ብርቱዎቹ ሴቶች ለብርቱ ሥራ ታጭተዋል

በሕይወት አጋጣሚ በርካታ ፈተናዎች ያጋጥማሉ። በሴቶች ላይ የሚደርሱት ፈተናዎች ደግሞ በባህሪም በክብደትም የላቁ እንደሆኑ መረጃዎች ያመላክታሉ። ከእነዚህ ውስጥም በትምህርት ብቁ ሆኖ ለመገኘት የሚያልፉበት መንገድ አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል። ሴቶች የእውቀት አድማሳቸውን ለማስፋት ሲታትሩ ከወንዱ በተለየ መልኩ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ማለፍ ግድ ይላቸዋል። ራሳቸውን ለማሳደግና ለማጎልበት መጀመሪያ የ‹‹እችላለሁ›› መንፈስን መገንባት ይኖርባቸዋል።

ብዙ ግዜ ማኅበረሰቡ የሚጭንባቸውን ብቻ ሳይሆን ‹‹ይችላሉ›› የሚላቸውን ጭምር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ለዚህም ተፈጥሯቸው ያግዛቸዋልና አስበውና አሰላስለው የሚወስኑ፤ ነገሮችን በብዙ ዓይን የሚያዩ እንደሆኑ ይታመናል። ይህንን እውን አድርገው ያሳዩ እንስቶች በርካቶች ቢሆኑም ግዜና አጋጣሚ ግን ይፈልጋሉ።

አብዛኛውን ግዜ ሴቶች በልዩ አጋጣሚ ካልሆነ በቀር ራሳቸውን ገልጠው አያሳዩም፤ አደባባይ ወጥተውም ጠንካሮች ስለመሆናቸው አይመሰክሩም። ልዩ አጋጣሚዎቹ በራሳቸው ካላስገደዷቸው በቀርም እነርሱን ፈልጎ ለማግኘት አስቸጋሪ የሚሆንበት ዕድል የሰፋ ነው። እኛም ብንሆን በአንድ ልዩ አጋጣሚ ነበር ብርቱ ናቸው ያልናቸውን ሴቶች ያገኘናቸው። ይህ ልዩ አጋጣሚ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በመዲናዋ በሚገኙ ሦስት ዩኒቨርሲቲዎች (ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ እና አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ) በ2016 ዓ.ም ከ3 ነጥብ 5 በላይ ውጤት በማምጣት በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቁት እንስት ተማሪዎችን የሸለመበት ዕለት ነበር።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት በ2016 ዓ.ም 3 ነጥብ 94 ውጤት በማስመዝገብ በሕግ በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቃ በዩኒቨርሲቲው የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ለመሆን የበቃችውና በቢሮው አማካኝነት ዳግመኛ ሽልማት የተበረከተላት ፍቅር ሽመልስ በቀዳሚነት ያገኘናትና ያነጋገርናት ወጣት ነች። ፍቅር ዘመኑ የውድድር እንጂ በፍላጎትና በምኞት የሚገባበት፤ ያሻነውን እንደልብ የምናገኝበት እንዳልሆነ ታምናለች። ብዙ ጥረትና ግረትን እንደሚፈልግ፤ በተለይም ለሴቶች ከመጀመሪያ ደረጃ ካልተቻለ ደግሞ ከሁለተኛ ደረጃ ይህም ካልሆነ ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ ጎበዝ የመባልን ስሜት ማዳበር፤ በእውነት ራስን ማጽናት እንደሚጠይቅም ታስባለች።

ሴቶች ያሉባቸው ፈተናዎች ከመመረቅ በላይ ነው የምትለው ፍቅር ተወዳድሮ ማሸነፍንና ትችላለች መባልን ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ጭምር ማሳየት ካልቻሉ ነገሮች እንደሚከብዷቸው ትገነዘባለች። በዚህም የተነሳ ገና ትምህርቷን ስትጀምር ይህንን እያደረገች እንደተጓዘች ታወሳለች። ዩኒቨርሲቲውን መቀላቀል በቀላሉ እንደማትችል ስለተረዳችም ገና ወደ ዩኒቨርሲቲው ሳትገባ ጀምሮ ዝግጅት ስታደርግ ነበር። የመረጠችውን እንደምታገኝ አምናም ትሰራ ነበር። በዚህም የ12ኛ ክፍል ውጤቷ ከፍተኛ እንዲሆን አስችሏታል። አልፋ ተርፋም ፍላጎቷ ሕግ መማር ስለነበር የሕግ ትምህርት ቤትን እንድትቀላቀል ሆናለች።

የፍቅር ሀሳብ ዩኒቨርሲቲውን መቀላቀል ብቻ አልነበረም። ከዚያም በላይ የላቀ ምኞትን የያዘ ነው። ትምህርቷን ስታጠናቅቅ የማዕረግ ተመራቂ ሆና የወርቅ ሜዳሊያ አንገቷ ላይ ማጥለቅን ትሻለች። ግቧን ለማሳካትም መጀመሪያ ዓመት ወደ ዩኒቨርሲቲ ስትገባ፤ ውስጧን አሳምና “በይቻላል” መንፈስ እቅድ በመያዝ ነበር። ሙሉ ትኩረቷን ለትምህርቷ ሰጥታም ጠዋት ማታ ለፋች። ጊዜዋን በአግባቡ ተጠቀመች።

‹‹ሴትን ልጅ የሚያስተምራት ብዙ ነገር ነው። አንዱ ጊዜ ነው።›› የምትለው ፍቅር፤ በጊዜ ምን ያህል ተጠቅማ ለስኬት እንደምትበቃ ቀድማ ተረድታለች። በዚህም በዩኒቨርሲቲ ውስጥ መምህር ብቻ ሳይሆን አስተማሪው ጊዜም ነው በማለት የሚያልፋት ነገር ሳይኖር ሰርታለች። ሴትነቷ ሳይበግራትም ያቀደችውን አግኝታለች።

ጊዜ በተለይ ለሴቶች ልዩ ትርጉም እንዳለው የምታስረዳው ፍቅር፤ ጊዜን በአግባቡ የምትጠቀም ሴት ነገዋን ያማረ ታደርጋለች፤ አለቆቿን ትቀንሳለች፤ በማኅበረሰቡ ዘንድም አክብሮትና ተዓማኒነትን ታገኛለች። የሥራም ሆነ ሌሎች አማራጮቿን ታበራክታለች። በአጠቃላይ ማንነቷን ለሌሎች የምትገልጥበትን መንገድ ትፈጥራለች ስትልም የራሷን ተሞክሮ ታነሳለች። ብዙ ሴት ተማሪዎች ደፍረው በማይገቡበት የሕግ ትምህርት መስክ ገብታ በከፍተኛ ማዕረግ የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቃ እንድትመረቅና ለሌሎች እንስቶች አርአያ እንድትሆን ያስቻላት ጊዜን በአግባቡ በመጠቀሟና በእቅድ በመመራቷ መሆኑን ትናገራለች።

‹የሴት ልጅ ስኬት ዝም ብሎ የሚመጣ አይደለም። ብዙ ትግልና ልፋትን ይጠይቃል። ሁልገዜ ማሸነፍንም ይፈልጋል። የሚሸነፈው ደግሞ አንድ ነገር ብቻ አይደለም። ማኅበረሰቡን አሳምኖ ጭምር ነው‹‹ትችላለች››ን መቀበል ይጠይቃል። ለዚህም የተሰጠንን ጊዜ በአግባቡ መጠቀም ይገባል።›› የምትለው ፍቅር፤ በአምስት ዓመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ይህንን ያደረገችው ከዚህ አኳያ መሆኑንም ታብራራለች። አክላም ማንኛውም ተግባር ትምህርትን ጨምሮ በእቅድ መመራት እንዳለበት ታስረዳለች። እናም ከጊዜ አጠቃቀም ባሻገር በአቅድ መስራት የስኬት መድረሻ ቁልፍን እንደማግኘት መሆኑን ታምንበታለች።

ፍቅር ‹‹ እቅድ ዛሬ ላስመዘገብሁበት ውጤት የመንገድ መብራት ነው። እቅድ መዳረሻችሁን ያሰፋላችኋል፤ ተፈላጊነታችሁን በማብዛትም ተወዳዳሪነታችሁን ከፍ ያደርጋል። አሁን ‹የት እገባ ይሆን› የሚለውን ጭንቀትም ያቀላል። ምክንያቱም በእቅድ ተመርታችሁ ውጤታማ ከሆናችሁ ፈላጊያችሁ ብዙ ነውና። ሁልግዜ ቅጥርን ብቻ አታስቡም። የራሳችሁን ሥራ የምትሰሩና ትርፋማ የምትሆኑ ዜጋ ያደርጋችኋል። እቅድ ከሌላችሁ ግን መዳረሻችሁን ልታውቁ አትችሉም። ዝም ብላችሁ የምትባትሉና በሌሎች ጫንቃ ላይ የምትሳፈሩ ያደርጋችኋል።›› ትላለች።

ሴቶች በትምህርቱም ሆነ በሌላው መስክ ውጤታማ ለመሆን ግልጽ እቅድ ማስቀመጥ ይኖርባቸዋል። ለውጤት ታትሮ መሥራት ይገባቸዋልም ስትል ልምዷን ታጋራለች። በርትቶ አጥንቶ በጥሩ ውጤት በማዕረግ መመረቅ ብቻውን በቂ እንዳልሆነም ጠቅሳ፤ ይህ እድል ግን መናቅ እንደሌለበት ታነሳለች። ምክንያቱም በከፍተኛ ማዕረግ መመረቅ በራሱ የሥራ በሮችን ሳናንኳኳ ማስከፈት እንደሆነ ታምናለች። ለዚህም እንደ ማሳያ የምትጠቅሰው የራሷን ተሞክሮ ነው። በጥሩ ውጤት በመመረቋ ከዩኒቨርሲቲው በር እንደወጣች ቀጥታ በዓለም አቀፍ ተቋም ውስጥ በሙያዋ ተቀጥራ እንድትሠራ ሆናለች።

የሕግ ምሩቋ ፍቅር እንደምትለው፤ ብዙዎች ውጤታማ በመሆናቸው በዚያው በዩኒቨርሲቲው የመቀጠር እድል አላቸው። የማይፈልጉ ከሆነ ደግሞ በራሳቸው ሥራ ለመፍጠር አይፈሩም። ውጤታማነታቸው በራስ የመቆም ባህልን እንዲያዳብሩ አግዟቸዋልና። በተለይም ሴቶች ይህንን እድል ሲያገኙ የሚወጡት የሚወርዱበት ፈተና ብዙ ልምድን የሚያቀዳጃቸው ነው። በዚህ ውስጥ ሲያልፉ ደግሞ እያንዳንዱ ነገር ያስተምራቸዋል። ነገን እንዴት እንደሚኖሩም እንዲረዱ ይሆናሉ። ችግር ቢገጥማቸው እንኳን እንዴት ማምለጥ እንዳለባቸውም ያውቃሉ።

ሴቶች ጥሩ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ የእህቶቻቸው ችግሮች ያሳስቧቸዋል። በሥራቸው ሁሉ ዘወትር እነርሱ እንዲካተቱ ይፈልጋሉ። ሴቶችን ማብቃት ራስን መተካት እንደሆነ ግልጽ ነውና በተሰማሩበት ሙያ ሁሉ ቢያግዟቸው ይመኛሉ። ለዚህም ራሴን አብነት ማድረግ እፈልጋለሁ ትላለች።

ፍቅር ‹‹እኔ ከሥራዬ ጎን ለጎን በርካታ ሥራዎችን ለማከናወን አቅጃለሁ። በተለይም ሴቶችን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በስፋት መስራት አስቤያለሁ። ከእነዚህ መካከልም በኢትዮጵያ ብሎም በአህጉሪቱ በሕግ ትምህርት የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል ማህበር ማቋቋም በዋናነት የሚጠቀስ ነው። ለዚህም ከሌሎች የሙያ አጋሮቼ ጋር እየመከርን እየተንቀሳቀስን ነው። ከዚህ ባሻገር በቀጣይ በሙያዬ የሴቶችን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ በኢትዮጵያ ሴቶት የሕግ ባለሙያዎች ማህበር በኩል ለሴቶች ነጻ የሕግ ማማከር አገልግሎት በመስጠት ላይ እሰራለሁ።›› ስትልም የቀጣይ እቅዶቿን አብራርታልናለች።

ሴቶች ጎበዝ፣ አንደኛ የሚሉ ንግግሮችን እየለመዱ ሲመጡ ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ ማለትን አያስቡም የየምትለው ደግሞ ሌላኛዋ ተሸላሚና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ላብራቶሪ የትምህርት ዘርፍ 3 ነጥብ 8 በማምጣት የተመረቀችው ተማሪ ኤፍራታ ወልደአረጋዊ ነች። ኤፍራታ እንደ ፍቅር ሁሉ ሴቶች ምቹ ሁኔታዎች ከተፈጠረላቸው በማንኛውም የትምህርት ዘርፍ ላይ ውጤታማ ይሆናሉ የሚል እምነት አላት። ሴቶች ከፍተኛ ውጤት ብቻ ሳይሆን ሀገር የሚለውጥ ተግባርን ጭምር የመከወን አቅም እንዳላቸው እንደዓለምም ሆነ እንደ አህጉር እንዲሁም እንደ ሀገር የሚታይ ሀቅ ስለመሆኑ ታነሳለች።

‹‹ሴቶች ወንዶች የተለዩት የሚያዩት የዛሬን ብቻ ሳይሆን የቀጣዩንም ጭምር ነው። ነገ ላይ መስራት፤ መደገፍ ስላለባቸው ነገር ያልማሉ። እንደ ሀገር ምን መስራት እንዳለባቸውም ያስባሉ። ትልቅን ቦታ እንጂ ትንሹን፤ ወዳታች የሚወርዱበትን ሁኔታ አይፈልጉትም። ከዚህ አንጻርም ሴቶች ብዙ ጊዜ የሚፈተኑት መጀመሪያ አካባቢ ነው። ነገሮችን ለመሞከር ይጨነቃሉ። ‹‹አላውቀውም፤ ይከብደኛል›› የሚሉ ነገሮችንም ያዘወትራሉ። ነገር ግን በግድም ይሁን የተመቻቸ ነገር ኖሯቸው ወደ ትምህርትና ሥራው ከገቡ በኋላ የሚቀድማቸው አይኖርም። ግባቸውን ለመምታት የቻሉትን ከማድረግም አይቦዝኑም። ይህ ደግሞ ከሚፈልጉት ስኬት ላይ ያደርሳቸዋል›› ትላለች።

ሴቶች እድል እንጂ አቅም እንዳላነሳቸው ራሷን ምስክር አድርጋ የምትጠቅሰው ኤፍራታ፤ ‹‹እኔ በትምህርት ቆይታዬ አንዳንድ ነገሮችን ብሳሳትስ ብዬ እፈራለሁ። በዚህም ብዙ ነገሮች አምልጠውኝ ነበር። ይሁን እንጂ ከብዙ ትግል በኋላ ራሴን በመምከር መሞከርን ልምዴ አደረግሁ። በዚህም የማልችላቸውን ችዬ አየሁ፤ የተሻልኩ ለመሆንም በቅቻለሁ። በተለይም በተግባር ስራ ላይ ውጤታማ የሚያደርገኝን ነገር አገኘሁ።›› በማለትም ስለ ለውጧ ነግራናለች። አክላም ሴቶች በምትማሩበትም ሆነ በምትሰሩበት ጊዜ እየፈራችሁም ቢሆን ከመሞከር አትቦዝኑ፤ የተሻለው ለእናንተ እንደሚገባ አምናችሁ ሥሩ ስትል ትመክራለች። በመሞከር ውስጥ እምነት፤ ጥንካሬ ይገኛል። ተመራጭነትና ተወዳዳሪነትም ይበዛል። ስለሆነም ሞክራችሁ ስለተሳሳታችሁት ሳይሆን ሞክራችሁ ስላሳካችሁት ነገር እያሰባችሁ ነጋችሁን ስሩ ስትልም ምክሯን ትለግሳለች።

ኤፍራታ ‹‹በትምህርትም ሆነ በሥራችን ጠንክረን ስንወጣ ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን እንጠቅማለን፤ አቋማችንን ማንም እንዳይገፋው እናደርጋለን፤ አቅማችን የት ድረስ እንደሆነ እናሳውቃለን፤ በራሳችን ላይም ሆነ በሌሎች ላይ ወሳኝ እንድንሆን እድል እናገኛለን፤ በተለይም እኛ ሴቶች ምን ያህል እንደምንችል መንገር ሳይሆን ማሳየት እንድንችል እንሆናለን። በጥረታችን ያገኘነው ከፍተኛ ውጤት ከማንም እንደማናንስና ለሰዎች ሁሉ የተሰጠ ቦታ የእኛም እንደሚሆን እናረጋግጣለን። ተሰሚነታችንን፤ ተቀባይነታችንንም እናሰፋለን። በአጠቃላይ ተግባራችን ፓስፖርት ሆኖን በፈለግነው ቦታ እንድንገባ እንሆናለን። እናም ይህንን ተጠቅመን በስራ ሕይወታችንም ስኬታማ መሆን ይገባናል›› ስትል በመጨረሻ መልዕክቷ ታሳስባለች።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You