ኢትዮጵያ በለውጥ ምህዋር ላይ ትገኛለች። ይህ ለውጥ ብዙ መልካም ነገሮችና ስኬቶች እንዳሉት ሁሉ ፈተናዎችም አሉበት። እነዚህን ፈተናዎች በትዕግስት፣ በጽናትና በአንድነት እያለፉ መልካም ነገሮችና ስኬቶችን ይዞ ወደፊት መጓዝ የግድ ይላል።
በመጪው መጋቢት 24 ቀን 2015 ዓ.ም አምስተኛ አመቱን የሚደፍነው የሀገራችን የለውጥ ጉዞ በበርካታ ድሎች የታጀበ ነው። ታላላቅ ፕሮጅክቶች ተጀምረው የተጠናቀቁበት፣ አደጋ ላይ የነበሩ እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶችም ከችግራቸው ወጥተው በስኬት ተጉዘው ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት የጀመሩበት የለውጥና የድል ዘመን ነው።
በግንባታ ሂደት ያሉት የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች እንዲሁም ተጠናቀው ስራ የጀመሩት የወዳጅነት ፓርክ፣ የአንድነት ፓርክ የሳይንስ ሙዝየም እና ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች የለውጡ ቱሩፋቶች ናቸው። በሀገር በቀል የኢኮኖሚ መርሃ ግብርም እነዚህን የለውጥ ትሩፋቶች ላይ ተጨማሪ ውጤት ማስመዝገብ የሚያስችሉ ሥራዎች በግብርና፣ኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፍ ተሰርተዋል፤ እየተሰሩም ነው።
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባትም ዘላቂነት ያለው የ 10 ዓመታት የኢኮኖሚ ዕቅድ ተቀርፆ ተግባራዊ እየተደረገ ነው። ዕቅዱ በግሉ ዘርፍ የሚመራ፣ ተወዳዳሪ፣ ሀብት ቆጣቢ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የኢንዱስትሪ ኢኮኖሚ ሽግግርን በማሳለጥ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገትን ለማስፈን ያለመ ነው።
በሀገር በቀሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብርም በዘላቂ ዕድገት መርሆዎች የተደገፈ በመሆኑ፤ ለግብርና፣ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለቱሪዝም፣ ለኢኮኖሚ ዕድገት ቁልፍ ምሰሶዎች ቅድሚያ ይሰጣል።
በታዳሽ ኃይል ልማት ዘርፍም ከውሃ፣ ከነፋስ፣ ከጸሃይ እና ከእንፋሎት ሃይል በማመንጨት እና እነዚህን እምቅ ሀብቶች መሰረት በማድረግ እአአ 2050 የካርበን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ ነው።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ለተከታታይ አራት ዓመታት 25 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል። ይኸው ስኬት 64 ሚሊዮን በጋዝ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ለአንድ ዓመት ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን የተበከለ አየር የሚያስቀር ነው።
ይህ ውጤት የተገኘው ባለፉት አራት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ 25 ሚሊዮን ዜጎች ችግኞችን በማፍላት፣ የችግኝ ጉድጓድ በመቆፈር፣ በመትከል በመንከባከብ በመሳተፋቸው ነው። በውጤቱም 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ በአፈፃፀም ግን 25 ቢሊዮን ችግኝ ተተክለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻው ሲጀመር 40 ሺህ ብቻ የነበሩት የችግኝ ማፍያዎች አሁን ላይ ወደ 121 ሺህ አድገዋል። በዓመት ሰባት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ችግኝ የማፍላት አቅም ላይ ደርሰዋል። አረንጓዴ ባህልን ከመፍጠር ባለፈ ዘመቻው ለ767 ሺህ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ያበረከተው ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦም ቀላል አይደለም።
በግብርና ልማትም በተለይ በፍራፍሬና ስንዴ ልማት፤ በበጋ መስኖ በተሰሩ ስራዎች የስንዴን ወጪ ንግድ ማድረግ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል። በሌሎችም ዘርፎች ተመሳሳይ ድሎችና እድሎች አሉ። ይህን መልካም ስራ፣ ድልና እድል አሟጦ በመጠቀም የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ደግሞ በትዕግስት፣ በፅናትና በአንድነት በማለፍ የብልጽግና ጉዞን የተቃና ማድረግ ያስፈልጋል።
ከላይ የተዘረዘሩትም ሆነ ያልተገለፁት ስኬቶች፣ ድሎችና ዕድሎች ቢኖሩም በአንፃሩ ደግሞ ፈተናዎች አሉ። ከእነዚህ ፈተናዎች አንዱ ከፀጥታና ደህንነት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥመው ነው። ይህ ፈተና የሚመነጨው ካልዳበረ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ባህል እንዲሁም የተቋማት ግንባታ ጠንካራና ዘላቂነት ያለው አለመሆን ነው።
የሃሳብ ልዩነት በውይይትና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፍታት ሲገባ፤ ሥልጣንም በምርጫ መያዝ የግድ ሆኖ እያለ፣ የሚሸጥ ሃሳብ ይዞ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ጥረት ማድረግ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሁሁ መሆኑ እየታወቀ፤ ይህን ወደ ጎን በመተው በግጭት ለማትረፍ የሚፈልጉ ኃይሎች የብልጽግና ጉዞው፣ ድሎቹና ዕድሎቹ ላይ ፈተናዎች በመሆናቸው በጽናት ታግሎ ማለፍ ይገባል። ሕዝብም ሆነ ሀገር ከሰላም እንጂ ከግጭት ማትረፍ እንደማይችል ለሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ ከነበረው ጦርነት ተምሮ የግጭት ነጋዴዎች በአንድነት በቃችሁ ሊላቸው የግድ ነው።
ከዋጋ ንረትና ኑሮ ውድነት ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ ፈተናዎችም በተለይ ሰው ሰራሽ የሆኑትን የንግድ ሥርዓቱ ዘመናዊ በማድረግና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ መፍታት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ብቻውን ሳይሆን ኅብረተሰቡንም ባሳተፈ መልኩ መስራት የግድ ይላል። በመልካም አስተዳደር ረገድ የሚስተዋሉ ችግሮችንም የአሰራር ሥርዓት በማዘመን መልካም አገልግሎት በመስጠት ማስተካከል ይገባል።
በአጠቃላይ መፃኢ የሀገራችን እድል ከፈተና ይልቅ ተስፋ ድልና ዕድሎች የሚበዙበት ነው። ስለሆነም ሁሉንም ችግሮችና ፈተናዎች ከእኛ ጥንካሬ በታች መሆናቸውን አውቀን በፅናትና በአንድነት ታግለንና ሰርተን ማሸነፍ አለብን!
አዲስ ዘመን መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም