የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ፣ ብሔራዊ እንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት፣ ዕዳና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ተጠሪ የሆኑ የልማት ድርጅቶች ናቸው።
ይህ ተቋም እነዚህን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በመምራት ኦዲት ሪፖርቶች ማፅደቅ፣ በኦዲት ግኝቶች ላይ የእርምት እርምጃ መወሰዱን መከታተል፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች አፈጻጸም እና ተወዳዳሪነት እንዲሻሻል ማድረግ ዘመናዊ የኮርፖሬት አስተዳደርና የኮርፖሬት ፋይናንስ ሥርዓትን መዘርጋት፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አስፈላጊ ችሎታ፣ ልምድ እና ዕውቀት ባላቸው ሰዎች የሚመሩበትን ሥርዓት መዘርጋት፣ ተግባራዊነታቸውን ማረጋገጥ፣ አዳዲስ የኢንቨስትመንት መስኮችን እና የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን በማጥናት እንዲፈቀድ ለመንግሥት የውሳኔ ሀሳብ ማቅረብ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እንዲፈርሱ፣ እንዲዋሃዱ ወይም እንዲከፋፈሉ ለመንግሥት የውሳኔ ሀሳብ ማቅረብ፣ ሲፈቀድም ተግባራዊ ማድረግ፣ የትርፍ ድርሻ ክፍፍል ፖሊሲ ማዘጋጀት ከሚተገብራቸው ተግባራቶቹ ውስጥ ናቸው።
በተጨማሪም በየበጀት ዓመቱ ከልማት ድርጅቶች ለመንግሥት ስለሚከፈል የትርፍ ድርሻ ክፍያ ለገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የውሳኔ ሀሳብ ማቅረብ፣ ተግባራዊነቱን መከታተል፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሂሳብ ከመዝገብ መሰረዝን በሚመለከት ለገንዘብ ሚኒስቴር ምክረ ሀሳብ ማቅረብ፣ አፈጻጸሙን መከታተል፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን አፈጻጸም እና ሁኔታ የሚያሳይ የመረጃ ሥርዓት ማደራጀት፣ የፋይናንስ አጠቃቀማቸው፣ የብድር አወሳሰድና አመላለሳቸውን በቅርበት በመከታተል የተጠቃለለ የሂሳብ ሪፖርት ለገንዘብ ሚኒስቴር ማቅረብ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለምርምር እና ለፈጠራ በቂ በጀት እንዲመድቡ ያደርጋል። የተገኘውን የምርምና እና የፈጠራ ውጤት እንዲያሰራጩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ እና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሚመለከቱ መረጃዎች ማዕከላዊ አስቀማጭ ሆኖ ማገልገል፣ የልማት ድርጅቶች አፈጻጸም የሚመለከቱ የውል መረጃዎችን ማሳወቅ ከተግባራቶቹ ጥቂቶቹ ናቸው።
እነዚህን የልማት ድርጅቶችን በመምራት በርካታ ተግባራትን ያከናውል። ለአብነትም የመንግስት የልማት ድርጅቶች አፈጻጸም እና ተወዳዳሪነት እንዲሻሻል ማድረግ ዘመናዊ የኮርፖሬት አስተዳደርና የኮርፖሬት ፋይናንስ ሥርዓትን መዘርጋት፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አስፈላጊ ችሎታ፣ ልምድ እና ዕውቀት ባላቸው ሰዎች የሚመሩበትን ሥርዓት መዘርጋት፣ ተግባራዊነታቸውን ማረጋገጥ፣ አዳዲስ የኢንቨስትመንት መስኮችን እና የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን በማጥናት እንዲፈቀድ ለመንግሥት የውሳኔ ሀሳብ ማቅረብን ያካትታል።
በተጨማሪም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እንዲፈርሱ፣ እንዲዋሃዱ ወይም እንዲከፋፈሉ ለመንግሥት የውሳኔ ሀሳብ ማቅረብ ሲፈቀድም ተግባራዊ ማድረግ እና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ስትራቴጂያዊና ዓመታዊ ዕቅድ መያዛቸውን ማረጋገጥ፣ ዕቅዶቹን ማፅደቅ፣ አፈጻጸማቸውን መቆጣጠር፣ መከታተል፣ መገምገም፣ የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ኦዲት ሪፖርቶች ማፅደቅ እና በኦዲት ግኝቶች ላይ የእርምት እርምጃ መወሰዱን መከታተል ከሚያከናውናቸው ተግባራትም ጥቂቶቹ ናቸው። የዝግጅት ክፍላችን የተቋሙን የሥራ እንቅስቃሴን በተመለከተ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሐብታሙ ኃይለሚካኤል ጋር ቆይታ አድርጓል።
አዲስ ዘመን፡- የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ታሪካቸው ምን ይመስላል?
አቶ ሐብታሙ፡– የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከ100 ዓመት በላይ አስቆጥረዋል። በአራት ምዕራፎችም የተቋቋሙ ወይንም ገጽታ ያላቸው ናቸው። በንጉስ አጼ ኃይለ ስላሴ ዘመን፣ በደርግ ዘመን፣ በኢህዴግ እና ከለውጡ ወዲህ የተመሰረቱ ናቸው። በኃይለስላሴ ጊዜ የነበሩት በቁጥር በጣም ጥቂት ሲሆኑ፤ የነፃ ገበያን ማቆጥቆጥ ተከትሎ የመጡ ናቸው። ነፃ ኢኮኖሚ እያበበ የነበረበት ወቅት ሲሆን መንግስት ብዙ ሚና ነበረው። በደርግ ዘመን ደግሞ አቆጥቁጠው የነበሩትን የግል ባለሃብቶችን ሃብት በመውረስና ሶሻሊዝምን እንደ ፍልስፍና በመቁጠር ብዙውን ሃብት ጠቅልሎ የያዘ ሲሆን መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ትልቅ ሚና ነበረው። ብዙ ኮርፖሬሽኖችም የተፈጠሩበትም ነበር።
ሌላኛው ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ የነበረው ሲሆን የመንግስትን ድርሻ ለመቀነስና አብዛኛዎቹ በመንግስት እጅ ወደ ግል የተዘዋወሩበትና የመጀመሪያው የፕራይቬታይዜሽን ሂደት የጀመረበት ነው። ኮርፖሬሽኖችና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እንደገና የተዋቀሩበት ወቅት ነው። በዚህ ወቅት 320 የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ፕራይቬታይዝ ተደርገዋል። በዘመነ ኢህአዴግ የኢትዮጵያን አየር መንገድ ከመሳሰሉት በስተቀር በርካቶች ትርፋማ አልነበሩም።
አራተኛው ምዕራፍ ከአራት ዓመት በፊት በተጀመረው የሪፎርም ሥራ ሲሆን፤ በዚህ ወቅትም በርካቶች በኪሳራ ውስጥ ነበሩ። ሆኖም አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም በመተግበሩ ተቋሙም በአዲስ መንገድ የተቋቋመበት ነው። በዚህም ድርጅቶች ተወዳዳሪና ትርፋማ እንዲሆኑ የተጀመረበት ሂደት ነው። የድርጅቶቹ የማኔጅመንትና የፋይናንስ ሥርዓቱም በአግባቡ መሰራት የጀመረበት ወቅት ነው። በተለያዩ ወቅቶችም የተለያዩ አደረጃጀቶችን ያለፈ ተቋም ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከሪፎርሙ ወዲህ የአገርን ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ የተከናወኑ አንኳር ሥራዎች ምንድን ናቸው?
አቶ ሐብታሙ፡- አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ከተተገበረ ጀምሮ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል። የመጀመሪያው በሦስት ዘርፎች ላይ የትኩረት ነጥቦች ለይተን የልማት ድርጅቶችን ስንደግፍ ነበር። የመጀመሪያው ‹‹ፕሮትፎሊዮ›› ማኔጅመንት ነው። ይህ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው የልማት ድርጅቶችን ሥምሪትና ውጤታማነት ማረጋገጥ ነው። ሌላው የድርጅቶቹን አስተዳደር ማስተካከል ሲሆን ሦስተኛው የተቋሙን አቅም ማጠናከር ነው።
‹‹ፕሮትፎሊዮ›› ማኔጅመንት አኳያ ከለውጡ በፊት በርካታ የልማት ድርጅቶች ከሳሪና አክሳሪ የነበሩ ናቸው። አንዳንዶቹ አገርን ችግር ውስጥ የከተቱም ነበሩ። እነዚህን ወደትርፋማናት የመመለስ ሥራ ነበር። ለዚህም አስዳደሩን ማስተካከል ይገባ ነበር። ለዚህም የኮርፖሬት አስተዳደር በሁሉም የልማት ድርጅት መተግበር ነበረብን። ቦርዶችም ሲዋቀሩ በዚህ ደረጃ የተቃኙ ነበሩ። የልማት ድርጅቶችም የበለጠ ውጤታማ የማድረግና መንግስት የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆንበትን አካሄድ መከተል ችለናል። የግል ባለሃብቱ የሚሰማራበትን ኢኮኖሚ ክፍል ማድረግ ተችሏል። የኢትዮ-ቴሌኮምን በአብነት ማንሳት ይቻላል። ገበያውን ነፃ ተደርጓል። የአቅም ግንባታን በተመለከተ 16 የኢኒሼቲቭ እርምጃዎች ተቀርፀው ተተግብረዋል። ዓለም አቀፍና ተወዳዳሪ በሆኑ ተቋማት አቅም ግንባታ ስራዎች ተሰርተዋል፤ በአሁኑ ወቅትም እንደቀጠለ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከሪፎርሙ በፊት ትርፋ ያልሆኑና አሁን ወደ ትርፍ ህዳግ የመጡት እነማን ነበሩ፤ እንዴትስ ትርፋማ ሆኑ?
አቶ ሐብታሙ፡- የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ወደ ሪፎርም ከመግባቱ በፊት በስሩ 36 ድርጅቶች ነበሩ፤ አሁን ያሉት ዘጠኝ ናቸው። በዘጠኙ ላይ አትኩሬ ለመናገር ያክል በከፍተኛ ችግር ውስጥ ከነበሩት አንዱ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ነበር። በነበረው ከፍተኛ የሆነ አመራር፤ አደረጃጀትና አሰራር ችግር የተነሳ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነበር። ባንኩ በዚህም መክሰርና የተበላሸ ብድር ያለው ባንክ ብቻ ሳይሆን ሊዘጋ የተቃረበ ነበር።
ይህ ባንክ በ1900 ዓ.ም ሲቋቋም ጀምሮ የመንግስትን ፖሊሲ ለማስፈጸም የተቋቋመ ሲሆን በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል። ነገር ግን ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ የግለሰቦች ዓላማ ማስፈፀሚያ በመሆኑ ብዙ ቢሊዮን ሃብት ባክኗል፤ ከስሯል። በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠርና ወደኪሳራ የገቡ ፕሮጀክቶችን እንዲሸከም የተደረገበት የአመራርና የአሰራር ክፍተት የነበረበት ነው። ይህን ባንክ ለመታደግ መጀመሪያ የተደረገው የአመራር ለውጥ ማድረግ ነበር። ቀጥሎ አመራሩ፣ አሰራር እና አደረጃጀት ለውጥ በማድረጉ ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ወደ ትክክለኛ መንገድ ተመልሷል። የኪሳራ እና የተበላሸ ታሪክ ቀርቶ ትርፋማ የሆነ ባንክ ነው።
ሌላው የኢትዮ-ኢንጅነሪንግ ግሩፕ በቀድሞ ስሙ ሜቴክ ነው። ይህ ተቋም ለራሱ መጥፋት ብቻ ሳይሆን አገርን ይዞ ሊጠፋ የነበረ ተቋም ነው። ትልልቅና በቢሊዮን የሚቆጠር ፕሮጀክቶችን እንዲያስተዳድር ተደርጎ የነበረ ነው። አቅምና ብቃት ሳይኖር የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓት ሳይዘረጋ ቢሊዮኖች የፈሰሱበትን ፕሮጀክት ለማስተዳደር ሲንቀሳቀስ ነበር። የዚህ ደግሞ በጣም የከፋ ነበር። የውስጥ ቁጥጥር፤ የማኔጅመንት፣ ሃብት አስተዳደር የሌለው ሃብትና ሥራው በግልጽ የማይታወቅ እና ሌሎች ችግሮች ነበሩበት። የአመራር፣ አሰራርና አደረጃጀት ችግሮቹ ከፍተኛ ነበር።
ኢንዱስትሪውን የሚመጥን የሰው ኃይል ሳይሆን የግለሰቦችን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ ነበር። ይህ መክሰር ብቻ ሳይሆን ግዙፍ ተቋም የሚመስል ግን የህዝብን ሃብት ይዞ እየሰጠመ የነበረ ተቋም ነው። እነዚህን ችግሮች በማስተካከል በዚህ ዓመት ወደ አትራፊነት መጥቷል።
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት 128 ዓመት ያስቆጠረና ኢትዮጵያን በመላ ዓለም ያስተዋወቀ ተቋም የነበረ ሲሆን
መክሰር ያልነበረበት ግን በኪሣራ ውስጥ የቆየ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ወደትርፋማነት መጥቷል። ሌሎችም በዚህ መልኩ ውጤታማ እየሆኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ልማት ባንክ ኪሳራ ውስጥ የነበረ ተቋም ነው። የተበላሸ ብድርና በቢሊዮን የሚቆጠር ኪሣራ ኃላፊነትን ማን ወሰደ?
አቶ ሐብታሙ፡– የልማት ባንክ የተበላሸ ብድር ስንል በተለያየ መንገድ ይገለፃል። ለምሳሌ አንዳንድ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች የውጭ ባለሃብቶች ይዘዋቸው የነበሩና ትልልቅ የሆኑና የባንኩን 50 እስከ 60 ከመቶ ሃብት የሚይዙት ሲሆኑ ባንኩ ወደ ትርፋማነት የመጣው እነዚህን ማስተዳደር በመቻሉ ነው። ጥለው ከአገር የወጡና የከሰሩም አሉ። እነዚህን ተረክቦ ወደ ጤናማነት መመለስ ችሏል።
ከዚህ ውጭ ግን በአሰራር የተበላሹ ብሎ መንግስት በዋስትና የያዛቸውንና እያስከበረ ያለበት ሁኔታ አለ። ለምሳሌ በጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ክልል በእርሻ ሥም ብድር የተወሰዱበትን መንግስት ይዟቸው ለሌሎች ለማስተላለፍ እየሠራ ነው። መንግስት ለመጠባበቂያ ብሎ የያዘውን በመጠቀም ወደ ትርፍም እየመጡ ነው። ከዚህ ውጭ ደግሞ ወደ ህግ የሄዱም አሉ። እርሻዎቹ አሁንም በባንኩ እጅ ናቸው፤ ወደ ሌሎች ባለሃብቶች የማስተላለፍ ሂደት ላይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ትርፋማ የሆኑ ተቋማት የስኬታቸው ሚስጥር ምን ነበር?
አቶ ሐብታሙ፡- በእኛ ሥር ያሉት ውስብስብ ችግር የነበረባቸው ዕዳ እና ውዝፍ ስራ የነበረባቸው ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ ስትራቴጂካሊ የፖሊሲ ስራዎች ናቸው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርፋማ ይሆናሉ ብለን የማንጠብቃቸው ግን የፋይናንስ ጤናማነታቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ የምናደርጋቸው ናቸው። ልማት ባንክ ትርፋማነቱን ጠብቆ ይሄዳል። የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ትርፋማ እየሆኑ ይመጣሉ።
ኢትዮ ኢንጅነሪንግ በተመሳሳይ መንገድ ትርፋማ ይሆናል። ግን የዚህ ትልቁ ችግር በስሩ ያሉ ዘጠኝ ኢንዱስትሪዎች የሚጠቀሙት ውጭ ግብዓት ነው። አሁን የዕዳና ካፒታል ማሻሻያ እየተደረገለት ነው። ትርፋማ የሆኑት የተሻለ ልምድ እንዲቀስሙም እየተደረገ ነው። ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮጵያ አየር መንገድ ልምድ እየወሰዱ ነው። ዓለም አቀፍ ተቋማትንም በመቅጠርም ስልጠና እየሰጠን ነው። ከጀርመን ፍራንክፈርት ማኔጅመንት ትምህርት ቤት ጋር በመነጋገር ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ኢንተርፕራይዞች ላሏቸው ክልል ለአንድ ዓመት የሚዘልቅ በ21 ርዕሶች ላይ ስልጠና እየሰጠን ነው። እስካሁን 10 ስልጠና ሰጥተናል። ይህ የልማት ድርጅቶችን ትርፋማ የሚያደርግና ችግሮቻቸውን በራሳቸው እንዲፈቱ ያስችላቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- የመንግስት የልማት ድርጅቶች አንዱ ችግር የነበረው የውስጥ ኦዲት ደካማ መሆኑን የህዝብ እንደራሴዎች በተደጋጋሚ ሲያነሱት ነበር። ይህ አሁን ተሻሽሏል?
አቶ ሐብታሙ፡- አንድ ተቋም ትክክለኛ የፋይናንስ ተቋም ነው የሚባለው የፋይናንስ ሁኔታው ሲታወቅ ነው። ስለዚህ የእኛ ትልቁ ስራ የነበረው የኮርፖሬት ፋይናንስና አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት ነው። የልማት ድርጅቶች ወቅታዊ ሂሳብ እንዲኖራቸው ነው በዚህም በጣም ሰርተናል። የኦዲት ባክሎክ እንዲዘጋ ተደርጓል። ኢትዮ ኢንጅነሪንግን ጨምሮ ይህ ተሰርቷል። ኢትዮ ኢንጅነሪንግ እስከ 2012 ዓ.ም ሂሳቡን እየዘጋ እያፀዳ ነው። የኋላ የሂሳብ ታሪኩን እየዘጋ 2013 እና 2014 ዓ.ም ይቀራቸዋል። ግን ቀድሞ የነበረውን እየዘጉ አሁን እየተሻሻሉ ነው። ሂሳብ መያዝና ሰነድ መመዝገብ ከማይቻልበት ታሪክ ወጥተዋል። ከኋላ ታሪኩ የተነሳ የኦዲት ሁኔታው ችግር ያለበት ቢሆንም ችግሮችን ለማስተካከል እየሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ከሰርቨሩ ላይ የነበረው ዳታ ሙሉ ለሙሉ እንዲጠፋ ተደርጓል። ይህ ሆን ተብሎ መረጃው እንዲጠፋ የተደረገበት ነው። በዚህም ከ3 እስከ 4 ሚሊዮን የሚጠጋ ሰነድ በእጅ አንድ በአንድ ሰብስቦ በመመዝገብ ሂሳባቸውን ወቅታዊ ለማድረግ እየሰሩ ነው። አንዳንዶቹ ደግሞ ሂሳባቸውን በወቅቱ መዝጋት ብቻ ሳይሆን በዘመናዊ አሰራር እያዘመኑት ነው። ብሔራዊ እንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። ከግድፈትም ነፃ የሆነ ኦዲት ናቸው። የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት እና ዕዳና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽንና ሌሎች ድርጅቶችም ዘመናዊ አሰራር ውስጥ እየገቡ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ፕራይቬታይዝ የሚደረጉት ምን ዓይነት ድርጅቶች ናቸው?
አቶ ሐብታሙ፡– ቀደም ብሎ ሲሠራ በነበረው ሁኔታ 320 ድርጅቶች ፕራይቬታይዝ ተደርገዋል። አሁን ባለው አሰራር የመጀመሪያው የመንግስትን የትኩረት መስክ ዒላማ አድርገው ነው። መንግስት ገበያ ውስጥ ድርሻ ቢኖረው ጠቃሚ ይሆናል ወይ የሚለው ይታያል። አሁንም የፖሊሲ ተቋማት የምንላቸው አሉ። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ እና የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በዚህ ውስጥ የሚታዩ ናቸው።
በእርግጥ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ፕራይቬታይዝ መሆን ይችላል፤ ግን ካለው ማበረታቻ አንፃር ደፍሮ የማይገባበት ነው። ከዚህ ውጭ መንግስት በክፍለ ኢኮኖሚው ውስጥ መቆየት አስላጊ ካልሆነ እንዲለቀቅ ይደረጋል። ዋናው የገበያ ፍላጎት ሳይሆን የሴክተሩ ጉዳይ ይታያል። ማትረፍና መክሰር ብቻ የሚታይ አይደለም። ለምሳሌ ኢትዮ ቴሌኮም በጣም አትራፊ ነው። ግን መንግስት ለነፃ ገበያ ያለው አመለካከትና ፍላጎት ያለውን ምልከታ ያሳያል። በተጨማሪም ለመንግስት የገንዘብ አቅምንም ያሳድጋል። ስለዚህ መንግስት ፕራይቬታይዝ የሚያደርገው ብዙውን ጊዜ መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ሚና እንዲቀንስና ነፃ ገበያ እንዲኖር ከመሻት ነው። ከዚህ ቀደም እርሻዎች፤ ኢንዱስትሪዎች እና ሆቴሎች ለግል ባለሃብቶች ተላልፈዋል።
አሁን ፕራይቬታይዝ ልናደርጋቸው የምናስባቸውና በመንግስት የአክሲዮን ድርሻ ተይዘው ያሉ ተቋማት አሉ። እነርሱን ባለሃብቶች እንዲገቡበት ይፈለጋል። ለምሳሌ በመንግስት እና በግል አጋርነት ያሉ እንደ ቢ.ኤም ጨርቃጨርቅ፣ አፍሪካ ጁስ፣ አብያታ ሶዳ አሽ እና አምቼ ናቸው። ሌሎች ደግሞ የመንግስትን ፍላጎት አድርገን እንሄዳለን። በእኛ ተጀምረው የነበሩ የስኳር ፋብሪካዎችም ኢትዮ-ቴሌኮም ወደ ሌላ ተቋም ሄደዋል።
አዲስ ዘመን፡- ድርጅቶች ፕራይቬታይዝ ሲደረጉ የክልል መንግስታት እና የፌደራል መንግስት አልፎ አልፎ ይገባኛል የሚሉ ጥያቆችም ይነሱበታል ይባላል። ሚናቸው የተለየ ነው?
አቶ ሐብታሙ፡- የመንግስት የልማት ድርጅቶች የህዝብ ናቸው። የእኛም መሪ ሐሳብ ‹‹የህዝብን ሐብት ለህዝብ›› የሚል ነው። እነዚህ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ከክልል ጋር የሚያገናኛቸው የለም። የሚቋቋሙት በአዋጅ 2584 ነው። የህዝብና የመንግስት ስለሆኑ መንግስትን ወክለን የምናስተዳድረው እኛ ነን። ግን እነዚህ ድርጅቶች በአካል በሆነ ቦታ ወይንም ክልል ይገኛሉ። ስለዚህ እንደማንኛው ዜጋ መጠቀም ይችላሉ። ግን እነዚህን ድርጅቶች የማስተዳደር ፍላጎት ቢኖሯቸው እንኳን አሰራሮች አሉ። ለምሳሌ ክልላዊ የልማት ድርጅቶች አሉ። ግን የበለጠ ትርፋማ እና ተወዳዳሪ የሚሆኑ ከሆነ መንግስት ለክልል ሊያስተላልፍ ይችላል።
ለአብነትም ባህርዳር እና ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅን ለአማራ ክልል በሽያጭ አስተላልፈናል። አርሲ እና ባሌ እርሻ ለኦሮሚያ ክልል ተላልፏል። አሰላ ብቅል ፋብሪካ ለዩኒዮኖች ተላልፏል። በየክልሎቹ የተላለፉ አሉ። ስለዚህ የልማት ድርጅቶችን አንዱ ክልል ላስተዳድር የሚልበት ነገር የለም። ግን ለአሰራር አመቺ ከሆነ መንግስት የሚጠቅመውን ያደርጋል። ስለዚህ እስካሁን እኔ ላስተዳድር ብሎ ገፍቶ የመጣ ክልል የለም። ሆኖም አልፎ አልፎ የወሰን መግፋት ይኖራል። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት በመላ አገሪቱ 80 ቅርንጫፎች አሉት። በየቦታው በጣም ትልልቅ ቦታ አለው። ይህን ለሌሎች የማስተላለፍና የመግፋት ሁኔታ አለ። ይህን በመነጋገር የማስተካከል ሁኔታዎች አሉ። በአጠቃላይ ግን የወሰን፣ ይዞታ ማስከበር ላይ ግን ችግር አልፎ አልፎ አለ።
አዲስ ዘመን፡- ድርጅቶች ፕራይቬታይዝ ሲደረጉ ከአገር ውስጥ ባለሃብቶች ይልቅ ወደ ውጭ ባለሃብቶች የማድላት ዝንባሌዎች አሉ የሚል ወቀሳም አለ። እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ሐብታሙ፡– ይህንን በመረጃ ማስደገፍ አስፈላጊ ነው። እስካሁን ከ300 በላይ ድርጅቶች ተላልፈዋል። ከግብርና 27 ድርጅቶች፣ ከኢንዱስትሪ 161፣ ቅርንጫፎችን ጨምሮ ከአገልግሎት 180 ድርጅቶች ተላልፈዋል። ከእነዚህ ለባለሃብቶች ወደ 200፣ ለሰራተኞች 45 ድርጅቶች ተላልፈዋል። ሌሎች ደግሞ በመንግስትና ባለሃብቶች የጋራ ልማት ናቸው። እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ ባለው መረጃ መሰረት ከእነዚህ ውስጥ ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች የተላለፈው 87 ከመቶ ነው። 13 ከመቶ የሚሆነው የተላለፈው ለውጭ ባለሃብቶች ነው። በእርግጥ ከእነዚህ ውስጥ ትንባሆ ሞኖፖልን ወስደን ብናይ በጣም ብዙ ብር ነው የያዘው። በዋጋ ብናየው ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች 315 ድርጅቶችን በአስር ቢሊዮን ብር ለአገር ውስጥ ድርጅቶች ተላልፈዋል። ለውጭ የተላለፈው 39 ቢሊዮን ብር ደግሞ የተላለፈው 13 ከመቶ የሚሆነው ነው። ስለዚህ መንግስት ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች ትልቅ ድጋፍ ያደርጋል።
የውጭ ባለሃብቶች ሲመጡ ግን የውጭ ምንዛሪ፣ የዕውቀት ሽግግር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ከግምት ውስጥ ይገባል። ከዚህ ውጭ ግን ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ባለሃብቶች የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር በተከታታይ ለአምስት ዓመታት ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል። በቢዝነስ ፕላናቸው መሠረት መሄዳቸውን ይከታተላል፤ በዚህም አብዛኞቹ ውጤታማ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- የታዳጊ አገራት ድርጅቶች ‹‹ፕራይቬታይዝ›› ሲደረጉ በምዕራባውያን በመጠቅለል በአገራት ሉዓላዊነትና ነጻነት ይጋፋል የሚል የምሁራን ትችት አለ። በዚህ ረገድ ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ሐብታሙ፡- ኢትዮጵያ በዚህ አትታማም። ከለውጡ ወዲህም የተሄደበት መንድ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢኮኖሚ ስብራትን ማስተካከል ነው። ለዚህ ደግሞ እነዚህ ሴክተሮች ወሳኝ ናቸው። ባደጉትም አገራት ጭምር ይህ ሴክተር ትልቅ ግምትና ዋጋ አለው። መንግስት ይህን በጥንቃቄ ነው የሚሰራው። ከውጭ ያለው ጫና እያንዳንዱ ሴክተር ክፍት ይደረግ የሚል ነው። ነገር ግን አገራችን ሁሌም ጥንካሬዋን የምታሳይበትና የጽናቷ ሚስጥር የለውጥ እሳቤዎች ይህን አጠንክረው የሚሄዱ ናቸው። የህዝብና አገር ጥቅም የሚያስከብር ስራ ብቻ ነው የሚሰራው። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጠንካራ አቋም ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ባለሃብቶች ኢኮኖሚውን በሞኖፖል የሚይዙበት ዕድል የለም። የሚቀረጹ ህጎች፣ ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎችና አፈጻጸም ሂደቶችም ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ነው። ውድድርን በማያቀጭጭ መልኩ ነው የምንሰራው። የአፍሪካ አገራት ያለፉበትን መንግስት እናውቃለን። እኛ ይህን በማወቃችን ጥንቃቄ የተወሰደበት ነው፤ በቀጣይም ክፍት ለሚደረጉት መንግስት በልዩ ትኩረትና ጥናት ነው የሚያካሂደው። ለኢኮኖሚ ወሳኝ የሆኑ ተቋማት አሁንም ክፍት አልተደረጉም። የፕራይቬታዜሽን ህጋችንም ጠንካራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ምዕራባውያን በመንግሥት ላይ ጫና እያደረጉ አይደለምን?
አቶ ሐብታሙ፡- የምናየው ነገር ነው። የፋይናንስ ተቋማትን ክፍት አድርጉ የሚል ከፍተኛ ግፊት አለ። መንግስት ጥናት እያደረገ ነው። ጥናት ላይ ተመስርቶ የሚወሰን ነው። ዘግተን የማናቆያቸው ሴክተሮች አሉ። ነገር ግን በመንግስት በቂ ዝግጅት እና ጥናት ከተደረገ በኋላ የሚወሰን ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እያመሰገንኩ ተጨማሪ ሐሳብ ካለ ዕድሉን ይጠቀሙ።
አቶ ሐብታሙ፡– አመሰግናለሁ። የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ስምሪት ውጤታማ ለማድረግ አቅደን እየሰራን ነው። የሁሉም ድርጅቶች ሪፎርም በታሰበው ልክ እንዲሄድ የተጀመረው ጥረት በጣም ጥሩ የሚባል ነው። የመንግስት የልማት ድርጅቶች የሂሳብ አያያዛቸውና ግልፀኝነት እንዲኖረውና ጠንካራ እንዲሆን እየሰራን ነው። ማኔጅመንቱንም አጠናክረን እንቀጥላለን። በየጊዜው እየዘመነ ይሄዳል። የሃብት ጥራታቸውም በፈጠራ የታገዙ እንዲሆኑ ይደረጋል። በአሁኑ ወቅት ዘጠኙ ድርጅቶች ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ሃብት እያንቀሳቀሱ ነው።
በቀጣይ ለአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ ትልቅ አበርክቶ እንዲኖራቸው በትኩረት የሚሠራ ይሆናል። በኪሳራ ውስጥ የነበሩ ድርጅቶችም ወደ ትርፋማነት እየመጡ ነው። ይህም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖረው ሚና እየቀነሰ ይሄድ ይሆናል እንጂ ወሳኝ በሚባሉት ላይ እጁን ማስገባቱ አይቀርም። ቻይና እና ፈረንሳይም በዚህ ደረጃ ነው ያሉት። የአገር ኢኮኖሚ ችግር ሲገጥመው፤ ለመፍትሄው የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚና በጣም ትልቅ ነው። በመሆኑም የእኛ የልማት ድርጅቶችም ኢኮኖሚውን በመደገፍ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው። ስለዚህ በቀጣይም ይህ ሥራ በተጠናከረ መንገድ የሚከናወን ይሆናል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም