በወርሃ የካቲት የትግራይ ክልል ታይታይ ቆራሮ ወረዳ አረንጓዴ ለብሳለች። ወደ ቀኝ ዞር ሲሉ የበቆሎና የሽንብራ ሰብል ወደ ግራ መለስ ሲሉ የቲማቲም፣ ጎመንና ሽንኩርት አትክልቶች ይታያሉ። አርሶ አደሮቹ እዚህም እዚያ ማሳቸው ውስጥ ውሃ ሲያጠጡ፣ ሲኮተኩቱና ሲያረሙ ይታያል። እነዚህ ታታሪ አርሶ አደሮች የተፈጠረውን ሰላም ተጠቅመው ዕርዳታ ከመጠበቅ ይልቅ ቶሎ ወደ በጋ መስኖ ልማታቸው ተመልሰው ሽምብራ፣ በቆሎ፣ ሽንኩርት፣ ጎመንና ቲማቲም እየለሙ ናቸው፡፡
ከሽሬ ወደ አክሱም ከተማ ባደረግነው ጉዞ ወቅትም ከ12 እስከ 16 ዕድሜ የሆናቸው ህጻናት የበቆሎ እሸት መንገድ ላይ ቆመው ሲሸጡም አየን። የታይታይ ቆራሪት ወረዳ በመስኖ የለማ ሰፊ ማሳ የሚታይባት ከጦርነት በኋላ የመስኖ ልማት እየተካሄደባት የምትገኝ ምሳሌ የምትሆን ወረዳ መሆኗን ቦታው ላይ ሆነን በአይችን ተመልክተናል። አርሶ አደር ገብረሚካኤል ሀዱሽም በግማሽ ሄክታር መሬት ሽንኩርትና ጎመን ሲያለማ አገኘነው። አርሶ አደሩ ይህን የመስኖ ልማት እንድናካሄድ ያደረገን ሰላም በመፈጠሩ ነው ይላል። በአካባቢው በተከሰተው ጦርነት የእርሻ ልማት ማካሄድ ቀርቶ ቤት ተቀምጦ ማሳለፍም ለሕይወት አስጊ እንደነበር ያስታውሳል። የእርሻ ስራ ከሕይወታችን ጋር የተሳሰረና የተቆራኘ ቢሆንም፣ የሰላም መናጋቱ ከምንወደው ሙያችን ጋር አራርቆናል ሲል ይገልጻል፡፡
ያ ሁሉ ክፉ ጊዜ አልፎ፣ ሰላም ተፈጥሮ ዳግም ወደ መስኖ ልማታችን በመመለሳችን ደስተኞች ነን የሚለው አርሶ አደር ገብረሚካኤል፣ ይህ በሰላም ስምምነቱ የተገኘው ሰላም ወደ ቀደመው ሰላማዊና የተረጋጋ ሕይወታችን እየመለሰን በመሆኑ ልንጠብቀው ይገባል ይላል፡፡ አርሶ አደር ገብረሚካኤል፤ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አርሶ አደሩ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እንደሚያስፈልገው ጠቅሶ፣ የግብርና ባለሙያ ሊደግፈው ይገባል ይላል። እነ አርሶ አደር ገብረሚካኤል ባለፉት ሁለት ዓመታት እነዚህን ነገሮች አላገኙም፤ አሁን ግን ሰላም በመፈጠሩ መንግስት ማዳበሪያም ሆነ ምርጥ ዘር አቅርቦትን እንደሚያሟላልን ተስፋ እናደርጋለን ሲል አርሶ አደሩ ተናግሯል።
ሌላውን አርሶ አደር ፀጋይ በርሄን በበጋ መስኖ ባለማው አንድ ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ማሳው ውስጥ አገኘነው። በዚህ ማሳው ያለማቸውን ሽንኩርት፣ በቆሎ፣ ሽምብራና ጎመን የውሃ መሳቢያ ሞተር ተጠቅሞ ውሃ ሲያጠጣ ተመልክተናል። አርሶ አደሩ የተፈጠረው ሰላም በረከት ይዞለት እንደመጣ ይናገራል፡፡ አርሶ አደሩ በመስኖ ሊለማ የሚችል ሁለት ሄክታር መሬት ቢኖረውም፣ በማዳበሪያና በዘር እጥረት ምክንያት ማልማት የቻለው አንድ ነጥብ ሄክታር መሬቱን ነው። ከሁለት ዓመት በፊት ባለው ሁለት ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት ከፍተኛ ገቢ ያገኘውና ሞዴል አርሶ አደር ተብሎ መሸለሙን የሚናገረው አርሶ አደር ፀጋይ፤ በክልሉ በተከሰተው የሰላም መናጋት የመስኖ ልማቱ መስተጓጎሉን ይገልጻል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት ለመታደግ ቤተሰባቸውን ይዘው አካባቢውን ለቀው ሄደው እንደነበር አርሶ አደሩ ይናገራል። አርሶ አደር ጸጋይ አሁን የተፈጠረውን ሰላም በመጠቀም ከብት በመሸጥ ከነጋዴዎች አንድ ኩንታል ማዳበሪያ በ14 ሺህ ብር ገዝቶ የመሰኖ ልማት ስራውን እንደገና ጀምሯል። የማዳበሪያ ዋጋ መናርና የነዳጅ እጥረትም ለመስኖ ልማቱ ፈታኝ እንደሆነበት ጠቁሞ፣ የማዳበሪያ ዋጋ ባያሻቅብ ኖሮ አሁን በመስኖ ባለማው መሬት ላይ ከሚያገኘው ምርት የተሻለ ያገኝ እንደነበርም ይገልጻል፡፡ አንድ አርሶ አደር ከብቱን የሚሸጠው ሌላ አማራጭ ሲያጣ ነው የሚለው አርሶ አደሩ፤ ጥረን ግረን ካመረትነው አብዛኛውን የሚወስደው የማዳበሪያ ዋጋ ነው፤ ማዳበሪያ አቅርቦት በማሟላት ረገድም መንግስት ድጋፍ ቢያደርግልን የተሻለ ለማልማት ብርታት ይሆነናል ነው ያለው። ከዚህ አኳያም ማዳበሪያና የነዳጅ እጥረት ለመስኖ ልማታቸው ችግር መፍጠሩን ጠቅሶ፣ መንግስት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቋል።
ሰላም ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለእንስሳቱም፣ ለስነ ምዳሩም፣ ለእጽዋቱም ያስፈልጋል የሚለው አርሶ አደሩ፤ አሁን የተፈጠረውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ አርሶ አደሩ፣ ነጋዴውና ተማሪው ጠብቆ ሊይዘው ይገባል ብሏል። ሰላም ባይኖር ኖሮ አሁን ነጋዴውም አርሶ አደሩም፣ የሕዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎችም ስራቸውን እንደገና መጀመር አይችሉም ነበር፤ ለከፋ ችግርም እንጋለጣለን፤ ዳግም ይህ እንዲሆን ስለማንፈልግ ሁላችንም ሰላማችንን ልንጠብቅ ይገባል ሲሉ አርሶ አደር ፀጋይ መልዕክቱን አስተላልፏል። ሽምብራና በቆሎ በመስኖ እያለሙ ያገኘናቸው አርሶ አደር ስዩም ወልደጸዮንም የአርሶ አደር በርሄ ሀሳብን ይጋራሉ። እሳቸውም ያላቸውን አንድ ሄክታር መሬት በመስኖ የማልማት ስራቸውን እንደገና ጀምረዋል። ይህም የሆነው ሰላም በመፈጠሩ ነው። ‹‹ከዕርዳታ ለመላቀቅ ይኸው የመስኖ ስራችንን ዳግም ጀምረናል›› የሚሉት አርሶ አደሩ፤ የዕርዳታ እህል ከመጠበቅም አምርቶ እንደመመገብና ገበያ አውጥቶ እንደመሸጥ የሚያስደስት ነገር የለም ነው ያሉት፡፡
ሰላም፣ ሰላም፣ ሰላም እያልን ሰላም ተፈጥሮልናል የሚሉት አርሶ አደር ስዩም፤ አሁን ከእኛ የሚጠበቀው ጠንክረን ሰርተን ምርታችንን ማፈስና ለገበያ ማቅረብ ነው ሲሉ ይገልጻሉ። ይህን ለማድረግ ማዳበሪያና ነዳጅ መሰረታዊ ጉዳይ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ለእዚህም የመንግስት ድጋፍ አስፈላጊና ወቅታዊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አሁን መጪው የመኸር ወቅት በመሆኑ ከአሁኑ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ካልቀረበለት አስቸጋሪ ነው የሚሉት አርሶ አደሩ፤ መንግስት ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ካቀረበልን የእኛ ስራ በትጋት የእርሻ ስራችንን ማካሄድና ሰላማችንን መጠበቅ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡ በወረዳው በመስኖ ሊለማ የሚችለው መሬት አንድ ሺህ 558 ሄክታር መሬት ቢሆንም በተከሰተው የሰላም መናጋት ምክንያት የነዳጅና የማዳበሪያ እጥረት በመኖሩ እስካሁን አንድ ሺህ 100 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች እየለማ ይገኛል የሚሉት በትግራይ ክልል የሰሜን ማዕከላዊ ዞን የታይታይ ቆራሮ ወረዳ የመስኖ ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ እዮብ ገብረመድህን፤ በተከሰተው ጦርነት የአካባቢው ሕዝብ ልማቱ ተስተጓጉሎና ለከፋ ችግር ተጋልጦ መቆየቱን ይገልጻሉ። አሁን በተፈጠረው ሰላም ከአራት ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ቶሎ ወደ መስኖ ልማቱ ተመልሰዋል ነው ያሉት።
አርሶ አደሩ ያጋጠመውን የማዳበሪያና የምርጥ ዘር ችግር ተቋቁሞ እያለማ እንደሚገኝ አቶ እዮብ ጠቅሰው፣ በዚህ በኩል መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚኖርበትም አመልክተዋል። በቆሎ ሽምብራ፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲምና በርበሬ በወረዳው በበጋ መስኖ እየለሙ ከሚገኙ የሰብል አይነቶች መካከል እንደሚጠቀሱም አመልክተዋል። የጦርነቱ ወቅት እንኳንስ ስለልማት ሊያስብ፣ ሰው ሕይወቱን ለማትረፍ አካባቢውን ለቆ ለሚሄድ የሚገደድበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን የተረጋጋ ሰላም በመፈጠሩ አርሶ አደሩ ወደ ስራ ገብቷል ብለዋል፤ ለልማትም ተነቃቅቷል ሲሉ ገልጸዋል። የወረዳ የግብርና ባለሙያዎችም ከአርሶ አደሩ ጎን ሆነው እየደገፉት እንደሚገኙ፣ የሙያ ምክርም እየሰጡት መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜ የግብርና ባለሙያዎች በተቻለ መጠን አርሶ አደሩ የተፈጠረውን ሰላም ተጠቅሞ ፈጥኖ ወደ ልማት እንዲገባ እያበረታቱት ናቸው የሚሉት አቶ እዮብ፤ የማዳበሪያ እጥረት ቢኖርም አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ማዳበሪያን ተጠቅመውም ወደ ልማቱ እንዲገቡ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ ይህም አርሶ አደሩ በአጭር ጊዜ ራሱን እንዲያቋቁምና የተረፈውንም ገበያ አውጥቶ እንዲሸጥ የሚያስችል ነው። ገበያውን ለማረጋጋትም ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል። እስካሁን በመስኖ መልማት እየተቻለ ያለማ መሬት ይታያል፤ በሂደት እየለማ ይሄዳል። ምክንያቱም የቀሩትን የመስኖ መሬቶች ወደ ልማት ለማስገባት እየተሰራ ነው። በአሁኑ ጊዜ ባንክ በመከፈቱ አርሶ አደሩ ከባንክ ያለውን ብር አውጥቶ ከነጋዴዎች ዘርና ማዳበሪያ በመግዛት ወደ ልማት እንዲገባ ዕድል መፈጠሩን ጠቅሰው፣ አርሶ አደሩም ከተረጂነት መውጣት አለብኝ ብሎ ወስኖ ወደ መስኖ ልማት እየገባ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
በትግራይ ክልል ታይታይ ቆራሪት ወረዳ የበቆሎና የሽምብራ፣ የቆስጣና የሰላጣ ምርቶች ደርሰው ወደ ገበያ እየወጡ መሆናቸውን ተመልክተናል። ቀደም ሲል በአካባቢው አንድ የበቆሎ እሸት ዋጋ እስከ 25 ብር ደርሶ ሲሸጥ ነበር። አሁን ከስምንት እስከ 10 ብር ድረስ ይሸጣል። የበጋ መስኖ ልማት መካሄዱም አርሶ አደሮች የከብቶች መኖ በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው መሆኑን ባለሙያዎቹ አብራርተውልናል። በጦርነት ምክንያት የትግራይ ክልል ሕዝብ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጦ እንደነበር የሚናገሩት በትግራይ ክልል የፌዴራል መንግስት አስተባባሪ አቶ ታከለ ቶሎሳ፣ በተደረሰው የሰላም ስምምነት ሰላም በመፈጠሩ ሕዝቡ ወደ መደበኛ ሕይወቱ እንዲመለስ ሰፊ ስራ ተስርቷል ይላሉ። በዚህም መደበኛ እንቅስቃሴዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ የመጡበት ሁኔታ መፈጠራቸውንም ተናግረዋል።
ሰላም ከሌለ ምንም ነገር መስራት አይቻልም፤ አሁን አንጻራዊ ሰላም የተገኘ ስለሆነ የምናየው የመስኖ ልማትም የሰላም መገለጫ ነው የሚሉት አቶ ታከለ፤ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አርሶ አደሩ ለውሃ መሳቢያ ሞተሩ ነዳጅ አግኝቶ ወደ መስኖ ልማት እንዲገባ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። የነዳጁ ተደራሽነት እኩልና አስተማማኝ ነው ባይባልም ጥሩ ጅምር መኖሩን ይናገራሉ። አቶ ታከለ እንዳሉት፤ ከማዳበሪያ አቅርቦት አኳያም አሁን የግብርና ግብዓቶችን ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ተስፋ ሰጪ ስራዎች እየተሰሩ ነው። ሰላሙ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ በመጪው ክረምት በማንኛቸውም የአገሪቱ ክፍሎች እንደሚገኙ አርሶ አደሮች የትግራይ ክልል አርሶ አደሮችም ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና ጸረ ተባይ ኬሚካሎች እንዲያገኙ ይደረጋል። ይህም በአጭር ጊዜ ወደ መደበኛ የእርሻ ስራቸው ሊመለሱ እንደሚችሉ ያመለከታል፤ ይህ የመስኖ ልማት ጅማሬም ለእዚህ ማሳያ ነው፡፡
ህብረተሰቡ በጣም ሰላም ፈላጊ ነው የሚሉት አቶ ታከለ፣ በገጠር በከተማም ባወያየንባቸው መድረኮች ህብረተሰቡ ሰላም ፈላጊና ከመንግስት አገልግሎት ፈላጊ መሆኑን ገልጾልናል ሲሉ ተናግረዋል። በሌላ በኩልም ማንኛውም የወረዳው ነዋሪ የጤና ችግር ካጋጠመው ወደ መንግስት ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ሄዶ በነጻ ህክምና እንዲያገኘ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ የሆነው ሰላም በመፈጠሩ መሆኑን ጠቅሰው፣ ህብረተሰቡ ይህን ሰላም ለማስቀጠል የሚጠበቅበትን ድርሻ መጫወት ያለበት መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡ እነዚህ ችግር ያልበገራቸው ታታሪ አርሶ አደሮች አስፈላጊውን የግብርና ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ ግብዓቶች እንዲያገኙ መደገፍ ያስፈልጋል። ከዕርዳታ በመላቀቅ የራሳቸውን ፍጆታ ከመሸፈን አልፈው ለገበያ በማቅረብ ገበያውን በማረጋጋት ረገድም ትልቅ ድርሻ ይኖራቸዋል። አርሶ አደሮቹ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በሚያስፈልጋቸው ወቅት ላይ በመሆናቸው የሚመለከተው አካል ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል እንላለን፡፡
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2015 ዓ.ም