ኢትዮጵያ በርካታ ቋንቋ ተናገሪ ሕዝቦች ያለባት ሀገር ነች።ዘርፈ-ብዙ ባህላዊ እሴቶች፤ ወግ ልማዶች መገኛም ነች።ይህች መልከ ብዙ ህብረ-ብሔራዊት ሀገር ታዲያ ዛሬም ድረስ አንድነቷንና ህብረቷን ከነውብ ባህሎቿ ጠብቃ ማቆየት የቻለችው በእነዚህ ለዘመናት ትውልድን እየተሻገሩ በመጡት እሴቶች፤ ወጎችና ልማዶች ነው።በዛሬው ‹‹የሀገርኛ›› አምዳችንም ተዝቀው ከማያልቁት ውብ ባህላዊ ስርዓቶች መካከል አንዱ የሆነውን የከፋ ብሔረሰብ ወግና ልማድ በጥቂቱ ልናስቃኛችሁ ወደድን።
የከፋ ሕዝብና አካባቢው በተለይ የሚታወቀው የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታ በሆነው ቡና ነው። በዚህም ከፋዎች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ሕዝብ ዘንድ እውቅና አላቸው። ከዚህም ባሻገር ይህ ብሔረሰቡ በሀገሪቱ በጥንታዊ የመንግስት ምስረታ ይታወቃል። ይህ ደግሞ የላቀ ታሪክ ባለቤት ያደርጋቸዋል። ለኢትዮጵያውያን የጋራ ጉዞ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱም እንደሆኑ ያረጋግጥላቸዋል። ዛሬ የምናነሳው ግን አንዱን ክፍሉን ነው። ይህም የዚህ ብሔረሰብ እሴት ከሆኑት ስርዓቶች ውስጥ ባህላዊ የሠርግ እና ለቅሶ ሥርዓቶቹን ሲሆን፤ ተከተሉን።
የከፋ ሕዝብ የሠርግ ሥነ ሥርዓት
አቶ በቀለ ወልደማሪያም የተባሉ ፀሐፊ በ1996 ዓ.ም ‹‹የከፋ ሕዝቦች እና መንግሥታት አጭር ታሪክ›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መፅሐፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት፤ የከፋ ሰው በደስታም ጊዜ ደስታውን ይካፈላል።ለምሳሌ ልጁን የሚድር ቤተሰብ እንደቅርበቱና ከዚህ በፊት ይኸው ቤተሰብ ለሌሎች ባደረገው የድጋፍ መጠን ገንዘብ እንዲሁም ለድግሱ የሚሆን የተዘጋጀ የምግብና የመጠጥ አቅርቦት ትብብር ይደረግለታል። በሐዘን ጊዜም እንዲሁ የሐዘን ዘፈን እንደሚዘፈን ሁሉ በሠርግ ጊዜም የሠርግ ልዩ ልዩ ዘፈኖች ይዘፈናሉ።
ለሠርግ ብቻ የሚዜም ዜማ ያለና በተወሰኑ የሠርጉ ሂደቶች ለምሳሌ፡- በሁለቱ ሙሽሮች ማለትም በወንድና ሴቷ ቤት ሲደርስና ሙሽሪትን ይዘው ወደ ወንዱ ቤት ሲደርሱ የተለያዩ ዘፈኖች ይዘፈናሉ።ይህ ደግሞ በህብረተሰቡ ዘንድ የተለመደ ነው።በተጨማሪም በዚህ የሠርግ አጋጣሚ ሌሎች የተለያዩ መልዕክቶች ያሏቸው ዘፈኖች ለሚፈለገው አካል ይደርሳሉ።ይህ የሠርግ አጋጣሚ ወንዶችና ሴቶች በአንድነት እንዲዘፍኑና እንዲጨፍሩም ያደርጋቸዋል።
እንደ አቶ በቀለ ማብራሪያ፤ በከፋ ባህል መሠረት የተደበቁ ምስጥሮች እና አሽሙሮች እንዲሁም የተቋውሞ ወይም የጀብዱ ተግባራትን የሚያወሱ መልዕክቶች ዘፈን በማውጣት ይተላለፋሉ።በተለይም ከፍተኛ የመከፋት ሁኔታ ሲኖር አልፎ አልፎ ተቃውሞውን በልቅሶው ዜማ የማስተላለፍ ልምድ አለ።ሆኖም በዋናነት ሠርግና ክብረ በዓላት የሕዝብን ስሜት ለማስተላለፍ ልዩ አጋጣሚዎች ናቸው።
የከፋ ባህላዊ የጋብቻ ሥርዓት ለአቅመ-አዳም ለደረሰ ልጅ በወላጆቹና በዘመድ ጥቆማ ከተመረጠች በኋላ እና ከተቻለም ወንዱ በሆነ መንገድ እንዲያያት ከተደረገ በኋላ የሚጀምር ነው።ምርጫውም በተለያየ መንገድ ስለ ሥነ- ምግባሯና ሙያዋ እንዲሁም ስለቤተሰቧ ሥነ- ምግባር ጥናት ከተደረገ በኋላ ይከናወናል።በእናትም ሆነ በሰባት በኩል ዝምድና ብቻ ሳይሆን የጎሳ አንድነት ያላቸው ቤተሰቦች በፍጹም ሊጋቡ አይችሉም።ይህም ማለት ከሴትና ወንድ ተጋቢዎች እናቶችና አባቶች መሀል በእናትም ሆነ በአባት በኩል ለምሳሌ፡- በሴቷ አራት አያቶች እና ከወንዱ አራት አያቶች መሀል በጎሳ ተመሳሳይ የሆነ ካለ ጋብቻው ይቀራል ሲሉ አቶ በቀለ ያስረዳሉ፡፡
እናት ወይም ቤተሰቡና አግቢው ከተስማሙ በኋላ ሽማግሌ በመላክ ልመና ይደረጋል።የሴቷ ቤተሰብ ለመልሱ ቀጠሮ ይሰጣል፣ የራሱን ጥናት አድርጎ መልሱን ያሳውቃል።መልሱ አሉታዊ ከሆነ በአብዛኛው በመልዕክተኛ አማካይነት ለወንዱ ቤተሰብ ይደርሳል። አዎንታዊ ከሆነ ግን ቀድሞውኑ የተላኩት ሽማግሌዎች ተመልሰው እንዲሰሙ ቀጠሮው ይጠበቃል።ለዚህም በተለያየ መንገድና በተለይም በእናቷ በኩል የሴቷ ስሜት የሚጣራ ሲሆን የወላጆች ወሳኝነት ግን ከፍተኛ ቦታ ይኖረዋል፡፡
ከዚያም በሁለቱም ተጋቢዎች ቤተሰብ ቤት ሠርግ የሚደገስ ሲሆን፤ ጋብቻው በተራራቀ አካባቢ በሚገኙ ቤተሰቦችም መሐል ስለሚሆን የጥሎሽ ስጦታው የሚከናወነው በሠርጉ ዕለት ይሆናል። ይህም ሙሽራውና አጀቢዎቹ ከመድረሳቸው አስቀድሞ የተወሰኑ ሰዎችን በመላክ የሚከወን ነው። የሚጠበቀውን ያህል ጌጣጌጥና ስጦታ ካልመጣ ግን ውዝግብ ሊፈጠር ይችላል። በአብዛኛው ግን በዋስ የሚያልቅበት ስርዓት አለ።ሆኖም ዋስ የተጠራበት ጉዳይ እስከ ምላሹ ዕለት ተሟልቶ መታየት ይኖርበታል።
እንደ ጸሐፊው ማብራሪያ፤ ወንዱ ሙሽራና አጃቢዎቹ ሲመጡ መቃረባቸውን የሚያሳውቁበት ልዩ መልዕክት አለ።ይኸውም ‹‹ሻመቶ›› የሚባል ከቀንድ የተሰራ የሙዚቃ መሳሪያ ድምጽ ነው። ከሙሽራውና አጃቢው ቀደም ብሎ በሚሄድ በሽማግሌዎች በሚመራ ቡድን የጥሎሽ አሰጣጡ ሥነ- ሥርዓት ይካሄዳል። ከዚያም ከሴቷ ቤተሰብ የይግቡ መልዕክት ሲደርስ የወንዱ አጃቢዎች ለሠርግ ብቻ የሚዘፈን ጨዋታ ይጀመራል። ወንዱን ሙሽራ የሚያሞግስና በትዳር ዘመናቸውም ከሴቷ የሚጠበቀውን ባህሪይ የሚያትት መልዕክት ያለበት ዘፈንም እየዘፈኑ ወደ ውስጥ ይዘልቃሉ።
በጋብቻው ወቅት ከወንዱ ወገን የቀኝ ሚዜና የግራ ሚዜ የሚባል ሁለት ሚዜዎች ይኖራሉ። ከሁለቱ ሚዜዎች የቀኝ ሚዜው ትልቅ ኃላፊነት ያለበት ነው። ምስጢረኛና የቁርጥ ቀን ጓደኛ ተደርጎ ይወሰዳል። በትዳር ዘመናቸውም በተጋቢዎች መሐል አለመግባት ሲፈጠር የመጀመሪያው አማካሪና መፍትሔ ሰጪ እርሱ ነው። ይኸው የቀኝ ሚዜ በሠርጉም ዕለት ሙሽሪትን ከወላጆቿ ቤት ስትወጣ በጀርባው አዝሎ ከቤት የማስወጣት ኃላፊነት ያለበት ነው። በጉዞው ወቅትም ከዚሁ በተረፈ ለሙሽሪት ጃንጥላ መያዝ፣ በፈረስ ላይ ስትቀመጥ ከጎኗ ሆኖ ደግፎና ተንከባክቦ የማድረስ ኃላፊነት አለበት።ወደ ወንዱ ቤት ሲመለሱ በጉዞ ላይ ሙሽሪት ከፈረስ ላይ የምትወርድበት አጋጣሚ ቢፈጠር በእግሯ መሬት እንዳትረግጥ የመሸከም ወይም መርገጫ ማንጠፍም የቀኝ ሚዜ ግዴታ ነው ይላሉ ጸሐፊው።
በከፋ ባህላዊ ጋብቻ የሴት ሚዜ የሚባል ነገር የለም።በዕለቱም ሆነ በጊዜያዊነት ለተወሰነ ጊዜ ሴቷን የምትደግፍ ረዳት ሴት አብራ የምትሄድበት አጋጣሚ አይኖርም። ስለዚህም ተንከባካቢዋ የወንዱ ሚዜ ብቻ ነው። በጉዞ ወቅት ሙሽሮቹ በተለይም ሴቷ ሙሽራ የምትቀመጠው ፈረስ ወይም ባዝራ ላይ እንጂ በቅሎ ላይ አይደለም።ይህ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ በዋናነት በቅሎ መካን ስለሆነች ሙሽሪትም በቅሎ ላይ ከተቀመጠች መሐን ልትሆን ትችላለች ተብሎ ስለሚታመን ነው።በተመሳሳይ በቅሎ የመደንበር ባህርይ ሊኖራት ስለሚችል ከአደጋ ለመከላከል መሆኑን አቶ በቀለ ያስረዳሉ፡፡
በከፋ ባህል ሙሽሪት ስታገባ የተለያዩ ስጦታዎችን ከወላጆቿ ቤት ይዛ ትሄዳለች። ከእነዚህም ውስጥ በተለያየ ቀለማት ከተነከረና በትንንሹ ተሰንጥቆ ከተዘጋጀ ዘንባባ የሚሰራ ልዩ ውበት ያለው ‘ሻጎ’ የሚባል የሰሌን ምንጣፍ እና ትራስ አንዱ ነው። በተለያየ ሥዕል የተዋበና ከቆዳ የተሰራ ‘ናቶ’ የሚባል የመኝታ ምንጣፍና ትራስም ሌላኛው ነው። በሙሽሪት ቤት በሴቷ ወላጆችና ቤተሰብ እንዲሁም ወደ ሙሽራው ቤት ሲደርሱ በሙሽራው ወላጆችና ቤተሰብ አባላት የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ይካሄዳል፡፡
ወንዱ ቤት ሲደርሱ ከሠርጉ ቤት ደጃፍ ‘አንብሮ’ የተባለ ነጭ ሰሌን ተነጥፎና ጦር ተተክሎ የሚጠብቃቸው ሲሆን፤ የቀኝ ሚዜው ደግፏት ሙሽሮቹና ሚዜዎች ጦሩን ሦስት ጊዜ ከዞሩ በኋላ ቁጢጥ እንዲሉ ተደርጎ ይመረቃሉ። ሙሽሮቹና ሚዜዎቻቸው ከተወሰኑ የቅርብ ጓደኞቻቸው ጋር በአብዛኛው ከወራት ወይም ከበርካታ ቀናት በኋላ ወደ ሴቷ ቤተሰቦች ለምላሽ የሚጠሩ ሲሆን በተለይም ሙሽሮቹ በምላሹ ወቅት ለቀናት በሴቷ ወላጆች ቤት ይቆያሉ።
ይህ የተለመደው የጋብቻ ሥርዓት ቢሆንም አልፎ አልፎ በጠለፋ ጋብቻ ሊፈፀም ይችላል።ይህም የሚሆነው ሽማግሌ ተልኮ የሴቷ ቤተሰብ ፍቃደኛነት ከተረጋገጠ በኋላ ለመሰረግ አቅም ሲያንስ ወይም አልመች ሲል፤ አልፎ አልፎም ሁለቱ ተጋቢዎች ከተፈቃቀዱና ከተስማሙ በኋላ የቤተሰብ ተፅዕኖ ሲኖር ሆኖ፤ በጣም በተወሰነ ደረጃ ግን ከሴቷ ወገንና ከቤተሰቦቿ አሉታዊ ምላሽ ተሰጥቶም ቢሆን በተወሰኑ ቤተዘመዶቿ በኩል ድጋፍ ሲኖር ሊሆን ይችላል።
በባህላዊ ሥርዓት ከዚህ ውጭና ምንም አይነት ፍንጭ ሳይሰጥ ጠለፋ አይካሄድም።ጠለፋ ከተካሄደም በኋላ ልጅቷ ስለመጠለፏና ማን እንደጠለፋት በተዘዋዋሪ መንገድ መልዕክት ለቤተሰቧ እንዲደርስ ይደረጋል። ቀጥሎም ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ሽማግሌ ተልኮ ዕርቅ ይጠየቃል። በአብዛኛውም ከተደጋጋሚ ጥረት በኋላ ስምምነት ላይ ተደርሶ የሴቷ ቤተሰብ መልስ ይጠራል ሲሉ ነው አቶ በቀለ በመፅሐፋቸው ያብራሩት።
በከፋዎች ዘንድ ዝምድና አንዴ ከተመሰረተ ግንኙነቱ ጥብቅ ነው።ከዝምድና ሁሉ ደግሞ የአማችና ጋብቻ ወይም ‘ናቾ’ እና የሚዜነት ትስስር በከፍተኛ ክብርና ጥንቃቄ የሚያዝ ጠንካራ ግንኙነት ነው።በብሔረሰቡ የክርስትና ዝምድና (አበልጅነት) እና ሚዜነት ከሥጋ ዝምድና ያላነሰ ትስስርና ፍቅር ይቸረዋል።ለዚህ ግንኙነት የሚታጨው ሰውና ቤተሰብም ልዩ ክብር ያለው ከሆነ ነው።በጋብቻ ትስስር በተገናኙ ቤተሰቦችም መሀል መከባበር እንዳለ ሆኖ ከሁለቱም ወገን ታናናሾች ታላቆችን ከማክበራቸው የተነሳ ሰላምታ ሲሰጥ ‹‹መሬት ልተኛልዎ›› (ሽዎች ቀቦና) በማለት እጅ የመንሳትና የማክበር ሰላምታ በመሰጣጣት ነው።በዚህ መልኩ ሰላምታ የቀረበለት ታላቅም የዚህን አፀፋ ከመሬት በላይ ኑር (ሾወ ዳምባ ቤብ) በማለት ይመልስለታል በማለት ያስቀምጡታል በመጸሐፋቸው።
የከፋ ሕዝብ የለቅሶ ሥርዓት
አቶ በቀለ በመጽሐፋቸው እንዳስነበቡት፤ በከፋ ሰው ሲሞት የሃዘን ጥሪ ወይም የድረሱልኝ ጥሪ የሚተላለፈው ከእንጨት ተፈልፍሎ በተሰራ ገንዳ (ሆኮ) እንደ ደውል በመምታት ይሆናል።በጥሪው መሰረትም በመንደሩ ውስጥ የሚኖሩ ወንዶችና ሴቶች ይደርሳሉ። ሟች ያገባ ወይም ያገባች ከሆኑ የሩቅ ዘመድ አዝማድ እስከሚሰበሰብ ድረስ የቀብሩ ሥነ-ሥርዓት አይፈፀምም። እስከዚያው ድረስና ከቀብርም በኋላ በየለቅሶው ጣልቃ ወንዶችና ሴቶች ለየብቻቸው ክብ በመስራት በለቅሶ ጊዜ ብቻ ወይም ደግሞ አልፎ አልፎ በሕዝቡ ላይ በደል ሲደርስ መከፋቱን በተዘዋዋሪ መንገድ ለመግለፅ የሚያዘወትረውን ዜማና ልዩ ውዝዋዜ እያሰሙ ይቆያሉ።
ወንዶች ብቻ የሚሳተፉበት የለቅሶ ጊዜ ዜማና ውዝዋዜ ‘ሂቾ’ ሲባል፤ የሴቶች ደግሞ ‘ጎሞ’ በመባል ይጠራል። ይህም የዜማ ዓይነትና ውዝዋዜ በመሪርና፤ ሟችን የማያውቀውንም ጭምር በሚያስለቅስ የሙሾ ድርደራና ልቅሶ መሀል አልፎ አልፎ የሚካሄድ ነው።የሂቾና ጎሞ የግጥም ይዘት የሟችን ደግነት፣ ጀግንነት፣ ችሎታና ብቃት የሚዘረዝር ነው። እንዲሁም ስለሞቱና ከሞት በኋላ ስለሚታወስለት ደግ ሥራም ይወሳል።
ይህ ዜማና ውዝዋዜ በየለቅሶው መሐል ሲደረግ ለቀስተኛው መጠነኛ እረፍት እንዲያደርግና እንዲፅናና ይረዳል።ይሁንና ይህ ዜማና ውዝዋዜ ባለፉት ጊዜያት በተደረጉ የተለያዩ ተፅዕኖዎች የተነሳ እየተረሳና እየጠፋ የመጣ ቢሆንም በቅርቡ ደግሞ የተፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም በብዙ አካባቢዎች እንደገና የማንሰራራት ሁኔታ ታይቶበታል ይላሉም ጸሐፊው።
በለቅሶ ጊዜ የሟች የቅርብ ዘመዶች ሁሉ ፀጉራቸውን ይላጫሉ፤ በአንገታቸው ላይ ነጭ ክር ያስራሉ የሚሉት ፀሐፊው፤ በጠቅላላው የሟች ቤተሰቦች መሪር ሐዘን የሚያዝኑበት ጊዜ ነው።ከቀብር በኋላም ለረጅም ጊዜ ከጎረቤትና ከዘመድ ቤት ቡና እና ቁርስ እንዲሁም ምግብና መጠጥ የሚቀርብ መሆኑን ይጠቅሳሉ። የዚህ አይነቱ እዝን ማምጣት ከጉርብትና እና ከዝምድና በተጨማሪ እንደ ብድርም ተደርጎ የሚወሰድ እንደሆነም ያስረዳሉ።
ጨና እና ጌሻ ወረዳ አካባቢ ደግሞ ከዋናው የለቅሶ ቀን ሌላ ቀጠሮ ተይዞ እና ከሩቅ ያለ ዘመድ ሁሉ ተነግሮት ደመቅ ያለ የለቅሶ ሥነ-ሥርዓት የሚካሄድበት ሁኔታ አለ። በተለይም በጋብቻ የተሳሰረ ማለትም አማች ከሆነ እንደዚህ ዓይነቱ ቀጠሮ ቀን በከፍተኛ አጀብ በመቅረብ ለቅሶና ሂቾ ማድረጋቸው ግድ እንደሆነ ያነሳሉ።
በከፍኛ ቋንቋ የመቃብር ቦታ ‘ማሾ’ የሚባል ሲሆን፤ በቀድሞው ዘመን ደግሞ የከፋ የመንፈስ አባቶች ወይም ‹‹አላሞ›› እና ነገስታት የሚቀበሩበት ቦታ የተለየ እንደነበር የብሔረሰቡ ታሪክ ያስረዳል።ይህም የመንፈስ አባቶች የቀብር ቦታ ‘ጉቶ’ ሲባል የነገስታት ደግሞ ‘ሞጎ’ እያሉ ይጠሩታል። የነገስታቱን መቃብር በተመለከተ አቶ በቀለ በጽሁፋቸው ሲያስረዱ፤ ከመጨረሻው ንጉሥ ‘ከአዲዮ ጋኪ ሻሮቺ’ በስተቀር ሁሉም የከፋ ነገስታት የተቀበሩት በአንድ ቦታ ሲሆን፤ ይህም የነገስታት የመቃብር ቦታ የሚገኘው በጠሎ ወረዳ፣ ሻዳ ቀበሌ ልዩ ስሙ ሾሻ በሚባል አካባቢ ነው።የመንፈስ አባቶቹ ግን በየዝርያቸውና በሚወክሉት መንፈስ መሰረት ለየራሳቸው በተለዩ ቦታዎች ይቀበራሉ፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም