ደብረ ታቦር፡- በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ሲካሄድ የቆየው የመጀመሪያው “መጻህፍት የእውቀት ገበታ መዛግብት የታሪክ ትውስታ” የውይይት መድረክ ተጠናቀቀ።
ትኩረቱን የመጻህፍት ቅርሶች እና የታሪክ መዛግብት አያያዝ ላይ ያደረገው መርሃ ግብር በኢትዮጵያ ብሄራዊ መዛግብት እና ቤተ መጻህፍት አገልግሎት ትብብር በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ላለፉት ሁለት ቀናት ሲካሄድ ቆይቷል። በመርሀ ግብሩ ቆይታም ኢትዮጵያ የባለ ብዙ መጻህፍት ቅርሶችና የመዛግብት ሀብት ባለቤት ብትሆንም በአግባቡና በሥርዓት ሰንዶ ከመያዝ እንዲሁም ትውልድ እንዲማርባቸው ከማድረግ አንጻር ሠፊ ክፍተት እንዳለ ተመላክቷል።
የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አነጋግረኝ ጋሻው (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ እንደ አገር በቅርስ አያያዝ ዙሪያ ሰፊ ክፍተት ያለባት ሀገር ናት። ስለሆነም ምሁራን እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ከቅርስ ሀብት ልማት ባሻገር ወደ ቱሪዝም ምንጭነት መቀየር ይኖርባችኋል ብለዋል። በዚህ ረገድ የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ብዙ ስራዎችን እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን የመዛግብት እና የጽሁፍ ቅርስ ለማልማትና በተገቢው መንገድ ለመጠበቅ የበጌ ምድር ቤተመዛግብት ማዕከል ከፍቷል ያሉት ዶክተር አነጋገረኝ፤ የደቡብ ጎንደር ዞን በተለይም የደብረ ታቦር አካባቢ እምቅ የጽሁፍ እና የመዛግብት ሀብት ባለቤት መሆኑ እና አዲስ ማዕከል መከፈቱ ለሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እንደ ተምሳሌትነት የሚጠቀስ እንደሆነ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻህፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኑአምላክ መዝገቡ በበኩላቸው፤ አገልግሎት መስሪያቤቱ መረጃዎችንና የሥነ ጽሁፍ ሀብቶችን በዘመናዊ መንገድ ለመጠበቅ ስራዎች እየተሠሩ ነው። ከ አንድ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው አምስት ሺህ 2 መቶ 78 መጻህፍት፤ ለደብረታቦር ዞን ማረሚያ ቤት፣ ለሕዝብ ቤተ መፃህፍት፣ ለመጀመሪያና ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በስጦታ መልክ አበርክቷል። የመጻህፍት ሀብት አያያዝና የመዛግብት ጥበቃ ላይ ትኩረት መደረግ አለበት። የመጻህፍት ስጦታው ወደፊትም የሚቀጥል ይሆናል ያሉት ዳይሬክተሩ የጽሁፍ ቅርሶችንና መዛግብትን መጠበቅ የሁሉም ሃላፊነት ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያን የጽሁፍ ቅርሶች እና የመዛግብት ሀብትን በአግባቡ ለመጠበቅ ከተፈለገ ምሁራኑና የሚመለከታቸው አካላት በልዩ ትኩረት መስራት አለባቸው ነው ያሉት።
እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፤ ከሆነ የኢትዮጵያ ሀብቶች በተለያዩ ምክንያቶች እየተዘረፉ እና እየጠፋ ይገኛሉ፤ ይህንን በዘላቂ መንገድ ለመፍታት የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ የጥንት ዘመን ፈላስፋ ምድር፣ የሥነ ጽሁፍና የድልብ መዛግብት መገኛ ናት ያሉት ዶክተር ሂሩት፤ ይሁን እንጂ በአግባቡ ባለመጠበቃቸውና ባለመልማታቸው ትውልዱ እየተበደለ ይገኛል፤ ሀገርም ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም አጥታለች ነው ያሉት።
ጉባኤው በኢትዮጵያ ሥነ ጽሁፍ ዕድገትና አያያዝ እንዲሁም የመዛግብት ሀብቶችን በሚመለከት ጥናታዊ ጽሁፎችም ቀርበው ውይይት ተካሂዷል።
መሠረት በኃይሉ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2015 ዓ.ም