በዚያን ዘመን..ለመሆኑ በየትኛው ዘመን?..ዘመኑን የሚወክል አሀዛዊ ቁጥር ስለሌለ ዝም ብሎ በዚያን ዘመን ማለቱ ይሻላል። እናም በዚያ ዘመን ሴትነትም ሆነ የሴቶች መብት ከትልቅ ዋርካ ስር እንደምትገኝ አበባ ነበረች። ዋርካው ካልራራላት በቀር ጸሃይም ሆነ ዝናብ ማግኘት ብርቋ ነው። እንደ ዛሬው የሴቶች መብት እያልን አቤት የምንልበት ፍርድ ቤትም ሆነ የሚሰማ ዳኛ ያልነበረበት ዘመን። እንዲያውም ከነጭራሹ የሴቶች መብት የምትለው ሀረግም አልተፈጠረችም ነበር። ነገር ግን በአንድ ወቅት፣ ከዛሬ መቶ ሰላሳ ዓመታት በፊት የሴትነት መብት ባንዲራ ይዛ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ እንደ ተወርዋሪ ኮከብ ብልጭ ብላ የጠፋች አንዲት ሴት ብቅ ብላ ነበር። የሴትነት ቁንጮ የጀግንነት ተምሳሌት እሷም የቃቄ ውርድወት ናት።
የቃቄ ውርድወት ተወልዳ ያደገችው በዛሬዋ የጉራጌ ዞን የምሁር አክሊል ወረዳ ውስጥ ነበር። መቼም በአይኑ ያያት ሁሉ ስለ ጀግንነትዋ ብቻ ሳይሆን ስለ መልካምነቷና ምትሃታዊ ውበቷም ጭምር ሳያደንቅ አያልፍም። ውርድወትን ቆንጆ ናት ከማለቱ ይልቅ ውበት ስጋ ለብሶ የተገለጠባት ሴት ናት ማለቱ ይቀላል። በቤተሰቦችዋ እንደ አይን ብሌን የምትታይና በወንድም እህቶቿ ተከባ በእንክብካቤ ያደገች ነበረች። የቃቄ ውርድወት እየተባለች ብትጠራም የእሷ ስም ግን ውርድወት ነው። የቃቄ ደግሞ የወላጅ አባቷ ስም ነው። ውርድወት ከልጅነቷ ጀምሮ ያለ እድሜዋ ጀብዱ መስራት የሚያስደስታት ሴት ነበረች።
ውርድወት ወደ ሴቶች መብት ተሟጋችነት እንድትገባ የገፋፋት አንድ ምክንያት ነበራት። በልጅነት አስተዳደጓ እንደሌሎቹ የአካባቢዋ ሴቶች ችግር የሚባለውን ነገር እምብዛም አታውቀውም። ምክንያቱ ደግሞ በእንክብካቤ ያደገች የባለአባት ልጅ ናትና። ታዲያ ይህችን ቆንጆ ልዕልት የራሱ ለማድረግ የአባቷን ደጅ ያልረገጠ ወንድ አነበረም። ስለ እርሷ ውበት የሰማ በሙሉ እድሌን ልሞክር በማለት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ዘመኑ ደግሞ ዘመድ ከዘመዱ፣ አህያም ከአመዱ ነበርና የወላጆቿ ምርጫ ሆኖ እንደ እነርሱ ባለጠጋ ለነበረ ለአንድ ባለአባት ልጅ ዳሯት። በድሮው ዘመን በአገራችን በተለይ ደግሞ በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ ባለጠጋ የሆነ ወንድ የባለጠግነቱ ማሳያ በሀብትና ንብረቱ ቁጥር ብቻ ሳይሆን በሚስቶቹም ቁጥር ጭምር ነው። እንግዲህ ብዙ ያለው ብዙ ያገባል ማለት ነው። ውርድወትም የገጠማት ከዚህ የተለየ አነበረም። የእኔ ነው ብላ ቤቱ የገባችለት ሰው፣ የእሷ ብቻ ሳይሆን የብዙ ሴቶች ባል ነበር። ይህ ጉዳይ ውርድወትን ይቆረቁራትና ምቾት ይነሳት ነበር። በትዳር ሕይወቷ ቀናትን እያስቆጠረች በመጣች ቁጥር እልህ የታከለበት ቁጣና ንዴት እየንተከለከለ ከውስጧ መገንፈል ጀመረ። እናም በደልን በጸጋ ተቀብሎ መኖር አልሆንላት አለና አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባት ወሰነች። ነገሩን በሀሳቧ ማውጠንጠንና እለት ከእለት ለብቻዋ መብሰልሰሉን ተያያዘችው። በመጨረሻም አንድ ሀሳብ ከአዕምሮዋ ከተፍ አለላት።
ሀሳቧን ከግብ ለማድረስና ብዙ ሴቶችን ከተጫነባቸው የጭቆና ቀንበር ለማላቀቅ በቀየሰችው መንገድ መሰረት የትግል ጉዞዋን ጀመረች። በመጀመሪያም ጎረቤቷ ከነበሩ ሴቶች ዘንድ በመሄድ ስለ ጉዳዩ አማከረቻቸው። ብዙ ሴቶችም ሀሳቧን በመደገፍ ይህንን ትግል በመደገፍ ሊቀላቀሏት ፈቃደኛ ሆኑ። ውስጥ ለውስጥ በነበራቸው ቅስቀሳም ቁጥራቸው እየተበራከተ ሄደ። አንድ ቀን ውርድወት ሴቶቹን ሁሉ በመሰብሰብ ይህንን ንግግር አደረገችላቸው፣ ‹‹ወንዶቹ ቀን ቀን በጀፎሮ (በቤተ-ጉራጌ አውራ መንገዶች) በሚገኙ ዋርካዎች ስር ሆነው ሲወያዩ፣ ገበጣና የተለያዩ ጨዋታዎች በመያዝ እንዳሻቸው እየተዝናኑ ውለው ማታ ይገባሉ፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የፈለጉትንና ሀብት ንብረታቸው የሚፈቅደውን ያህል ሴት ያገባሉ፡፡ ባሎቻችን ቢናፍቁን እንኳን እነርሱ ፈልገውን እስካልመጡ ድረስ መቼም አናገኛቸውም። እኛ ሴቶቹ ክብራችንን ገፈው እንደሚስት ሳይሆን እንደ እቃ በገንዘባቸው ይሸምቱናል..ለምን! ስለምንስ እንዲህ ይሆናል! ማግኘት ያለብንን የሴትነት ክብርና ወግ ስንነጠቅ በፍርሃት አንገት ደፍተን እስከመቼ እንኖራለን? ከዚህ በኋላ እያንዳንዳችን ከቤታችን በመጀመር ድምጻችንን አንድ አድርገን ይህንን የተጫነብንን ቀንበር ልንሰብር የግድ ነው!›› በዚህም ንግግራ የሴቶቹን የተኛ ልብ በወኔ ቀሰቀሰችው። ስብሰባውም በውስጥ እየተደጋገመና በቁጥርም ሆነ በስነልቦና ክንዳቸው እየጠነከረ መጣ።
የሚስቶቻቸው ባህሪ ከጊዜ ወደጊዜ እየተቀየረና እየጠጠረ የመጣባቸው ባሎች በሁኔታው ግራ በመጋባት መጨነቅ ጀመሩ። ሴቶቹ ከነበራቸው ድብቅ ስብሰባና ውስጣዊ ፍርሃት በመውጣት የራሳቸውን ነጻነት አውጀው በጆፎሮ ላይ መሰብሰብ ቀጠሉ። በማህበረሰቡ ባህል ሴቶች በአደባባይ ላይ ከተሰበሰቡ እንደ ነውር ይታያል። ይህን ጥሰው በአደባባይ በመሰብሰባቸው ምን ጉድ መጣብን ሲሉ ወንዶቹ እርስ በእርስ በጥያቄ ፊት መተያየት ጀመሩ። ነገሩም አላማረቸውምና አንዳች ነገር እየዶለቱ እንደሆነም ጠረጠሩ። በአንደኛው የስብሰባ እለትም ወንዶቹ ወደ ቃቄ ውርድወት ባለቤትና የአካባቢው ሰብሳቢ ሆደሆነው ወደ አጋዝ ፍርችየ ዘንድ በመሄድ በባለቤቱ መሪነት እየተካሄደ ያለውን የሴቶቹን ጉዳይ በሸንጎ ይጠይቅላቸው ዘንድ አወጉት።
አጋዝ ፉርችየም ይሄድና ሴቶቹን ‹‹ምንድነው?›› ይላቸዋል፡፡ እነርሱም መልሰው ‹‹ምንድነው?›› ይሉታል፡፡ ‹‹ሴት ልጅ በጀፎረ መሰብሰብ ነውር ነውና አይቻልም›› ይላቸዋል፡፡ እነሱም ‹‹የሚያሰባስበን ጉዳይ ስለገጠመን እንሰባሰባለን›› ብለው ይመልሱለታል፡፡ ጀግናው ፉርችየ እዚህ ላይ ፈተና ገጠመው፡፡ በጣም የሚወዳት እልኸኛ ሚስቱን ውርድወትን ፊት ቢመለከት ፈጽሞ ሌላ ሆነችበት። ስልጣኑን እንኳን ሳይፈሩ የሚሞግቱት የሴቶቹ ሁኔታ ያስደነገጠው ፍርችየም ፈራ ተባ እያለ በእርጋታ ‹‹እሺ አሁን ጉዳያችሁ ምንድነው?›› ሲል ደግሞ ጠየቃቸው። ሴቶቹም ሁለት መሰረታዊ የሆኑ ጉዳዮች እንዲስተካከልላቸው እንዲህ በማለት ጠየቁ። ‹‹አንደኛ እናንተ እንዳሻቹ፣ ባሻችሁ ጊዜና ቦታ ስትዝናኑ ውላችሁ ስትገቡ እኛ ደግሞ ቤታችንን ለማቅናት ደፋ ቀና ስንል ውሎ ይመሻል። በአንዲት ሴት ላይም ብዙ ሴት ታመጣላችሁ። ስለዚህ እኛ ሴቶችም የፈለግነውን የማግባት መብት ይሰጠን። ይህ ካልሆነ ደግሞ አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት ብቻ ይሁን። ሁለተኛ ወንድ እንጂ ሴት ልጅ ባሏን የመፍታት መብት ስለሌላት በደል እየደረሰባትም ችላ የግዷን ትኖራለች። ፍቺ ስትፈጽምም የምታልፈው መከራ ብዙ ነውና ለዚህም መፍትሄ እንፈልጋለን!›› በማለት የ’አንቄት’ ህግ እንዲነሳላቸው ጠየቁ። ‘አንቄት’ በጉራጌ ማህበረሰብ የሰማንያ ውል እንደማለት ነው። በዚህ ልማዳዊ ህግ መሰረት አንዲት ሴት ባሏን ስትፈታ ባሏ ‹ፈትቼሻለሁና የወደደ ያግባሽ› በማለት ደጋግሞ ሶስት ጊዜ ሳይመርቃት በራስዋ ፈቃድ ጥላ የወጣች እንደሆን የተረገመችና ቀጣዩም ትዳርዋ ያልተባረከ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል። ሴቶቹ በሶስተኛ ደረጃ ያነሱት ደግሞ ‹‹ሴቶች በጆፎሮ መሰብሰብ አለባቸው፤ ስለዚህ ክልከላው መቆም አለበት›› የሚል ነበር።
ነገሩን በዝርዝር የሰማው ፍርችየ ጉዳዩን ይዞ ወደ ወንዶቹ ዘንድ ተመለሰ። የሴቶቹ አመጽ እየጨመረ በመምጣቱ፣ ጉዳዩ ለወንዶቹ እረፍት የሚነሳ ነበርና በጋራ መከሩበት። አንድ ወንድ ለአንድ ሴት የሚለው ሀሳብ ደግሞ የሁሉንም ቤት ያንኳኳ አስጨናቂ ነጥብ ሆነባቸው። ከሁለትና ከሶስት ሚስት ጋር የተሳሰረው ወንድ ሁሉ ጉዱ ፈላበት። በዚህ ላይ የፍቺ ነጻነቱን ቢሰጧቸው በአንዴ ወደ አዘቀጥ ውስጥ መግባታቸው እንደማይቀር ገብቷቸዋል። የሴቶቹ ህብረት እየጠነከረ፣ ከአካባቢው እየወጣና እየተስፋፋ ሙሉ የሰባት ቤት ጉራጌን እያካለለ በመሆኑ፣ ይህን አመጽ በጉልበት መሞከር ደግሞ በእሳት ላይ ቤንዚን ማርከፍከፍ መስሎ ታያቸውና የሚዙት የሚጨብጡት ጠፋቸው።
በአካባቢው ሽማግሌዎች ተጀምሮ መቋጫ ያላገኘው የእነ ውርድወት ጉዳይ በቤተ-ጉራጌዎች የሽምግልና ስርዓት መሰረት ከአንዱ ወደ አንዱ፣ ደረጃ በደረጃ ከጎሳ ጠቅላላ ጉባኤ ወደ ኩታ ገጠም ጎሳዎች ጉባኤ፣ ከዚያም ወደ ጠቅላላ ቤተ-ጉራጌ ሸንጎ ወይም የኧጆካ ሸንጎ ወደሚሰኘው የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ ወደሆነው ባህላዊ ምክር ቤት አመራ። በበሳልና ጠቢብ አባቶች የሚመራውና ምንም የማይፈታው ነገር የለም የተባለለት ይህ ሸንጎ ለመጀመሪያ ጊዜ እጅግ በጣም ፈታኝና ውስብስብ ጉዳይ ገጠመው። እንቆቅልሹን ለመፍታትም ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግና ጉዳዩን በጥልቀት በማጤን ከሶስት ጊዜ በላይ የተለያዩ ቀጠሮዎችን ቢሰጥም ለመፍታት ግን ከበደው። በቀጠሮ ብዛት የተሰላቹት ሴቶቹ አሁንም በአስቸኳይ ውሳኔ ይሰጠን ሲሉ ጩኸታቸውን ለሸንጎው አሰሙ። ሸንጎውም የውሳኔ ቀነ ቀጠሮ ሰጥቶ አሰናበታቸው። በዚህ መሃል ታዲያ አደጋ ያንዣበበበት የሸንጎው አባላት ሴቶቹን በግል እያገኙ ይደልሏቸው ጀመር፡፡ ሴቶቹ ግን ወይ ፍንክች! አሉ። የጀርባ አጥንታቸው የነበረችው ውርድወት ደግሞ ‹‹ገላችሁ አፈር አልብሱኝ እንጂ በሕይወት እያለሁ ፈጽሞ አልተወውም›› በማለት የቆራጥነቷን ጥግ አሳየቻቸው። ውርድወትን ማሸነፍ ጉዳዩን በድል እንደማጠናቀቅ ነውና ሸንጎውን በዝግ በማድረግ እሷን መርቻ መንገድ ማሰስ ጀመሩ። የአንቂት ስርዓትን ለእሷ ብቻ እናንሳላት በሚል ሀሳብ ግማሹ ቢስማማም ባለቤቷ ፍርችየ በጣም የሚፈራ ሰው እንደመሆኑ ከፊሉ እንዴትስ ተብሎ በእሱ ላይ መወሰን ይቻላል ሲሉ ሞገቱ። በስተመጨረሻም ባሏን ፍርችየን ለመማጸን ወስነው ሄዱ። እሱን ማሳመንም ቀላል አልነበረምና ከብዙ ልፋት በኋላ ለሚስቱ ውርድወት የአንቂት ስርዓትን ለማንሳት ተስማማ። ይህ ለሸንጎው ትልቅ እፎይታን የፈጠረ ጉዳይ ነበር። ከዚህ በመቀጠልም ወንዶቹ አንድ ሚስጥራዊ ስብሰባ አደረጉ። ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን ታውቆ ስለነበረ በዚህ እለት የትኛዋም ሴት ወደ ሸንጎ እንዳትመጣ ወንዱ ቢችል አባብሎ አሊያም አስገድዶ ከቤት እንዲያስቀራት ተባለ።
የዚያን ሰሞን ወንዶች ለሚስቶቻቸው የሚያሳዩት ፍቅርና እንክብካቤ ልዩ ነበር። አንዳንዶቹ የእንሰት ተክሎች፣ ላሞች፣ በግና ፍየሎች በጉቦነት ለሚስቶች ሽልማት እየተባሉ ተሰጡ፡፡ ወንዶቹ ትልቁ ጥረታቸው የቀጠሮውን ጉዳይ እንዲሰርዙና ሀሳቡንም እንዲረሱት ነበር። ጥቂቶቹም ተሳካላቸውና የሚስቶቻቸውን ሀሳብ ማስለወጥ ቻሉ። አንዳንዶቹም ቢሆኑ ከባሎቻቸው በደረሰባቸው ዛቻና ማስፈራሪያ ነገም ሌላ ቀን ሲሉ ለጊዜው ለመተው ወሰኑ። የቀጠሮው እለት ሽማግሌዎቹ በጠዋቱ ቦታ ቦታቸውን ይዘው በመጠባበቅ ላይ ነበሩ።
ውርድወት ፊቷ እንደጠዋት ጮራ እያበራ ከጃንጥላዋ ስር በሰጋር በቅሎዋ ስትከንፍ ደረሰች። ከስፍራው ቁጭ ብላ ሴቶቹን በጉጉት እየጠበቀች ደቂቃዎች እየነጎዱ ሰዓቱ ሄደ። በጣም እየተበሳጨች ሄዳ ከበቅሎዋ በመቀመጥ ወደከፍታ ቦታ ወጥታ ይመጡ እንደሆን ብላ ከእሩቅ ብትመለከት ዝር የሚልም የለም። ተመልሳ ሽማግሌዎቹ ጋር በመምጣት ሌላ ቀጠሮ እንዲሰጧት ብጠይቅም አውቀው ነገሩን ያበላሹት እራሳቸው ናቸውና የማይሆን ነው ሲሉ እምቢ አሏት። ሴቶቹ ሁሉ ትዳራቸውን መርጠዋልና አንቺም ሂጂ ቢሏት፤ እሷ ግን አይሆንም ሴቶቹ ሁሉ ባሎቻቸውን ፈርተው አሊያም ተታለው ቢቀሩም እኔ ለራሴ አለሁና ፍርድ እንድትሰጡኝ ብላ በግትር አቀማ ፀናች፡፡ በዚህ ጊዜ ሽማግሌዎቹም አማራጭ አልነበራቸውምና የአንቂት ስርዓትን አነሱላት። የቃቄ ወርድወት የራስዋን መብት በማስከበርዋ ደስ ቢላትም፤ ሴቶቹን ሁሉ ነጻ የማውጣት ትግሏ በተለያዩ ሴራዎች በመፍረሱ እያዘነች ተመለሰች። ከዚህ በኋላም ወደ አባትዋ ቤት ተመልሳ የራሷን ኑሮ ቀጠለች። በሰራችው ስራም ስሟ ከአካባቢዋ አልፎ በአገሪቱ ሁሉ ናኘ። ህልሟ በጊዜው ባይሳካም በትንሹም ቢሆን የሴቶቹን አይን አብርታለችና ብዙ ነገሮችም እየተለወጡ መጡ። ፈር ቀዳጅ በሆነው የሰለጠነ አስተሳሰብና ተግባሯ ባለትልቅ አዕምሮ ሴት ናትና በዚህ ሳምንት በተከበረው የሴቶች ቀን ልትመሰገን ይገባታል።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም