የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በመሠረታዊነት በሀገር ውስጥ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የምግብ ፍጆታ አቅርቦትን ማሟላት አንዱና ዋነኛው ተግባሩ ነው። ከዚህም ባለፈ በሀገር ውስጥ የሚታየውን የዋጋ ንረት የማረጋጋትና የስርጭት መጠን ክፍተትን የማስተካከል ኃላፊነት አለው። ኮርፖሬሽኑ ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር በርካታ ኃላፊነቶች ያሉበት ቢሆንም ባለፉት በርካታ ዓመታት አገልግሎቱን በሚፈለገው ልክ መስጠት የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶች የተሟሉለት እንዳልሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
ኮርፖሬሽኑ በአራት የሥራ ዘርፎች ማለትም በእህልና ቡና ንግድ ሥራዎች፣ በኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ፣ በኢትዮጵያ የፍጆታ ንግድ ሥራ እና የግዢና ማማከር ተቋማትን በማዋሐድ እየሠራ ያለ ተቋም ሲሆን በተለይም በእህልና ቡና ንግድ ከ70 ዓመታት በላይ የአገልግሎት ልምድ አለው። በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድም ከ40 ዓመታት በላይ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ ኮርፖሬሽኑ በአራቱም የንግድ ዘርፎች ሲሠራ በቆየባቸው በርካታ ዓመታት ለኪሳራ ተዳርጎ እንደነበር ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ኮርፖሬሽኑ ከኪሳራ በመውጣት ውጤታማ ሥራ እየሠራ እንደሆነ ነው ይሄው መረጃ የጠቆመው። ኮርፖሬሽኑ የመንግሥት የልማት ድርጅት እንደመሆኑ ለማኅበረሰቡ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ አቅርቦት ማሟላትና በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ማድረግ ዋነኛ ተግባሩ ነው።
በተለይም ሕዝብ በስፋት በሚኖርባቸው ትላልቅ ከተሞች ላይ የአቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት ሲፈጠር ግንባር ቀደም ሚናን መጫወት ከኮርፖሬሽኑ ይጠበቃል። በቀጣይም በሀገሪቱ በየጊዜው የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ከመከላከል ጀምሮ ገበያን በማረጋጋት የተለያዩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ ከኮርፖሬሽኑ የሚጠበቅ እንደሆነ ይታመናል።
በመሆኑም ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት ከአምራቹ እስከ ተጠቃሚው ያለውን የአቅርቦትና የግብይት ሰንሰለት ጤናማና ውጤታማ በማድረግ፤ ጤንነቱና ደህንነቱ የተጠበቀ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚው ተደራሽ ማድረግ የሚያስችለውን ሥራ አጠናክሮ ለመቀጠል በዝግጅት ላይ ይገኛል። ኮርፖሬሽኑ በሀገሪቱ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማና በዙሪያዋ ለሚገኙ የክልል ከተሞች ጭምር የተሻለ የምርት አቅርቦት ለማቅረብ ፈታኝ ሆኖበት የቆየውን ችግር የሚቀርፍለትን ዘመናዊና ባለዘርፈ ብዙ ቅይጥ አገልግሎት የሚሰጥ ሕንጻ አስገንብቶ ለመጠቀም አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያከናወነ ይገኛል።
የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳሉት፤ የኮርፖሬሽኑ ዓላማ ለማኅበረሰቡ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ አቅርቦት ማሟላት ነው። ይህም ሲባል አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ የእህልና የጥራጥሬ ምርቶችን ያቀርባል። በአገሪቱ ምርት በስፋት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች ያለውን ምርት ገዝቶ፣ አከማችቶና አደራጅቶ እጥረት ወዳለባቸውና ሌሎች ተጠቃሚዎች ወደሚገኙበት አካባቢ ተደራሽ በማድረግ ኅብረተሰቡ ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝቶ መጠቀም እንዲችል የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት ወሳኝ ነው።
ከሰሞኑም ኮርፖሬሽኑ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በተለምዶ የሺ ቶታል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ባለ 10 ወለል ቅይጥ አገልግሎት የሚሰጥ ሕንጻ ግንባታ ሥራ ማስጀመሩም ለዚሁ ነው። ባለማቀዝቀዣ የቅይጥ ሕንጻ ግንባታው በተለይም የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ደረጃቸውን በጠበቀ መንገድ ሳይበላሹ ለረጅም ጊዜ ማቆየት የሚያስችል ሲሆን፤ ከዚህም ባለፈ ኮርፖሬሽኑ ከአምራቹ የሚቀበለውን የአትከልትና ፍራፍሬ ምርት ያለብልሽት ጥራቱን ጠብቆ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ነው።
በአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ በዓመት ውስጥ በተወሰኑ ወራት ብቻ ምርት የሚገኝ በመሆኑ፣ ከምርት ወቅት በኋላ የምርት እጥረት በሚከሰትባቸው ወራት ኮርፖሬሽኑ ምርት አከማችቶ የሚያቆይ ይሆናል። አከማችቶ ያቆየውን ምርትም አውጥቶ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ያደርጋል። በተለይም ሰፊ ቁጥር ያለው ሕዝብ ይኖራል ተብሎ በሚገመትባቸው ሰፋፊ ከተሞች ውስጥ የመንግሥት ሠራተኞችን ጨምሮ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ምርቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባል። ኮርፖሬሽኑ ከሚያቀርባቸው የምርት አይነቶች መካከልም አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ የዳቦ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ጥራጥሬና ሌሎችም ይገኙበታል።
ኮርፖሬሽኑ ለመንግሥት ሠራተኞችና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች ከሚያቀርበው ምርት በተጨማሪ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመሄድ ለሚሠሩና ሀገራዊ ኃላፊነት ውስጥ ለሚገኙ ማለትም ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለፌዴራል ፖሊስና ለመሳሰሉት በተመሳሳይ ለምግብ ሬሽን የሚውል ምርት እያቀረበ እንደሆነም አቶ አቻ ይገልፃሉ።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንደሚናገሩት፤ ኮርፖሬሽኑ፤ ከአዲስ አበባ ከተማ በረጅም ርቀት ላይ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በግል፣ በማኅበርና በትላልቅ ኩባንያዎች ጭምር የሚመረተውን አትክልትና ፍራፍሬ እስከ 900 ኪሎ ሜትር ርቀት ተጉዞ ምርቶቹን በቀጥታ ከአምራቾች ገዝቶና አደራጅቶ ለገበያ ያቀርባል።
ይህም አምራቹን በማበረታታት፣ ምርቱ ገበያ እንዲያገኝና በተመጣጣኝ ዋጋ መሸጥ እንዲችል ያደርጋል። አምራቹ ካመረተ በኋላ ገዢ በማጣት ማምረት እንዳያቆም ተመጣጣኝ ዋጋ ለአምራቹ በመክፈል ምርቱን ይገዛዋል፤ በተመሳሳይ ደግሞ በከተሞች የሚገኘው ምርት ፈላጊ ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛት እንዲችል አጓጉዞና አደራጅቶ በማቅረብ ማኅበረሰቡ ተመጣጣኝ ምግብ ማግኘት እንዲችል ያደርጋል።
‹‹የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በቀላሉ የሚበላሽ እንደመሆኑ ከተመረተበት አካባቢ ወደ ተጠቃሚው እስኪደርስ ባለው ምልልስ ተበላሽቶ የሚጣለው ምርት ይበልጣል›› የሚሉት አቶ አቻ፤ ይህም በሀገሪቱ ለረጅም ጊዜ የቆየና አሁንም ያልተፈታ መሠረታዊ ችግር እንደሆነ ያስረዳሉ። ችግሩን ለመፍታት ከትራንስፖርት ጀምሮ ማቀዝቀዣ ያላቸው ተሽከርካሪዎችና ሌሎች መሠረተ ልማቶችም ያስፈልጋሉ። ምርቶቹ ከተጓጓዙ በኋላም ማቆየት የሚያስችል ማቀዝቀዣና ማደራጃ መጋዘኖች አስፈላጊና ወሳኝ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ አቻ፤ ይህም ጤንነቱና ደህንነቱ የተጠበቀ ምርት ተደራጅቶ ለተጠቃሚው እንዲደርስ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከአዲስ አበባ ረጅም ርቀት ተጓጉዘው የሚመጡት የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በቀላሉ ለብልሽት የሚጋለጡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህን ችግር ለመፍታት ዘመናዊ ባለማቀዝቀዣ የቅይጥ ሕንጻ ግንባታው ወሳኝ ሆኖ መገኘቱን ይናገራሉ። የገበያ ማዕከልና የቢሮ አገልግሎትን ጨምሮ የሚገነባው ይህ ግንባታ ለበርካታ ጊዜ ታቅዶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አቻ፤ ግንባታው ሲጠናቀቅም ኮርፖሬሽኑ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎችና በዙሪያው ለሚገኙ የክልል ከተሞች ምርቶቹን ያሰራጫል። ኮርፖሬሽኑ የሚያቀርባቸው የተለያዩ ምርቶችም ማኅበረሰቡ ትክክለኛ የጥራት ማረጋገጫዎችን ተረድቶ ሊገዛና ሊጠቀምበት የሚያስችለው ነው ብለዋል።
‹‹የሀገር ውስጥ ምርት ደረጃውን የጠበቀና የሚፈለገውን የጥራት ደረጃ ያሟላ መሆን እንዲችል ባለማቀዝቀዣ የቅይጥ ሕንጻው አይነተኛ ሚና ይኖረዋል፤ በተለይም በኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ውስጥ ለሚገኘው የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ዘርፍ አበርክቶው የጎላ ነው›› ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ኮርፖሬሽኑ በአገር ውስጥ አትክልትና ፍራፍሬን የሚያመርቱ ኩባንያዎች፣ ግለሰቦችና ማኅበራት እንደ ብርቱካን አይነት ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችን በማምረት ከሀገር ውስጥ ባለፈም ወደ ውጭ ገበያ ይቀርባል። ለአብነትም በተያዘው በጀት ዓመት 64 በመቶ ፍራፍሬዎችን ወደ ውጭ ገበያ መላክ የተቻለ ሲሆን በቀጣይም ይኸው ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ከአትክልትና ፍራፍሬ በተጨማሪ ቡናና የቅባት እህሎች እንዲሁም ጥራጥሬዎች ወደ ውጭ ገበያ ስለመላካቸው የጠቀሱት አቶ አቻ፤ የአቅርቦት እጥረቱ ክፍተት ቢኖረውም ከዕቅዱ አንጻር ግን የተሻለ ክንውን ያለው መሆኑን አስረድተዋል።
እንደዋና ሥራ አስፈፃሚው ማብራሪያ፣ ኮርፖሬሽኑ ገበያ የማረጋጋት ሥራን የሚሠራ በመሆኑ በተለያየ ጊዜ የሚፈጠረውን የምርት አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት ኮርፖሬሽኑ አማራጭ ሆኖ ይቀርባል። በተለይም ለመንግሥት ሠራተኞችና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የተለያዩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያን በማረጋጋት ቀዳሚ ነው። ለአብነትም በአሁኑ ወቅት በጤፍ ምርት ላይ እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ጤፍ ገበያ ላይ በኩንታል ከስምንት ሺ ብር በላይ ሲሸጥ ኮርፖሬሽኑ አንድ ኩንታል ነጭ ጤፍ በ5,250 ብር ለአዲስ አበባና ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሠራተኞች፣ ለተማሪዎች ምገባ፣ ለኅብረት ሥራ ዩኒየኖች፣ ለማረሚያ ቤቶች፣ ለፌደራልና ለኦሮሚያ ፖሊስ፣ እንዲሁም ለድሬዳዋ፣ ለባሕርዳርና ለደሴ ከተማ ነዋሪዎች በማቅረብ ገበያውን በማረጋጋት ሰፊ ሥራ እየሠራ ይገኛል።
ሲሚንቶ፣ ዘይትና ሌሎች ምርቶችንም በማቅረብ ገበያን የማረጋጋት ሥራ እየሠራ የሚገኘው ኮርፖሬሽኑ፤ በተለይም ፓልም የምግብ ዘይት ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በተሰጠው ኮታ መሠረት ለአዲስ አበባ፣ ለአማራ፣ ለሱማሌ፣ ለድሬዳዋ፣ ለሐረር፣ ለደቡብ ምዕራብ እና ጋምቤላ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በአዲስ አበባ ማሠራጫ ዋጋ ባለ ሶስት ሊትር 314 ብር፤ ባለ አምስት ሊትር 510 ብር፤ ባለ 20 ሊትር በብር 2,003 ብር የትራንስፖርት ሂሳብ ታክሎ በኅብረት ሥራ ዮኒየኖች አማካይነት በማሠራጨት ገበያውን በማረጋጋት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።
ኮርፖሬሽኑ የተለያዩ ምርቶችን ገበያው በሚፈልገው መጠን በስፋትና በብዛት በማቅረብ ሙሉ ለሙሉ ገበያውን የማረጋጋት አቅም ላይ አልደረሰም የሚሉት አቶ አቻ፤ ለዚህም እጅግ ሰፊ የሆነ የመሠረተ ልማት፣ ትራንስፖርትና የካፒታል አቅም እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። ይሁንና ወደፊት አቅሙን በማጠናከርና መሠረተ ልማቶችን በማሟላት ገበያን የማረጋጋት ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ኮርፖሬሽኑ የአገር ውስጥ ምርትን ሰብስቦና አደራጅቶ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ በሀገር ውስጥ እጥረት የሚታይባቸውን ምርቶች ከውጭ የሚያስገባ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አቻ፤ የኅብረተሰቡን ፍላጎት በአገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ሰባት ወራት ከዕቅዱ ከ70 በመቶ በላይ ማከናወን የቻለ ሲሆን፤ አጠቃላይ ለገበያ ባቀረባቸው ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ጥራጥሬ፣ ስኳርና ሌሎች ምርቶች በሰባት ወራት 257 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱንም አስታውቀዋል። ትርፍ ሲባል እንደሌሎች ነጋዴዎች የተትረፈረፈ ትርፍ ማትረፍ እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ ወጪውን በገቢ መሸፈን የሚያስችል መጠነኛ ትርፍ እንደሆነም ጠቁመዋል።
እንደ አቶ አቻ ገለጻ፤ ኮርፖሬሽኑ በተለይም አምራቹን ለማበረታታት በዋናነት ከፍተኛ ምርት ተመርቶ ገበያ በሌለባቸው አካባቢዎች በመግባት ምርቱን አውጥቶና አደራጅቶ እጥረት ወዳለበት ቦታ እንዲሸጥ በማድረግ ሰፊ ሥራ እየሠራ ይገኛል። በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚገበያዩባቸው ከ54 በላይ የአትክልትና ፍራፍሬ መሸጫ ሱቆች አሉት። ፓስታ፣ማካሮኒና ሌሎች ምርቶች የሚሰራጩባቸው ደግሞ ከአራት በላይ ቦታዎች ሲኖሩት፣ ከ11 በሚበልጡ ቦታዎችም ስንዴ፣ በቆሎና ሲሚንቶ ያሰራጫል። ኮርፖሬሽኑ በአጠቃላይ 211 በሚደርሱ ማሰራጫና ማከፋፈያዎች የተለያዩ ምርቶችን በማቅረብ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት በመስጠት ገበያ የማረጋጋት ሥራ እየሠራ ይገኛል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 6 ቀን 2015 ዓ.ም