በእልህ አስጨራሹ የማራቶን ሩጫ ሁሉም ተወዳዳሪ አሸናፊ የሚሆን ነው የሚመስለው። ገና የማስጀመሪው ተኩስ ሲተኮስማ ሁሉም እየተጋፋ ሲሮጥ አሸናፊ ይመስላል። ነገር ግን ያ ሁሉ የማሸነፍ ወኔ እየቀነሰ መጥቶ በመሃል መንጋው መበተን ይጀምራል። መራራቅ ይጀምራል። በመጨረሻ ውድድሩ ሲጠናቀቅ ግን አንደኛ የሚሆነው ሰው ይታወቃልና ሪቫን በጥሶ አሸናፊ ይሆናል። ከአሸናፊው ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጠው ሰው ሲጠበቅ! ሲጠበቅ! በደቂቃዎች ዘግይቶ ይመጣል። ለሶስተኛና አራተኛ ደረጃ የሚጠበቁትማ የት ጠፉ? እየተባሉ ቆይተው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ካጠናቀቁት የበለጠ ዘግይተው ይመጣሉ።
እዚህ ጋር ስለማራቶን ሩጫ ለማውራት አይደለም የፈለኩት ስለ ሕይወት ሩጫ እንጂ። ልክ እንደማራቶን ሩጫ ሁሉ የሕይወት ሩጫም በቅድሚያ ፍጥነት፣ በመሃል መቀዝቀዝ በስተመጨረሻ ደግሞ ከናካቴው ከሩጫው ውጭ መሆን አለ። ሰዎች በሕይወት ኡደት ውስጥ ሁሉንም ነገር ይጀምራሉ። ትምህርት፣ ስራ፣ የፍቅር ግንኙነት፣ ሌላም ሌላም ነገር ይጀምራሉ። በአብዛኛው ግን የሚጀምሯቸው ነገሮች ፍፃሜ የላቸውም።
ትዳር ጥሩ ነው። የትዳር ጥሩነትን ሰዎች ተገንዝበው ውሃ አጣጫቸውን ፈልገው በሠርግ ያገባሉ። ለጊዜውም ፍቅራቸው ደርቶ በፍቅር ክንፍ ይላሉ። ቀናት፣ ወራትና አመታት ያልፋሉ። ጋብቻ የወለደው ፍቅራቸው ግን ዘላቂነት ሳይኖረው በአጭር ተደምድሞ ፍቺ ይፈፅማሉ።
መቼም በዚህ ምድር ገንዘብ ማግኘትና ኑሮውን ማሻሻል ብሎም ሕይወቱን መለወጥ የማይፈልግ ሰው የለም። ለዛም ነው ብዙ ሰዎች አዳዲስ ቢዝነሶችን የሚጀምሩት። ነገር ግን ስንት ተለፍቶበት የተሰራው ቢዝነስ በአመቱ ብትንትኑ ሲወጣ ይታያል። ያ ሁሉ ህልም በአጭር ይቀጫል።
ይህም የብዙዎቻችን ሕይወት ችኮላ የተሞላበት እንደሆነና ትእግስት እንደሌለው ያሳያል። የአብዛኛዎቻችን ክፍተትም ነው። ትእግስት በአለማዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሚስጥር ነው። ለዛም ነው የታገሰ አፈሰ የሚባለው። ለዛም ነው ትእግስት ዘሯ መራራ ቢሆንም ፍሬዋ ጣፋጭ ነው የሚባለው። የሰዎች ትእግስት ግን የመቶ ሜትር ሩጫ ያህል በጣም አጭር ናት።
እያንዳንዱ ሰው አቅምና አውቀት ቢኖረውም ፤ በሰዎች ቢከበብም ትእግስት ከሌለው የዘራውን ሊያጭድ አይችልም። የለፋበትን አያሳካም። በክረምት የዘራኸውን በመኸር የምታጭደው ታጋሽ ከሆንክ ብቻ ነው። በሕይወትህ ውስጥ ደስተኛ የምትሆነው የትእግስትን ጥበብ ከተላበስክ ብቻ ነው። ብዙ ሰዎች ይጣደፋሉ። ይቻኮላሉ። ነገሮች ለምን በቶሎ አይሳኩልኝም ይላሉ። የሕይወት ትእግስት በጥቂቱም ቢሆን የገባቸው ግን መታገስ ይጀምራሉ። ትእግስታቸውም ፍሬ አፍርቶ በሕይወታቸው ስኬታማ መሆን ይችላሉ። ለመሆኑ መታገስ ማለት ምን ማለት ነው?
መታገስ ማለት ለጊዚያዊ ደስታ ብለህ ነገህን የሚጎዳ ውሳኔ አለመወሰን ነው። ስትታገስ ሀያሉ ጊዜ ካንተ ጋር ነው። ሁሉን አሳልፎ ጥሩውን ቀን ያመጣልሃል። ስትታገስ የፈጀውን ጊዜ ይፈጃል እንጂ ከናቁህና ዝቅ አድርገው ካዩህ ሰዎች በላይ ከፍ ትላለህ። ስትታገስ ግዙፍ መስሎ የታየህ ችግር ምን ያህል ቁጫጭ እንደነበር ይታይሃል። የፈጣሪ ታናሽ ወንድም የሚባለውን ኃያሉን ጊዜ ከጎንህ ማሰለፍ ከፈለክ ታገስ ወዳጄ!
አሜሪካ ኮሎራዶ ግዛት ውስጥ የተፈጠረ ታሪክ ነው። ሰውዬው ወርቅ ለማውጣት ብር ተበድሮ፣ ማሽንና መሬት ገዝቶ ቁፋሮውን ጀመረ። ነገር ግን ቢቆፈር ቢቆፈር ወርቁ ሊገኝ አልቻለም። ብዙ ሞከረ አልተሳካለትም። ተስፋ ቆረጠ። እናም ‹‹እዳዬም እየበዛ ነው። ስለዚህ ለምን ሸጬ አልወጣም›› ብሎ ማሽኑንና መሬቱን ሸጦ ወጣ። በቦታው ላይ ሌላ ወርቅ ቆፋሪ መጣ። እርሱ ግን ከመቆፈሩ በፊት የማእድን ባለሙያ ቀጥሮ ወርቁን ማስፈለግ ጀመረ። አስገራሚ ነገር ተፈጠረ። የማእድን ባለሙያው አንድ ነገር አወቀ። ለካ ወርቁ ያለው የመጀመሪያው ሰውዬ ካቆመበት አንድ ርምጃ ርቀት ላይ ነበር። ያ የመጀመሪያው ወርቅ ቆፋሪ ምን ያህል ሊቆጨውና ሊፀፅተው እንደሚችል አስቡት።
እኛም ካልታገስን የለፋንበትን ማጨድ አንችልም። ስለዚህ እየለፋንና እየጣርን ከሆነ አንድን ነገር ከማቆማችን በፊት አንድ እርምጃስ ቢሆንስ የቀረኝ፣ አንድ ሳምንትስ ቢሆን የቀረኝ፣ አንድ ወርስ ቢሆን የቀረኝ፣ አንድ ዓመትስ ቢሆን የቀረኝ፣ የምፈልገው ነገር ሊመጣልኝና ሊሳካልኝ ትንሽ ጊዜ ቢሆንስ የቀረኝ ብለን ትግላችንን ማቆም የለብንም። መታገስ አለብን።
ልፋቱን ለፍተህ፤ ላብህን ጠብ አድርገህ እንዴት ልትበላ ስትል አይንህ ሌላ ያያል። ያቆሙ አሸንፈው አያውቁም። ተስፋ የቆረጡ ተረስተዋል። መንገድህ በጉም ተሸፍኖ ይሆናል። ልመለስ አትበል። እስከሚታይህ ድረስ ሂድ። ቢዝነሱ ውጤት የለውም አትበል። ስንት አመት ሰርተህ ነው፤ ምን ያህል ሞክረህ ነው እንዲህ የምትለው? ‹‹የምወደው ስራ ቢሆንም ምንም ለውጥ አልሰጠኝም ላቆመው ነው›› አትበል። ፅዋው እስኪሞላ ታገስ። ዞር ብትልም ሌላኛው ስራ የሕይወት ምእራፍ ያንተን ትእግስት ይፈልጋል። የተኛውም ነገር ያንተን ትእግስት ይፈልጋል።
አንዳንዴ ከእኛ ያነሰ አቅም፣ እውቀትና ገንዘብ ያላቸውና ኧረ በጭራሽ እኛ ላይ አይደርሱም የምንላቸው ሰዎች፤ ለአብነት እንኳ በትምህርት ቤት እያለን ከኋላ የሚቀመጠው ያ ረባሽ ልጅ ዛሬ ትልቅ ቦታ ደርሷል። እንዴት እኔን በለጠኝ የምንላቸው ሰዎች አግብተዋል። ትዳር መስርተው ልጆች ወልደዋል። ከእኛ የተሻለ ሕይወት እየመሩ ነው። እኛ እኮ ከእነርሱ የተሻልን ነበርን። ታዲያ ለምን ይመስላችኋል እነርሱ እኛን የበለጡን። አቅም አጥተን አይደለም። ሰነፍም ሆነን አይደለም። ስላልታገስን ነው። ጥረታችንን ስላቆምን ነው።
መታገስ ዋጋ ያስከፍላል። ፍሬው ግን ጣፋጭ ነው። በሕይወታችን ካልታገስን የሆነ ነገር እያጣን ነው። አንድ ጫካ በዛፍ ለመሞላት ብዙ አመታትን ይጠይቃል። ጫካውን ለማውደም ግን አንዲት ክብሪት በቂ ናት። የለፋህበትን ለማፍረስ አንድ የችኮላ ውሳኔ በቂ ነው። ትእግስት ግን ሁሌም ዋጋ ያስከፍላል።
ጥሩ ነገር አይደል የምትፈልገው፤ ታዲያ ምን ትጠብቃለህ አሪፍ ዋጋ ክፈላ። እመነኝ አይቆጭህም፤ ለምን ታገስኩ ብሎ የቆጨው ሰው የለም። ልፋቱን አታቁም፤ ስፖርቱን ስራ፤ መፅሃፉን አንብብ፤ በጠዋት ተነስ፤ ገንዘቡን አስቀምጥ፤ ልፋትህንም አታቁም። ታገስ ሕይወትህን ትቀይራለህ። በአንዴ ተለውጬ በዙሪያዬ ያሉትን ሰዎች መቼ ባሰገረምኳቸው አትበል። ለውጥ ሂደት ይጠይቃል። ጊዜ ይጠይቃል። መታገስ ይጠይቃል።
አንድ ድንጋይ ወርውረህ የሾላ ፍሬ አታረግፍም። ደጋግመህ በደንብ መወርወር አለብህ። መልፋት አለብህ። ታገስ፤ ካልታገስክ ለውጡን አታየውም። አትጓጓ፤ ከጓጓህ ከመንገድ ትቀራለህ። ህልምህ የስኬትህ መንገድ ነው። መንገዱን የምትሄድበት መኪና ግን ፅናት ነው። ያለ ፅናት የትም አትደርስም። ለአላማህ ስትል መፅናትና መታገስ አለብህ። የምፈልገው አልሆነም አትበል። ሞክሬ እኮ አልተሳካም አትበይ። እስኪሆን ድረስ መታገስ አቃተኝ በል። ጥግ ድረስ መሄድ መሞከር ከበደኝ በይ።
እንዲህ ስንል መፍትሄው ግልፅ ነው። መፍትሄው ወይ መታገስ ነው አልያም አካሄድ ቀይሮ በአዲስ መንፈስ መሞከር ነው። ማቆም የሚባል ነገር የለም። ለችግርህ ጊዜ የራቁህ በስኬትህ ጊዜ ዙሪያህን ቢከቡህ እንዳትገረም። የዛሬም ሺ ዓመት ሰዎች እንደዚህ ነበሩ። አየህ ታጋሽ ስትሆን እውነተኛ ለውጥ ታያለህ። ሰዎች ያደንቁሃል። ያከብሩሃል። ካልታገስ ግን ከሰዎች ትለምናለህ። ከሰዎች ትጠብቃለህ። ከሰዎች እንደመጠበቅ ልብ ሰባሪ ነገር ደግሞ የለም። ራስህን አትጠራጠረው። ራስህን የምታምን ከሆነ ታገስ። ራስን እንደመጠራጠር ህልም ገዳይ ነገር የለም። ትእግስት ይኑርህ። ‹‹ሁሉም ነገሮች ቀላል እስኪሆኑ ድረስ ከባድ ነበሩ›› ይላል ፐርሺያዊ ገጣሚ ሰአዲ።
የጎደለህ ትንሽዬ ትእግስት ነው እንጂ የምትፈልገው ነገር ካንተ አያመልጥም። ታገስ ማለት ግን ቁጭ ብለህ ተመልከት ማለት አይደለም። ጥረትህን ሳታቆም ጠብቅ ማለት ነው። አንዳንዴ ምንም ነገር ሳይጎድለን ትእግስት ማጣት ብቻ ባለንበት ያስቀረናል። ይህች ዓለም ትንፋሹን ዋጥ አድርጎ ለረጅም ጊዜ የቆየ የሚያሾፍባት መድረክ ናት። ለምሳሌ መዝናናት፣ ፈታ ማለት እያማረህ ‹‹ቆይ እስኪ ዛሬ ይለፈኝ›› ማለት ከጀመርክና ያን ጊዜ ለሚጠቅምህ ነገር ከተጠቀምከው አትጠራጠር ትክክለኛው መንገድህ ላይ ነህ። ያ ተከታታይ ድራማ ዛሬ ይለፈኝና ስራ ልስራ ማለት ከጀመርሽ ለውጡን በቅርቡ ታይዋለሽ። ትእግስት ማለት ገንዘብ አውጥቶ ፈታ ማለት ያምርህና ግን ለምን አንደኛዬን ጥሩ አቅም ሲኖረኝ አልዝናናም ብሎ ወጥሮ መስራት ነው።
አንተ እኮ ብዙ ፈተና ያለፍክ ሰው ነህ። አበቃልህ ሲባል ለዛሬ ደርሰሃል እኮ። ጠንካራ ነህ። አሁን ያለህበት ላይ ለመቆም አንተን መሆን ይጠይቃል። ያንተን ጥንካሬ ይጠይቃል። እውነት ነው ወደኋላ የሚጎትት መጥፎ ትዝታ ይኖርሃል። እርሱን እያሰብክ በመቆጨት የሚባክነውን ጊዜ አስብ። ያንተን ጊዜና ትኩረት የሚፈልጉ ብዙ ጉዳዮች አሉ። እንዴ ህልምህስ! ስራህስ! የነገ የፍቅር፣ የትዳርና የቤተሰብ ሕይወትህስ! ከእነርሱ የሚተርፍ ጊዜ ኖሮህ ነው ቀንህ በጭንቀት የሚያልፈው። እርግጠኛ ነኝ ብዙ ነገር መቀየር ማሳደግ የተሻለ ሕይወት መኖር ትፈልጋለህ። ያንን ማድረግ የምትችለው ጥረትህን ካላቆምክ ብቻ ነው። ከታገስክ ብቻ ነው።
እለፋለሁ መቼ ነው የሚሳካልኝ ብለህ አትፀፀት፤ አትዘን። ታገስ! ሕይወት ለሚታገሱ ብቻ ናት። ርስቱን የሚወርሱት፣ የሚስቁት ፣ የአድማስ ጥግ የሚጓዙት የታገሱ ብቻ ናቸው። ፍሬዋን የሚበሉት ታግሰው የጠበቁ ብቻ ናቸው።
ሰውዬው ኮፍያ አድርጓል። ጃኬት ደርቧል። ቀብረር ! ቀብረር! እያለ እየተጓዘ ነው። ከላይ ፀሐይና ንፋስ ያዩታል። ንፋስ በግልፍተኝነትና በጉራ ወደ ፀሐይ ዞሮ እንዲህ አላት፤ ‹‹ይኸውልሽ ፀሐይ እኔ አቅሜን ለማሳየት የዚህን ሰውዬ ኮፍያውንም ጃኬቱንም በአንድ ጊዜ ነው የማስወልቀው›› አላት። ፀሐይም ‹‹እስኪ እንያ›› አለች። ንፋስ በሃይለኛው መንፈስ ጀመረ። ሃይሉን ተጠቅሞ የሰውዬውን ኮፍያ ለማውለቅ የሚችለውን ሁሉ አደረገ። ሰውዬው ግን ንፋሱ ሲነፍስ ጃኬቱን ሰብሰብ አደረገ። ኮፍያውንም ጫን አድርጎ ያዘው። ንፋስም ተበሳጨ። ይበልጥ በኃይል ነፈሰ። ሰውዬው ግን ይበልጥ ኮፍያውን አጥብቆ ያዘ። ጃኬቱንም አጠበቀ።
ፀሐይ ፈገግ እያለች ወደንፋስ ዞራ እንዲህ አለች። ‹‹የታለ ኮፍያውን ያወለከው፣ የታለ ጃኬቱን ያስጣልከው እስኪ ደግሞ እኔ ላሳይህ›› አለችው። ፀሐይ ቀስ ብላ መውጣት ጀመረች። መፍካት ጀመረች። ወከክ ማለት ጀመረች። ሰውዬው ንፋሱ ስለጠፋ እጁን ለቀቅ አድርጎ ኮቱን አስተካከለ። ከኮፍያው ላይ እጁን አወረደ። ፀሐይ ቀስ እያለች መሞቅ ጀመረች። መጋል ጀመረች። ሰውዬው ሞቀው። ጃኬቱን ቀስ አድርጎ አወለቀ። በድጋሚ ኮፍያውን አውልቆ በእጁ ያዘ። ፀሐይ ወደ ንፋስ ዞራ እንዲህ አለችው። ‹‹አንዳንዴ ነገሮች በጉልበት አይደሉም። በፍጥነት አይደሉም›› አለችው።
በሕይወትህ ውስጥ ስለሮጥክ አትቀድምም። ስለሰራህ ብቻ አትቀየርም። አንዳንዴ ረጋ ብለህ ማሰብ አለብህ። ወዴት እየሄድኩ ነው ማለት አለብህ። መሮጥ መፍጠን ብቻ ሕይወት አይቀይርም። መታገስ አለብህ። ሰላም!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 2 ቀን 2015 ዓ.ም