
የሕግ መዝገበ ቃላት ሰበርን አንድ ሕጋዊ ሥልጣን ያለው አካል የሰጠውን የፍርድ ወይም የውሳኔ አስገዳጅነት ወይም ቅቡልነት መስበር፣ ዋጋ ማሳጣት (መሰረዝ)፣ ወይም መመለስ ነው ሲሉ ይበይኑታል:: የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት ሰበርን በሚመለከት በአንቀጽ 80 (3) ሀ እና ለ ላይ ደንግጓል:: በዚህ ድንጋጌ መሰረት የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስሕተት ያለበትን ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም በሰበር ችሎት የማየት ሥልጣን እንደሚኖረውና ዝርዝሩም በሕግ እንደሚወሰን ተጠቅሷል:: እንዲሁም የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች “መሰረታዊ” የሆነ የሕግ ስሕተት ያለበትን የክልል ጉዳዮች የተሰጠውን የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም በሰበር ችሎት የማየት ሥልጣን እንደሚኖረውና ዝርዝሩም በሕግ እንደሚወሰን ያስቀምጣል::
ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የሰበር ጉዳዮችን የሚመለከቱት በመደበኛ ችሎት ሳይሆን በሰበር ችሎት እንደሆነ፣ ጉዳዮች በሰበር ችሎት ለመታየት የመጨረሻ ውሳኔ ሊሰጥባቸው የሚገባ መሆኑ እንዲሁም የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ሲሆን ብቻ መታየት እንዳለባቸው በግልጽ ተቀምጧል::
ይህንን የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ ለማስፈፀም ከወጡ ዝርዝር ሕጎች መካከል በፌዴራል ደረጃ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1234/13 በአንቀጽ 10 ላይ እንደተመለከተው “የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሰረታዊ የሕግ ስሕተት የተፈጸመባቸውን የመጨረሻ ውሳኔዎች በሰበር ለማየት ሥልጣን ያለው መሆኑን ያመለክታል:: በዚህ አዋጅ መሰረትም የመጨረሻ ውሳኔዎች የሚባሉት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸው ጉዳዮች፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መደበኛ ችሎት የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸው ጉዳዮች እና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መደበኛ ችሎት በይግባኝ ወይም በሰበር አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸው ጉዳዮች ናቸው::
ሌላው የሕግ ማሕቀፍ በ1997 ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 454/1997) ሲሆን በዚህ አዋጅ አንቀጽ 4 መሰረት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከ አምስት ባላነሱ ዳኞች በሰበር አይቶ የሚሰጠው የሕግ ትርጉም በየትኛውም ደረጃ በሚገኙ የክልል ወይም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅነት እንደሚኖረው ይደነግጋል::
ከላይ በተጠቀሱት አስረጂዎች መሰረት ሰበር ማለት መሰረታዊ የሕግ ስሕተት ያለበት የፍርድ ውሳኔ የሚታረምበትና የሚስተካከልበት ብሎም አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የሚሰጥበት ሂደት ነው::
በሰበር ችሎት የተሰጠው ውሳኔ በሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ በክልልም ይሁን በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅነት የሚኖራቸው ይሆናል:: ይህም ማለት የተሰጡት ውሳኔዎች በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ እንደ ሕግ ያገለግላሉ ማለት ነው:: ጉዳዩ በሰበር ፍርድ ቤት ቀርቦ ከመታየቱ በፊት በጠቅላይ ፍርድ ቤት መደበኛ ችሎት ቀርቦ ያስቀርባል አያስቀርብም የሚል ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል እንዲሁም ይህ የሰበር ውሳኔ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ የፍርድ ሂደት ወይም የፍርድ ውሳኔ ይሆናል::
ለመሆኑ በሰበር ችሎት የሚታዩ ጉዳዮችስ እንዴት ያሉ ናቸው ? ፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር በሚከተል ሀገር ውስጥ በፌዴራል ሰበር ችሎት እና በክልል ፍርድ ቤቶች መካከል የሚኖረው ግንኙነት ምን መልክ አለው ?
“በፌዴራል ሥርዓት ውስጥ የሰበር ችሎት ሚና እና አተገባበር” በሚል ርዕስ ባዘጋጁት ጥናታዊ ጽሑፍ የሰሩት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ቀነዓ ቂጣታ እደሚናገሩት፤ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ 25/1988 ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የፌዴራል ሰበር ችሎት በሕገመንግሥት የተጣለበትን ኃላፊነት እየተወጣ ይገኛል:: ሰበር በሕገመንግሥቱ ላይ በተቀመጠው አግባብ መሰረታዊ የሕግ ክፍተት የተፈጸመበትን የመጨረሻ ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮችን አይቶ የማረም ሥልጣን አለው:: ዋነኛ ዓላማውም እንደ ሀገር ወጥና ተገማች የሆነ የተረጋጋ የሕግ አተረጓጎም እንዲኖር ማድረግ ነው:: የሀገራችን ሰበር ችሎት በፌዴራል ሥርዓት ውስጥ የሚሠራ በመሆኑ በየጊዜው ምን አይነት ጉዳዮችን ማየት አለበት እና ሥልጣኑ እስከ ምን ድረስ ነው የሚሉ ጥያቄዎች ይነሱበታል::
የፌዴራል ሥርዓቱ በሕግ ከተመለከተው ለክልል ከተሰጠው ሥልጣን ጋር በተያያዘ የሥልጣን ወሰኑ እስከምን ድረስ ነው የሚለው ጉዳይ ምሁራንን እንደሚያከራክር ጠቁመው፣ ሰበር የክልል ጉዳዮችን ማየት የለበትም የሚሉ ክርክሮችም ይደረጋሉ:: አዋጅ 25/1988 ይሄንን ችግር የፈታ አልነበረም:: ሰበር ግን በተግባር በተለምዶ ሥራውን ቀጥሏል:: አዋጅ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት የሚለውን በሙሉ ያለልዩነት ሲያይ ነበር ነው የሚሉት::
አዋጅ 34/2012 ከክልል ለሚመጡ ጉዳዮች የፌዴራል ሥርዓቱን ታሳቢ ያደረገ መስፈርቶች ማስቀመጡን የሚጠቅሱት ዳኛ ቀንዓ፤ በክልሎች የታዩ ጉዳዮችን ሰበር አይቶ ማረም የሚገባው በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ መሆኑን አስቀምጧል:: ይሄ ማለት ክልሎች ራሳቸውን የማስተዳደር ስልጣን ስላላቸው ያንን ማክበር እንደሚገባና ሰበር ሁሉንም ጉዳዮች ሰብስቦ ማየት ከጀመረ የማይወጣው ስለሚሆን ሕግ አውጪው ይሄንን በማሰብ የሰበር ዳኞች ሥልጣን መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ጉዳይ ነው የሚባለው ምን ሲሆን ነው የሚለውን አዋጃ 1234 አንቀጽ 2፣4 እና 10 ስር አስቀምጦታል::
በእነዚህ አንቀጾች ስር ስምንት ያህል ጉዳዮችን አስቀምጧል:: ከዚህ ውስጥ ለክልል ጉዳዮች ሦስት መስፈርቶች ተካትተዋል:: ይህ የተደረገው ሰበር በሕገመንግሥቱ ላይ በታሰበው አግባብ ዓላማውን እንዲያሳካ እንዲሁም በዝርዝር ሕግ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ጥሰት የተፈጸመበትን ጉዳይ እንዲያርም እንዲሁም ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ጉዳዮችን አይቶ የፍትህ አስተዳደር ውስጥ ሚናውን እንዲወጣ ለማስቻል ነው ብለዋል::
የክልል ውሳኔዎች በሦስት ማሕቀፎች የሚታዩ ናቸው:: አንደኛ ሕገመንግሥትን የሚቃረን ውሳኔ ሲሆን ነው:: ሁለተኛ የክልል ሕግ አተረጓጎም ሲጣስ እና ጉዳዮቹ የሕዝብ ጥቅምና ሀገራዊ ፋይዳ ካላቸው ብቻ በሰበር ይታያሉ:: ሦስተኛው የክልል ፍርድ ቤት ውሳኔ አስገዳጅ የሰበር ውሳኔን የሚቃረን ከሆነ ነው:: መጀመሪያ መለየት ያለበት አስገዳጅ የሰበር ውሳኔ የትኛው ነው የሚለው ነው:: ያንን የሚቃረን የክል ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ካለ ሰበር ያርመዋል ማለት ነው:: በዚህ መልክ ሰበር የሚፈጽማቸው የሕግ ትርጉሞች ተፈጻሚ እንዲሆኑ የመቆጣጠር ኃላፊነቱን ይወጣል ሲሉም አክለዋል::
እንደ ዳኛው ገለጻ፤ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጣቸው ውሳኔዎች አስገዳጅነት ያላቸው ናቸው:: የሕግ ትርጉም ከሰጠ አስገዳጅነት አላቸው:: ይሄ አስገዳጅነት በክልልም ሆነ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ላይ ተፈጻሚነት አለው:: የትኛውም ፍርድ ቤት ይሄንን አክብሮ አገልግሎት መስጠት አለበት:: ካልሆነ ግን ጉዳዩ አፈጻጸሙን ተከትሎ በተለምዶ ወደ ሰበር ስለሚመጣ ሰበር ራሱ ያርመዋል:: ሰበር ከአዋጅ 554 ወይም ከአወዋጅ 2588 ጀምሮ አሁንም ሥራ ላይ ባለው በ1234/2013 የሚሰጣቸው በርካታ ውሳኔዎች አሉ::
ሰበር በርካታ ሥራዎችን ይሠራል:: ብዙ መፍትሔዎችን ሰጥቷል:: ነገር ግን አሁንም ችግሮች ስላሉና የጉዳዩ ፍሰት ብዙ ስለሆነ የጉዳዮቹ መብዛት ከየት የመጣ ነው በሚል በቅርቡ በተካሄደው የዳኞች ጉባኤ ሰፊ ውይይቶች መካሄዳቸውን የሚያነሱት ዳኛ ቀንዓ፤ በፌዴራል ሥርዓት ውስጥ መሆናችን በፍርድ ቤት ደረጃ የሚገናኝን አንዱ ጉዳይ ሰበር ችሎት ነው:: ሁለተኛው በውክልና ለክልሎች የተሰጠ የፌዴራል የዳኝነት ሥልጣን ነው:: ስለዚህ በሰበር ጉዳይ ለመወያየት ተገቢው መድረክ ይህ የዳኞች ጉባዔ ነው ባይ ናቸው::
የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ክቡር ዳኛ ፊጣ ደቻሳ “የሰበር ችሎት ውሳኔዎች ከክልል ፍርድ ቤቶች እይታ” በሚል ርዕስ ባሰናዱት ጥናዊ ጽሁፍ፤ በሰበር ከሚሰጡ ውሳኔዎች አስገዳጅነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ዳስሰዋል:: በኢትዮጵያ በሁለት ትይዩ ደረጃ የተቋቋሙ ፍርድ ቤቶች (ዱአል ኮር ሲስተም) ቢኖሩም መሰረታዊ የሆነ የሕግ ክፍተት ተፈጽሟል ወይስ አልተፈጸመም ብሎ ሁለቱን የሚያገናኘው የፌዴራል ሰበር ነው:: በፌዴራል ሰበር ሰሚ ዙርያ ብዙ የተጻፈና የተነገረ ቢሆንም አሁንም ችግሮች መኖራቸውን አትተዋል::
የሥልጣን ወሰንን በማመላከት ረገድ በተለይም የመጀመሪያዎቹ አዋጆች ውስንነት እንደነበራቸው የሚጠቅሱት ዳኛው፤ የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች የሥልጣን ክፍፍል መነሻው የቱ ጋ ነው ስንል የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልል ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ወሳኝ አካል ነው ይላል:: የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፌዴራል ጉዳይ ላይ የመጨረሻው ወሳኝ አካል ነው ይላል:: ከዚህ ውጭ የሁለቱ ፍርድ ቤቶች ሥልጣን ምንድን ነው የሚለውን በዝርዝር አያስቀምጥም:: የፌዴራል የዳኝነት ሥልጣን ለክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በውክልና ተሰጥቷል:: የፌዴራል ሰበር ችሎት ስልጣን በአዋጅ 25/1988 ላይ ግልጽነት የለውም:: የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 80 ንዑስ ቁጥር ሦስት በውክልና ለክልሎች የተሰጠ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ስልጣንም በግልጽ አያስቀምጥም ብለዋል::
ፍርድ ቤቶች በፌዴራለ ሥርዓት ውስጥ ሚናቸው ምንድን ነው ? በክልልና በፌዴራል መንግሥታት መካከል ያለው የሥልጣን ክፍፍል ላይ ውሳኔ መስጠት ይችላሉ ? በሁለቱ ፍርድ ቤቶች መካከል ያለው በተዋረድ እና በጎንዮሽ ግንኙነት እና ልዩነትስ ምንድን ነው ? የሚሉት ጉዳዮች በቀጣይም ይበልጥ መብራርት አለባቸው ሲሉም መክረዋል::
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት በበኩላቸው፤ ከሰበር ስልጣን አተገባበር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች አሉ:: ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ለምሳሌ የሰበር ሰበርን ብንወስድ ብዙ ጽሁፎች የተጻፉበትና ክርርክሮች የተካሄዱበት ነው:: በአዋጅ ቁጥ 734/2013 የተወሰነ መፍትሄ ተሰጥቶታል:: አሁንም የሚነሱ ነገሮች ስላሉ ውይቶች መደረጋቸውን ይቀጥላሉ ብለዋል::
በኢትዮጵያ ውስጥ በክልል እና በፌዴራል ደረጃ ትይዩ የዳኝነት አካላት አሉ ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ እነዚህ ሁለት የዳኝነት አካላት በየራሳቸው በሕገመንግሥቱ የተሰጣቸው ሕግ የመተርጎም ሥልጣን አለ:: ነገር ግን ሔደው ሔደው በፌዴራል ጠቅላ ፍርድ ቤት ውስጥ ባለው ሰበር ችሎት ላይ ጉዳያቸው ሊታይ ይችላል:: ይሄ የሚሰጠን ትርጉም አለ:: ለምሳሌ በሕግ አውጪውና በአስፈጻሚው በኩል ስንመለከት ተመሳሳይ ነገር የለም:: ይህ ተርጓሚው ጋር ስንመጣ ግን የሚያገናኛቸው የሰበር መዋቅር አለ ነው የሚሉት::
አያይዘውም፤ ከሁለቱ ፍርድ ቤቶች የተወጣጡ ዳኞች በታደሙበት ዘንድሮ በተካሄደው የዳኞች ጉባኤ ላይ በዚህ የጋራ ጉዳያቸው ላይ እንዲወያዩ ተደርጓል:: የፌዴራል ሥርዓት ስለሆነ የምንከተለው በራሳችን ሄደን ፍትህን ማስፈን አንችልም:: የፍትህ ጉዳይ በድንበር የማይወሰን፤ በሥልጣን ገደብ የማይታጠር እና በአካባቢ የማይገደብ ስለሆነ ይሄን የጋራ ጉዳይ ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ማስተዳደር እንዲቻል በጋራ መነጋገርና መፍትሔ መፈለግ ያስፈልጋል ብለዋል::
በተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም