በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1989 ዓም የሕፃናት ልብ ሕሙማንን የሚደግፍ መርጃ ማዕከል ያቋቋሙ ናቸው። አንድ ብር ለአንድ ልብ በሚል ሀገራዊ ንቀናቄ በመፍጠር ወገን ለወገኑ እንዲደርስ ምክንያት ሆነዋል። የልብ ታማሚዎችን እርዳታ በማስተባበር ወደ ውጪ መላክ የመጨረሻ ግብ አለመሆኑንም ተረድተው የሕክምና ተቋማት እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲገነባ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርገዋል።
እኚህ ባለራዕይ የብዙ ሺህ ሕፃናት ነፍስን ከስቃይ ያዳኑ፤ የልብ ሕመም (በተለይ የሕፃናት) ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው አምባሳደር የሆኑ ናቸው። እኚህ ሰው የሕፃናት ልብ ሐኪምና በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል መሥራች ዶክተር በላይ አበጋዝ ናቸው። የዝግጅት ክፍላችን የእኚህን የኢትዮጵያውያን ባለውለታ የሕይወት ገፅታ እንደሚከተለው ይቃኛል።
ትውልድና እድገት
ዶክተር በላይ አበጋዝ በ1937 ኅዳር 12 በደሴ ከተማ ነው የተወለዱት። እድገታቸው ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞን በምትገኘው ኩታ በር ነው። ፍቅር፣ ብዝኃ ባሕልና ሃይማኖት አሰባጥራ የያዘችው ወሎ እኚህን ታላቅ ሰው ብታፈራም ዛሬን አሻግራ ተመልክታ የኢትዮጵያ ባለውለታ እንደሚሆኑ ገና አልተገለጠላትም ነበር። ነገር ግን አንድ እውነታን መካድ አይቻልም፤ የሰሜኑ ክፍል የአብሮነትና የመቻቻል ምሳሌ ወሎ ‹‹የሀገር ኩራት የሕዝብ አለኝታ›› ባለውለታዎችን ማፍራት ሁሌም አይነጥፍባትምና አንጋፋውን የጤና ዘርፍ ጀግና ሳትሰስት ጀባ አለችን።
የያኔው ብላቴና የዛሬው የልብ ሕሙማን አለኝታ ዶክተር በላይ በኩታበር የሕይወትን መንገድ አሐዱ ብለዋል። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በዚያው በኩታበር ነበር የጀመሩት። በቀለም ትምህርት አንቱ የተባሉና ብሩህ አዕምሮ ከታደላቸው ታዳጊዎች ውስጥ አንዱ ነበሩ። አባታቸው አቶ አበጋዝ በኩታ በር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርና ዳይሬክተር ነበሩ። ይህ አጋጣሚ ደግሞ እርሳቸውም በተፈጥሮ የታደሉት ፀጋ ጋር ተደምሮ ስኬታማ የትምህርት ግዜን እንዲያሳልፉ ምክንያት ሆኗቸዋል።
ወሎ ከጉያዋ ለሚወጡ ልጆቿ የቀለም ትምህርት ብቻ አትለግስም። ይልቁኑ አብሮ የመኖር ብልሀትን፣ የሃይማኖት መቻቻልን፣ ለሀገር እና ለሕዝብ የመኖር ጥበብን ጨምራ ታሳድጋለች። ዶክተር በላይ ይህን ጥበብ ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ተምረው አድገዋል። መክሊታቸውን ያወቁበትን መዳረሻ ራዕያቸውን የቀረፁበትን ትምህርት ከኩታ በር ባሻገር ከታዋቂውና በደሴ ከተማ ከሚገኘው ወይዘሮ ስህን ትምህርት ትምህርት ቤት ቀስመዋል። ይህ ትምህርት ቤት አንጋፋና ለሀገር ባለውለታ የሆኑ በርካታ ግለሰቦች የወጡበት ታዋቂ የአስኳላ መንደር ነው።
ዶክተር በላይ አበጋዝ እርሳቸውን ጨምሮ ከ12 እህትና ወንድሞቻቸው ጋር ነው ያደጉት፤ ለእናትና አባታቸው ሦስተኛ ልጅ ናቸው። ከቀለም ትምህርት ባሻገር የአደን ዝንባሌም ነበራቸው። ያደጉበት አካባቢ ገጠራማ የኢትዮጵያ ክፍል መሆኑ ለዚህ ዝንባሌያቸው ልዩ አስተዋፅዖ ነበረው። የልጅነት ጊዜያቸውን ከትምህርት ባሻገር ለምግብነት የሚውሉ እንደ ቆቅ፣ ጅግራና ሌሎች የዱር እንስሳትን በማደን ያሳልፉ ነበር።
ይህ ልምዳቸው ከተፈጥሮና መልክዓ ምድር ጋራ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ያስተሳሰረ ነበር። ያደጉበት ባሕልና እሴት ደግሞ ከሰዎች ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንዲያዳብሩ፣ ሩህሩህ ማንነት እንዲገነቡና ለማኅበራዊ እሴቶች ትልቅ ስፍራ እንዲኖራቸው አድርጓቸዋል። ለዚህ ነው ሁለንተናዊ ስብዕናን የገነቡ መነሻቸውንም ሆነ መድረሻቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ ትጉህ ሰው ለመሆን የበቁት።
ከፍተኛ ትምህርት
ዶክተር በላይ አበጋዝ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በከፍተኛ ውጤት ካጠናቀቁት መካከል ናቸው። ይህንን አቅማቸውን የተገነዘበው በሐረር የሚገኘው የያኔው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የጦር አካዳሚ ለውትድርና ትምህርት ከመረጣቸው ባለ ብሩህ አዕምሮ መካከል አንዱ ነበሩ። በጊዜው የትምህርት ውጤታቸው ከፍተኛ የሆኑ ተማሪዎች በአካዳሚው እየተመረጡ የውትድርና ሳይንስን በማጥናት በከፍተኛ የሀገሪቱ ቦታዎች ላይ ይመደቡ ነበር። እርሳቸውም ይህ ዕጣ ደርሷቸው በእጩ መኮንንነት ወታደራዊ ሳይንስ ተምረው እስከ ሌተናል ኮለኔልነት ማዕረግ ደርሰዋል:: በጊዜው ከትምህርቱና ወታደራዊ ማዕረጉ ባሻገር በአካዳሚው ለሁለት ዓመታት መምህር ሆነው አገልግለዋል። በጊዜው የነበራቸው ንቁ ተሳትፎና በውትድርና ሙያቸው ባሳዩት የላቀ አፈጻጸምም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አራት ጊዜ ተሸልመዋል፡፡
ዶክተር በላይ አበጋዝ፤ በልጅነታቸው የሕክምና ባለሙያ (ዶክተር) የመሆን ልዩ ፍላጎት ነበራቸው። ይህ ሕልማቸው እውን ይሆን ዘንድ የላቀ የትምህርት ውጤት እንደሚያስፈልግ በማወቃቸው ጠንክረው ለመማራቸው ምከንያት ነበር። ወደ ሐረር አካዳሚ ሲገቡም የልጅነት ሕልማቸውን ታሳቢ አድርገው ነበር። የውትድርና ሳይንስ መማራቸው ደግሞ ይበልጥ ወደ ሙያው እንዲሳቡና ሙሉ ለሙሉ ወደ ሕክምናው እንዲገቡ ገፊ ምክንያት ሆኗቸዋል።
በአካዳሚው ለሁለት ዓመታት ካስተማሩና ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ለአራት ጊዜያት በላቀ አፈፃፀም ከተሸለሙ በኋላ ቀጣይ ጉዞ ያደረጉት የልጅነት ሕልማቸውን ከዳር ወደሚያደርሱበት ዩኒቨርስቲ ነው። የሐረር ቆይታቸው አብቅቶ የሕክምና ትምህርት ለማጥናት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለመግባትና ውጤታማ ለመሆን ጊዜ አልፈጀባቸውም። በ1961 ዓም የዩኒቨርስቲውን የሕክምና ኮሌጅ ተቀላቅለው በትምህርት ቆይታቸው በነበራቸው ውጤታማነት ተሸላሚ ሆነው አጠናቀቁ። የዶክተር በላይ የሕይወት ጉዞ አቅጣጫውን በመቀየር ለማነንነታቸው መሠረት የሆነውን ማኅበረሰብ በጤናው ዘርፍ ለማገልገል መንገዳቸውን ጀመሩ።
እውቀትን ወደ ተግባር
ዶክተር በላይ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የጦር አካዳሚ ብሔራዊ አገልግሎት በውጤታነት አጠናቀው ወደ ሕክምና ትምህርት ገብተዋል። ትምህርታቸውንም በሚገባ ጨርሰው ዳግም ብሔራዊ አገልግሎት ትርጉም ወዳሳያቸው ውትድርና በሕክምና የሙያ መስክ ተመለሱ። በአዲስ አበባ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል በመግባት ለዳር ድንበሩ የሚዋደቅ ወታደር እና ውትድርናን ዳግም ማገልገል ጀመሩ። ይህ ጊዜ በቅርብ ላጠናቀቁት የሕክምና ትምህርት ይበልጥ እንዲቀርቡና ሙያቸውን ተግባር ላይ አውለው ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ ምክንያት የሆናቸው ነበር።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1977 ወደ አሜሪካ ተጉዘው ዳግም የሕክምና ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ሲያገለግሉ ቆዩ። ይህ ቆይታቸው ሙያውን የበለጠ እንዲያከብሩት ኢትዮጵያም በዘርፉ አንድ ተጨማሪ ጉምቱ ባለሙያ የምታፈራበት አጋጣሚን እንዲፈጠር አስቻለ። ይህን ጊዜ ነበር ለተጨማሪ ትምህርት ሀገራቸውን መልቀቅ የግድ የሆነባቸው።
ዶክተር በላይ ከጠቅላላ ዶክተርነት ወደ ስፔሻላይዝድ ያደረገ ሕክምና ባለሙያ ያሸጋገራቸውን ትምህርት በሀገረ አሜሪካ ነበር የተማሩት። በቆይታቸው ዛሬም ድረስ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ስማቸው ገንኖ እንዲጠራ ምክንያት የሆናቸውን የሕፃናት ሕክምና ዶክተር እንዲሁም የሕፃናት ልዩ የልብ ሐኪም የሚያደርጋቸውን ትምህርታቸውን በብሩክሊን ሜዲካል ኮሌጅና በኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ በስኬት አጠናቀቁ። በጥቅሉ በአሜሪካን ሀገር ለ6 ዓመታት ቆይተው ዳግም ሊያገለግሏት ቃላቸውን ወደሰጧት ሀገራቸው ኢትዮጵያ ተመለሱ።
ቁጭት የወለደው ራዕይ
ዶክተር በላይ አበጋዝ ያስተማረ ወገናቸውን አልዘነጉም። ይህንን ማድረግ የሚያስችል ስሪትም አልነበራቸውም። ይልቁኑ በሠለጠነ ሀገር ላይ ምንም ሳይጎልባቸው መማራቸው ሀገራቸውን ይበልጥ እንዲወዱ፣ መልካሙን ሁሉ ለኢትዮጵያ እንዲመኙ ነበር ያደረጋቸው። የሕፃናት የልብና ጠቅላላ ሕክምና ስፔሻላይዝ ማድረጋቸው ደግሞ በኢትዮጵያ ለመታከም አቅም የሌላቸው ዜጎች ዕድል ፈንታ እንዲያሳስባቸው ያደረገ ነበር።
የልብ ሕክምና አሁንም ድረስ እጅግ ውድና ውስብስብ ሁኔታዎችን መጋፈጥ የሚጠይቅ ነው። በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ይህንን ሕክምና በቀላሉ ለማግኘት የሚታሰብ አይደለም። በዚህ ምክንያት ብዙዎች ሕይወታቸውን ያጡ ዘንድ ተገድደዋል። ይህንን እውነት መቀልበስ ደግሞ የዶክተር በላይ የዘወትር ሕልም ነበር።
ለስድስት ዓመት በትምህርት በቆዩባት አሜሪካ ውስጥ ነበር የሕፃናት የልብ ሕክምና በነፃ ለወገናቸው መስጠት የሚያስችል ድርጅት ለማቋቋም ማሰብ የጀመሩት። የመጀመሪያው ውጥናቸው የቻሉትን ያህል ሕፃናት ሕክምናው ወደሚገኝበት ሀገር በመላክ ማሳከም ሲሆን፤ ቀስ በቀስ ደግሞ የልብ ሕሙማን ሐኪም ቤት በሀገራቸው በመክፈት፣ ባለሙያ በማፍራትና በቂ ዘመናዊ መሣሪያዎችን በማሟላት ሕፃናት ታማሚዎችን የመርዳት ግዙፍ እሳቤ ነበራቸው።
ዶክተር በላይ ከአሜሪካ መልስ ሆስፒታሉን መገንባት፣ የሕክምና መሣሪያውን ማሟላት፣ የሰው ኃይል ማግኘትና ዘላቂነቱን ማረጋገጥ የሚሉ አራት የራዕያቸውን ምሰሶዎች በአዕምሯቸው ጠንስሰው መምጣታቸውን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል። በተለይ ‹‹መጀመር ሳይሆን ቁምነገሩ ዘላቂነቱን ማረጋገጥ ነው›› በሚለው ሀሳባቸው ይታወቃሉ።
እርሳቸው ስለዚህ ውጥን ሲገልፁ “በኢትዮጵያ የልብ ሕክምና ማዕከል የማቋቋም ሀሳብ የተጠነሰሰው በ1970 ዓ.ም በአሜሪካ ነው፤ በልብ ሕክምና ሙያ ለመሠልጠን (ስፔሻላይዝድ ለማድረግ) በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቅኩበትን የትምህርት ማስረጃ እና የወደፊት ፍላጎቴን የሚገልጽ ሀሳብ ለኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ አቀረብኩ፤ ቃለ መጠይቅ ያደረገችልኝ ፕሮፌሰር ኢጂኒ ዶይል፤ ‘የምንቀበለው 10 ሰዎችን ነው፤ አንተ የተቀመጥኸው 10ኛ ላይ ነው፤ ባቀረብከው ማመልከቻ ውስጥ ጥሩ እና ደስ የሚሉ ነገሮች አይቻለሁ፤ ስላቀድካቸው ነገሮች ከአንደበትህ መስማት እፈልጋለሁ፤ እውነት ትምህርትህን ስትጨርስ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰህ በልብ ሕክምና ትሠራለህ?’ በማለት ስትጠይቀኝ:: እኔም “አዎ!” በማለት በእርግጠኝነት መለስኩላት” ይላሉ፡፡
ከስድስት ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያን አፈር ከረገጡ ጀምሮ ለውጥናቸው መሳካት ከላይ እታች ይሉ ጀመር። የሚያውቋቸውን ሰዎች የሕፃናት ልብ ሕሙማን መርጃ ማዕከል የማቋቋም ሕልማቸውን በማጋራት ድጋፍ ማሰባሰብ ጀመሩ። ይህንን ተግባራቸውን የሚያከናውኑት ጎን ለጎን በተማሩት የሕክምና ዘርፍ ወገኖቻቸውን እየረዱ በተጨማሪነት ነበር።
በዶክተሩ መዝገበ ቃል ውስጥ ‹‹አይቻልም›› የሚል ቃልም ትርጉምም የለውም። ያሰቡትን ለማሳካት ዓመታትን ፈጅተዋል። መርጃ ማዕከሉ ሕጋዊ ሰውነት ይዞ መቋቋም እንዲችል ብዙ ውጣ ውረድን ያልፉ ዘንድ የግድ ብሏቸዋል። ከዚህ ውስጥ የመንግስት ቢሮክራሲ ቀዳሚው ነው። ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ በተራድዖ ድርጅትነት እንዲመሠረት ፈቃድ የሚሰጥ አካል ተባባሪነት መጥፋቱ ግን ከእቅዳቸው አላሰናከላቸውም።
ኋላ ላይ በብዙ ጥረት ፈቃዱን በማግኘታቸው በ1989 ዓም በይፋ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከልን አቋቋሙ። የመጀመሪያው እቅዳቸው ግቡን መታ። ሕጋዊ የተራድዖ ድርጅት ፍቃድ ከማግኘታቸው በፊት ለ108 የሚደርሱ ሕፃናትን በግላቸው ከውጪ ሕክምና ተቋማት ጋር ግንኙነት እየፈጠሩ በነፃ ሕክምና እንዲያገኙ አድርገው ነበር። በወቅቱ የአንድን ህፃን ሕክምና ለማሳካት በትንሹ እስከ 7 ሺህ ዶላር ይጠይቅ ነበር።
የማዕከሉ እውን መሆን
ዶክተር በላይ የልብ ሕክምና የሚሹ ሕፃናትን እርዳታ በማስተባበር እና ልዩ ልዩ ድጋፎችን በማፈላለግ ማሳከሙን ቀጠሉበት። ሂደቱ በእጅጉ አድካሚና ከፍተኛ ጥረትን የሚሻ ነበር። በጊዜው ግለሰቦች ድርጅቶች (አየር መንገድን ጨምሮ) ያስተባብሩ ነበር። ሆኖም ሕፃናቱን ከነቤተሰቦቻቸው ለመላክ አስቸጋሪ በመሆኑ ሌላ ፈተና ይደቅንባቸው ጀመር። ባዕድ ሀገር አንድን ሕፃን ያለቤተሰቡ መላክ ከሚያገኘው ሕክምና ባሻገር ያልተጠበቀ ድብርት ውስጥ የሚከት ነበር።
እርሳቸውም በልጅነት አዕምሯቸው ታካሚዎቹ የሚፈጠርባቸውን የሥነ ልቦና ጫና ለመቀነስ መላ ይፈይዱ ጀመር። ይህ መፍትሔ ዘላቂ መሆን አለበት፤ የችግሩ ሁሉ መፍቻ ሊሆንም የግድ ይላል። እስከዚያው ግን ሕፃናቱን ወደ ውጪ በመላክ ማሳከማቸውን አላቆሙም ነበር። በዚህም እስከ 2001 ዓም ድረስ 2ሺህ 600 ሕፃናት ወደተለያዩ ሀገራት ተጉዘው ሕክምናውን እንዲያገኙ አድርገዋል።
ከዚህ በኋላ ነበር ከፍተኛ ወጪና ውስብስብ ቴክኖሎጂ የሚጠይቀውን የልብ ሕክምና በዚሁ በሀገር ውስጥ እውን ማድረግ ጊዜው መሆኑን ያመኑበት። ለእቅዱ መሳካት ደግሞ እውቀት፣ ገንዘብ እና ሁሉን አቀፍ ቅንጅት ይጠይቃል። በዚህ ወቅት ነበር ‹‹አንድ ብር ለአንድ ልብ›› የሚል ንቅናቄ በዶክተር በላይ አበጋዝ ሀሳብ ጠንሳሽነት በመላው ኢትዮጵያ የተጀመረው።
ይህ ገንዘብ ማሰባሰቢያ ሥርዓት ሆስፒታሉን ለመገንባት እንዲውል ታስቦ የተጀመረ ነበር። ሂደቱ ከፍተኛ መነሳሳትን ፈጠረ። በውጤቱ በነበረው መንግሥት እውቅናን ተቸረው። ባለሀብቶችም እጃቸውን ዘረጉ። የዶክተር በላይ ለበርካታ አስርተ ዓመታት ሲለፉበት የነበረው ሕልማቸውን እውን የሚያደርጉበት ጊዜ ደረሰ። እዚህ ጋር ነበር የሼህ መሐመድ አላሙዲን ታላቅ ውለታ የሚነሳው።
ሼህ መሐሙድ አላሙዲን በጊዜው የዶክተር በላይ አበጋዝ ራዕይ ገዛቸው። ለዓላማቸው እውን መሆን የድርሻቸውን ሊወጡ ወሰኑ። በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ ለማዕከሉ በመንግሥት በተሰጠው ቦታ ላይ 100 ሚሊዮን ብር በሚፈጅ ወጪ ለልብ ታማሚ ሕፃናት በነፃ ሕክምና የሚሰጥ ማዕከል ተገነባ። ዘላቂነቱ እንዲቀጥል ደግሞ በብሥራተ ገብርኤል አካባቢ ማዕከሉ የሚያስተዳድራቸው ሕንፃዎች ተገነቡ ።
‹‹ኢትዮጵያ ተመልሰህ የልብ ሆስፒታል በሌለበት፣ መሣሪያ በሌለበት፣ ባለሙያ በሌለበት፣ እንዴት ነው የልብ ሕክምና እሠራለሁ የምትለው?›› የሚለው የዶክተር በላይ መምህር ጥያቄ መልስ አገኘ። ባለራዕይው የሀሳባቸው ተገዢ መሆናቸውን አስመሰከሩ። እቅዳቸውን ለማሳካት ዓመታት ቢፈጅባቸውም ተስፋ ሳይቆርጡ በኢትዮጵያውያን ቀናነትና በባለሀብቱ ሼህ መሐሙድ አላሙዲን ከፍተኛ አስተዋፅዖ ሆስፒታሉን ገነቡት።
ዘመናዊ የልብ ቀዶ ሕክምና መሣሪያዎች “ቼይን ኦፍ ሆፕ ዩኬ” በሚባል ድርጅት ተሟላላቸው:: የልብ ቀዶ ሐኪሞች (ካርዲዮሎጂስቶች) ደግሞ የሚኒያፖሊስ የልብ ቀዶ ሐኪም በሆኑት በዶክር ቪብ ክሸንት እና ታዋቂ በሆነው የሕንድ ናርያና ሆስፒታል ሠልጥነው ዝግጁ ሆኑ:: ዶክተር በላይ እውቀት፣ ሀብት እና አንድነትን አስተባብረው በሺዎች ለሚቆጠሩ ሕፃናት ደረሱ።
የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከሉ በ2001 ዓ.ም ምረቃው ተደርጎ በይፋ በአገር ውስጥ የልብ ሕክምና አገልግሎት መስጠት ጀመረ። ዶክተር በላይ ውለታ አይረሱምና የታላቁ ባለሀብት ሼህ አሕሙድ አላሙዲን ከፍ ያለ አስተዋፅዖ የሚዘክር ማስታወሻ አኑረውላቸዋል። ማዕከሉ በአንድ ሰው ራዕይ እዚህ ይድረስ እንጂ ለተግባራዊነቱ በርካቶች የድርሻቸውን ጡብ ማስፈራቸውን ይናገራሉ።
ለዚህም ነው ምስጋና ከአፋቸው የማይጠፋው። በተለይ ዶክተር በላይ ማዕከሉ ተቋማዊ መልክ እንዲይዝ የቦርድ አባላትንና ሥራ አስፈፃሚ በማዋቀር ለ16 ዓመታት እንዲመራ ዘላቂ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው ተግተው ሠርተዋል። በሂደቱም በርካቶች ለዚህ በጎ ዓላማ ተሰልፈዋል። አሁንም ድረስ አርቲስት መሠረት መብራቴን ጨምሮ በርካታ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የዚህ ራዕይ ተጋሪ ሆነው ይገኛሉ።
በጎነት በዚህ ልክ ለምን?
በዶክተር በላይ የማዕከሉ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ‹‹ጨለማን ከመርገም አንድም ሻማ ቢሆን መለኮስ ይሻላል›› የሚል አባባል ተሰቅሎ ይገኛል። አሁን እርሳቸው በጡረታ ጊዜ ላይ ቢሆኑም ይህ ጥቅስ ግን ከግድግዳው ላይ አልተነሳም። ማዕከሉን ተረክቦ የሚያስተዳድረው አዲሱ ትውልድ ተቋሙን ለማስቀጠል በሚያስችሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሲወያይ በዚህ ቢሮ ይሰበሰባል። ይህ አጋጣሚ የእርሳቸው ራዕይ ከተቻለ በተሻለ መልኩ ለማስቀጠል አሊያም ባለበት ሳይንገዳገድ እንዲቆይ ብርታትን ለአመራሮቹ የሚሰጥ ነው። እርሳቸውም ቢሆን ይህንን ምክር ለግሰው ነው በጡረታ ከማዕከሉ በክብር የተሰናበቱት።
‹‹በእውነት ሰው የምንሆነው ለሌሎች ማሰብ የጀመርን ቀን ነው›› የሚል አባባል አላቸው የእርሳቸው የመኖር ፍልስፍና በዚህ ጥብቅ የበጎነት እሳቤ ላይ የተመሠረተ ነው። ራዕያቸው ከራሳቸው አልፎ በሌሎች ላይ የመጋባት ኃይል አለው። ኢትዮጵያዊ ፍቅር፣ ሩህሩህነት ያላብሳል። በእርሳቸው እሳቤ ሰው ሆኖ አንድም የማይጠቅም የለም። ተፅዕኗችን ምንም ያህል ጥቂት ቢመስለንም ለውጥ በበጎነት ላይ ከተሳተፍን ለውጥ ማምጣት እንደምንችል በተደጋጋሚ ሲመክሩ ተደምጠዋል።
እሳቸው ከ1970 ዓ.ም ጀምሮ ተግተው መሬት እንዲነካና ወጤታማ እንዲሆን ያደረጉት የሕፃናት የልብ ሕሙማን መርጃ ማዕከል አሁንም የዚህኛውን ትውልድ ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ ይሻል። ማዕከሉ ተገንብቶ፣ መሣሪያዎች ተሟልተውለት ሥራ ቢጀምርም አሁንም ድረስ በአላቂ ዕቃዎች ምክንያት በሙሉ አቅም የሚፈለገውን ግልጋሎት አለመስጠቱ እንደ ምክንያትነት ይነሳል። ዛሬም በጎ ልብ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ለማዕከሉ እርዳታ በማሰባሰብ አምባሳደር በመሆን እየተጉ ቢገኙም በቂ ግን አይደለም። በኢትዮጵያ የልብ ሕክምና የማግኘት አጋጣሚው ፍፁም ቀላል እስኪሆን ድረስ መሥራትን ይጠየቃል። ዶክተር በላይም ራዕዩን ሁሉም ይጋራው ሲሉ በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።
ዶክተር በላይ በኢትዮጵያ ሕክምና ዘርፍ ላይ የገዘፈ አሻራን ማኖር ችለዋል። እርሳቸው ግን ከዚህም ያለፈ ራዕይ አላቸው። የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከሉን ከመመስረታቸው ባሻገር እውቀትና ጉልበታቸውን ለልዩ ልዩ ትርጉም ያላቸው ተቋማት ሳይሰስቱ ሰጥተዋል። የሕጻናት ሕክምናን በማስተማር፣ ስለ ሙያውም ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን በማሳተምም ይታወቃሉ፡፡
በዚህ ሳያበቁ ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ የአሜሪካ ፔዲያትሪክስ አካዳሚ፣ የኢንተርናሽናል ሶሳይቲ ኦፍ ሃይፐርቱንሽን ኢን ብላክስ፣ ፓን አፍሪካን ሶሳይቶ ኦፍ ካርዲዮሎጂ እና የ ዘ ናሽናል ድራግ አድቫይዘሪ ቦርድ ኦፍ ኢትዮጵያ አባል ሆነው አገልግለዋል። የኢትዮያን ሜዲካል ጆርናል በአባልነት፣ በረዳት ዋና ጸሐፊነት እና በሊቀ መንበርነት አገልግለዋል፡፡
በሀገር በቤተሰብ ጠንካራ እምነት ያላቸው እኚህ ታላቅ የኢትዮጵያውያን ባለውለታ ከባለቤታቸው ሲስተር ሐና በላይ 1965 ትዳር መሥርተው ሁለት ወንድ ልጆችን አፍርተዋል። ልጆቻቸው የእርሳቸውንና የባለቤታቸውን የሙያ ፈለግ የተከተሉ ናቸው።
የሕይወት ዘመን አበርክቶ
የዶክተር በላይ የሕይወት ዘመን ስኬቶች አንዲሁ በአጭር ጽሑፍ ተዘርዝሮ የሚያበቃ አይደለም። ይሁን እንጂ ተፅዕኗቸው በእያንዳንዱ ኢትዮጵያውያን ደጃፍ የደረሰ ነበር። ለዚህ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ደጋግመው አመስግነዋቸዋል። ለበርካታ አስርተ ዓመታት ሀገራቸውን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለሠሩት ሥራ በ2008 ዓ.ም በልብ ሕክምና ዘርፍ ባደረጉት በጎ አስተዋፅዖ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ማዕረግ ተቀብለዋል::
በ2006 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚ ነበሩ፤ የልብ ሕሙማን ሕክምና መርጃ ማኅበር ምስረታ 30ኛ ዓመት ሲከበርም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እጅ የሕይወት ዘመን አገልግሎት ዕውቅና የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ዶክተር በላይ ከዚህም ያለፈ ለትውልዱ ማስተማሪያ የሚሆን ማስታወሻዎች ሊኖራቸው እንደሚገባ የዝግጅት ክፍላችን ያምናል።
የእርሳቸው የሕይወት ዘመን ሥራዎች በሙዚየም ውስጥ ሊቀመጡ ይገባል። ይህ መሆኑ በጎነት በመጪው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ጉልህ ስፍራ እንዲኖረው ያስችላል። በዘመናቸው ታላላቅ ውለታዎችን ለሀገራቸው ሠርተው ያለፉ ኢትዮጵያውያን የሚዘክርና ሥራዎቻቸውን በመሰነድ በሙዚየምነት የሚያስቀምጥ ተቋምም ያስፈልጋል።
ማዕከሉ ዛሬ
የዶክተር በላይ ራዕይ የወለደው የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል ዛሬ 10 ሺህ ለሚደርሱ ሕፃናት እፎይታን ሰጥቷል። ዛሬም ድረስ በማዕከሉ ወረፋ የያዙ ሕክምናን የሚሹ ሕፃናት ይገኛሉ። በተጠባባቂ ዝርዝር ውስጥ 7 ሺህ የሚደርሱ ሕፃናት ይገኛሉ። የማዕከሉ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ኅሩይ ዓሊ ማዕከሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ የልብ ሕሙማን በአቅም ውስንነት መድረስ አይችልም ይላሉ። ሁሉም ኢትዮጵያውያን ከተረባረቡ ግን የመሥራቹን ራዕይ እውን ማድረግ ይቻላል ይላሉ።
ማዕከሉ የዶክተር በላይ አበጋዝ ራዕይ የወለደውን ተቋም ለማስቀጠል የተለያዩ ስልቶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ አንዱ የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄዎችን ማካሄድ ነው። በዚህ በያዝነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የገና ፆም ወቅት እስከ በዓሉ ድረስ የሚቆይ የርዳታ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ይፋ አድርጓል። የተለያዩ ዘላቂ የገቢ ማሰባሰቢያዎችም መንገዶችንም ለመፍጠር እየሠራ ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ይህንን ንቅናቄ የተቀላቀሉ ኢትዮጵያዊ ታላላቅ ተቋማት መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ኅዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም