‹‹ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት እኔም ሙሉ አካል ነበረኝ።በሬ ጠምጄ የቤተሰቦቼን እርሻ ማርስም ጎበዝ ነበርኩ።ያኔ በተወለድኩበትም ሆነ በየትኛውም ሥፍራ ክብር ሲሰጠኝ ቆይቷል።እግር ነበረኝና እንደ ዛሬ የሚንቀኝና የሚያጠቃኝም አልነበረም ›› ይሄን ምሬትና ቁጭት አዘል አስተያየት የሰጡን ቅድስተ ማርያም አካባቢ ያገኘናቸው መሪ ጌታ ታሪኩ አበበ ናቸው።
ደጋግመው ‹‹ሙሉ አካል ያስከብራል›› የሚሉት መሪ ጌታ ታሪኩ እንዳጫወቱን ተወልደው ያደጉት መርሀ ቤቴ ደራ ከተማ ነው።ከሰባት ዓመት በፊት ታዲያ በገጠር ቀመሷ ደራ ከተማ ውስጥ በሙሉ አካላቸው ሲንቀሳቀሱ ኖረዋል።ሁሉም የሰውነታቸው ክፍል ምንም ችግር ያልነበረበት ጤናማም ነበሩ።በሬ ጠምደውም ከአሥር ገዝም በላይ የቤተሰቦቻቸውን እርሻም አገላብጠው የሚያርሱ ጎልማሳ ነበሩ።በቤተ ክህነት ትምህርት ከፊደል ጀምረው እስከ መሪ ጌታ የደረሰ ዕውቀት በመቅሰማቸውም በአካባቢያቸው በነበረው የደራ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ለዓመታት በድቆናም እያገለገሉ ቆይተዋል።ሙሉ አካል በነበራቸው ጊዜ በዚሁ በቤተ ክህነት የተማሩትን ዜማና ግጥም መሰረት ያደረገ የቅዳሴ ስነስርዓት ትምህርት መሰረት አድርገውም ይቀድሱም ነበር።ታዲያ ያኔ ክብር ነበራቸው።ብዙ የሚያውቋቸው ሰዎች ሰላምታ ሲሰጧቸው እንኳን እጥፍ ዘርጋ ብለው ነበር።በየትኛውም ሥራ ለመሳተፍም ቀዳሚው ተመራጭ እሳቸው ነበሩ።ከእርሻና ከቤክርስቲያን ግልጋሎት ውጪ ጠመንጃቸውን ይዘው ጎምለል ጎምለል ዞር ዞር በማለት አካባቢያቸውን የሚጠብቁ ተፈሪም ነበሩ፡፡
የዛሬ ሰባት ዓመት ግን ይሄን ክብራቸውን የገፈፈ አደጋ ገጠማቸው።እራሳቸውንና አካባቢያቸውን የሚጠብቁበት ጠመንጃቸው እንዳይቆሽሽ ሁሌም እንደሚያደርጉት እየወለወሉ ነበር።የሚወለውሉት ላያቸው ላይ አስቀምጠው ነው።በሚወለውሉበት ሰዓት ጥይት መውጫ አፈ ሙዙ ታፋቸው ስር ነበርና ጠመንጃው ባርቆ የግራ ታፋቸውን ገንጥሎ ጣላቸው። በዚህ ምንክንያት አካል ጉዳተኛ ሆኑ።ግን በአካላቸው ላይ በደረሰው ጉዳት ምክንያት እንደበፊቱ ሥራ ለመሥራት አልቻሉም።ቤተክህነትም በቀድሞ አገልግሎታቸው ልታስቀጥላቸው አልቻለችም።ምንም እንኳን አካል ጉዳተኝነት ስራን ባይከለክልም በሕብረተሰቡ ውስጥ የነበረው የተዛባ አመለካከት ሥራ ሰርተው ራሳቸውን ማስተዳደር አንዳይችሉ አደረጋቸውⵆ ‹‹እንዲህ ሆኜ የተወለድኩበትና ያደግኩበት አካባቢ አልኖርም›› በማለትም ጊዜ ሳያጠፉ ፈጥነው ወደ
አዲስ አበባ መጡ።አዲስ አበባም ቢሆን ሕብረተሰቡ ለአካል ጉዳተኛ ያለው አመለካከት የበለጠ የተዛባ በመሆኑ መፍትሄ እንዳልሆናቸውም አቶ ታሪኩ ይናገራሉ።
“እዚህ ከመጣሁ ጭራሽ ክብሬንም በአካሌ ጉዳት ምክንያት የተገፈፍኩ እስኪመስለኝ ድረስ ጥቃትና ንቀት ደረሰብኝ›› ሲሉም ይናገራሉ።እንደሚሉት አዲስ አበባ የመጡት የዛሬ ሰባት ዓመት አደጋው እንደረሰባቸው ነው።ታዲያ ያኔ መጠለያም አልነበራቸውምና በጣም ተቸግረዋል።ውሎ ሲያድር ጃን ሜዳ መግቢያ አካባቢ ያሉ የመከላከያ አባላት እዛው አካባቢ ቆርቆሮ በቆርቆሮ የሆነች ልታስጠልላቸው የምትችል ተንቀሳቃሽ ቤት ተጋግዘው ሠሩላቸው።በዚህች ቤት ውስጥ እየኖሩም በአቅማቸው የዕለት ጉርሳቸውን የሚሸፍን ሥራ ማፈላለጉን ተያያዙት።ግን ደግሞ በአቅሜ ልሰራ የምችለውን ዘበኝነት እንኳን ቅጠሩኝ ብለው የጠየቋቸው ብዙ ሰዎች ሳቁበቸው።ተሳለቁባቸው።ሌላው ቀርቶ ሲቀድሱበት በነበረው የቤተክህነት ሙያቸው በሰበካ አስተምሮት ለማገልገልም አራት ኪሎ መንበረ ፓትሪያክ መቀመጫ በሆነችው ቅድስተ ማርያም ገዳምም ጠይቀዋል።ሆኖም በአካላቸው ጉዳት ምክንያት ሥራ መቀጠር በቀላሉ አልሆነላቸውም።ግን ደግሞ በወቅቱ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የሠሩላቸው ቆርቆሮ በቆርቆሮ ቤት በአገልግሎት ብዛት አርጅቶና ወላልቆ ነበርና ሥራው ይሄንንም ለማደስ የሚያስችል ገቢ ለማግኘት ስለሚያስፈልጋቸው ብዙ ሲደክሙ ቆይተዋል።
ያም ሆነ ይህ ከዛው ከቅድስተ ማርያም አካባቢ ሳይጠፉ ጧፍና ሻማ ሲያገኙ በመሸጥም ሲያጡም ከአገራቸው ቋጥረው የመጡትን ገንዘብ በመብላት እንዲሁም የቆርቆሮ ቤታቸውን በማሳደስ ዓመታት ሲያስቆጥሩ ቆዩ።ታዲያ አንድ ዕለት በዚያው በቅድስተ ማርያም ገዳም አካባቢ ታላቋ የዓለም የሰው ዘር ቅሪት ሉሲ የምትገኝበትን ሙዚየም ተደግፈው ከነዊልቸራቸው ቁጭ እንዳሉ ፍሬን የተበጠሰበት መኪናም እላያቸው ላይ ሊወጣ ሲል ነፍስ ይዟቸው ዘለው በመነሳት ብረቱ ላይ በመንጠልጠል ድነዋል።ቁጭ ባሉበት የገጠማቸውና ሕይወታቸውን የተፈታተነ አደጋ ይሄ ብቻ አልነበረም።አንዱ አሽከርካሪ ከነውልቸራቸው በአንድ ጎናቸው ይገጫቸዋል። የገጫቸውም አካላቸው በመጎዳቱ ብዙም ጥንቃቄ ሊያደርግ በማያስችለው ንቀት ነበር።እንዲህም ሆኖ በአንድ በኩል ያለው ዊልቸራቸው በመጎዳቱ ከእሳቸው ይልቅ እግራቸውን ተክቶ ከወዲያ ወዲህ የሚያንቀሳቅሳቸውን ዊልቸር ነበርና ያሳሰባቸው እንዲያሰራላቸው ይጠይቁታል።ሆኖም አሽከርካሪው በጄ አላለም በንቀት እያየ ጭራሽ አሾፈባቸው።መኪና ውስጥ ገብቶም ሊሄድ ሲሞክር ትዕግስታቸው ከልክ በማለፉ አጠገባቸው ተቀምጦ በነበረው አንድ አካል ጉዳተኛ ክራንች የሰውየውን መኪና መስትዋት በሁሉም በኩል አደቀቁት።ወንጀለኛ ተብለውም ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰዱ።ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ የታሰሩበት ቦታ የነበረው መፀዳጃ ዳገታማ በመሆኑ ለእሳቸው አይመችም ነበር።ታዲያ ይህንን በትህትና አሳወቁ።ሆኖም የሚሰማቸው አላገኙም።ከዚህ ሁሉ በመነሳት መሪ ጌታ ሕብረተሰቡ ለአካል ጉዳተኛ ያለው ዝቅተኛ አመለካከት ጉዳተኛውን ይበልጥ የሚያጠቃና የሚያስንቅ ወይም ዝቅ አድርጎ የማየት እንደሆነም ያወሳሉ።“ይሄን የምለው ዝም ብዬ እና ከመሬት ተነስቼ ሳይሆን በራሴ ከደረሰብኝ በመነሳት ነው››ይላሉ።ፍላጎቱ ቢኖራቸውም ሊያሰራቸው የሚችል ሰው አለማግኘታቸውንም እንደ ምክንያት ያቀርባሉ።ማንኛውም በአካል ጉዳተኞች ዙርያ የሚደረግ ድጋፍ ሁሉንም አካል ጉዳተኞች ተደራሽ ማድረግ አለበት የሚል ሀሳብም አዘውትረው ሲያንፀባርቁ ይደመጣሉ፡፡
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር የአካል ጉዳተኞችና አድቮኬሲ ዴስክ ቡድን አስተባባሪ አቶ ሲሳይ ጥላሁን ሕብረተሰቡ ለአካል ጉዳተኞች ያለው አመለካከት በአካል ጉዳተኞች ላይ ተደራቢ ችግር የሚፈጥር መሆኑን ይናገራሉ።አሁንም አመለካከቱ ሙሉ በሙሉ አለመቀረፉንና ለመቅረፍ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መገኘታቸውንም ያወሳሉ።እንደ አገር የሚደረገውም ድጋፍ ሁሉንም የአካል ጉዳተኞች ተደራሽ እንዲያደርግ እየተሰራ መሆኑን ያነሳሉ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም