ሰላም ልጆች እንደምን አላችሁ ! ትምህርት እንዴት ይዟችኋል? ለሁለተኛ ሴሚስተር ፈተና ዝግጅት ማድረግ የሚቻለው በዕየለቱ የምትማሩትን ትምህርት ከሥር ከሥር በማጥናት እንደሆነ ታውቃላችሁ አይደል? ይሄን ካወቃችሁ በጣም ጎበዞች ናችሁ:: ግን ደግሞ ከጥናት ጎን ለጎን ባለ ትርፍ ጊዚያችሁ ስለ ሌሎች ከትምህርታችሁ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያያዙ ብዙ ነገሮችንም ማወቅ ይገባችኋል::
ለምሳሌ የእንስሳት መዘክሮች ወይም ሙዚየሞች ብትጎበኙ ጥሩ ትምህርት ታገኛላችሁ:: ክፍል ውስጥ የተማራችሁትን ትምህርትም በተግባር ለማረጋገጥ የሚያስችል ዕውቀት ትቀስማላችሁ:: ልጆች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው የእንስሳት የተፈጥሮ ቅርስ መዘክርን ስንቶቻችሁ ታውቁታላችሁ?
በመዘክሩ ውስጥ የተለያዩ እንስሳቶች ይገኛሉ:: ከእነዚህ መካከል የተለያዩ የወፍ ዝርያዎች ይጠቀሳሉ:: ለዛሬ እኛም መዘክሩን ላልጎበኛችሁት ልጆች ስለእነዚህ የወፍ ዝርያዎች ልንነግራችሁ ወደናል:: አስጎብኛችን ወይዘሮ አምሳለ ተፈራ ይባላሉ:: እርሳቸው እንደነገሩን ይሄ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው የእንስሳት የተፈጥሮ ቅርስ መዘክር በኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው መዘክር (ሙዚየም) ነው:: ከተመሰረተ ዘንድሮ 54ኛ ዓመቱን ይዟል::
ቀደም ሲል ሥፍራው የዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር እንጂ የሙዚየም አልነበረም:: ከጥናትና ምርምሩ ዝግጅት በኋላ በቀጣይ ምን ይሁን በሚል ምክክር ተደርጎ ነው ለእንስሳት መዘክርነት እንዲውል የተወሰነው:: ታዲያ በቀን ከስድስት ሺህ ተማሪዎች በላይ ያስተናግዳል:: ለጉብኝት ከሚመጡት ተማሪዎች በአብዛኛው በክፍል ውስጥ የተማሩትን በተግባር ለማረጋገጥ የሚመጡ ናቸው::
የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ወደ መዘክሩ ለጉብኝት ከመምጣታቸው በፊት በደብዳቤ ፕሮግራም ያሲዛሉ:: የመግቢያ ዋጋው ለተማሪ አምስት ብር ለአዋቂዎች ደግሞ 15 ብር ነው:: አገር ውስጥ ነዋሪ የሆኑ የውጭ ዜጋ ጎብኝዎች ደግሞ 50 ብር ይከፍላሉ:: መዘክሩ የአውድ ዓመት በዓላትን ጨምሮ ከእሁድ እስከ እሁድ ለጉብኝት ክፍት ነው::
እኛ እንደጎበኘነው ታዲያ በመዘክሩ የተለያዩ እንስሳቶች በስድስት ክፍሎች ተከፋፍለው ለጉብኝት ቀርበዋል:: አስጎብኛችን እንደነገሩን አምስተኛውና ስድስተኛው ክፍል የተለያዩ የወፍ ዝርያዎች የሚገኙበት ነው:: የወፍ ዝርያዎቹ በዚህ ክፍል ውስጥ ብቻ ያሉት አይደሉም:: ገና ያልተሰበሰቡና ወደ ክፍሉ ያልመጡ ብዙ የወፍ ዝርያዎች አሉ:: ታዲያ በራሪዎቹ የወፍ ዝርያዎች በሙሉ በመጠን አነስ ያሉ ናቸው:: ከእነዚህ ወፎች ውስጥ ሁሌ በአካባቢያችሁ ሲበሩ የምታይዋቸው ወፎችና እርግቦች ይገኙበታል::
እነዚህ ወፎች ጥራጥሬ ነው የሚመገቡት:: ቢሆንም መሬት ላይ ያገኙትን ነገር ሁሉ እየለቀሙ ወደ ጎጇቸው ይወስዳሉ:: በተለይ አኝከን የተፋነውን ማስቲካም የሚወጡበት ጊዜ ቀላለል አይደለም:: ነገር ግን ማስቲካው ጉሮሯቸው ላይ ስለሚለጠፍ ተሰቃይተው ይሞታሉ:: ስለዚህ አስጎብኛችን ማስቲካ አኝከን ከመትፋታችን በፊት በወረቀት ጠቅልለን መጣልና ወፎቹን ከስቃይና ሞት መታደግ እንዳለብን ነግረውናል::
በመዘክሩ ውስጥ ውሃ ውስጥና ውሀ አካባቢ የሚገኙም የወፍ ዝርያዎችም አሉ:: ወፎቹ በሙሉ ዋናተኛ ናቸው:: እንደ ዳክየና ዝይ ያሉ ዋናተኞቹ ወፎች እግሮቻቸው አንድ ላይ የተያያዙና የተጣበቁ ሲሆኑ፤ ሥጋ በል የሆኑ ወፎችም በክፍሉ ውስጥ አሉ:: ስጋ በሎቹ ወፎች አፋቸው ወይም መንቁራቸው በጣም የሾለና የታጠፈ ነው:: የሚመገቡትን እንስሳ ወግተው ለመግደልም የሚያስችሏቸው ሹል ጥፍሮቻቸውና ጠንካራ አፎቻቸው ናቸው:: ልጆች ንስር የሚባለውም ከእነዚሁ የወፍ ዝርያዎች ይካተታል:: ንስሮች በአብዛኛው የሞተ እንስሳ አይበሉም:: በሕይወት ያለ እንስሳ በማደን ራሳቸው ገድለው ነው የሚመገቡት:: ከርቀትም እስከ አምስት ኪሎ ሜትር ወደ ታች መውረድና መብረር እንዲሁም ከፍታ ላይ መብረር ይችላሉ::
ሴክረተሪ በርድ የሚባሉም የወፍ ዝርያዎች አሉ:: የስማቸው መነሻ ላባቸው ሲሆን፤ በድሮ ጊዜ ቀለም ተነክሮ ይጻፍበት ስለነበረ ከጸሐፊነት ጋር ተያይዞ የወጣላቸው ነው ይባላል:: ሌላው ምክንያት አፈጣጠራቸው በዓይን ሲታዩ አጭር የለበሱ፤ የተኳኳሉና ጫማ የለበሱ መምሰላቸው ነው:: ሴክረተሪ በርዶች ሥጋ በል የወፍ ዝርያ ናቸውም::
ሌላው በመዘክሩ ውስጥ ያለው ቅልጥም ሰባሪ የሚባል የወፍ ዝርያ ሲሆን፤ ይሄ ወፍ አጥንት ወይም ቅልጥም ይዞ በጣም ወደ ላይ ከፍ ብሎ እየበረረ ይሄድና ትልልቅ ድንጋይ ፈልጎ አጥንቱን ወደ ታች ይለቀዋል:: አጥንቱ ሲሰበር ከከፍታ ወደ ታች ወደ መሬት ይወርድና ከውስጡ ያለውን መቅኒ ወይም ቅባትና የአጥንት ስብርባሪ ይመገባል:: በዚህም መገኛው ብዙ ጊዜ ተራራማ ቦታዎች ላይ ነው::
ልጆች አሁን ስድስተኛው ክፍል ውስጥ ስንገኝ በዚህ ክፍል ውስጥ ያሉት የወፍ ዝርያዎች ጥንብ አንሳ የሚባሉት አይነት ናቸው:: በአብዛኛው የሚመገቡት የሞተ እንስሳትን ነው:: በዚህ ትይዩ በአብያታ ሐይቅ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ወፎች ይገኛሉ::
ጥሬም ሥጋም የሚበሉ የወፍ ዝርያዎች በዚህ ክፍል ውስጥ አሉ:: ከእነዚህም ወፎች መካከል ቆቅና ጅግራ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው:: ወፎቹ ቀለማቸው ይለይ እንጂ ቅርጻቸው ዶሮ ይመስላል:: ሥጋቸውም እንደ ዶሮ ሁሉ ይበላል:: አብራቸው ጉጉት የምትባል የወፍ ዝርያ ትገኛለች:: ጉጉት በአብዛኛው ማታ ማታ ታድናለች:: በአብዛኛው ዓይናቸው የሚያየውም በማታ ብቻ ነው::
እርኩም እንዲሁም አሞራ ወይም ቁራ ብለን የምንጠራቸውና ዝርያቸው ከወፍ የሚመደብ የወፍ ዝርያዎችም ሌሎቹ በስድስተኛው ክፍል የሚገኙ ናቸው:: ወፎቹ ሥጋም ጥሬም ይመገባሉ:: ቁራዎቹ አንገታቸው ላይ ነጭ አለባቸው:: የቁጥቋጦ ቁራ የምትባልም አለች:: ይህች ቁራና በቀቀን ከተሰኙት የወፍ ዝርያዎች ውስጥ ግንባረ ቢጫ በቀቀኖች በተጨማሪም ሰማያዊ ክንፍ ዝይን ወፎች በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ ዝርያዎች ናቸው:: ስለዚህ ሄዳችሁ ጎብኙ በማለት ለዛሬ አበቃን:: መልካም ሰንበት !!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም