የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት ዘመናትን የተሻገረ ነው:: መረጃዎች እንደሚያሳዩትም አሜሪካ በዓለም ላይ ካሏት ጠንካራ አጋሮች መካከል ኢትዮጵያ በሦስተኛ ደረጃ ተቀምጣ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ::
በተለይም በንጉሡ ዘመን ኢትዮጵያ እንደ ዋነኛ የአሜሪካ አጋር የምትወሰድና በዚሁ ምክንያትም በተለይ በሚሊቴሪው ዘርፍ አሜሪካ ጠንካራ ድጋፍ ስትሰጥ ቆይታለች:: ቀጥሎ የመጣው የደርግ መንግሥት ይከተለው በነበረው ርዕዮተ ዓለም የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ተቋርጦ የቆየ ቢሆንም የኢሕአዴግ መንግሥት ስልጣን ከያዘ በኋላ ግንኙነቱ እንደገና ታድሶ የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር:: ከለውጡ በኋላ ትግራይ ውስጥ ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የርስ በርስ ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ መንግሥታት ግንኙነት ዳግም መሻከር የታየበትና የአፍሪካ ሀገራት ከቀረጥ ነጻ በሆነ መልኩ ሸቀጦቻቸውን እንዲያስገቡ ከፈቀደችው የንግድ ዕድል ኢትዮጵያ እንድትሰረዝ እስከማድረግ ደርሶ ነበር::
ሆኖም ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷ በተከበረበት ሁኔታ በሃገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለ መግባትና ለዓለም አቀፋዊ ሰላምና ደኅንነት በጋራ የመቆም የጥንት የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ ላይ በመመሥረትም በጦርነቱ ወቅት ጭምር ከአሜሪካ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ እንዳይበላሽ በብዙ ስትጥር ቆይታለች::
ይህም ጥረቷ ፍሬ አፍርቶ ጥቅምት 23 ቀን 2015 በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል በፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መጠነኛ ለውጥ አሳይቷል:: በሂደትም የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ስምምነቱን ለመተግበርና የሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎቱ በአግባቡ እንዲዳረስ እያደረገው ያለው ድጋፍ በአሜሪካ ዘንድ በጎ ምላሽ አስገኝቷል:: ይህ ደግሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሰሞኑን አዲስ አበባ እንዲገኙ አድርጓቸዋል:: የብሊንከን ጉብኝት ከጦርነቱ መቆም በኋላ በከፍተኛ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣን የተደረገ ጉብኝት ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት የሰሜኑ ጦርነት እንዲቋጭና ይህንኑ ተከትሎም የሰብዓዊ ዕርዳታ በአግባቡ እንዲዳረስ፤ የተቋረጡ መሠረተ ልማቶች መልሰው አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ወደ ነበረበት እንዲመለስ በማድረግ ረገድ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አከናውኗል:: በሌላም በኩል የሰላም ሂደትን የሚያጠናክረውን የሽግግር ፍትሕ ለመተግበር በሂደት ላይ ነው:: ይህ ደግሞ በአጠቃላይ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት በመሆኑ በጦርነቱ ምክንያት ተበላሽቶ የነበረው የአሜሪካ እና የኢትዮጵያ መንግሥታት ግንኙነት ወደ ቀድሞው ቦታው እንዲመለስ ያስቻለ ነው::
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የአሜሪካ ዋና አጋር ሆና ዘመናትን ዘልቃለች:: በዚህም ሁለቱ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነትንና መከባበርን ባማከለ መልኩ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ሲመሩ ቆይተዋል:: በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ዋነኛ ስጋት የሆነውን ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ሁለቱ ሀገራት ለዓመታት ያህል ተጨባጭና ውጤታማ ሥራ ሲሠሩ ቆይተዋል:: ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ያላት አቀማመጥ፤ የሕዝብ ብዛት፤ እያደገ ያለ ኢኮኖሚ ባለቤት መሆኗና በቀጣናው ያላት ተጽዕኖ ፈጣሪነትና ተደማጭነት በዓለም አቀፍ ፀጥታና ደኅንነት ጂኦ ስትራቴጂካዊ ተፈላጊነት ያላት ሃገር ያደርጋታል::
ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትስስሮችን የሚያጠናክሩ ታላላቅ ተቋማትን በመመሥረት ጭምር በዓለም ዲፕሎማሲ መድረክ ጉልህ ሚና ስትጫወት የቆየች አገር ናት:: ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስከ አፍሪካ ኅብረትና ኢጋድ ድረስ የዲፕሎማሲ አሻራዋን ያሳረፈችባቸው ተቋማት በርካታ ናቸው:: ለዓለምና ቀጣናዊ ሰላም መስፈን ጦር ማሰማራትን ከማንም ቀድማ የጀመረችው ኢትዮጵያ፣ እንደ ጎረቤት ሶማሊያ ያሉ አገሮች ሰላማቸው ጸንቶ እንዲቆሙ ለማስቻል ብዙ መስዋዕትነትም የከፈለች ሀገር ናት::
ስለሆነም እንደአሜሪካ በመሳሰሉ ሀገራት የኢትዮጵያ ሚና በአግባቡ የሚታወቅና ግንኙነቱም በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ ላይ የተመሠረተ ነው:: ምስራቅ አፍሪካ የሽብርተኞች መናኻሪያ እንዳይሆን ኢትዮጵያ እየተጫወተችው ያለው ሚና አካባቢውን በትኩረት ለምትከታተለው አሜሪካ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው:: በሌላም በኩል ኢትዮጵያ ወደ ተለያዩ ሀገራት ሰላም አስከባሪ ሠራዊቷን በመላክ በአፍሪካ ብሎም በዓለም ሰላም እንዲሰፍን የበኩሏን ሚና የምትጫወት ሀገር ነች:: ሆኖም ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ መልኩ ያላትን ሚና በአግባቡ እንድትወጣ ደግሞ የተረጋጋ ሰላምና የተጠናከረ ኢኮኖሚ ያስፈልጋታል::
ስለሆነም ከአሜሪካ እና ከፍተኛ ተደማጭነት ካላት ዓለም አቀፍ ተቋማት ብድር፣ ያለባትን የዕዳ ክፍያ ጊዜ ማሸጋሸግ፣ በጦርነቱ መዘዝ የተነፈገቻቸውን እርዳታዎች እና የበጀት ድጎማዎችን እንዲሁም ወደ አጎዋ የቀረጥ እና ታሪፍ ነጻ ንግድ መመለስ ከአሜሪካ የሚጠበቁ የቤት ሥራዎች መሆን ይገባቸዋል:: ከዚህ አንጻር የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ ቆይታ ረጅም ዘመናት የቆውየን የኢትዮ አሜሪካ ግንኙነት ላቅ ወዳለ ደረጃ የሚያሸጋግር እንደሚሆን ይታመናል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም