በማዕድን ሚኒስቴር መስሪያ ቤት እገኛለሁ። በስፍራው “ማይኒንግ ጋለሪ” እየተባለ የሚጠራውን የማዕድን ሙዚየም ለመመልከት ነው በቦታው የተገኘሁት። በሙዚየሙ ውስጥ በተለምዶ “ደበጃን” እያልን በምንጠራቸው የተለያየ መጠን ባላቸው ጠርሙሶች ውስጥ “በፈሳሽ” መልክ የተለያዩ ናሙናዎች ለእይታ ቀርበዋል።
ከፈሳሹ አንደኛው የምግብ ዘይት የሚመስል መልክ ያለው ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ጥቁር ነው። የተጣራና ያልተጣራ ይሆናል ብዬ ገመትኩ። ነገር ግን ጥቁሩ ነዳጅ ሲሆን የምግብ ዘይት የሚመስለው ደግሞ የተፈጥሮ ጋዝ መሆኑን ከባለሙያ ማብራሪያ ተረዳሁ። የተመለከትኳቸው ነገሮች በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ነዳጅ መኖሩን ለማረጋገጥ ቁፋሮ ተካሂዶ የተወሰዱ ናሙናዎች ናቸው።
በሌላ ክፍል ውስጥ ደግሞ በውጭ ኩባንያዎች ቁፋሮ ተካሂዶ የተገኘውና በተለያየ የመረጃ አያያዝ ዘዴ ገላጭ ጽሁፍ ተደርጎበት የተደራጀ መረጃ ይገኛል። ክፍሉም “ዳታ ቤዝ ኮር ሀውስ” ይባላል። በዚህ ክፍል ውስጥ በእጄ ነካክቼ ያየሁት ድንጋይ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ቁፋሮ ተካሂዶ የተገኘና የነዳጅ ሀብት ስለመኖሩ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው። ተደራጅተው የተቀመጡት መረጃዎች ለማልማት ፍላጎት ያለው ኩባንያ ሲገኝ በቀላሉ መረጃ እንዲያገኝ የሚረዱ ናቸው። ኩባንያዎች የኋላ ታሪኩን ይዘው የራሳቸውን ጥናት ጨምረውበት ወደ ተግባር ለመግባት የሚያስችላቸው እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም።
በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ነዳጅና ጋዝ መኖሩን የሚያረጋግጥ የተደራጀ መረጃ በሚገኝበት “ዳታቤዝና ኮር ሀውስ” ውስጥ በውጭ ኩባንያዎች በተለያየ ጊዜ ከተሰበሰቡት መረጃዎች መካከል በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚገኘው ኦጋዴን ቤዚን መረጃ ይጠቀሳል። ለአብነትም ሲንክሌር (Sinclair) በተባለ ኩባንያ እ.አ.አ ከ1945 እስከ 1956፣ ኤልዋርዝ (elwareth) በተባለው ኩባንያ ከ1959 እስከ 1967፣ በቴኔኮ (tenneco) ኩባንያ ከ1969 እስከ 1974 ደግሞ ኋይትስቶን (Whitstone) ኩባንያ ከብዙዎቹ መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
በአማራ ክልል ወሎ ወረኢሉ አካባቢ በአባይ ቤዚን እ.አ.አ ከ2008 እስከ 2014 ፋልከን ፔትሮሎየም ሊሚትድ (palken petroliam limited) በተባለ ኩባንያ የተሰበሰበ መረጃ እንዲሁም ቤሲፕ ፍራንላፕ (Beciep franlap) በተባለ የፈረንሳይ አማካሪ ኩባንያ እኤአ ከ1985 እስከ 1998 በአጠቃላይ የተጠናቀረ የኢትዮጵያ የነዳጅ አለኝታ መረጃ በክፍሉ ውስጥ ይገኛል።
እንዲህ መረጃዎቹን ተዘዋውሬ ባየሁ ጊዜም “የኢትዮጵያ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ለምቶ መቼ ይሆን የአገር ኢኮኖሚ ዋልታና ማገር የሚሆነው?” የሚለው የብዙዎች ጥያቄ በእኔም ውስጥ ሲመላለስ ነበር። በኢትዮጵያ የነዳጅ ሀብት ዙሪያ በኩባንያዎች የተሰበሰቡ መረጃዎችን አደራጅቶ ማስቀመጥ ወደ ልማቱ ለመግባት ጥሩ መንደርደሪያ ነው። እሱ ብቻውን ግን በቂ ነው ማለት አይቻልም። ይህን ሀብት አልምቶ ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል።
እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ይህን ሀብት አልምቶ መጠቀም አልተቻለም። ሃብቱን አልምቶ ወደ ምጣኔ ሃብታዊ አቅም ላለመቀየር እንደ ምክንያት ከሚነሱት ውስጥ አንዱ የአገር ውስጥ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ነው። ዓለም አቀፍ የነዳጅ ኩባንያዎች የሚያደርሱት አሉታዊ ተጽእኖም ሌላው ምክንያት ነው። ወደ ልማቱ በፍጥነት ለመግባት የሚያስፈልገው መዋእለ ነዋይ ከፍተኛ መጠን ያለው መሆኑም ሌላኛው ምክንያት ነው። በዘርፉ ብቁ ባለሙያ ከማስፈለጉም ባሻገር ሰላምና መረጋጋት፣ የመንግሥት ቁርጠኝነትም ወሳኝ መሆናቸው በሌላ በኩል ይነሳል። በእነዚህ ምክንያቶች የኢትዮጵያ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት አንዴ ተስፋ ሰጪ ውጤት ሲያስመዘግብ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወሬው ደብዛው እየጠፋ ማነጋገሩን እንደቀጠለ ነው።
በስፋት ከሚነሳው በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚገኘው የኦጋዴን ቤዚን ነዳጅ ቀጥሎ በአማራ ክልል ወሎ ወረኢሉ አካባቢ መሬት ሰንጥቆ ያለከልካይ እየፈሰሰ ስለመሆኑ ተደጋግሞ የተነሳ ጉዳይ ነው። በተለይ በአባይ ቤዚን መሬት ሰንጥቆ የወጣው የተፈጥሮ ጋዝ ጉዳይ ሲያነጋግር ቆይቷል። በዚህ አካባቢ ስላለው ነባራዊ ሁኔታና አጠቃላይ በተፈጥሮ ጋዝ ሀብት ዙሪያ ዘርፉን የሚመራውን የማዕድን ሚኒስቴር የሚመለከተውን ባለሙያ አነጋግረናል። በሚኒስቴሩ ከፍተኛ የፔትሮሊየም ባለሙያና በአሁኑ ጊዜም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፒኤችዲያቸውን እየሰሩ ያሉት አቶ ተፈራ ዓለሙ የሰጡንን ማብራሪያ ይዘን ቀርበናል።
አቶ ተፈራ የጂኦፊዚክስ ባለሙያ ናቸው። በቅድሚያም ሙያውን መሠረት ያደረገ ማብራሪያ ሰጥተውናል። እርሳቸው እንዳሉት፤ ጂኦፊዚክስ የመሬት ውስጥ ሃብት አያያዝና አፈጣጠርን የሚያጠና ዘርፍ ሲሆን፤ በመሬት ውስጥ ምን አይነት የተፈጥሮ ሀብት እንዳለ ወይንም እንደሚገኝም ያጠናል። ከዚህ ውስጥም ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ይጠቀሳሉ።
ከዚህ አኳያም ኢትዮጵያ ፔትሮሊየም መገኛ ምቹ የሆኑ ወደ ስድስት አካባቢዎች አሏት። እነርሱም ኦጋዴን፣ አባይ፣ መቀሌ፣ ጋምቤላ፣ መተማ፣ ስምጥሸለቆን ተከትሎ ደግሞ ሪፍትቫሊ ቤዚን ናቸው። ከነዚህ መካከልም በስፋት ጥናት የተካሄደውና ጥሩ የሚባል ደረጃ የደረሰው የኦጋዴን ቤዚን ነው። አባይ ቤዚንም ቢሆን ከኦጋዴን ቤዚን ባልተናነሰ ይጠቀሳል። በእነዚህ አካባቢዎች ያለው የፔትሮሊየም ሀብት ክምችት ከፍተኛ እንደሆነ መረጃዎች ቢያመላክቱም፣ ሀብቱ ሰፊ የጥናት ሥራ ማድረግን ይፈልጋል።
በዘርፉ ጥናት የመስራትና ወደ ትግበራ የመግባት ጉዳይን አስመልክቶ አቶ ተፈራ እንደገለጹት፤ የጥናት ሥራዎች የሚደረጉት በውጭ ኩባንያዎች ወይንም ባለሀብቶች ሲሆን፣ በእዚህ በኩል ለአብነትም የአሜሪካ፣ የሩሲያ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በቻይና ኩባንያዎች ይጠቀሳሉ። እነዚህ የነዳጅ ፍለጋ ጥናት ሥራዎች አብዛኛውን ጊዜ ቀጣይነት የላቸውም። ለእዚህ በምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥ ደግሞ የመሪዎች መለዋወጥ ወይንም አገራዊ ለውጥ አንዱ ነው፤ ይህን ተከትሎም የኩባንያዎች አብሮ መክሰም እንደሚያጋጥማቸው ይገልፃሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ኩባንያዎች በገንዘብ አቅም ውስንነት ሥራውን አቋርጠው ይወጣሉ። የኩባንያዎች መለዋወጥና የተለያዩ ምክንያቶች የዘርፉ ሥራ ዘላቂና ተከታታይ እንዳይሆን አድርጎታል። ይህም ሆኖ ግን በየወቅቱ ከየኩባንያዎቹ የተገኙት መረጃዎች ተደራጅተው ይያያዛሉ። ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች ባሻገርም ከፖሊሲ ጋርም የሚያያዙ አንዳንድ ውስንነቶች ለጥናትና ትግበራው አለመሳካት የራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ።
“ያለፉ ተሞክሮዎች ይህን የሚያሳዩ ቢሆኑም አሁን ደግሞ ዘመኑ ተለውጧል” የሚሉት አቶ ተፈራ፤ አገር ማደግ የምትችለው ባለው የተፈጥሮ ሀብት ላይ እንደሆነ መነሻ በማድረግ መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል። በዚሁ መሠረትም ሀብቱን መለየትና በምን ደረጃ ሊለማ እንደሚችል አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራ እንደሆነ ነው የጠቆሙት።
ለአሰራር ምቹ እንዲሆን የፍለጋና የማስተዳደር ሥራ የሚያከናውን ክፍል መለየቱን የሚናገሩት የጂኦፊዚክስ ባለሙያው፤ በዚሁ አሰራርም እርሳቸው የሚገኙበት ክፍል በዘርፉ ለመሰማራት ጥያቄ የሚያቀርቡ ኩባንያዎች ሲመጡ እንደሚያስተናግድ ይገልፃሉ። ወደ ሥራም ሲገቡ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ያስረዳሉ።
ክፍሉ ከዚህ በተጨማሪም በኩባንያዎቹ የተሰበሰቡ መረጃዎችን ያደራጃል ያሉት ባለሙያው፣ ለማልማት ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች ሲመጡም መረጃውን እንዲያገኙ በማድረግ ወደ ልማቱ የሚገቡበትን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ያብራራሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ እስካሁን በተከናወነው ሥራም በኢትዮጵያ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ከተለያዩ አገራት የመጡ ብዛት ያላቸው ኩባንያዎችን ማስተናገድ ተችሏል። ኩባንያዎቹም ጥሩ የሚባል ሥራ ሰርተዋል። በአጠቃላይ በዘርፉ እንደ አገር በተሰራው ሥራ በኦጋዴን ቤዚን አካባቢ ለተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ከ670 በላይ የጉድጓድ ቁፋሮዎች በማከናወን የፍለጋ ስራ ተሰርቷል። ከዚህ ውስጥ 19 የሚሆኑት ለምርት የተዘጋጁ ጉድጓዶች መሆናቸው ተረጋግጧል።
እንደ አቶ ተፈራ ገለፃ፤ በደቡብ ኦሞ አካባቢ “ታሎ” የሚባል የእንግሊዝ ኩባንያ ወደ አራት ጉድጓዶች በመቆፈር የሰራው ሥራም ይጠቀሳል። ይሁን እንጂ አመርቂ ውጤት ባለማግኘቱ ሥራውን ለማቋረጥ ተገድዷል። ቀጣይ ሥራዎች ቢሰሩ ግን ውጤት እንደሚገኝበት በኩባንያው በተሰራው ሥራ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
አርባ ምንጭ አካባቢም አንድ ኩባንያ የጂኦፊዚክስ ጥናቶችን አከናውኖ ሊቆፈር የሚችል ቦታ ከለየ በኋላ በገንዘብ እጥረት የቁፋሮ ሥራው ሳይካሄድ ቀርቷል። የዚህም መረጃ የሚያሳየው ሊመረመር የሚችል መሆኑን ነው። አቅም ያላቸው ኩባንያዎች በሥፍራው ላይ ቢሰሩ ውጤት ማግኘት እንደሚችሉ አመላካች ነገር መኖሩን ነው መረጃው አሳይቷል። ጋምቤላ ክልል ውስጥም እንዲሁ ሁለት ጉድጓዶች ተቆፍረዋል። ደቡብ ሱዳን አካባቢ ያለውን የተፈጥሮ ጋዝ መነሻ በማድረግ ኢትዮጵያ ውስጥም ሀብቱ ሊኖር ይችላል በሚል በአካባቢው ላይ ሙከራው ተደርጓል። ቁፋሮው የተከናወነበትና የማእድን ሀብቱ ይኖራል ተብሎ የተገመተበት አካባቢ ባለመጣጣሙ ለጊዜው ሥራው ተቋርጧል።
የጂኦፊዚክስ ባለሙያው በአባይ ቤዚን የተፈጥሮ ጋዝ ስለመኖሩ ምልክቱ የታየው ፋስሽት ጣሊያን ኢትዮጵያን በኃይል በወረረበት ወቅት ስለመሆኑ መረጃዎችን ዋቢ አርገው ይጠቅሳሉ። እንደ አንደእሳቸው ገለጻ፤ በወቅቱ የነበረው መረጃም በትክክል ሀብቱ የተገኘበትን ሥፍራ አላመላከተም። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እኤአ በ1979 ባለሙያ በስፍራው ልኮ ባካሄደው ጥናት አካባቢው ላይ በሳይንሱ መጠሪያ “ማቹርድ ነዳጅ” የሆነ የተፈጥሮ ጋዝ መገኘቱን አረጋግጧል። መረጃው ከየትኞቹ የአለት አይነቶች እንደተገኘም በወቅቱ ለማጠናቀር ተችሏል።
ከዚያ በኋላም “ቤሲፕፍራንላፕ” የተባለ የፈረንሳይ ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኝ የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት ዙሪያ በተለያዩ ኩባንያዎች የተደረጉ የፍለጋ ጥናቶችን አሰባስቦ የኢትዮጵያ የነዳጅ አለኝታ ‹‹petroleum potential of Ethiopia›› በሚል ስለሀብቶቹ አይነት፣ የሚገኙባቸውን ሥፍራዎች፣ በምን ደረጃ ላይ እንደሆኑና ምን ሊደረጉ እንደሚችሉ ጭምር ምክረሀሳብ ያካተተበት መረጃ በሚኒስቴሩ ይገኛል። እኤአ በ1998 የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው ወሎ ወረኢሉ አካባቢ የተገኘው ነዳጅ ሀብት የትኛው የአለት አይነት አመንጪ እንደሆነ፣ የነዳጁ አይነትና መረጃው በሙሉ ተካትቷል። መረጃው የተሰሩትን ሥራዎች ለማሳየት ከማገዙ በተጨማሪ ሀብቱን በማስተዋወቅ በልማቱ የሚሳተፉ ኩባንያዎችን ወይንም ባለሀብቶችን ለመሳብ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።
እነዚህን መረጃዎች መሠረት አድርጎ “ፋልከን ፔትሮሊየም” የተባለ ኩባንያም የአባይ ቤዚን ሶስት ከፍሎችን (ብሎኮች) ለማጥናት ከማዕድን ሚኒስቴር ፈቃድ ወስዶ ተጨማሪ ሥራ ሰርቷል። ኩባንያውም በአካባቢው “ኮንአቦን” እና “ወረኢሉ” በሚባሉ አካባቢዎች ሊቆፈር የሚችሉ ሁለት ቦታዎችን ለይቷል። በአካባቢዎቹ ላይ እስከ ሁለት ቢሊየን በርሜል የሚገመት ነዳጅ ሊኖር እንደሚችል የኩባንያው መረጃ አመልክቷል። ኩባንያውም ይሄን ሀብት ለማግኘት ሲሰራ የቆየ ቢሆንም፣ በገንዘብ አቅም ማነስ ባለመቀጠሉ ውጤቱን ማየት አልተቻለም። በአሁኑ ጊዜ መሬቱን ሰንጥቆ ወጥቶ ለገሂዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ላይ እየፈሰሰ የሚገኘው የተፈጥሮ ነዳጅ ዋና የመገኛ ሥፍራው ሌላ ቦታ ነው። ዋና የመገኛ ስፍራዎቹ ኮንአቦንና ወረኢሉ የሚባሉት አካባቢዎች ነው።
“ሥራዎች እየተጀመሩ የሚጓተቱና የሚቀሩ ከሆነ የሚፈለገው ውጤት ላይ እንዴት መድረስ ይቻላል? በሚኒሰቴሩ በኩል ሊደረግ የሚችል እገዛስ የለም ወይ?” የሚል ጥያቄ ለአቶ ተፈራ አነሳንላቸው። እሳቸው በሰጡትም ምላሽ፤ ኩባያዎች ለሥራ የሚያስፈልጋቸውን ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር ውስጥ እንዲያስገቡ መንግሥት መፍቀዱን፣ ባለሙያዎቻቸውንም ይዘው እንዲመጡና በህግ በኩል ኩባንያው ውጤታማ ሆኖ እንዲጠቀም የሚያስችለው ምቹ ሁኔታ መኖሩን አስታውቀው፣ እነዚህ ሁሉ ለኩባንያዎቹ ድጋፍ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በነዳጅና በተፈጥሮ ጋዝ በኩል ወደ ልማት የተቀየረ ነገር ባይኖርም፣ በፍለጋ ግን ጠንካራ ሥራ መሰራቱን የገለጹት አቶ ተፈራ፤ ዘርፉን ለማልማት የገንዘብ አቅምና ባለሙያም የሚፈልግ እንደሆነ ይገልፃሉ። በአገር አቅም የሚቻል ባለመሆኑ አቅሙ ባላቸው የውጭ ኩባንያዎች ላይ የተወሰነ እንደሆነም ይናገራሉ። አቅም ኖሯቸው የሚመጡ ኩባንያዎችም በገንዘብ አቅም ተፈትነው የሚመለሱበት ሁኔታ እንደሚያጋጥም ተናግረዋል።
ኩባንያዎች የማእድን ሀብቱን ካገኙ በኋላ ከልማቱ የመጋራት መብት እንኳን እያላቸው በስራው ያልቀጠሉበት ሁኔታ ጥያቄ ሊያጭር ይችላል። ያም ሆኖ ግን ተስፋ ሳይቆርጡ ፍለጋውንም ወደ ልማቱ የሚገባ ባለሀብት ማፈላለግ ላይም ጠንክሮ መስራት የግድ ይላል። በተለይ ደግሞ እንደ አገር ያሉ ተግዳሮቶችን መፈተሽም ይጠበቃል።
ከተግዳሮቶች አንዱ የሆነውን አገራዊ ለውጥ ሲኖር ወይንም መሪዎች ሲለዋወጡ የልማት ሥራውም አብሮ እንደነባራዊው ሁኔታ የሚለዋወጥ ሁኔታ እንዳይኖር በማድረግ ወይም ስራው ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ላይ ጠንከር ያለ ሥራ መሰራት እንዳለበት ባለሙያው ያስገነዝባሉ። የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት ለኃይል ፍጆታ ብቻ ሳይሆን በግብርናው ዘርፍ ለማዳበሪያም ግብአት የሚውል ዘርፈብዙ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም በማመን ለማዳበሪያ ግብአት እንደውል እያጠና መሆኑን አመልክተዋል። በዘርፉ ቀደም ሲል ተደራጅተው የተቀመጡትን መረጃዎች በማስተዋወቅ ኩባንያዎችን የመሳብ ሥራም መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም