ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ አሁንም የሚተዳደረው በግብርና ነው፡፡ ኢትዮጵያም ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት በሚታረስ የእርሻ መሬትና በግብርና ምርት ቀዳሚ ሀገር ናት፡፡ሆኖም በተቃራኒው የግብርና ምርቶችና ሌሎች መሰረታዊ አቅርቦቶች እጥረት ካለባቸውና ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ከሚታይባቸው ሀገራትም አንዷ ናት፡፡ በአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣምና በተለያዩ ብልሹ የንግድ አሰራሮች ምክንያት በየቀኑ እየጨመረ የሚሄደውም የሸቀጦች ዋጋ መናር በዜጎች ላይ ከፍተኛ የኑሮ ውድነትን በመፍጠር ሕዝቡን ለችግር እየዳረገ ነው፡፡
በተለይም ኀብረተሰቡ በዕለት ተዕለት በሚጠቀምባቸው መሰረታዊ ፍጆታዎች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዜጎችን ኑሮ እየተፈታነው ይገኛል። በእህል፣ በጥራጥሬ ፤ በአትክልት ምርቶች፤ በግንባታ ዕቃዎች እና በቤት ኪራይ ላይ የዋጋ ጭማሪው ትኩረት የሚፈልግ ሆኗል፡፡ ነገሩን ይበልጥ ከባድ የሚያደርገው ደግሞ የዋጋ ግሽበቱ እየጨመረ ያለው የምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ላይ ትራንስፖርት፣ የትምህርቤት ክፍያና የመሳሰሉት ሲጨመሩበት የሕዝቡን ኑሮ ፈታኝ እያደረገው ነው፡፡
በየቀኑና በየሰዓቱ የሚጨምረው የሸቀጦች ዋጋ በተለይም ዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል ኑሮ በጣም እንዲከብደው ምክንያት ሆኗል፡፡ መሽቶ በነጋ ቁጥር ‹‹ከገበያ ጠፍተዋል››፤‹‹ዋጋ ጨምሯል›› የሚሉት አገላለጾች እየተለመዱ ነው፡፡
የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት ከፍተኛ ፈተና እየገጠመው ያለው ከዋጋ ግሽበት በተያያዘ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቢሰማም ችግሩን በሚፈለገው መጠን አለመቀረፉ በየሰዓቱ የሚጨምረው የሸቀጦች ዋጋ መናር በቂ ማሳያ ነው፡፡ ምግብ ነክ የሆኑና መሠረታዊነታቸው የታመነባቸው የፍጆታ ዕቃዎች በፍራንኮ ቫሉታ አሠራር ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ እና የመድኃኒት፣ ነዳጅ፣ ማዳበርያ፣ ዘይት እና ሌሎችም መሠረታዊ ሸቀጦች ግዢ አቅርቦት አቅርቦት እንዲቀላጠፍ የማስተካከያ ርምጃ የተወሰደና ግብረኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ የተገባ ቢሆንም የኑሮ ውድነቱን ወደ ላይ ከመገስገስ ሊያቆመው አልቻለም፡፡
በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት በተሰሩ የግብርናውን የማዘመን ስራዎች በሀገሪቱ ምርታማነት እንደጨመረ ቢታመንም በተለያዩ ህገወጥ አሰራሮችና የቁጥጥር መላላት ምክንያት ምርቱ ሸማቹ ህብረተሰብ ጋር በቀላሉ ለመድረስ ካለመቻሉም በሻገር የዋጋ ንረትም እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል፡፡ በተለይም በህገወጥ ኬላዎች አካባቢ የሚታየው ስርዓት አልበኝነት የሰብል ምርቶች ዋጋ በከፍተኛ መጠን ሊያሻቅብ ችሏል፡፡ በየኬላው የሚፈጸመው ህገወጥ ቀረጥና ብልሹ አሰራሮች የግብርና ምርቶች ወደ ተጠቃሚው በቀላሉ እንዳይደርስ እንቅፋት ከመሆኑም ባሻገር በተለይ በከተሞች አካባቢ የዋጋ ንረት እንዲባባስ ምክንያት እየሆኑ መጥተዋል፡፡
ከታህሳስ እስከ የካቲት ባሉት ወራት በኢትዮጵያ ምርት ወደ ጎተራ የሚገባበትና በገበያው ውስጥም ምርት በስፋት የሚታይበት ቢሆንም ባለፉት ወራት የታየው የዋጋ ግሽበት ከዚህ እውነታ የተለየ ነው፡፡ በመሳለሚያና በመርካቶ አካባቢ ያሉ ነጋዴዎች እንደሚናገሩትም በየካቲት ወር ብቻ በጤፍ፤በዱቄት፤በፓስታና መኮረኒ ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ለሸማቹ ፈታኝ ነው፡፡ ጤፍ በአንድ ወር ብቻ በኩንታል እስከ ሁለት ሺህ ብር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ፓስታና መኮረኒ ላይ በአንድ ወር ብቻ በኪሎ እስከ 30 ብር ጭማሪ ታይቷል፡፡
በአጠቃላይ የኅብረተሰቡን ላይ ትልቅ ጫና እየፈጠረ ያለውን የኑሮ ውድነት አሳስቦት ተገቢ የሆነ መፍትሄ ለማፈላለግ የሚደረገው ጥረት ከችግሩ መጠንና ፍጥነት ጋር የሚመጣጠን ስላልሆነ ተጨማሪ የመፍተሄ ርምጃዎችን የሚፈልግ ሆኗል ፡፡
በአጠቃላይ የኑሮ ውድነት የአብዛኛውን ድሃ ኅብረተሰብ ከባድ የኑሮ ፈተና እየሆነ መምጣቱን በመገንዘብ አሁን ከተሰጠውም ትኩረት የበለጠ ማድረግ የመፍትሄው አንድ እርምጃ ሊሆን ይገባል፡፡ መንግሰትን ጨምሮ ነጋዴዎችና ሌሎችም የዘርፉ ተዋንያን በተጨባጭም ለኑሮ ውድነቱ ተገቢውን ትኩረት መስጠቱን የሚያረጋግጡ ርምጃዎችን በተጨማሪነት መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የአቅርቦት ሥርዓቱን ማሰተካከልና ምርታማነት ማሳደግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ያለው ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 2 ቀን 2015 ዓ.ም