኘም ነበር።
ሆኖም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ በተካሄደው ስምምነትም ምርጫው መካሄድ እንዳልነበረበት የሚገልጽ ሃሳብ ሰፍሮ እናገኘዋለን። ምርጫው ሕገ ወጥ በመሆኑም በትግራይ የሽግግር መንግሥት ይቋቋማል፤ በሂደትም ምርጫ ተካሂዶ ክልሉን የሚያስተዳድር መንግሥት ይጸናል። ስለሆነም አሁን ባለው ሁኔታ የትግራይ ሕዝብን ሰላም የሚያስጠበቅውና ሕጋዊ ውክልና ያለውም የፌዴራል መንግሥት ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ በትግራይ ሕዝብ ተመርጫለሁ የሚል ሕጋዊ አካል የለም። ስለሆነም ከዚህ ውጭ የሚቀርቡ ጉዳዮች በፕሪቶርያው ስምምነት መሠረት ተቀባይነት የላቸውም፤ በዚህ ጉዳይ ሊቀመጥ የሚችል ቅድመ ሁኔታም የለም የሚሉ ሃሳቦች በግልጽ ነጥረው ወጥተዋል። በስምምነቱም መሠረት ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ቢጀመሩም አልፎ አልፎ ወደ ኋላ የመመለስ ሁኔታዎች ይታያሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ አሁንም ተቋማት የሚሰጡትን ውሳኔ አለመቀበል ነው።
ሰሞኑን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የሕወሓትን የፓርቲ ሕጋዊነትን በተመለከተ ለሦስት ወራት መታገዱን አስታውቋል። ለዚህ ደግሞ በዋነኝነት ሕውሓት ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂድ የተሰጠው የስድስት ወራት ጊዜ በመጠናቀቁ ለሦስት ወራት ከፖለቲካ እንቅስቃሴ መታገዱን ምርጫ ቦርድ ይፋ አድርጓል። ሕወሓት በልዩ ሁኔታ ከተመዘገበ ጊዜ አንስቶ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ የምርጫ ቦርድ ታዛቢዎች በተገኙበት ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ መተዳደሪያ ደንቡን ማፅደቅ እና አመራሮችን መምረጥ ቢኖርበትም ‹‹ይህንን ባለማክበሩ›› እግዱ እንደተጣለበት ምርጫ ቦርድ ይፋ አድርጓል።
ሕወሓት በልዩ ሁኔታ ከተመዘገበበት ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ የካቲት 3 ቀን 2017 ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂድ በሕግ የተሰጠው የስድስት ወራት ጊዜ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
ሕወሓት አዋጅ እና መመሪያዎችን ባለማክበር ‹‹ጉልህ ጥሰት ፈጽሟል›› ያለው ምርጫ ቦርድ ይህ ውሳኔ ከደረሰው ቀን ጀምሮ ለሦስት ወራት በምንም አይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳይሳተፍ ቦርዱ ማገዱን ገልጿል።
ሆኖም አንዳንድ የሕወሓት አመራሮች ቦርዱን እንደማይቀበሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ጭምር መረጃ ሲያስተላልፉ ታይተዋል። ይህ ደግሞ ቀደም ሲል የነበረውን ጥፋት መድገም እና አሁን ወደ ግጭት የሚወስድ ስለሆነ የምርጫ ቦርድን ውሳኔ ከማክበር የተሻለ አማራጭ የለም።
በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ያህል የዘለቀውና የብዙዎችን ሕይወት የቀጨው፤ ያፈናቀለውና ለስደት የዳረገው ጦርነት የተቋጨበት የፕሪቶርያው ስምምነት ከተፈረመና ኢትዮጵያም ፊቷን ወደ ሰላም ካዞረች ከሁለት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ አንጻራዊ ሰላም ከመስፈኑ ባሻገር የትግራይ፤ የአማራና የአፋር አርሶ አደሮች ወደ ግብርና ሥራቸው ተመልሰዋል፤ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን እንደገና የማቋቋም ሥራዎች ተጀምረዋል፤ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ተመልሰዋል፤ የተፈናቀሉ ዜጎችም ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሰፍረዋል። በአጠቃላይ ሕይወት ከጦርነቱ በፊት እንደነበረችው ለመመለስ በመንግሥትና በሌሎች ግብረ ሠናይ ድርጅቶች እንዲሁም በመላው ሕዝብ ተሳትፎ የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል።
በተለይም መንግሥት በጦርነቱ በእጅጉ የተጎዳውን የትግራይ ሕዝብ መልሶ ለማቋቋምና ጦርነቱ ያሳረፈበትን ሥነልቦና ለማከም በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የጥላቻውን ጉም በመግፈፍ ወደ ትግራይ በግንባር ቀደምነት የተጓዘው በአፈ ጉባዔው የተመራው የፌዴራል መንግሥቱ ልዑክ ነበር። ይህ ልዑክ ከተጓዘ በኋላ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የባንክና የአውሮፕላን አገልግሎቶች በፍጥነት እንዲጀምሩ ተደርገዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተመሠረተ ጊዜ መሳሳብና መጓተትን ለማስቀረት ሲባል የአመራሩን ድርሻ ክልሉ እንዲወስድ በማድረግ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፋታ አግኝቶ ፊቱን ወደ ሰላምና ልማት እንዲያዞር ተደርጓል።
የግብርና ሥራውን ለማገዝ የሚመለከተው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በክልል ደረጃ ከሚጠበቅበት በላይ ሠርቷል። ዩኒቨርሲቲዎችንና ትምህርት ቤቶችን ወደ አገልግሎት ለመመለስ የትምህርት ሚኒስቴር በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። በክልሉ ተቋርጦ የነበረውን ትምህርት እንዲጀመር ከማድረግ ባሻገር ከሁለት ዓመታት በኋላ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ተማሪዎች እንዲወስዱ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ተችሏል።
የመከላከያ ሠራዊት የሕዝቡን ችግር ለመፍታት ከራሱ በጀት ቀንሶ አያሌ ተግባራት አከናውኗል። የሰላም ስምምነቱን እንደ ዕድል በመጠቀም ሕዝብን ከችግር በማዳን፣ መንግሥታዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማስመጀመር ኃላፊነቱን ተወጥቷል። ከፌዴራል መንግሥቱም አልፎ ክልሎች ከአነስተኛ በጀታቸውና ገቢያቸው በመቀነስ የትግራይ ክልልን ደግፈዋል።
ሆኖም በመንግሥት በኩል የተደረገውን ያህል የሚመጥን ምላሽ ከዚያኛው ወገን አልተገኘም። በሰበብ አስባቡ የፕሪቶርያውን ስምምነት የሚጋፉ ድርጊቶችና አሉታዊ ሃሳቦች ጭምር በየጊዜው ሲደመጡና ሲታዩ ሁለት ዓመታት አልፈዋል። የፕሪቶርያው ስምምነት የሰላም ስምምነቱን የፈረሙ አካላት ከአሉታዊ ድርጊቶችና ንግግሮች እንዲታቀቡ የሚያስገድዳቸው ቢሆንም ከመንግሥት ውጪ ያሉት አካላት ስምምነቱን የሚጥሱ ድርጊቶችና ሃሳቦችን ሲያንፀበርቁ ታይተዋል። ሰሞኑን ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠውንም ውሳኔ ላለመቀበል ማንገራገር አንዱ ማሳያ ነው።
ሆኖም የፕሪቶርያው ስምምነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚያጸናና የዜጎችን ሰቆቃ የሚቀርፍ ስምምነት በመሆኑ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሚተገበር ነው። ስምምነቱ የኢትዮጵያን መሠረት ከማጽናቱም ባሻገር በጦርነት ሰቆቃ ውስጥ የነበሩትን የትግራይ፤ የአማራና የአፋር ሕዝቦችን እፎይታ ያጎናጸፈ ነው።
ከፕሪቶርያው ስምምነት ቀጥሎ የተካሄደው የናይሮቢ ስምምነት መተማመንን የፈጠረና ኢትዮጵያ የጀመረችውን የሰላም መንገድ የሚያጸና ነው። በተለይም በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጡ መሠረተ ልማቶችንና ሰብዓዊ ድጋፎችን በሚፈለገው መልኩ ለማድረስ መሠረት የጣለ ነው። በዚሁ መሠረትም በትግራይ፤ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ተቋርጠው የነበሩ የቴሌኮሙኒኬሽን፤ የኤሌክትሪክና የባንክ አገልግሎቶች መልሰው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ለማድረግ አስችሏል።
ስለዚህም ለሀገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መሠረት የሆነውና የዜጎች ሰቆቃ እንዲበቃ ያደረገው የፕሪቶርያው ስምምነት ቅድመ ሁኔታ የለውም፤ ስለሆነም በስምምነቱ መሠረት መፈጸም ከሁሉም ወገን የሚጠበቅ ግዴታ ነው። ያለውም ብቸኛው አማራጭ ይህንን ስምምነት ማስፈፀም ነው።
ነገር ግን ከመንግሥት ውጪ ያሉ አካላት እነዚህን ስምምነቶች በተደጋጋሚ ሲጥሱ ይታያሉ። ይህ ደግሞ እንደ ሀገር የሰፈነውን የሰላም አየር የሚበርዝና ዳግም ወደ ጥፋት የሚወሰድ በመሆኑ የፕሪቶርያው ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር ሁሉም አካላት የሚጠበቅባቸውን ሊወጡ ይገባል።
በተለይም በፕሪቶርያው ስምምነት መሠረት በሕገመንግሥቱ መሠረት ሕጋዊ ተቋማት ማክበር ዳግም ወደ ግጭት እና ጦርነት እንዳንገባ የሚያደርግ በመሆኑ ተቋማት የሚሰጡትን ውሳኔ ማክበር እራስንም ሆነ ሀገርን ከጥፋት መታደግ ነው።
አሊ ሴሮ
አዲስ ዘመን የካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም