ኢትዮጵያ በግብርናው መስክ ምርትና ምርታማነት እያደገባት ትገኛለች። ግብርናው የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት የጀርባ አጥንት መሆኑ ቀጥሏል፤ ዘርፉ የሀገሪቱን የምግብ ፍጆታ ከመሸፈን አልፎ፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝት በኩልም ተጠቃሽ መሆኑን ቀጥሏል።
ባለፈው በጀት ዓመት ቡና አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር በማስገኘት ከዘርፉ መሪ የሆነበትን ሁኔታ ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል። የሆርቲካልቸር ዘርፍም በተመሳሳይ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ችሏል። በተያዘው 2015 በጀት ዓመት ባለፉት ሰባት ወራትም እነዚህ ዘርፎች በውጭ ምንዛሪ ግኝታቸው ተጠቃሽ መሆን ችለዋል።
በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እየተመዘገበ ያለው ውጤትም ሌላው የዘርፉ ለውጥ ማሳያ ነው። ባለፈው በጀት አመት 26 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በበጋ መስኖ ማግኘት ተችሏል፤ ዘንድሮ ይህን አኃዝ 52 ሚሊዮን ለማድረስ እየተሠራ ነው።
ሀገሪቱ በስንዴ ልማት ላይ ክረምት ከበጋ እያከናወነች ያለችው ውጤታማ ተግባር ሀገራዊ የስንዴ ፍጆታዋን በራሷ እንድትችል አድርጓል፤ ይህን ተከትሎም ስንዴ ከውጭ ማስገባት አቁማለች። ስንዴ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ችላለች።
በግብርናው ዘርፍ ሃገሪቱ ይህን ያህል ርቀት መጓዝ ብትችልም፣ በሀገሪቱ እየተመላለሰ ከሚከሰት የድርቅ አደጋና ከሚያስከትለው ችግር መውጣት ግን አልቻለችም። ዛሬም ድርቅ የአርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ሕይወት እየፈተነ ይገኛል። ባለፈው ዓመት በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ ዞኖች የተከሰተው ድርቅ አርሶ እና አርብቶ አደሮችን በእጅጉ ፈትኗል፤ የእነዚህ ወገኖች ለጋሽ እጆች ለእርዳታ ፍለጋ ተዘርግተዋል፤ እንደ ዓይናቸው ብሌን የሚመለከቷቸውን ከብቶቻቸውን ዓይናቸው እያየ ድርቁ ጨርሶባቸዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንስሳት ማለቃቸውን ነው መረጃዎች ያመለከቱት።
ዘንድሮም በተመሳሳይ በሶማሌ፣ ደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች ድርቁ ተከስቷል። ድርቁ በተለይ የኦሮሚያ ክልሉን የቦረና ዞን ክፉኛ መትቶታል። በዚህም ምንም እንኳ በድርቁ የሞተ ሰው ባይኖርም የዞኑ ሕዝብ ለከፍተኛ ጉዳት መዳረጉን ተከትሎ እርዳታ ጠባቂ ለመሆን ተገዷል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንስሳቶቹም አልቀዋል።
በሃገሪቱ ለሚከሰተው ድርቅ ምክንያቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታየው የአየር ንብረት ለውጥ መሆኑ ይታመናል። ይህን ችግር መፍታት የሚቻለው በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄድ ዘላቂነት ያለው ርብርብ ነው።
ይህ ችግር በሰዎችና በእንስሳቶቻቸው ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት በመቀነስ በኩል ግን መሥራት ይቻላል፤ በድርቅ በተደጋጋሚ የተጠቃችው ኢትዮጵያ በዚህ በኩል ተሞክሮውም አላት። በአካባቢ ጥበቃ ወይም ተፋሰስ ልማትና በመሳሰሉት ላይ መሥራት አንዱ መፍትሔ ተደርጎ ሲሠራበት ቆይቷል። አርሶ አደሮችን በዚህና በሌሎች የሴፍቲኔት መርሐ ግብሮች በማሳተፍ ተጨማሪ ገቢ ሊያገኙባቸው የሚችሉ ሥራዎችን እንዲሠሩ በማድረግ ጥሪት እንዲያፈሩ ሲሠራ ቆይቷል። ይህን ተከትሎም በአካባቢዎቹ በአርሶ አደሮች ሕይወት ላይም ለውጥ ማምጣት የተቻለባቸውም ሁኔታዎች እንዳሉ ይታወቃል።
አሁን ድርቁ እንዲከሰት ያደረገው ምክንያት ካለፉት ድርቅ መነሻዎች ይለያል፤ ድርቁ የተከሰተው ላለፉት ሦስትና ከዚያ በላይ ዓመታት በቦረና አካባቢ መጣል የነበረበት ዝናብ ሳይጥል በመቅረቱ ነው። እንዲህ በተከታታይ ጊዜ ዝናብ በሚጠፋበት ሁኔታ የሚከሰተው ድርቅ የከፋ ችግር ሊያደርስ እንደሚችል አሁን በቦረና ዞን ከደረሰው ድርቅና ካስከተለው ጉዳት መገንዘብ ይቻላል።
ድርቅ የሚያስከትለውን ችግር የሚቋቋም ጥሪት ቢቋጠር እንኳ እንዲህ አይነቱ ድርቅ የሚያስከትለውን ችግር መመከት ይከብዳል። ሌላ ሰፊ ሥራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ችግሩ ያመለክታል።
ቀጣዩ መፍትሔውም ከእስከ አሁኖቹ መፍትሔዎች የሰፋ መሆን ይኖርበታል። እንደሚታወቀው፤ ሀገሪቱ ለእርሻ ሊውል የሚችል በቂ መሬት፡ የሰው ሀብትና የውሃ አቅም በሚገባ አላት። እነዚህን አቀናጅቶ በዘላቂነት በመሥራት ድርቅ እየተመላለሰ ሊያደርስ የሚችለውን ችግር መቀነስ ይቻላል።
በሀገሪቱ ለእርሻ ሥራ ሊውል ከሚችለው መሬት ከፍተኛ መጠን ያለው መሬት እየታረሰ አይደለም። ሀገሪቱ በመኸርም በመስኖም ሊለማ የሚችል መሬት በተለይ በቆላማ አካባቢዎች ላይ በስፋት አላት፤ ለእርሻ ሥራ ከዋለው መሬትም የሚገኘው ምርት ሲታሰብም የሚጠበቀውን ያህል አይደለም።
ለመስኖ ልማት ሊውሉ የሚችሉ ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች፣ ሐይቆችና የከርሰ ምድር ውሃ ባለጸጋም ናት። ሰፊ የክረምት ወቅት ያላት እንደመሆኑም በቂ የዝናብ ውሃም አላት።
በሰው ሀብት በኩልም በግብርና ሥራው ላይ ካለው ማኅበረሰብ በተጨማሪ ሰፊ ወጣት አላት።
ሥራ ያለው ከተማ ብቻ አድርገው እየተመለከቱ ወደ ከተማ እየፈለሱ ያሉ ብዙዎች ናቸው። ይህ ሁኔታ መቀየር አለበት። ድርቅ የሚያስከትለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚከናወኑ የተለያዩ ተግባሮች እንዳሉ ሆነው ሀገሪቱ ያላትን ሰፊ መሬት፣ የሰው ሀብትና ውሃ አቀናጅቶ መሥራት ላይ ማተኮር ይገባል።
ሀገሪቱ ሊታረስ የሚችል በቂ መሬት፣ ለመስኖ አገልግሎት ሊውሉ የሚችል በቂ የውሃ ሀብትና በቂ የሰው ኃይል አላት ማለቱ ብቻውን የትም አያደርስም። እነዚህ ሀብቶች ዜጎችን ድርቅ ከሚያደርሰው ጉዳት እንዲታደጉ ከዚያም አልፎ የሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት ምሰሶ መሆን አንዲችሉ አድርጎ መሥራት ያስፈልጋል። ወጣቶቹን በማሰልጠን፣ መሬት በማዘጋጀት በዘመናዊ ግብርና ሊሠማሩ የሚችሉበትን ዕድል መፍጠር ያስፈልጋል።
ይህን ማድረግ እንደሚቻል በበጋ ስንዴ መስኖ ልማት የተከናወነው ተግባርና የተገኘው ውጤት ሁነኛ ማሳያ ነው። ሀገሪቱ ስንዴ በበጋ ማምረት ችላለች። የማምረት አቅሙም በየዓመቱ እየጨመረ ነው። ልማቱ የተካሄደው በመኸርና በበልግ ወቅት ሥራ ላይ በሚውለው ማሳ ላይ ነው።
ሀገሪቱ በግብርናው መስክ ለውጥ ያሳየችው በትንሽ ቦታ፣ የውሃ አቅምና የሰው ኃይል ላይ በመሥራት ነው። ይህን ልማት በሀገሪቱ ድንግል መሬቶች ላይ ማካሄድ ቢቻል ውጤታማነቱም እጥፍ ድርብ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም። ይህ ሲሆን ድርቅ ሊያስከትል የሚችለውን ችግር በዘላቂነት መቋቋም ይቻላል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2015 ዓ.ም