ሰላም የብዙ ነገር መሰረት ነው። ከሁሉም በላይ ፣ ግለሰባዊ ፣ ማኅበረሰባዊ እና ሀገራዊ ዛሬዎች ሆኑ ነገዎች በተደላደለ መሰረት ላይ ሊቆሙ የሚችሉት ሰላምን መሰረት አድርገው ነው። ከዚህ የተነሳም የሰላም ጉዳይ የማይመለከተው አካል አለ ብሎ መናገር አይቻልም። በዘመነ – ግሎባላይዜሽን እውነታው ዓለም አቀፋዊ ገጽታ የመያዙ ነገር ደግሞ ዕለት ዕለት የምንታዘበው ጉዳይ ከሆነ ሰንብቷል።
ከዚህ የተነሳም የሰላም ጉዳይ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ሆኗል፤ ስለ ሰላም የሚጮሁ ድምጾችም እየተበራከቱ መጥተዋል። ይህም ሆኖ ግን አሁንም በሰላም እጦት ምክንያት ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ሀገራትና ሕዝቦች ቁጥር ጥቂት የሚባል አይደለም። ሰላማቸውን ለማስመለስ እያደረጉት ያለውም ጥረት እያጋጠመው ያለው ፈተና ቀላል የሚባል አልሆነም። ሀገራቱ ቀደም ባሉት ወቅቶች ለሰላማቸው የነበራቸው የተዛባ አስተሳሰብ፤ ሰላማቸው ከእጃቸው ከወጣ በኋላ መልሶ ለመያዝ እያደረጉት ያለውን ጥረት ውስብስብ አድርጎታል፤ ከሰላም እጦታቸው ጀርባ ያሉ ብዙ እጆችንም በቀላሉ መግራት የሚያስችል አቅም መፍጠር ተስኗቸው፤ ሕዝቦቻቸው ለከፋ ስደት መከራና ስቃይ ተዳርገዋል። ለብዙዎች ይተርፉ የነበሩ የሌሎችን እጅ ጠበቂ አድርጓቸዋል።
ለዚህም የቅርቦቹን ሊቢያን ፣ ሶሪያን ፣ኢራቅን እና የመንን ማየት ይቻላል። እነዚህ ሀገራት በእጃቸው ከነበረው ሰላም ብዙ ትሩፋቶች ነበሯቸው። ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወታቸው ዛሬን አሻግሮ ነገን በተሻለ ተስፋ እንዲጠብቁ፤ በሰላም ወጥተው ለመግባት ብቻ ሳይሆን የዕለት ጉርሳቸው ሀሳብ እንዳይሆናቸው ዋነኛ አቅም ሆኗቸውም ነበር። ከሰላም እጦቱ በኋላ የሆነው ግን የተገላቢጦሽና የከፋ ነው። በእኛም ሀገር እየሆነ ያለውን ነገር በጊዜ መግራት ካልተቻለ ሊፈጠር የሚችለው አደጋ ከኛ አሁናዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እውነታ አንጻር ሀገራቱ ካጋጠማቸው የከፋ እንጂ የሚቀል ሊሆን አይችልም። እያንዳንዱ ዜጋ እያጋጠሙን ባሉ ችግሮች ዙሪያ በኃላፊነት መንቀሳቀስ ካልቻለ ማንም ሊመጣ ከሚችለው አደጋ ራሱን ሊታደግ አይችልም።
አሁን ላይ እንደ ሕዝብ ስለ ሰላም ያለንን አስተሳሰብ ከፍ ማድረግ ይጠበቅብናል ፤ ሰላም በአግባቡ ያለ ዋጋ ልትጠበቅ የምትችለው በሰላምና በሰላም ወቅት ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ ሰላምን ለመጠበቅ የሚደረጉ ጥረቶች ሊያስከፍሉ የሚችሉት ዋጋ በቀላሉ ታስቦ ግምታዊ ስሌት የሚሰጠው አይደለም። “በእጅ የያዙት ወርቅ” እንደሚባለው የሰላም ዋጋዋ ሳይቀልብን መንቀሳቀስ ጊዜው የሚጠይቀው ግዴታ ነው። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን መላው ሕዝባችን ስለ ሰላም አዘውትሮ በማሰብና በመቆም ከአሉባልታ፤ ካልተረጋገጠ ወሬና ውንጀላ ራሱን በመለየት በተረጋጋና በሰከነ መንፈስ ፤ ኃላፊነት በሚሰማው መልኩ ሀገራዊ ሰላሙን ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ንቁ ተሳታፊ ሊሆን ይገባል።
በተለይም የግጭት ቆማሪዎች ዋንኛ ሰለባ ሊሆን የሚችለው ወጣቱ ትውልድ የወደፊት ተስፋው መሰረት ሰላም መሆኑን በሚገባ ተገንዝቦ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ያለ ማንም ወትዋች /ስብከት/ የሰላም ሀዋርያ ሆኖ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል። ለዚህ የሚሆነውን ዝግጁነት በየዕለቱ ማደስም ይኖርበታል። እስካሁን በነበረው የሰላም እጦት እንደ ሀገር የከፈልነው ዋጋም ሆነ አሁንም እየከፈልነው ያለው ማንንም ተጠቃሚ ያደረገ አይደለም፤ ሊያደርግም አይችልም። ግጭቱ ወንድሞቻችንን ፤በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ሀብትና ንብረት አሳጥቶናል።
ይህ አይነቱ ሀገራዊ ችግር ዳግም እንዳይከሰት ከሁሉም በላይ በእጃችን ያለውን ሰላም በተሻለ መልኩ ልንጠብቀው እና ልንከባከበው ይገባል። ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠርና በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ባለመቻላችን የምናጣው ሰላም ሊያስከፍለን የሚችለው ዋጋ የከፋ መሆኑን ለመረዳት ከትናንት ታሪካችን በላይ ሌላ አስረጅ መጠበቅ አያስፈልግም !
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2015 ዓ.ም