የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም በብዙ የዓለማችን ሀገራት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው በጥናት ተረጋግጧል። በሀገራችን ያለውን ነገር ብናይ ‹‹እውነትም እፎይታን የሰጠ ተግባር ነው›› ማለታችን አይቀርም። ምክንያቱም ጠዋት በልተው ማታ የማይደግሙ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ የሚመገቡበትን እድል አግኝተዋል። በ2008 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ለችግሩ ተጋላጭ በሆኑ የቅድመ መደበኛና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ የተደረገው ይህ የትምህርት ቤት ምገባ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው።
ምገባው የተጀመረበት ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም መኖሩ ግድ የሚለው ክስተት እንደ ሀገር በመፈጠሩ ነበር። ይህ ክስተት በ2008 ዓ.ም የተከሰተው ድርቅ ሲሆን፤ በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጫናን ፈጥሯል። ተጽእኖ ወደ 2009 ዓ.ም ተሸጋሪም ነበር። እናም ይህንን ታሳቢ በማድረግ ወላጆች ለልጆቻቸው የትምህርት መሳሪያዎችን በማቅረብና በመመገብ ወደ ትምህርት ቤት የመላክ እድላቸው ዝቅተኛ ነውና ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ተማሪዎቸ የምግባ ፕሮግራሙን ተግባራዊ እንዲሆን ተወስኗል።
ይህንን አላማ ለማሳካት በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤት መሻሻል ፕሮግራም ዳይሬክቶሬት የማስተግበሪያ መመሪያ አውጥቷል። የማስተግበሪያ መመሪያው የአስቸኳይ ጊዜ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራምን እንዴት መከወን ይችላል የሚለውን የሚመልስ ሲሆን፤ ከትምህርት ሚኒስቴር እስከ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች ኃላፊነት የሚሰጥ ነው። በተጨማሪም መመሪያው በክልሎች መካከል የአሰራር አቅጣጫ እና ግልጸኝነት ለመፍጠርና በስራ ላይ ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት እንዲያስችላቸው አቅጣጫ የሚጠቁም ነው። ከምግብ እቅድ አዘገጃጀት ጀምሮ እስከ ምገባው ድረስ የተሰሩ ስራዎችን በአግባቡ አደራጅቶ ለመያዝ፣ ለመከታተል ፣ ለመገምገምና በወቅቱ ሪፖርት ለማድረግም ያግዛል የተባለለት ነበር።
የአስቸኳይ ጊዜ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራሙ ዋና ዓላማ በ2007 ዓ.ም በኢሊኖ ተጽእኖ በተከሰተው ድርቅ የምርት መቀነስ ችግር በተከሰተባቸው በስምንት ክልሎች ውስጥ ለሚገኙ ችግሩ በከፍተኛ ደረጃ በተባባሰባቸው 202 ወረዳዎች ለሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን የሚያግዝም ነው። በ2009 ትምህርት ዘመን የአስቸኳይ ጊዜ ትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ተግባራዊ በማድረግ በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ሊያደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተጽእኖ በመቀነስ የትምህርት ጥራትንና ተሳትፎን እንዲሻሻል ማስቻልም ነው፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራሙ ተማሪዎች ምግብን ከአካባቢው በህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች ከተደራጁ አርሶ አደሮችና ምርት ካለባቸው አካባቢዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በክልል ትምህርት ቢሮ እና በዞን ትምህርት መምሪያ ደረጃ በመግዛት የምግብ እጥረትና ዝቅተኛ የትምህርት ተሳትፎ ባለባቸው ወረዳዎችና ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ተማሪዎች ምግብ በጊዜ በማቅረብ ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡
ፕሮግራሙ በጤናው፤ በግብርናውና በትምህርት ሴክተሩ መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል የተባለለትም ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ባለፈው ሳምንት የተከበረውን የአፍሪካ የትምህርት ቤት ምገባ ቀንን ጉዳይ እናንሳ። ስምንተኛው አገር በቀል የአፍሪካ የትምህርት ቤት ምገባ ቀን ሲከበር ‹‹የሀገር ውስጥ የምግብ ፍጆታ ግዢ ስርዓትና ቀጠናዊ የአቅርቦት እሴቶችን በማሳደግ ሀገር በቀል የአፍሪካ ትምህርት ምገባን በማረጋገጥ ትምህርት ማሻሻል›› በሚል መሪ ሀሳብ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነበር። ይህ ደግሞ ሁለት ነገሮችን እንደ አህጉር ብሎም እንደሀገር ለማረጋገጥ ያስችላል።
የመጀመሪያው ጉዳያችን ትምህርት ነውና የምግብ አቅርቦቱ እንዲሳለጥና ተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ እንደልባቸው እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ሙሉ ትኩረታቸው ትምህርታቸው ላይ እንዲያደርጉ ያግዛቸዋል። ይህ አይነት አሰራርን እንደአፍሪካ ለመከተል አቅጣጫ መቀመጡም ሀገራት ግብዓቶችን በተሻለ ዋጋ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ምክንያቱም ሀገር በቀል ምርቶችን ከአምራቹ በመቀበል የሚስተናገዱበት ነው። የአፍሪካ የትምህርት ቤት ምገባ ቀን በአፍሪካ ህብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ በተከበረበት ወቅት የአፍሪካ ህብረት የትምህርት ሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኮሚሽነር ኮሚሽን ፕሮፌሰር ሙሀመድ ቤልሆሲን እንዳሉት፤ በአንድ ላይ ካልሰራን በተናጠል የምናደርገው ነገር ውጤታማ አያደርገንም ነው። ስለሆነም መተባበር ይኖርብናል። ለትብብራችን መጠናከር ደግሞ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠናውን ሥራ መጠቀም እጅግ አስፈላጊ ነው። በብዙ ነገር ይጠቅመናል።
በ2016 የአፍሪካ ህብረት በአስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የአፍሪካ ትምህርት ቤት ምገባ ወደ ሥራ እንደገባ ያነሱት ፕሮፌሰር ሙሀመድ፤ የምግብ ፍጆታን ከአርሶ አደሩ በመግዛት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መስመር መዘርጋት አንዱ አላማው ነው። ይህንን ያደረገበት ምክንያት ደግሞ የመጀመሪያው ተማሪዎችን በተሻለ መልኩ ተጠቃሚ ለማድረግ ሲሆን፤ ሁለተኛው የሥራ እድል ለመፍጠር ነው። በዚህም እስካሁን ባለው መረጃ በአፍሪካ 300 ሺ የሚደርሱ ዜጎች በትምህርት ቤት ምገባው የሥራ እድልን አግኝተዋል። የኮቪድ 19 የትምህርት ምገባውን ቢያስተጓጉለውም 34 የሚሆኑ የአፍሪካ ሀገራት የትምህርት ቤት ምገባውን የሚያከናውኑ ሲሆን፤ በተለይ ደግሞ ሀገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባው የእነርሱ መለያ እንደሆነም በመድረኩ ተነስቷል። ለዚህ በአብነት የምትጠቀሰው ደግሞ ብራዚል ስትሆን፤ የብራዚል አምባሳደር በኢትዮጵያ ጃንዳራ ፌረር ዶሳንቶስ በክብረ በዓሉ ላይ እንዳሉት፤ የትምህርት ቤት ምገባ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጥ፣ የአመጋገብ ስርአትን የሚጠብቅ እንዲሁም የትምህርት ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎችን የሚደግፍ ነው። በዚህ ዙሪያ ብራዚል የዳበረ ተሞክሮ አላት። ስለዚህም ይህንን ልምዷን ለአፍሪካ ሀገራት ለማጋራትና ለመደገፍ ቁርጠኛ ነች።
ሀገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባ እንደ አህጉር ብዙ ነገሮችን የለወጠ ነው የተባለ ሲሆን፤ 2021 እና 2022 ሪፖርት እንደሚያመላክተው፤ እንደ አፍሪካ 65 ነጥብ 9 ሚሊዬን የሚሆኑ ተማሪዎች በምገባው ተጠቃሚ ሆነዋል። አምስት ነጥብ ሶስት ሚሊዬን የሚጠጉ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ደግሞ በኢትዮጵያ ተጠቃሚ የሆኑ ናቸው። በዚህ የምገባ ፕሮግራም ላይ የዓለም ምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ 82 የሆኑ አጋር ድርጅቶች የሚሳተፉ ሲሆን፤ የአፍሪካን የትምህርት ቤት ምገባን ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት ይሰራሉ። ነገር ግን ይህ ወጪ በቂ አይደለም። ምክንያቱም ብዙኃኑ በአፍሪካ ሀገራት ድጋፍ እየተሰራበት በመሆኑ ወጪው ከአቅማቸው ጋር ይያያዛል። ከፍተኛ ወጪ ከተጠየቀ ሊቆምም የሚችልበት ሁኔታ አለ። እናም ሀገር በቀል ላይ የሚሰራው ሥራ ከዚህ ባሻገር ሊታይ ይገባል። ማስፋቱ ላይም እንደአህጉር ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋልም ተብሏል።
የትምህርት ቤት ምገባ በተለይም በሀገር በቀሉ ላይ ትኩረት ያደረገ ምገባ መኖሩ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት። አንደኛው ተማሪዎች ትምህርታቸውን በትክክል እንዲከታተሉ እና ተሳትፎአቸውም እንዲጨምር ያደርጋል። በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በአካባቢያቸው የተለመዱ፣ ለጤና ተስማሚ እና አካል ገንቢ የሆኑ ምግቦችን እንዲመገቡ ያስችላቸዋል። ይህ አይነት ምገባ አነስተኛ ገበሬዎችን የማምረት አቅም ማሳደግ ላይም ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። የገበያ ዕድልም የሚፈጥር ነው። ህብረተሰቡ በትምህርት ቤት ጉዳዮች ወይም ክንውኖች ውስጥ በበቂ ሁኔታ እንዲሳተፍም ያስችላል። ለገጠር ድሀ ሴቶችና ወጣቶች የስራ እድል በመፍጠርም በኩል ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። በአጠቃላይ በጥሩ የአመጋገብ ሥርዓት ተማሪዎች ጤናማ እንዲሆኑ፤ ትምህርታቸውን ሳያቋርጡ እንዲከታተሉና በርትተው እንዲማሩ በማስቻል ፕሮግራሙ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋልም ተብሏል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙትና በቀኑ መከበር ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፤ ሀገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባ የተማሪዎችን ጤንነት ለመጠበቅና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከሚያግዙ ተግባራት ውስጥ አንዱ ነው። እንደ አህጉርም ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የሚደግፍ መሆኑ አያጠያይቅም። ስለሆነም ችግር ፈችነቱን ለማየት በተደረገ ጥናትም መጠነ ማቋረጥን በማስቀረት፣ መጠነ መድገምን በመቀነስ፣ የተማሪዎችን ውጤት በማሻሻል በአጠቃላይ ለትምህርት ጥራት መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለውና አጠናክሮ መቀጠሉ ሥራችንን ያሳካዋልም ሲሉ ተናግረዋል።
እ.አ.አ በ2030 በሁሉም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የምገባ መርሀ ግብር በማስፋት ቢያንስ አንዴ የምገባ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ የትምህርት ቤት ምገባ የተማሪዎችን የምግብና የጤና ሁኔታ በማሻሻል ጉልህ አስተዋጽኦ ያደርጋል። በትምህርት ዘርፉ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተጽእኖ በመገምገም ሀገራችን እየተገበረች ላለው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተለይም ደግሞ የትምህርት ሴክተር ልማት ፕሮግራም ላይ ጉልህ ሚናን ይጫወታል። እናም ሥራው እንዲጠናከር ሁሉም የበኩሉን ማበርከት እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል።
ሌላኛዋ ተሳታፊና በዓለም አቀፍ ደረጃ በዚህ መርሃ ግብር ሽልማትን የተቀበሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ሲሆኑ፤ በወቅቱ እንዳሉት፤ ይህ የምገባ ስርዓት ለአዲስ አበባ ከተማ የተለየ ትርጉም ያለው ነው። ምክንያቱም 700 ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎችን ተጠቃሚ አድርጓል። በእርግጥ እንደ አዲስ አበባ የምገባ መርሃ-ግብሩ የጀመረው በ2011 ዓ.ም ነው። በትንሽ ተማሪዎች ለያውም በተቸገሩት ብቻ ላይ ትኩረቱን ያደርግ ነበር። አሁን ግን ችግሩ ብዙዎች ላይ የሚታይ በመሆኑ አስፍቶ በከተማ ደረጃ ከ700 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል። በሂደቱም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል። ይህ ደግሞ አዲስ አበባን በዘርፉ የሚሰጠውን ዓለም አቀፍ ሽልማት ማሸነፍ እንድትችል አድርጓታል።
‹‹ይህ የምገባ ሥራ ሲጀመር ለተማሪዎቻችን ምግብ ብቻ ሳይሆን ፍቅርንም እየሰጠን ሀገሩን የሚወድ ጠንካራ ዜጋ የማፍራት ሥራንም ለማከናወን ነው›› ያሉት ከንቲባዋ፤ ትላንት ስንጀምረው ቀላል ይመስል የነበረው የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ዛሬ ላይ አድጎ እና ዓለም አቀፍ እውቅናን አግኝቶ የተለያዩ ሀገራት ልምድ የሚወስዱበት ሥራ በመሆኑ እጅግ ደስ ብሎኛል። ከዚህ በኋላ ትውልድ የመገንባት ሥራችንን አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል። ስለዚህም ልዩ ትኩረታችን ለተማሪዎቻችን ምግብ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ፍቅርንም መስጠት ላይ እናደርጋለን። ሀገሩን የሚወድ ጠንካራ ዜጋ የማፍራት ሥራችን መቼም አይቋረጥም ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። አዎ ሰውን መመገብ ሀገር ወዳዶችን መፍጠር ነው። ምክንያቱም በርሃባቸው ሳይሆን በሥራቸው የሚያስታውሷትን ልጆቿን እናፈራለንና። ስራው በዘርፉ ያሉ ሰዎች ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነውና ሁላችንም በትምህርት ቤት ምገባው ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ጉዳዮች ላይ መሳተፍ ይገባናል በማለት ለዛሬ የያዝነውን ሀሳብ ቋጨን።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2015 ዓ.ም