ኢትዮጵያውያን መልከ ብዙ ፤ ዓይነተ ልዩ ልዩ ነን። የተለያየ ሃይማኖት፣ ባሕልና እምነት ያለን፣ ባለብዙ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦችም ነን። እንደ መልክዓምድሩ አቀማመጥ እንደየክልሎቻችን ስፋትና ዓይነት ተፈጥሮ የለገሰችን በርካታ ገጸ በረከቶችም አሉን። እነዚህን ሁሉ ገጸ በረከቶች የምንቋደሰው በመተሳሰብ፣ በመተባበርና በአንድነት ሆነን ነው። ደስታና ኃዘናችንን የምንካፈለው፤ ችግሮቻችንን በጋራ የምናሳልፈው በመረዳዳትና በመተሳሰብ ባለን ኢትዮጵያዊ ባሕላችን ነው። ይሄ የኢትዮጵያዊነታችን መገለጫ አንዱ ምልክታችን ነው።
በጀግንነትም ዓለም የመሰከረው ታሪክ የዘገበው የድል ባለቤቶች ነን። በሀገር ላይ ጠላት እጁን ሲያነሳ ቀፎው እንደተነካበት ንብ ሆ ብሎ መነሳት የምንታወቅበት የጀግንነት ታሪካችን ነው። ይሄ የጀግንነት መገለጫችን ታዲያ ጠላት ከውጪ ሲመጣ ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች በሚያጋጥሙ ጊዜም ‹‹የወገን ደራሹ ወገን ነው›› በሚል ጠንካራ የጀግንነት አቋማችንን እናሳያለን ።
በተለየ ሁኔታ ውስጥ ሆነንም ለተቸገሩ ወገኖቻችን ከአለን ላይ አካፍለን በመስጠት ወገናዊነታችንን በተግባር እናረጋግጣለን። በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት የተፈናቀሉና ለችግር የተጋለጡ ወገኖቻችንን በመርዳትና በመደገፍ ፣ በዓላት በመጡ ቁጥር ያለንን ተካፍለን በጋራ በማሳለፍ ብዙ መልካም የሆኑ የመረዳዳት ዘመናትን አሳልፈናል። ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን የሚያጠናክሩ ብዙ ብዙ ተግባራትን ከውነናል። አሁንም ይህንኑ የመረዳዳትና የመተሳሰብ ተግባር ቀጥለናል። ወደፊትም አጠናክረን ልንቀጥልበት የሚገባን ነው።
በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት የድርቅ አደጋ ተከስቷል። በተለይ በየ10 ዓመቱ የሚከሰተው የድርቅ አደጋ ጉዳቱ ሰፋ ያለ ስለሚሆን በብዙ መልኩ በሀገር ላይ ፈታኝ ሆኖ አልፏል። ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት በተለይም ሕጻናት እና አረጋውያን በሰፊው ተጎጂ ይሆናሉ። የቤት እንስሳት ይሞታሉ።
አሁንም በተለያየ አካባቢ የሚኖሩ ወገኖቻችን ላይ የድርቅ ችግር አጋጥሟል። በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎቻችን ለችግር ተጋልጠዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ የቤት እንስሳቶች በድርቁ አደጋ ሞተዋል። በሕይወት ያሉት የወገኖቻችንን ርዳታ እየተጠባበቁ ናቸው። የወገኖቻችን ጉዳት የእያንዳንዳችን ጉዳት ነውና ልንደርስላቸው፣አይዟችሁ፣ አለንላችሁ ልንላቸው ይገባል። ለችግሩ የተጋለጡ ዜጎች የምግብ እህል ፣ ለሕጻናት አልሚ ምግብ ፤ ለቤት እንስሳቶች ደግሞ መኖ እና ውሀ በአስቸኳይ ያስፈልጋቸዋል። ከፊታቸው የተጋረጠባቸውን ችግር ማለፍና መቋቋም የሚቻለው እያንዳንዳችን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ የምንገኝ ዜጎች ለወገኖቻችን ስንደርስላቸው ነው።
ስለዚህ ለችግር የተጋለጡ ወገኖቻችንን ሕይወት ለማትረፍ ዛሬ ሁላችንም ልንረባረብ ይገባል። እስከአሁን ባለው ሂደት በዋናነት መንግሥት እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ ነው ። አንዳንድ ግለሰቦችም የአቅማቸውን ድጋፍ እያሰባሰቡና እየረዱ ነው። ይሄ በጣም የሚያስመሰግን ተግባር ቢሆንም ካለው ችግር ስፋትና አሳሳቢነት አንጻር ግን በቂ አይደለም። ስለዚህ በተደራጀና በተጠናከረ መልኩ ድጋፍ ማድረግና ለወገኖቻችን አለንላችሁ ልንላቸው ይገባል።
አሁንም ድርቁ በተለያዩ አካባቢዎች ጉዳት ማድረሱን ቀጥሏል። በተለይ አርብቶ አደሮች በሚኖሩባቸው ሰፊ የቤት እንስሳት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ችግሩ የገዘፈ ነው። በኦሮሚያ የቦረና ዞንን ጨምሮ በ10 ዞኖች ፣ በሱማሌ በሁሉም ዞኖች እንዲሁም በደቡብ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን ችግሩ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።
በሶማሌ ክልል ለተረጂነት ከተጋለጡት ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች መካከል አሁን ላይ እርዳታ እያገኙ ያሉት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ያህሉ ብቻ ናቸው። አሁንም 2 ነጥበ 4 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። እስካሁን ባለው ሁኔታ በዳዋን ብቻ ግመሎችን ጨምሮ 340 ሺህ የሚጠጉ እንስሳት በድርቁ ምክንያት የሞቱ ሲሆን ወደ 600ሺህ የሚጠጉት ደግሞ እጅግ አስጊ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።
በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተከሰተው ድርቅ እስካሁን ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምግብ ቀርቧል። የሕዝቡ የኑሮ መሠረት የሆኑትን የቤት እንስሳት ለመታደግም ውሃ በቦቴ እየቀረበ ይገኛሉ። የፌደራል መንግሥትና ክልሉ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል። ይሄ ደግሞ መንግሥት ኃላፊነቱን በመወጣት ያደረገው ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንጻር ግን በቂ አይደለም። ሁሉንም ድጋፍ በመንግሥት ብቻ መሸፈንም አዳጋች ነው። በመሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፣ በውጪ የሚኖሩ ዲያስፖራዎች ሁሉ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ለወገኖቻችን ልንደርስላቸው ይገባል። ለወገን ደራሽ ወገን መሆኑን በተግባር ማረጋገጥም አለብን!
አዲስ ዘመን መጋቢት 6 ቀን 2015 ኣ.ም