“ሰው ፖለቲካዊ እንስሳ ነው” ይላል የፍልስፍና አባት አርስቶትል፤ ሰው ፖለቲካዊ እንስሳ (Political Animal) ከሆነና ፖለቲካም የግድ ከሆነ፣ የትኛው መስመር ይበጀዋል፤ የቱስ ነው ትክክል፣ ማንስ ነው ታማኙ፣ የቱስ ነው አስተዋይ፣ ማንስ ነው ተስተዋይ? እነዚህን ሀሳቦች ይዘን አብረን እንዘልቃለን።
ዓለማችን አንድ መንደር ሆናለች፣ የሚያስፈልገን መከፋፈል ሳይሆን “መደመር” ነው፤ ይህ እውን የሚሆነው ደግሞ በሉዓላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ነው (ወይም አዲሱ የዓለም ሥርአት) ከምትለው አሜሪካ ጀምሮ፤ ያለው እድል አብሮ ማደግና በጋራ ተጠቃሚ መሆን ነው እስከምትለው ዘመናዊቷ ቻይና ድረስ የርእዮተ-ዓለም ጋጋታው ነጋ ጠባ ደም እንዳፋሰሰ እንጂ ሰላምን መሬት ሲያወርድ አልታየም። በተለይ የብሔር ፌደራሊዚም ነው የሚያስፈልጋችሁ በማለት የተመከሩ አገራት ፍዳቸውን እያዩ መሆኑ ጉዳዩን ዳግም ለመመርመር ያስገድዳልና መመርመር ያለበት ቢመረምረው አይከፋም።
ዓለምን ጉድ እየሰሯት ያሉት የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን ናቸው፤ በፍፁም፣ ዓለማችንን ለዚህ አይነቱ ምስቅልቅሎሽ የዳረጓት የተፈጥሮ ሳይንስ ምሁራን ናቸው የሚለው እሰጥ አገባ (እዚህ ላይ፣ ለ“ባላንስ” ሲባል፣ እናንተ በአግባቡ ብትመሯት ኖሮ እኛም የጦር መሳሪያ ተኮር ምርምሮችን ባላካሄድን ነበር የሚሉትን የተፈጥሮ ሳይንስ ምሁራንን አስተያየት ማንሳት ተገቢ ይሆናል) በተለያዩ ጊዜያት በከፍተኛ ደረጃ የመወያያ ርእሰ-ጉዳይ ሆኖ ኖሯል። ወደዛ አንገባም።
የስነልቦና አባት የሚባለው ሲግመን ፍሩድ የሁሉም ነገር መነሻ ‹‹ወሲብ›› ነው በማለት የስነምግባር ጥሰት ይፈፀም ዘንድ መሰረቱን የጣለው ሳይረሳ፤ ለዓለማችን መፍትሄው ኮሚኒዝም ብቻ ነው በማለት የኢምፔሪያሊዝምን ማጣፊያ ሥርአት የዘረጋውና ምድርን በሁለት ጎራ በመክፈል እያጠዛጠዘ የሚገኘው ካርል ሔንሪክ ማርክስ ሳይዘነጋ፤ ሰው ከዝንጀሮ ነው የመጣው በማለት ተከብሮ የኖረውን፣ የዓለምን የእምነት መሰረት በማናጋት ለሁለት የከፈለው ኢቮሊዩሽኒስቱ ዳርዊን ሳይታለፍ፤ የአውዳሚነት ባለሟሉ ፍሬደሪክ ኒች ሳይዘለል፤ (ከ“መሪ”ዎች) ተከታዮቹ እየበዙ የመጡትና ሕገመንግስት ለምኔው ኢድ አሚን ጋጋ ሳይሰረዝ . . . ሌሎችም በርካቶች ሁሉ ተደማምረው የዛሬዋ ዓለማችንን ውስብስብ አድርገዋት ይገኛሉ።
እነዚህና መሰሎቻቸው፣ ምንም እንኳን እነሱ ቢያልፉም፣ ለአእምሮ ጅምናስቲክ ብለውም ይሁን ለሰው ልጅ አስበው የሰነዘሯቸው ሀሳቦችና እሳቤዎች ዛሬም ድረስ ብዙዎችን ያለ እንቅልፍ እያሳደሩ ይገኛሉ። በአካዳሚው ደብር ሳይቀር በእነሱ ላይ የሚካሄደው ውዝግብ ሌላ ነው። ባለቅኔው ጎሞራው (ኃይሉ) በ“በረከተ መርገም” የወረደባቸው “ውርጅብኝ” እንዲህ በቀላሉ ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም።
እንደ አንዳንዶች፣ ዓለማችንን ከሚያዋክቧት ቀዳሚው የማህበራዊ ሳይንሱ ዘርፍ አካል የሆነው ፖለቲካ ነው። ድሮ ድሮ ኃይማኖት ነበር ቢባልም፤ ዛሬ እሱ ራሱ ተጠልፎ፣ በፖለቲካው ምህዋር ስር ሲሽከረከር እንጂ በነበረበት ሁኔታና አኳኋን ላይ ሆኖ እንኳን አይታይም። በግድ እንጠራጠር ካልተባለ በስተቀር እጅ ሰጥቷል። እንደውም፣ አንዳንዶች እንደሚሉት የኃይማነትና ኃይማኖተኛነት ጉዳይ 18ኛው ክፍለ ዘመን ላይ “ቻው” ብሏል።
እርግጥ ነው የፖለቲካን ጉዳይ እዚህ እንዲህ ነው፤ እንዲያ ነው፤ እንዲህ አይደለም፣ እንዲያ አይደለም . . . በማለት የመጨረሻ ብያኔን ልንሰጠው እንቸገራለን። ለመቸገራችን ትልቁ ምክንያት ደግሞ መስኩ ሁሉም የሚሳፈረው ባቡር፤ ማንም የሚጋልበው ፈረስ የመሆኑ ጉዳይ ነው። በያኙም እንደዛው።
የዛሬዋ ዓለማችን ጉደኛ ነች። ለጉደኛነቷ ደግሞ ዋናው ምክንያት ዛሬ ማንም ተነስቶ ፖለቲከኛ የመሆን ሙሉ መብት አለው። ፈሪሀ እግዚአብሔር ያደረበት ካልሆነ በስተቀር “አልችልም” ብሎ ነገር የለም። እንደፈለገው ማድረግ፤ ያገኘው ላይ ሁሉ መፍረድ ዘመኑ የሚፈቅደው “ተራማጅ” አስተሳሰብ ነው።
ድሮ ጥልቅ እውቀት ወደ ፖለቲከኛነት ያመጣ ነበር ነው የሚባለው። ዛሬ በሀሰት ትርክት የትም መድረስ ይቻላል ነው የሚሉት የዚህ አስተሳሰብ አራማጆችና የእውነት ተቆርቋሪዎች። ድሮ መንደሬ፣ መንደሬ ማለት ያሳፍር ያልነበረውን ያህል ዛሬ አገሬ፣ አገሬ ማለት፣ ፅድቁ ቀርቶ . . . እንዲሉ፣ ሊያስጠይቅ ሁሉ ይችላል ሲሉ ምንም አያፍሩም፣ አይፈሩምም።
ዛሬ “መንገዶች ሁሉ ወደ ብሔር ይወስዳሉ” የተባለ ይመስል (በተለይ በአፍሪካ) ብሔር፣ ብሔር . . . ያለ፣ የብሔር (በእውቀቱ ሥዩም አንዳንድ ሰዎች “እግዚአብሔር” ከሚለው፣ እንዲመቻቸው አድርገው “እግዚአ”ን ገንጥለው በማስቀረት “ብሔር”ን ፈጠሩ ካለው ጋር ግንኙነት የለንም) ፖለቲካን ያቀነቀነ ምንም ቢሆን ፆሙን አያድርም ነው የሚባለው። አንድም አማራጭ የፖሊሲ ሰነድ እጁ ላይ ሳይኖር በ“ብሔሬ ተጨቆነ” ትርክት ብቻ የወንበርና መንበር ቁንጮ ላይ ፊጥ ማለትና መቶጀር የመቻሉን ጉዳይ “በአይናችን እያየን ነው” የሚሉ “ፋራ”ዎች ብዙ ናቸው። ናይጄሪያን ምሳሌ እየጠቀሱ፤ ወደ ደቡብ ሱዳን ጎራ እያሉ መረጃ እያጣቀሱ፤ የሶማሌውን የጎሳ ትርምስ “እነሆ በረከት” በማለት . . . “ቺርስ!!!” የሚሉ የመኖራቸውን ያህል፣ “ተከድኖ ይብሰል እንጂ የትም ያው ነው” ባዮችም ቁጥራቸው ከእነ“ቺርስ! ” በላይ ነው።
ዓለምን ከሚገመግሙቱ፣ የቻይና ኮሚኒዝም ሀብት እንጂ መብትን አላጎናፀፈም፤ ከሚሉቱ ጀምሮ “የአሜሪካ ዲሞክራሲስ በአፍንጫዬ ይውጣ” እስከሚሉት ድረስ እስከሚዘልቁቱ ያሉት አስተያየቶች የትየለሌ ናቸው።
ከካፒታሊዝም/ኢምፔሪያሊዝም ጋር አይንና ናጫ የሆነውን ሶሻሊዝም/ኮሚኒዝም ለዓለማችን ብቸኛው አዋጭ (ረማጭ የሚሉት እንዳሉ ሆነው) የፖለቲካ ፍልስፍና ነው የሚል ክፍል የመኖሩን ያህል፤ አይደለም የእሱ ተቃራኒ የሆነውን ብቸኛው የዓለማችን መፍትሄ ነው የሚለውም በሽ በሽ ነው።
አንዳንዶች የድሮው (Mode of Production) ዘመነ ስልተ-ምርቶች (የጋርዮሽ፣ የባሪያ ፍንገላ፣ የፊውዳል እና የከበርቴ ስርዓቶች) በስንት ጣእሙ የሚሉ ናቸው። “ምክንያት” ሲባሉ፤ “ቢያንስ ቢያንስ በሰላም ወጥቶ መግባት፣ አብሮ መኖርን የሚከለክሉ አልነበሩምና” የሚለው አጭርና ግልፅ መልሳቸው ነው።
ደጋግመን እንዳልነው፣ ዓለማችን በተለያዩ ርእዮቶች ተወጥራ የተያዘች ነች። ሁሉም እንደየአቅሙና ፍላጎቱ የየራሱን ርእዮት ያራምዳልና ዓለማችን በአራቱም ማእዘን ብትወጠር የሚገርም አይሆንም።
ለመጀመሪያው ውጠራ ያችኑ አሜሪካንን በማሳያነት ሲያቀርቡ፤ ለሁለተኛው ውጠራ ደግሞ ሶቪየትንና ቻይናን በማስረጃነት ያቀርባሉ። እነዚህ፣ የሁለቱ ተቃራኒ የኢኮኖሚ ስርአቶች አራማጆች “የቱ ነው ትክክል?” ብለን እስክንጠይቅ ድረስ እያደናበሩን ያሉት ኃይላት፣ በተለይ ለአፍሪካ የሚጠቅማት ይሄ ነው፣ ይሄ ነው . . . በማለት (ያም ለኔ . . ያም ለኔ . . . እንዲል ድምፃዊው) መንታ መንገድ ላይ በመጣል በኩል እያደረሱት ያሉት ጥፋት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ቀዝቃዛው ጦርነት በዘመናዊ መልክ ተመልሶ የመጣ እስኪመስል ድረስ ምድር ቀውጢ ሆናለች።
ወደ አፍሪካችን ስንመጣ፣ ኮንጎ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ናይጄሪያ፣ . . . በምን ርእዮትና ፖለቲካዊ ፍልስፍና እንደሚመሩ እንኳን እኛ ራሳቸውም የሚያውቁት አይመስልም። አይኤስ (IS) እያተራመሳቸው ያሉትን አገራት ቤቱ ይቁጠራቸው።
የዶችቬሌው ነጋሽ መሀመድና ባልደረባው ወቅታዊውን የሱማሊያ ጉዳይ በስፋት በዳሰሱበት ዝግጅታቸው “ከሰሜንና ሰሜን ምስራቅ የኤደን ባህረ ሰላጤን የተንተራሰችው፣ ከደቡብና ደቡብ ምስራቅ የህንድ ውቅያኖስን የረገጠችው ያቺን ሾጣጣ፣ ስልታዊ ሀገርን ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣች ወዲህ አንድ አድርጎ ለመግዛት ብዙ ርእዮተ-ዓለምና ስልት ተሞክሮባታል። አብዲረሺድ አሊ ሸርማርኬ የምእራባዊያኑን፣ ዚያድባሬ ሶሻሊስታዊውን ርእዮተ ዓለም ገቢር አድርገውባታል። ጀነራል ፋራህ አይዲድ የጦር አበጋዝ አገዛዝን፣ ከአብዲ ቃሲም ሳላት አህመድ እስከ አብዱላሂ የሱፍ አህመድ የተፈራረቁት የጎሳ፣ የፖለቲካና የጦር አበጋዝ ስብጥር አስተዳደርን ሞክረውባታል። አልተሳካም።” በማለት ያለውን እውነታ ከነበሩት ሁኔታዎች ጋር አሰናስለው ይነግሩናል።
የርእዮተ ዓለም መጽሐፍ የሆነው “ማርክሲዝም ሌኒንዝም መዝገበ ቃላትም” “አፍሪካ ሶሻሊዝም (የ-)”ን በፈታበት ገጹ ላይ የሚያብራራውም የዚሁ ተመሳሳይ ሲሆን፣ ባጭሩ የአፍሪካ ችግር ወጥ የሆነ ርእዮተ ዓለም መከተል አለመቻልና በሶሻሊዝም ላይ ጥርት ያለ ሳይንሳዊ መሰረት ያለው ግንዛቤ አለመኖር ነው። ይህ ደግሞ እስከ አህጉሪቱ ህብረት ጽሕፈት ቤት ድረስ የአሰራር ጉዳትን አስከትሏል።
እንደምናውቀው፣ እንደ ሞዴል የምናያቸው የአውሮፓ አገራት (ለምሳሌ ግራ ዘመም ሶሻል ዲሞክራሲ አራማጇ ጀርመን) እና የዲሞክራሲ ወላጅ አባት የምትባለው አሜሪካ “እምንልሽን ካልሰማሽ” በማለት ሩሲያን የውጥር ይዘዋታል። የፑቲን ንክች ያባ ቢላዋ ልጅ አቋም ነው እንጂ ያገዳቸው ዜሌንስኪንን የመታደጉን ስራ አጥብቀው ከያዙት ቆይተዋል። ይህ ሁሉ የሚያሳያን በጦርነቱ እየተጎሳቆለች ያለችው ዓለማችን የትኛው ትክክል እንደ ሆነ ጠፍቷት መሀል መንገድ ላይ እየተናጠች መሆኗን ነው።
እያወራን ያለነው የቱ ትክክል እንደሆነና የትኛው ደግሞ ትክክል እንዳልሆነ ባለመለየት ስለመደናገራችን ቢሆንም፤ ሰው ፖለቲካዊ እንስሳ መሆን ስላለመሆኑ ቢሆንም፣ በዓለማችን የርእዮት ግጭት (ideological conflict) መኖሩንም፤ መኖሩ ብቻ ሳይሆን አገራት ተቃራኒ ርእዮቶችን ሁሉ እያስተናገዱ ስለ መሆናቸውም መመልከት ያልተገደበ መብት አለንና እንቀጥል።
በተለይ ቀዝቃዛውን ጦርነት ተከትሎ አገራትን ጠቅልሎ በስር የመያዝ ፖሊሲን (containment ትለዋለች) የምትከተለው አሜሪካ በምንም መንገድ ሩሲያን በቁጥጥሯ ስር የማድረግ እቅድና ስልቷ ሊሳካላት ያልቻለ ሲሆን፤ ትንቅንቁ እስካሁንም ጋብ ሲል አልታየም። የሁለቱ በሁለት ጎራ መከፋፈልና መጠዛጠዝ አውሮፓዊያኑን ሳይቀር ለሁለት ጎራ (የአሜሪካ ተከታዮቹ Western European nations፤ የሩሲያን ጎራ የሚደግፉ Eastern European nations) እንዲከፈሉ ያደረገ ሲሆን ይህ ጎራ አሁንም በዚያው መንገድ ላይ ብቻ ሳይሆን ጥላውን አፍሪካ ድረስ እንዳጠላ ነው ያለው። ችግሩ እኛ ለእኛ የትኛው ትክክል እንደሆነ መለየት ባለመቻላችን ማእበል እንደሚያላጋው ግንድ እዚህና እዛ እየተላጋን እንገኛለን። በተለይ የእነዚህ ሁለት ኃያላን (አሁን በምእራባዊያኑ ብሎክ የማትወደደው፤ በአፍሪካ ተመራጭ የሆነችው ቻይና ተጨምራለች) በዚህ በአሁኑ ዘመንና ሰዓት እንኳን የእነሱ የርእዮት ግጭት ዓለምን ምን እያደረጋት እንደ ሆነ እያየንና እየሰማን ነው። አፍሪካም “ከእኔ ወይስ ከእሱ” ከሚለው የልጆች ጨዋታ ባልተናነሰ መልኩ “ምረጭ” ተብላ ስቃዩዋን እያየች ስለመሆኗ እኛ፣ የአሁኑ ዘመን ህያዋን ምስክሮች ነን። አሁን ወደ ውስጥ እንምጣ።
እዚህ እኛ አገር ይኑር አይኑር አይታወቅም፤ ወይም፣ ወደ 140 የሚሆኑ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች (በፈረንሳይ ከ1814–1815 ይፈሉ የነበሩትን የፖለቲካ ክበባት የሚያስታውስ) ነበሩ በሚባልበት ጊዜ እንኳን “ተቃዋሚ” ከሚለው በስተቀር እከሌ እንዲህ ነው ተብሎ የፖለቲካ አቋሙ (political outlook ወይም position) ሲገለፅ አይሰማም። ግልፅ የፖለቲካ አቋም እንደሚያራምዱት የአውስትራሊያው ዲሞክራት፤ ኢንዶኔዥያው ጎልካር (Golkar) ፓርቲዎች ማለት ነው። (ለነገሩ እኮ የእኛ አገር የፖለቲካ ፓርቲዎች ምንም አይነት “ኢዝም”፣ አንዳችም አይነት የፖለቲካ አቋም . . . የላቸውም ተብለው መታማት ከጀመሩ ጊዜው ቆይቷል። አማራጭ ፖሊሲ ሲጠየቁ እንኳን “እሱን ምረጡኝና እነግራችኋለሁ” ባዮች መሆናቸው ሲያስተቻቸው እንደ ነበር የሚረሳ አይደለም።
በአንድ ሰሞን የጋራ ውይይታቸው ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ለተቃዋሚ “ፖለቲካ ፓርቲዎች ጽሕፈት ቤት እንስጥ ብንል ኮንዶሚኒየምም አይበቃን” ያሉትን የረሳ ሰው ከዚህ ጽሑፍ ጋር በሚገባ ላይግባባ ቢችል ባይገርምም፣ ዛሬ እነዛ ሁሉ ፓርቲዎች እምጥ ይግቡ ስምጥ ግን የሚታወቅ ነገር የለም።
ሌላው የኛዎቹ የሚታሙበት ዋናው ነገር “ነጠላ ጉዳይ” (ምሁራኑ Single-issue politics ይሉታል) ላይ ብቻ መንጠልጠልና ማተኮራቸው ሲሆን፣ እሱም “ብሔር” እና በብሔር ዙሪያ ላይ ያጠነጠነ፤ የሕዝቡንም ፍላጎት መሰረት ያላደረገ (ያደረገ የሚሉት እንዳሉም ሳንረሳ – ቢያንስ ራሳቸው ስለሚሉት) መሆኑ እያስወቀሳቸው ይገኛል።
በግልፅ እንነጋገር ከተባለ የእኛ አገር ፖለቲካም ይሁን ፓርቲዎቹ ለግለሰብ ነፃነት ግድ የለሾች ናቸው። በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው፣ ሁሉም ፓርቲዎች ጉልበተኞች ናቸው። የገዥ/ተገዥው ሳያንስ “የተሻልን ነን” የሚሉት ሁሉ ከዛው መስመር የወጡ ስለመሆናቸው አንዳችም መተማመኛ የለም።
አወዳደቃቸውም ያውና ተመሳሳይ ሲሆን፣ እርስ በርሱ ተጠላልፎ እንዘጭ ማለቱ ላይ የሚያክላቸው የለም። ቅንጅት በለው ተመሳሳይ ነው። ሌሎቹ በመቶዎች የሚቆጠሩትም እርስ በርስ ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን በልተው ነው ላይመለሱ የተጓዙት። ፖለቲካችን ሌላም ገጽታ አለው።
ባጠቃላይ፣ እኛ አገር፣ እንደ አንድ ጥንታዊትና ባለ ታሪክ አገር፣ አንድም እንኳን የወግ ጠባቂ (conservatism (”ወግ አጥባቂ”ነት ሳይሆን ”ወግ ጠባቂ”ነት)) እሚሉት አልያም የእውነተኛ ዲሞክራሲ የፖለቲካ ርእዮት አራማጅ ፓርቲ አለመኖሩ ለብዙዎች ትንግርት ሲሆን፣ ሁሉን ነገር ዛሬውኑ ጥርግ አድርጌ ካልለወጥኩ የሚለው ስር ነቀላዊነት (Radicalism)፤ ከእሱ የባሰው አውዳሚነት (Nihilism) . . .፤ እንዲሁም ሌሎች ከማቆጥቆጥም ባለፈ እየተንሰራፉ መሆናቸው ለብዙዎች ራስ ምታት እንደሆነ ይገኛል። (ግን ግን፣ እንደው ለነገሩ፣ “ሰው በተፈጥሮው ፖለቲካዊ እንስሳ ነው” (ጠቢቡ “Man is by nature a political animal” እንዳለው) ብለናልና፣ በአገራችን ከሚርመሰመሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል “እኔ የምከተለው የፖለቲካ ርእዮት ይሄ ነው” ብሎ፣ ለይቶ የሚያውቅ፣ አውቆም ለተከታዮቹ (ለህዝብ መቼም አይታሰብም) የሚያስረዳ ፓርቲ አለ? “የምንከተለው ርእዮት ምንድን ነው?” ብሎ የሚጠይቅስ የፓርቲ አባል አለ? ወይስ፣ እንደው ምናልባት “መላ ካለው” በሚል፤ ወይም “ሰው በተፈጥሮው ፖለቲካዊ እንስሳ” ስለሆነ የተደራጀ ፓርቲና የታቀፉ አባላት ናቸው ያሉን? ያለ ርእዮተ ዓለም ትጥቅ ለውጥ አመጣለሁ ብሎ መፎከርንስ የፖለቲካ “ሀሁ”ም ሆነ አምላክ ይፈቅደዋልን?)
ቸር እንሰንብት።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም