ኢትዮጵያ ሰፊ የዓሣ ሀብት እንዳላት መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህን የዓሣ ሀብት በማልማትም ሆነ በመጠቀም ረገድ ግን ብዙም አልተሠራበት። ይህም ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሣ መሆኑን ያመለክታል።
ልማቱ አለመዘመኑና ሀብቱንም ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚካሄድ የተጠናከረ ሥራ አለመኖር የትኩረት ማነስ ማሳያዎች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ። በአንድ ወቅት በዓሣ ሀብት ከሚታወቁ የኢትዮጵያ ክፍሎች አንዱ በሆነው ጋምቤላ ክልል ዓሣን አቀነባብሮ ለውጭ ገበያ በማቅረብ በዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት በመንግሥት በኩል አቅጣጫ ተይዞ እንቅስቃሴ ተጀምሮ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። ያም ቢሆን ወደ ውጤት ተቀይሮ አልታየም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በዚሁ በጋምቤላ ክልል ያለውን እምቅ የዓሳ ሀብት በማልማት ለመጠቀም የሚያስችል ፕሮጀክት ተቀርጾ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። የዚህ ፕሮጀክት ዋና ዓላማ የዓሣ ልማቱን ምርታማነት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማሳደግ ነው። ፕሮጀክቱንም የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን በበላይነት እየመራው ይገኛል። እኛም ስለፕሮጀክቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ከክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ያሲን በላይ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ በዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዓምዳችን ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- በጋምቤላ ክልል ስላለው የዓሣ ሀብትና ስለፕሮጀክቱ ቢገልጹልን?
አቶ ያሲን፡-በጋምቤላ ክልል ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች ይገኛሉ። በእነዚህ ሁሉ የውሃ አካላት ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያለው የዓሳ ሀብት አለ። በውሃ አካላቱ ውስጥ ወደ 138 አይነት የዓሣ ዝርያዎች እንደሚገኙ ከዚህ ቀደም የተደረጉ የጥናት ውጤቶች ያሳያሉ። አሁን ግን አዳዲስ ዝርያዎች ሊገኙ እንደሚችሉ፣ ከነባሮቹ መካከል ዝርያቸው የጠፋ ሊኖር እንደሚችልም ይገመታል። ክልሉ በሀገር ደረጃም በዓሣ ሀብት ከፍተኛ አቅም አለው ተብሎ እውቅና ተሰጥቶታል።
በመተግበር ላይ የሚገኘው ፕሮጀክት ተለምዳዊ (ባሕላዊ) በሆነ መንገድ የሚካሄደውን የዓሣ ልማት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመተካት ልማቱን ማሣደግ ነው። የምርት ማሳደጉ ሥራ ወደ ውጪ በመላክ በሀገር ኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ድርሻ እንዲኖረው ማድረግ በሚል የጋራ አስተሳሰብ ተይዞ የተጀመረ ነው። ፕሮጀክቱን ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን በጋራ እያከናወኑት ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፡- ፕሮጀክቱ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ያሲን፡- በፕሮጀክቱ ዓሣን ለማምረት ሥራ ስድስት ቦታዎች/ ሳይቶች/ በጥናት ተለይተዋል፤ ከስድስቱ ሳይቶች በ2013 መጨረሻ በ2014 መጀመሪያ ሦስት ፓይለት ፕሮጀክቶች ተለይተዋል። እነዚህም አበቦ ወረዳ ፣ጋምቤላ ከተማ እና ኢታንግ ወረዳ ናቸው። ጋምቤላ ከተማ ከሌሎቹ በተሻለ ከፍተኛ መጠን ያለው ዓሣ ይገኛል። በአሁኑ ጊዜም በነዚህ አካባቢዎች የሚለማውን ዓሣ ደህንነቱ ተጠብቆ ለአካባቢው ማኅበረሰብና አዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ለማቅረብ እቅድ ተይዞል። ጋምቤላ ያለው ማጠራቀሚያ ማዕከል ለስድስቱም ሳይቶች ማሰባሰቢያ ማዕከል አለው፤ እንደ ሌሎቹ ደግሞ የራሱ የሆነ በአንድ መስኮት ጤንነቱ የተጠበቀ ዓሣ የሚሸጥበት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በፕሮጀክቱ ምን አይነት ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ታስቧል?
አቶ ያሲን፡-ፕሮጀክቱ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ በአፍሪካ አምስተኛ ደረጃ ላይ ያለ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ይጠቀማል። ዓሣ ማስገሪያ ጀልባዎቹ ዘመናዊ ናቸው። ይህ ፕሮጀክት ከመከፈቱ በፊት ወጣቶች ዓሣ ለማስገር የሚጠቀሙት በእንጨት ጀልባ ነበር። ጀልባው እንዲንቀሳቀስ የሚደረገው በሞተር ነበር፤ አሁን ሞተሩ በነዳጅ ሳይሆን በፀሐይ ኃይል ወይም በኤሌክትሪክ ቻርጅ የሚንቀሳቀስ እንዲሆን ተደርጓል። ይህ የሆነበት ምክንያት ነዳጅ ከሆነ እየተንጠባጠበ ውሃ ሊበክል ስለሚችል ነው፤ ጤንነቱ የተጠበቀ ስንል ውሃ ውስጥ ያለው ዓሣ በሚንጠባጠበው ነዳጅ ችግር እንዳይገጥመው ለማድረግ ነው። በሌላ በኩል ውሃው ሊበከል ይችላል፤ ይህ ማለት ኅብረተሰቡ ሌላ አገልግሎት ሊጠቀም የሚችለውን ውሃም ይበከላል ማለት ነው።
ዓሣ አስጋሪዎቹ አሁን ዓሣውን የሚያቀርቡት እንደፊቱ በተለምዷዊ እቃ አይደለም፤ ማቀዝቀዣ(Ice box) ውስጥ አርገው መሆን አለበት። ሁሉም የማከማቻ ማዕከላት በረዶ ያመርታሉ። ዓሣውን አስግረው ሲጨርሱ ማቀዝቀዣው (Icebox) ውስጥ ያስቀምጡና ወደ ማከማቻ ማዕከሉ ያመጣሉ።
ማከማቻ ማዕከሉ ሦስት ክፍሎች አሉት። የመጀመሪያው መቀበያውና ፕሮሰስ የሚያደርጉ (ሥልጠና የተሰጣቸው ዓሣን ፕሮስስ የማድረግ ልምድ ያላቸው)
ሠራተኞች ያሉበት ክፍል ነው። ዓሣው ፕሮሰስ ከተደረገ በኋላ ወደ ሚቀጥለው ክፍል ይገባል፤ ይታሸግና ማቀዝቀዣ ( ፍሪጅ) ውስጥ ይቀመጣል።
ከጋምቤላ ክልል ወደ አዲስ አበባ እስኪላክ ድረስ ራሱን የቻለ አንድ ትልቅ ማከማቻ አለው። ማቀዝቀዣ (ፍሪጅ) ሲባል በተለምዶ በየቤታችንን የምንጠቀመው አይነት አይደለም። ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት በአይነቱ ለየት ያለ ነው። ዓሣ በጣም በቀላሉ ሊበላሽ የሚችልበት ሁኔታ አለ፤ አሁን ሥራ ላይ የዋለው ማቀዝቀዣ ዓሣው የተፈለገውን ያህል ጊዜ ቢቆይ እንዳይበላሽ ማድረግ የሚያስችል ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ነው። መብራት እንኳን ቢጠፋ የራሱ የሆነ አውቶማቲክ ጀነሬተር ያለው ነው፤ ወዲያውኑ ራሱ የሚያበራ መብራቱ ሲጠፋ ደግሞ ራሱ የሚያጠፋ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ከአበቦ ወረዳ እና ከኢታንግ ወረዳ እንዲሁም ሌሎች ሳይቶች ሲገነቡ ከእነዚያ ሳይቶች ዓሣዎችን የሚያመጡ የራሳቸው ማቀዝቀዣ ክፍል የተገጠመላቸው ባጃጆች አሉ። ስለዚህ ከሳይቶቹ ወደዋናው ማዕከል ስናመጣ ዓሣው በአየር ሁኔታ ወይም በሌላ ምክንያት ይበላሻል የሚል ስጋት አይኖርም።
አዲስ ዘመን፡- ፕሮጀክቱ ከተመረቀ በኋላ ምን ዓይነት ተግባራት እያከናወነ ይገኛል?
አቶ ያሲን፡- አሁን ወጣቶችን በማኅበር እያደራጀን ነው። አስጋሪዎች የራሳቸው ማኅበር አላቸው። የሚያቀናብሩትም /ፕሮሰስ የሚያደርጉትም/ የራሳቸው ማኅበር አላቸው፣ መረብ የሚሠሩ ወጣቶችም እንዲሁ ማኅበር አላቸው። በሦስቱም ሳይቶች እነዚህን ወጣቶች እያደራጀን እንገኛለን።
አሁን ሥራ ያልተጀመረበት ዋና ምክንያት ወጣቶቹ ዓሣውን ለማስገር የሚጠቀሙባቸው መሣሪያዎች ዘመናዊ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ግንዛቤ ብቻ ሳይሆን እውቀትም ስለሚያስፈልግ ነው። በየሳይቱ ምርጫው ተካሄዷል። ፕሮስስ የሚያደርጉ፣አስጋሪዎችና መረብ የሚሠሩ ወጣቶች ተለይተዋል። አንደኛ በማኅበራት ማደራጃ መስፈርት መሠረት እያንዳንዱ ማኅበር ስታንደርዱን የጠበቀ ማኅበር እንዲሆን ይደረጋል። ሁለተኛ ለእነዚህ ዘመናዊ ማሽኖች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ስለሚያስፈልግ ሥልጠና በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል።
በሦስቱ ሳይቶች መጀመሪያ ፕሮጀክቱን ሥራ ለማስጀመር ለ550 ወጣቶች የሥራ እድል ይፈጠራል። እነዚህ ወጣቶች በማኅበር ተደራጅተው ሕጋዊ ሆነው የሚገቡ ናቸው። ሆኖም ግን ማንኛውም ሰው በግሉ ዓሣ አስግሮ እዚያ አምጥቶ መሸጥ ይችላል። ዓሣው ጤንነቱ የተጠበቀ መሆኑና ትክክለኛ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ይወሰዳል፤ በተቀመጠው አሠራር ውስጥ አልፎ ለሽያጭ ይቀርባል።
ሁሉም በጥናት የተካተቱት ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ሲገቡ ደግሞ ሰነዱ ላይ እንደተቀመጠ በመደበኛ በማኅበር ለሚደራጁና በግላቸው ለሚያሰግሩ አምስት ሺ ሰዎች የሥራ እድል ይፈጥል ይላል:: አሁን ላይ ለዓሣ አስጋሪዎች፣ ለፕሮሰሰሮች እና ለመረብ ሠሪዎች ለእያንዳንዱቸው ራሱን የቻለ የአንድ ሳምንት ስልጠና 70 በመቶ በተግባር እና 30 በመቶ በንድፈ ሀሳብ/ቲዎሪ/ ሥልጠና ከሰጠን በኋላ እውቅና ያለው ሥራ ይጀመራሉ። አሁን ማሽኖችን ለመጠቀም ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ፕሮጀክቱ በዓመት ምን ያህል ዓሣ ማምረት ይችላል?
አቶ ያሲን፡– አሁን በዓመት 25 ቶን ዓሣ ሊያመርት እንደሚችል ይገመታል። ገና ጅማሮ ስለሆነ በጠበቅነው ልክ ላይገኝ ይችላል። ነገር ግን ከፍተኛ ድርሻ ያለው ነው ብለን እንወስዳለን። የዓሣ ምርቱ እየጨመረ እንደሚሄድ ምንም ጥርጥር የለውም። ሰው እየለመደው ሲሄድ ፍላጎቱም እየጨመረ ሲመጣ የዓሣ መጠኑ ከፍተኛ ስለሆነ ምርቱም እየጨመረ እንደሚመጣ ምንም አያጠያይቅም።
በምርቃት ወቅት የተወሰኑ ወጣቶች ለአምስት ቀናት ሥልጠና እንዲወስዱ በመደረጉ ዓሣ ከማስገር ጀምሮ ሁሉንም ሂደቶች በተግባር ያሳዩበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በዚህ ወቅት ጋምቤላ ክልል ጉር የሚባል ዓሣ አለ፤ ይህን ዓሣ ወጣቶች ናቸው ያመጡት። አንዱ 160 እስከ 170 ኪሎግራም የሚመዝን በመሆኑ በዕለቱ የተገኙ ሰዎች በእጅጉ ተገርመውበታል። ይህን ዓሣ ሁለት ሰዎች በእንጨት ተሸክመው ነው ያመጡት። የዓሣ ገበያውም ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ይታወቃል። በዓሣ ማስገር ላይ የሚሠማሩ ወጣቶች ያላቸውን አቅም አሟጠው ሊጠቀሙ እንደሚገባ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- አሁን የተፈጠረው የገበያ ትስስር ምን ይመስላል?
አቶ ያሲን፡-የገበያ ችግር ያጋጥመናል ብለን አናስብም። ጉዳዩን በተለያዩ ዜናዎች የሰሙ አካላት ዓሣውን ወደ አዲስ አበባ ለመላክ የጋራ አሠራር እንፍጠር እያሉ ነው። በዘርፉ ለመሠማራት የሚፈልጉ አካላት በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ የሚጠይቁ ሰዎች አሉ።
ሁሉም ሳይቶች ሥራ ጀምረው የማመላላሻ መኪናዎች ተገዝተው ወደ ሥራ እስከሚገቡ ድረስ የአቅም ውስንነት ሊኖር ስለሚችል የገበያ ትስስሩን ሊፈጥሩ የሚችሉ ቀና አስተሳሰብ ያላቸው ባለሀብቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ በጋራ መሥራት የሚያስችል አማራጭ አለ።
አዲስ ዘመን፡- ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ ምን ይጠበቃል ?
አቶ ያሲን፡– እነዚህን የፕሮጀክት ሳይቶች ስናጠናቅቅ ሦስት ዋና ዋና ተግባራት ይከናወናሉ። የመጀመሪያው ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር ነው። የጋምቤላ ወጣቶች ከልጅነታቸው ጀምሮ ዓሣ ማስገር ባሕላቸው ነው። ሁለተኛው አዲስ አበባ ያሉ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች በምንም አይነት መመዘኛ ቢታይ ጋምቤላ ካለው ዓሣ የማይበልጥ ዓሣ በውጭ ምንዛሪ ያስገባሉ። ይህንን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት ነው። የሀገራችን ምርት የሆነውን ዓሣ ለእነዚህ ሆቴሎች ማቅረብ ከቻልን የውጭ ምንዛሪ እንዲቀር ማድረግ እንችላለን።
ሦስተኛው የጋምቤላ የመሬት አቀማመጥ በጣም አመቺ ነው። ሜዳ ነው፤ ወጣ ውረድ የለውም። ስለዚህ ግራና ቀኝ ግንባታ በማካሄድ የዓሳ መጠንን መጨመር ይቻላል። ይህንን የምናደርገው ለሀገራችን ሆቴሎች ዓሣ ለማቅረብ ብቻ አይደለም፤ ወደ ውጪ በመላክም የውጭ ምንዛሪ በማግኘት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ድርሻውን የሚወጣ ሀብት አድርገን ለመጠቀም እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፡-ፕሮጀክቱ የሚጠቀመው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንደመሆኑ መጠን እነዚህ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ወደሥራ በማስገባት ረገድ ምን ታስቧል?
አቶ ያሲን፡- የዘመናዊ ማሽን ኦፕሬሽን እክል ሊያጋጥም ይችላል። ምክንያቱም አሁን የሚሰጠው ሥልጠና በጥልቀት የሚሰጥ አይደለም፤ ለጥቂት ቀናት ነው የሚሰጠው። ጊዜ ከማጠሩና ከመሣሪያዎቹ አዲስነት አንጻር የተወሰኑ ክፍተቶች ሊያጋጥሙን ይችላሉ፤ የሥልጠናው ጊዜ ውስን ስለሆነ ማሽኑን ኦፕሬት ሲያደርጉ የተወሰነ ችግር ሊያጋጥም ይቻላል። የጎላ ችግር እንዳይገጥም በሚል ወጣቶቹ ሥልጠና ሳይሰጣቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ አይደረግም።
አንደኛው የተሻለ ግንዛቤ ያላቸው ብቻ በትምህርት ደረጃቸውም ከዚያ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ወጣቶችን እናካትታለን የሚል ሀሳብ አለን። ሁለተኛው ማሽኖችን ያስገባው አካል ተበላሸ ሲባል ለመጠገን ወይም ለማስተካከል ቃል የገባ ስለሆነ ያግዘናል የሚል እምነት አለ።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻም ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለዎት?
አቶ ያሲን፡- የጋምቤላ የዓሣ አቅም ዛሬ የተፈጠረ ሳይሆን የቆየ ነው። እስካሁን በአቅም ውስንነት የተነሳ ሳናስተዋውቀው በመቆየታችን ሀብት ባክኗል። ይህን ሀብት አልምቶ በመጠቀም በኩል አሁን በጣም ከፍተኛ ፍላጎት አለ። ፍላጎቱ በጨመረ ቁጥር የገበያ ትስስሩ እየሰፋ ይሄዳል። በዘርፉ የሚሠማሩ ወጣቶች ከፍተኛ የኢኮኖሚ መሠረት ያገኛሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። የዓሣ ሀብቱ በክልልና በሀገር ደረጃ ለኢኮኖሚው የበኩሉን ሚና ሊያበረክት የሚችል ስለሆነ አቅምና ቀና አስተሳሰብ ያላቸው ቢደግፉ እኛም፣ ማኅበሩም፣ ክልሉም፣ ሀገርም ተጠቃሚ መሆን እንችላለን የሚሉ ግለሰቦች ካሉ ከኛ ጋር አብረው እንዲሠሩ ጥሪ አቀርባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልሱ ላደረጉልን ትብብር አመሰግናለሁ።
አቶ ያሲን፡– እኔም አመስግናለሁ።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2015 ዓ.ም