የኢትዮጵያን ገናና ታሪክና የነጻነት ልዕልናዋን ከሚገዳደሩ ተግባራት አንዱ እና ቀዳሚው ድርቅ እና ድርቅን ተከትሎ የሚከሰቱ የረሃብ የታሪክ ገጿ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ የቀደመ የታሪክ ገጿ ታዲያ “ኢትዮጵያ” የሚለውን ስም የቃላት መፍቻዎች ከረሃብ እና ድርቅ ጋር አያይዘው እንዲያሰፍሩት ያደረገ ጭምርም ነበር፡፡
ምንም እንኳን ይሄንን ስም ለመቀየር በተወሰዱ ተግባራት የስሙን ትርጓሜ ከመዝገበ ቃላት ላይ እንዲፋቅ ማድረግ ቢቻልም፤ ኢትዮጵያን ግን እየደጋገመ ከሚጎበኛት አስከፊ ድርቅ፤ ዜጎቿንም አልፎ አልፎ ደግሞ ይሄን ተከትሎ ከሚከሰት ረሃብ ሙሉ በሙሉ መላቀቅ አልተቻለም፡፡ በዚህ ረገድ የሩቁ ቀርቶ ቀረብ ካሉት አንጻር እንኳን ሲታይ በንጉሱ፣ በደርግ፣ በኢህአዴግም ሆነ በብልጽግና የአስተዳደር ዘመናት በየአስር ዓመቱ፣ በየአምስት ዓመቱ፣ በየሁለት ዓመቱ እየተደጋገመ ከመከሰት አልፎ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች አሁን ላይ ለተከታታይ አምስት የዝናብ ወቅቶች ሰማይ ለምድር ውሃ ለመለገስ የጨከነበትን ወቅት መመልከት ተችሏል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ቦረናን ጨምሮ አስር በሚደርሱ ዞኖች የተከሰተው ድርቅ እና ይሄን ተከትሎ ዜጎች ለከፋ የሰብዓዊ ችግር የተዳረጉበትን እውነት፤ በሶማሌ፣ በደቡብ እና ሌሎችም አካባቢዎች መሰል ችግሮችን እየተጋፈጡ ያሉ ወገኖችን እንደ ማሳያ መጥቀሱም የችግሩን አሳሳቢነት ለመገንዘብ የሚያስችል ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የእንስሳት “ዝርያን ለማቆየት” በሚባል ደረጃ እስከ መግለጽ የደረሰ የከፋ ችግር ገጥሟል፡፡
በአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ዜጎችም እንስሳቶቻቸውን ከማጣታቸውም በላይ ሕይወታቸውን ለማቆየት የሚችሉበትን እህል ውሃ ለማግኘት እጆቻቸውን ለመዘርጋት ተገድደዋል፡፡ የችግሩን አሳሳቢነት የተገነዘበው መንግስት እና መላው ሕዝብም ለወገኖቹ ለመድረስ የአስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረስ የወገኖቹን ሕይወት እየታደገ፤ ለእንስሳቱም መኖ እያቀረበ ይገኛል፡፡
ይሄን አይነት ድርቅ ሲከሰት ችግሩን በጊዜያዊነት ለመሻገር እና ዜጎችን ለመታደግ የሚሰሩ ስራዎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ለጊዜውም ቢሆን ዜጎች ሕይወታቸውን እንዳያጡና ችግሩን እንዲሻገሩ ያደረግልና፡፡ ይሁን እንጂ ድርቅ በመጣ እና ዜጎች ችግር ላይ በወደቁ ቁጥር የሚከወን የአስቸኳይ ድጋፍ ብቻውን የዜጎችን ሕይወት ሊለውጥ፤ ዘላቂ መፍትሄም ሊያመጣ አይችልም፡፡ በመሆኑም ድርቅ በተከሰተ ቁጥር ከሚከወን የሰብዓዊ ድጋፍ የዘመቻ ስራ የተሻገረ ተግባርን መከወን የተገባ ነው፡፡
በዚህ ረገድ አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ከማድረስ በተጓዳኝ፤ ተደጋጋሚ ድርቅ የሚያጠቃቸውን ቦታዎች እንዲሁም፣ በሰው ሰራሽ ችግር ምክንያት ለድርቅ እና ሌሎች ተፈጥሯዊ አደጋዎች የመጋለጥ ስጋት ያንዣበበባቸውን አካባቢዎች መለየት የመጀመሪያው ስራ ሊሆን ይገባል፡፡ እነዚህ ቦታዎች ከተለዩ በኋላ፣ እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ የየአካባቢውን ማኅበረሰብ ባሳተፈ እና ባለቤት ባደረገ መልኩ ድርቅን ለመከላከል የሚያስችሉ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች፤ የአረንጓዴ አሻራ ስራውን የሚደግፉ የችግኝ መትከል ተግባር፤ የውሃ ማቆር እንዲሁም አነስተኛ እና መካከለኛ የመስኖ ልማት ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችሉ ግድቦችን መገንባት ያስፈልጋል፡፡
ይሄን መሰል ተግባር በአንድ በኩል የአካባቢውን ለድርቅ የመጋለጥ ዕድል የሚቀንስ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ድርቅ ቢከሰት እንኳን ቀደም ብሎ የሚያዙ ውሃዎች እና የተሰሩ ግድቦችን ተጠቅሞ የመስኖ ስራዎችን ለማከናወን እና ችግሩን በራስ አቅም ለማሻገር የሚቻልበትን እድል ይፈጥራል፡፡
በዚህ ረገድ ቀደም ሲል ድርቅ በተደጋጋሚ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች የተሰሩ የተፋሰስ ስራዎች ያመጡትን ውጤት ለዚህ እንደ አንድ የውጤታማነት ማሳያ ተሞክሮነት የሚወሰዱ ሲሆን፤ በአንጻሩ ለአምስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ዝናብ ርቆት ለከፋ ድርቅ የተጋለጠው የቦረና ዞን ከእለት የተሻገረ ሩቅ አስቦ ያለመስራት የሚፈጥረውን ችግር ሕያው ምስክር ሆነው ይገለጻሉ፡፡ በመሆኑም ድርቅን ተከትለው የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል ከዕለት ደራሽ ድጋፍ ያለፈ ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም ወደሚያስችሉ ተግባራት ተገቢም የግድም ነው!
አዲስ ዘመን መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም