በኢትዮጵያ ውሹ ስፖርት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሠልጣኞች ሥልጠና እንደሚሰጥ ተገለጸ። የሥልጠናው አዘጋጅ የኢትዮጵያ ውሹ ፌዴሬሽን ሲሆን በአሁኑ ወቅት የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን የውሹ ስፖርት አሠልጣኝ የሆነው ቻይናዊው ማስተር ሑ ሊን ሥልጠናውን እንደሚሰጥ ተጠቁሟል።
ሥልጠናው ከመጋቢት 8 እስከ መጋቢት 10 /2015 ድረስ ለሶስት ቀናት በኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚ ይሰጣል። በሥልጠናው ጀማሪ አሠልጣኞች፣ መካከለኛ ኢንስትራክተሮች፣ ከፍተኛ ሲኒየር ማስተሮች የሚሳተፉ ሲሆን ሥልጠናውን የሚያጠናቅቁ ሠልጣኞች ከውጭ የሚመጣ ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት እንደሚበረከትላቸው ታውቋል።
ይህ ሥልጠና ከዚህ በፊት በፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት እና በክልል ፌዴሬሽኖች በኩል ለረጅም ጊዜያት ሲጠየቅ የነበረ እና ለስፖርቱ እድገትም ሆነ ለባለሙያው እጅግ አስፈላጊ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች እና በሁኔታዎች አለመመቸት ምክንያት ከዚህ በፊት ማዘጋጀት ሳይቻል ቆይቷል፡፡
ሥልጠናው በፌዴሬሽኑ እና በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ከፍተኛ ዝግጅት የተደረገበት እና ለቀጣይ ዓለም አቀፍ ሥልጠናዎችም በር ከፋች እንደሚሆን ተታምኖበታል፡፡ በመሆኑም ሥልጠናው ግቡን እንዲመታ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የስፖርቱ አሠልጣኖችን ተሳትፎ ይጠይቃል ተብሏል፡፡
የሥልጠናው ስፖርቱን በበሰሉና እውቀቱ ባላቸው ባለሙያዎች ለመምራት የሚደረግ ጥረት መሆኑም ተገልጿል፡፡ በሥልጠናው ከሁሉም ክልልና ከተማ መስተዳድሮች ጥሪ የተደረገላቸውና መስፈርቱን የሚያሟሉ አሠልጣኞች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተነግሯል፡፡ በሥልጠናው የሚሳተፉ አሠልጣኞች ከጥቁር ቀበቶ ጀምሮ እስከ ስድስተኛ ዳን ያላቸዉ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ቁጥራቸው ከ200 እስከ 250 የሚደርሱ አሠልጣኞች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ውሹ ፌዴሬሽን የውድድርና ሥልጠና ባለሙያ አቶ ገበየው ሙሉጌታ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ ስፖርቱ በባህሪታ የፍልሚያ ስፖርት ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በተደረገ ጥናት ከፍልሚያ ጥበብ ጋር ተያይዞ ሰፊ ክፍተቶች አሉበት። በዚህም መሰረት ያለውን ክፍተት ለመሙላት ሥልጠናውን ለመስጠት ፌዴሬሽኑ መወሰኑን ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡ ሥልጠናው ከዚህ ቀደም ከሚሰጡት ሥልጠናዎች ለየት የሚያደርገው ዓለም አቀፍ ደረጃዉን የጠበቀና ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጥ መሆኑ ነው። እንደ አቶ ገበየው ገለፃ፣ በከዚህ ቀደም አሠልጣኞች ወደ ቻይና ተልከው ለስድስት ወርና ለአንድ ዓመት ሥልጠናዎችን ይወስዱ ነበር። በዚህም ወደ ሰላሳ ስምንት የሚደርሱና ከተለያየ ክልልና ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ባለሙያዎችን ማሠልጠን ተችሏል። በተንጠባጠበ ሁኔታ ውጭ ልኮ ሥልጠና በመስጠት ውጤታማ መሆን ስለማይቻል ግን አንዴ ባለሙያ በማምጣት በርካታ አሠልጣኞችን ለማሠልጠን ተወስኗል።
ከሥልጠናው በኋላ በሚደረጉት አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በሳንሹ (በፋይት) የተሻሉና ሀገርን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለመምረጥ ጥሩ አጋጣሚ መፍጠር እንደሚቻልም ባለሙያው አስረድተዋል። ለዚህም እንዲሆን ከወራት በኋላ የኢትዮጵያ ውሹ ቻምፒዮና እንደሚዘጋጅ ታውቋል። ሥልጠናውን የሚወስዱት አሠልጣኞች ለውድድሩ ይዘው በሚቀርቡት ተወዳዳሪ ላይ የሚታይ የቴክኒክ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም ባለሙያው ተናግረዋል።
ሥልጠናውን ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ መስጠት ያልተቻለበት በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን የጠቆሙት ባለሙያው፣ ለስፖርቱ ትኩረት አለመሰጠት አንዱ ችግር መሆኑን አስረድተዋል። ከመንግሥት ጀምሮ ሚዲያና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለስፖርቱ ትኩረት መስጠት ከቻሉ ግን በቀላሉ ውጤት ማምጣት ከሚቻልባቸው የስፖርት አይነቶች ውሹ አንዱ እንደሚሆን ተናግረዋል።
“የውሹ ስፖርት ብዙ ማህበረሰብን በማቀፍ በትንሽ ወጪ ውጤት ማምጣት የሚቻልበት ነው” ያሉት አቶ ገበየው ስፖርቱ በሁሉም ክልሎች የሚዘወተር ስፖርት መሆኑን ተናግረዋል። ኦሮሚያ ክልል ብቻ በ2012 ላይ በተሰራው ዳታ ከ4ሺ 800 በላይ የውሹ ማሠልጠኛ ማዕከላት ያሉ ሲሆን በአዲስ አበባም በተለያየ ዲቪዚዮን በዓመት ሁለት ጊዜ የሚደረግ ውድድር አለ።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በውሹ ስፖርት በአፍሪካ ቻምፒዮናና በጥቂት ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳታፊ መሆን ችላ እንደነበር ያስታወሱት ባለሙያው፣ በቀጣይም በአህጉርና ዓለምአቀፍ ወድድሮች ተሳትፎ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል። ስፖርቱ በ2026 የኦሊምፒክ ስፖርት እንደሚሆን ቃል በመገባቱ ስፖርቱ በዓለም ላይ ምን ያህል ተወዳጅነትን እያተረፈ እንደመጣ ያሳያልም ብለዋል፡፡ በዚህም ፌዴሬሽኑ ሥልጠናዎችን ከመስጠት ባሻገር ተተኪዎችን ለማፍራት የተለያዩ ስራዎችን ከወዲሁ በመስራት ላይ ይገኛል። በአራት ክልሎች የታዳጊ ፕሮጀክቶች ተከፍተው በትግራይ፣ ደቡብና አማራ ክልል እየተሰራባቸው ነው። ይሁን እንጂ በሚፈለገው ደረጃ ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ የፋይናንስ እጥረት የፌዴሬሽኑ ችግር ሆኗል። ስፖርቱን በተመለከተ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆኑም በቀጣይ የማስተዋወቅ ስራዎች በስፋት እንደሚሰሩ ባለሙያው አክለዋል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን መጋቢት 6 ቀን 2015 ኣ.ም