ኢትዮጵያ ከሰብል ምርት በተጨማሪ በሆልቲካልቸር ዘርፍ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማምረት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ከጀመረች ሁለት አስርት ዓመታትን ማስቆጠሯን መረጃዎች ያመለክታሉ። ዘርፉ ከእድሜ አንጻር በርካታ አመታትን ያስቆጠረ ባይሆንም፣ አበረታች ውጤት እየተመዘገበበት ይገኛል። አገሪቷ ለዘርፉ ምቹ የሆነ የአየር ንብረት፣ ውሃ፣ ለም አፈርና በቂ ሰው ኃይል ያላት መሆኑ ዘርፉን ስኬታማ እንዲሆን አስችለውታል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በሆርቲካልቸር ዘርፍ ከፍተኛ መነቃቃት እየታየ ይገኛል፤ ዘርፉ በሁለት አስርት አመታት ጉዞው እስከ 2014 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ አጠቃላይ ከአራት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘት ችሏል።
በ2014 በጀት ዓመት ብቻ 589 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ከእቅድ በላይ 631 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝቶበታል። በተያዘው 2015 በጀት አመት ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ 414 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ በማስገኘት ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በግብርናው ዘርፍ ቀዳሚና አንጋፋ ከሆነው ከቡና ቀጥሎ የሁለተኛ ደረጃን መያዝ ችሏል።
አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬን በስፋት ማምረት የሚያስችል ዕምቅ አቅም ያላት መሆኑ የሚነገርላት ኢትዮጵያ፤ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አሁን ላይ ያላትን እምቅ አቅም በመጠቀም ከዘርፉ የውጭ ምንዛሬ በማግኘት ተጠቃሚ እየሆነች ትገኛለች። ዘርፉ በሥራ ዕድል ፈጠራና በቴክኖሎጂ ሽግግርም እንዲሁ የጎላ አስተዋጽኦ እያደረጉ ከሚገኙ ዘርፎች መካከል ተጠቃሽ እየሆነ መጥቷል።
በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አስተዋጽኦ ጉልህ ሚና ያለው የሆርቲካልቸር ዘርፍ በተለይ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ስኬታማ እየሆነ እንደመጣም መረጃዎች ያመለክታሉ። የዘርፉን ስኬት መነሻ በማድረግም በዛሬው የስኬት አምዳችን የሆርቲካልቸር ማህበርን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴና እያስመዘገበ ያለውን ስኬት እናዳስሳለን።
የኢትዮጵያ አበባ አምራቾችና ላኪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ነጋ መኳንንት እንደሚሉት፤ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ወደ ሥራ የገባው የሆርቲካልቸር ዘርፍ በቀዳሚነት አበባ አምርቶ ለውጭ ገበያ ያቀርብ ነበር። በሂደትም አትክልትና ፍራፍሬን ጭምር አምርቶ ለውጭ ገበያ ወደ ማቅረብ ተሸጋግሯል።
የሆርቲካልቸር ዘርፍ ካለፉት አስርት ዓመታት ወዲህ በተገቢው ሁኔታ እያደገ የመጣ ዘርፍ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰው፣ ባለፉት ጥቂት አመታት ከኮቪድ እና ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ዘርፉ ተቀዛቅዞ እንደነበርም አስታውሰዋል። የኢትዮጵያ አበባ አምራቾችና ላኪዎች ማህበርም ዘርፉ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ያለውን ፋይዳ በመረዳት የዘርፉን ዕድገት ከፍ ለማድረግና ለማነቃቃት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወኑን በዚህም ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አስታውቀዋል።
ኢንዱስትሪው እያስመዘገበ ያለውን ውጤት ማስመዝገብ እንዲችልም ማነቆ የሆኑ በርካታ ችግሮች መፈታታቸውንም ተናግረዋል። በመንግሥት መፈታት ያለባቸውን ችግሮች ከመንግሥት ጋር በመነጋገር እንዲፈቱ መደረጉን አመልክተው፣ የማስፋፊያ መሬት የጠየቁ አልሚዎች የማስፋፊያ ቦታ እንዲያገኙ የተደረገበትን ሁኔታም ፕሬዝዳንቱ በአብነት ጠቅሰዋል።
ማህበሩ ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠትና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ኢንዱስትሪው ከዓመት ዓመት እየተስፋፋ እንዲሄድና ውጤታማ እንዲሆን ሠርቷል ብለዋል። በአሁኑ ወቅትም ዘርፉ እየተነቃቃ መሆኑን ጠቅሰው፣ በ2012 እና 2013 በጀት ዓመታት ከተገኘው የአበባ ምርት ገበያ በበለጠ ካለፈው በጀት አመት ጀምሮ የተሻለ ገበያ መገኘቱንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
ዘርፉን ስኬታማ ለማድረግ የተከናወኑት ተግባሮች እንዳሉ ሆነው በርካታ አምራቾች የማስፋፊያ ቦታ ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ልማቱ መጠነኛ በሆነ ቦታ ላይ ብቻ እየተካሄደ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል። በቀጣይ ጥያቄውን ሙሉ ለሙሉ ለመመለስ የማስፋፊያ ቦታ በማዘጋጀት ዘርፉ የበለጠ ውጤታማ መሆን እንዲችል ይሰራል ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የሆርቲካልቸር ዘርፍ በዋናነት ኤክስፖርት ላይ ያተኮረ በመሆኑ ግብዓቱ ከውጭ የሚመጣና ገዢውም ውጭ ያለ ነው። በአገር ውስጥ ያለው አምራቹ ብቻ ነው። ስለዚህ እነዚህን አካላት በማገናኘት የገበያ ትስስር መፍጠር ከማህበሩ የሚጠበቅ ሥራ በመሆኑ ማህበሩ ይህንኑ እየሠራ ይገኛል። በተለይም የውጭ ባለሃብቶችን ወደ አገር ውስጥ በመሳብ ረገድ ማህበሩ ሰፊ ሥራ እየሠራ ነው።
ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት በበለጠ በሆርቲካልቸር ዘርፍ ተመራጭ መሆን ችላለች ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ለዚህም መንግሥት ለኢንቨስትመንቱ እያደረገ ያለው ማበረታቻ፣ የመልክአ ምድር አቀማመጧ፣ ለአውሮፓና ለመካከለኛው ምስራቅ ያላት ቀረቤታ እንዲሁም ፈጣን እና አስተማማኝ አገልግሎት የሚሰጠው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአበባ ኢንቨስትመንት ልማት ማደግ በዋናነት ተጠቃሽ መሆናቸውን አመልክተዋል። የእነዚህ ድምር ውጤትም ኢንዱስትሪው በአገሪቱ እንዲስፋፋና በስኬት መስመር ውስጥ እንዲገባ አስተዋጽኦ የጎላ ነው ብለዋል።
በአገሪቱ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኘው የሆርቲካልቸር ዘርፍ በተለይ አበባ አንድ ሺ ስድስት መቶ የሚጠጋ ሄክታር መሬት ላይ እየለማ እንደሆነ የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤ ከዚህ በበለጠ ስፋት ባለው መሬት ላይ መልማት ቢችል ዘርፉ የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆንም ነው ያስገነዘቡት። ለዚህም ማህበሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየሠራ እንደሆነ ገልጸዋል።
የውጭ ምንዛሪን በማምጣት፣ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ረገድ የጎላ አበርክቶ ያለውና በዕድሜ ትንሹ የሆነው የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ከቡና ቀጥሎ ተስፋ የተጣለበት ዘርፍ ስለመሆኑም በውጭ ምንዛሬ ግኝት በኩል እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ይጠቀሳል። በሥራ ዕድል ፈጠራም ተጠቃሽ መሆን ችሏል፤ በአበባው ዘርፍ ብቻ ከሁለት መቶ ሺ በላይ ለሚደርሱ ዜጎች በቋሚነት የሥራ ዕድል መፍጠር አስችሏል።
የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ማህበር 120 የሚደርሱ አምራች ላኪዎችን በስሩ ያቀፈ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት በአበባ ምርት የተሰማሩ ናቸው። ቀሪዎቹ 20 በመቶዎቹ ደግሞ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በእጸጣዕም ምርት የተሰማሩ ስለመሆናቸው ከማህበሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል። ማህበሩ የዛሬ 20 ዓመት ሲመሰረት አምስት የአበባ አምራቾችን ብቻ ይዞ ሲሆን፤ በወቅቱ አበባን ብቻ አምርቶ ወደ ውጭ ገበያ ያቀርብ ነበር።
ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት፤ ማህበሩ ሥራውን በአበባ ምርት ብቻ የጀመረ በመሆኑ በስፋት አምርቶ ወደ ውጭ ገበያ የሚልከውም ይህንኑ የአበባ ነው። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የእጸጣዕም ምርቶችን በማምረት ወደ ውጭ ገበያ መላክ ውስጥ ገብቷል። በዚህም አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል። በዘርፉ ተሳታፊ የሆኑትም 24 የሚደርሱ የማህበሩ አባላት ናቸው።
ከአጠቃላይ ሆርቲካልቸር ዘርፍ የአበባ ምርት ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ይናገራሉ። አሁን አሁን የአትክልትና ፍራፍሬ ገበያም ተወዳዳሪ እየሆነ መምጣቱን ፕሬዝዳንቱ አስረድተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ከአትክልትና ፍራፍሬ መካከል በተለይም የስትሮብሪ ምርት በአገሪቱ በስፋት ተመርቶ ለውጭ ገበያ እየቀረበ ይገኛል። አቦካዶ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በስፋት እየተመረተ ያለ ሲሆን፣ ሶስት አልሚዎችም ወደ ሥራው ገብተው ማምረት ጀምረዋል። ይህም በቀጣይ አንደ አበባው ሁሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፉ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ውጤታማ መሆን እንደሚችል አመላካች ነው።
አገሪቷ በአየር ንብረት፣ ውሃ ሀብት፣ ለም አፈር የታደለች በመሆኗ በዘርፉ በስፋት መሥራት እንደሚገባ ያስገነዘቡት ፕሬዝዳንቱ፤ በተለይም አነስተኛ በሆነ ቦታ ላይ በማምረት ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል ዘርፍ መሆኑም ከሌሎች የግብርና ዘርፎች ለየት ያደርገዋል ብለዋል። ስለዚህ አገሪቷ ለዘርፉ ያላትን እምቅ አቅምና ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነቷን ይበልጥ ማረጋገጥ የሚጠበቅባት ጊዜ አሁን ነው ሲሉም ያስገነዝባሉ።
በተለይም የአበባው ዘርፍ ከቡናና ከሌሎች የግብርና ምርቶች አንጻር ሲታይ ትልቁን ድርሻ በመያዝ ከቡና ቀጥሎ ሁለተኛው የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበት ዘርፍ መሆኑን ይገልጻሉ፤ አትክልትና ፍራፍሬም እንዲሁ እየተነቃቃ መሆኑን አመልክተው፣ ይህም የበለጠ ውጤታማ መሆን እንዲችልም ስራውን አጠናክሮ ማስቀጠል ይጠይቃል ብለዋል።
መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት ውጤታማ መሆን እንደተቻለ ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ፤ በተለይም በአሁኑ ወቅት ለዘርፉ ማነቆ የሆኑ የአሰራር ችግሮችን እየፈታ፤ በአዲስ ፖሊሲና በአዳዲስ እሳቤዎች ወደ ተግባር እየገባ ነው ይላሉ። ይህም ኢትዮጵያ ያሏትን በርካታ እምቅ አቅሞች መጠቀም እንድትችል ዕድል እንደሚፈጥርላት ተናግረው፣ መንግሥት ለዘርፉ እያበረከተ ካለው አስተዋጽኦ ጎን ለጎንም ማህበሩ ዘርፉን ለማነቃቃት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ማህበሩ የተለያዩ ኤክስፖዎችን በማዘጋጀት አገሪቷ ለኢንቨስትመንት ምቹ እንደሆነች በማስተዋወቅ እንዲሁም የገበያ ትስሰር በመፍጠር ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው። ለአብነትም ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራቾችና ላኪዎች ማህበር አዘጋጅነት በሚሊኒየም አዳራሽ የተካሄደውን ስምንተኛውን የሆልቲካልቸር ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ይጠቀሳል።
ኤክስፖውም ኢትዮጵያ በሆርቲካልቸር ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም የማስተዋወቅና ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስርን የመፍጠር፣ የአቅርቦት ሰንሰለትን የማሳደግ እንዲሁም የተወዳዳሪነት አቅምን የማጎልበት ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑ ተገልጿል።
በኤክስፖ መክፈቻ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ፤ የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ በአሁኑ ወቅት በግብርናው ዘርፍ ከቡና ቀጥሎ ትልቁ የውጭ ምንዛሬ ግኝት መሠረት መሆኑን ተናግረዋል። መንግሥት ዘርፉን ለማሳደግ አዲስ እያዘጋጀ ባለው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲም ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ከቡናና ሌሎች ኤክስፖርት ከሚደረጉ ምርቶች አንጻር የአበባ ዘርፍ ሁለት አስርት ዓመታት ያህል ዕድሜ ያለው ቢሆንም፤ ባጠረ ጊዜ ውስጥ በአነስተኛ ቦታ ላይ ጥሩ ውጤት እያሳየ መጥቷል። የአገሪቱ የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ከቡና ቀጥሎ ሁለተኛው ትልቁ የውጭ ምንዛሬ የሚገኝበት ሆኗል። ዘርፉ ከውጭ ምንዛሬ ግኝቱና ከሥራ ዕድል ፈጠራ አኳያ ሲታይ በእርሻ ኢንቨስትመንት በውስን ቦታዎች ሰፊ የሥራ ዕድል እየተፈጠረ እንደሆነም አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ካላት አግሮ ኢኮሎጂና የአየር ንብረት አንጻር የአትክልትና ፍራፍሬ ዓይነቶች ከየትኛውም አገር የተሻለ እምቅ ሀብት ያላት መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፉ፤ የግብርና አምዶች በሆኑት በምግብ ዋስትና ራስን መቻል፣ ወጪ ምርትን መጨመር፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እያሳየ ያለው ሂደት አበረታች እንደሆነም አመላክተዋል።
የተዘጋጀው ኤክስፖም ኢትዮጵያ በሆርቲካልቸር ያላትን እምቅ አቅም ለማስተዋወቅና ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስርን ለመፍጠር፣ የአቅርቦት ሰንሰለትን ለማሳደግ እንዲሁም የተወዳዳሪነት አቅምን ለማጎልበት ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በአበባ ኤክስፖርት ከአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ስትሆን ከዓለም በአራተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ከኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ማህበር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ሀገሪቱ በተያዘው 2015 በጀት አመት ከ770 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት መታቀዱን መረጃዎች ያመለክታሉ። ባለፉት ሰባት ወራት 414 ሚሊየን ዶላር ተገኝቷል።
በ2015 በጀት ዓመት ባለፉት ሰባት ወራት ከሆርቲካልቸር ዘርፍ 414 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ተችሏል፤
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 2 ቀን 2015 ዓ.ም